Sunday, 03 March 2013 08:18

አሸባሪው

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(1 Vote)

መግቢያ
…199… ዓ.ም ከዲላ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ድግሪ ተመረቅሁ፡፡ በአንድ የመንግስት መ/ቤት የሥራ ቅጥር አገኘሁ፡፡ በደቡብ ምዕራብ ጠርዝ በምትገኝ የጠረፍ ከተማ ተመደብኩ፡፡ “ልሂድ…ልቅር”…በሚል ስብከነከን አጐቴ እዚያች የጠረፍ ከተማ እኔ በተቀጠርኩበት መ/ቤት ለሦስት ዓመት የሰራ ሰው እንደሚያውቅ…በመጠነኛ የአእምሮ መዛባት ሥራውን መልቀቁን…በአሁኑ ሰዓትም ከመጠጥ ሱስ ጋር በተያያዘ የሰብስታንስ ሕክምና በአማኑኤል እንደሚከታተል…በጠቆመኝ መሰረት ሰውየውን ለማግኘት ወደ አማኑኤል ሆስፒታል አቀናሁ፡፡ አገኘሁትም፡፡ ተዋወቅን፡፡ አፍታም ሳይቆይ ዲስኩሩን እንደዶፍ አወረደው…

…አብዱልአዚዝ አልከኝ ስምህን…መጠነኛ የአእምሮ ችግር እንዳለብኝ አጐትህ ሳይነግርህ አይቀርም፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች አብደዋል - የሚያብዱም ይኖራሉ፡፡ እዚያች የምድር ጠርዝ የጠረፍ ከተማ ነገ ልሄድ ነው አልከኝ፡፡ ከአዲስ አበባ ቴፔ የሚለውን አውቶብስ ያዝ፡፡ …ሰበታን አልፈህ ተፍኪ ትደርሳለህ፡፡ ተፍኪ ላይ የጅማውን አባ ጅፋር ቁንጫ በልቷቸው ቅብጥርስዮ ብሎ የሚተርክልህ ተሳፋሪ ከጐንህ ታጣለህ ማለት ዘበት ነው፡፡ በተፍኪ ስመላለስ ይህንኑ የቁንጫ ታሪክ ሳልሰማ ያለፍኩበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ አባጅፋርን የበሏቸው ቁንጫዎች በከተማዋ የታሪክ ድርሳን ሲወሱ ይኖራሉ፡፡ ተፍኪ ስትደርስ ጉያህን…ብብትህን ሳትወድ በግድ ያሳክክሃል፡፡ ይህም ቁንጫዎቹ ያሳደሩት ዘመን የማይሽረው ተጽእኖ ውጤት ነው፡፡ ማን ያውቃል? የነዚያ ቁንጫዎች የልጅ ልጅ…ምንጅላቶች የእኛ ዘር የንጉስ ደም የመጠጡ ናቸው በሚል ለቁንጫ ነጋሲነት እንደልቼንሳ ሳይጠቀሙበት ይቀራል - ሞአ ቁንጫ ዘእምነገደ ሙጃሌ …ወሊሶን አቋርጠህ ወልቂጤ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ትገባለህ…ከጥቂት ሰዓታት ጉዞ በኋላ ወደ ጊቤ በረሃ ትደርሳለህ፡፡ እዚያ ዝርፊያ የተለመደ ነው፡፡ 
የበረሃው ዛር የሚያዛቸው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ደም የጠማቸው ዘራፊዎች እጅ ላይ ልትወድቅ ትችላለህ፡፡ …አብዱልአዚዝ ላስፈራራህ አይደለም፤ ከራሴው ገጠመኝ በመነሳት ነው፡፡ ጊቤ በረሃ ላይ ጐማውን በጥይት አስተንፍሰው አስቆሙን፡፡
አንድ ጠርብ የሚያክል ወደ አውቶብሱ ገብቶ “የኪስ ቦርሳህን” ብሎ ሲያንባርቅብኝ እንደ ህልም ትዝ ይለኛል፡፡ እንደተለቀቀ ቤት ኦና የቀረችውን ገንዘብ አልባ ቦርሳዬን ተሸማቅቄ አስረከብኩ፡፡ ቦርሳዬ ባዶ መሆኗን እንዳየ በያዘው የመሳሪያ ሰደፍ ጆሮ ግንዴን አናጋው፡፡ ያ የሰደፍ ምት አእምሮዬ ላይ ታትሞ ዛሬም ድረስ የሕይወቴ ቅዠት ሆኗል፡፡ …እናም አይበለውና የተሳፈርክበት አውቶብስ ዘራፊዎቹ በቁጥጥር ስር አውለውት ፀዓረሞት የመሰለ ሽፍታ ፊትህ ተገትሮ “ከቦርሳህ ገንዘብ፣ ከጣትህ ቀለበት፣ ከአንገትህ ሀብል!” ብሎ ቢያንባርቅብህ ያለህን በፍጥነት ከች!...ዘራፊውን ግን ፈጽሞ ቀና ብለህ እንዳታየው፡፡ አየኸው ማለት አለቀለህ፡፡ በያዘው ገጀራ ቢበዛ ሦስት ቦታ፣ ቢያንስ ሁለት ቦታ ይቆራርጥሃል፡፡ ሥራ ብለህ ወጥተህ ክልትው ማለት አለ፤ እንደወጡ መቅረት፡፡ የወላጆችህን መራር ሃዘን አናንሳው፡፡ ለፍቅረኛህ የአንተ ህልፈት መራር ይሆንባታል፡፡
የሕይወት ትርጉም ጣዕሙ ይጠፋባታል፡፡ መቼም ወጉ አይቀር ልቧ መሰበሩ አይቀርም፡፡ ይህ ግን ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ ጊዜ ምን የማይሽረው ጠባሳ አለ፡፡ አዲስ ህይወት - አዲስ ፍቅረኛዋን ለመጀመር አፍታም አይወስድባትም፡፡ ይብላኝልህ ለአንተ እንጂ እንጀራ ፍለጋ ወጥተህ በረሃ መሃል ፍግም ላልከው …እንዴ! አብዱልአዚዝ በፍርሃት እየተንቀጠቀጥክ እኮ ነው…እንዲህማ በአንዴ ተስፋ አትቁረጥ - ተስፋ ለመቁረጥ ገና በቂ ጊዜ አለህ፡፡
…አዳርህ ጅማ ይሆናል፡፡ ከጅማ ቀኑን ሙሉ ተጉዘህ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ቴፒ ትደርሳለህ፡፡ …ንገዱ ፒስታ ወቅቱም ክረምት በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ጉዞህ በበቅሎ ጀርባ ይሆናል፡፡”…
በየመሃሉ እረፍት እያደረግህ ለ10፡00 ሰዓት በበቅሎ ጀርባ ከሰገርክ በኋላ ለአይን ያዝ ሲያደርግ፣ እዚያች የአገር ጠርዝ ትደርሳለህ፡፡ ኮርቻ ያለመደው መቀመጫህ ተላልጦ…ጭንህ ተገሽልጦ…ፊንጢጣው ላይ ብጉንጅ እንደወጣበት ሁለት እግርህን አንፈራጠህ ፈንደድ...ፈንደድ እያልክ ዋናውን መንገድ ይዘህ ስትራመድ በአእምሮህ ሳለው…አሃሃሃ…አስቂኝ ትዕይንት ነው - ለተመልካቹ…ትራጀዲ ነው ለተዋናዩ…ለአንተ ማለት ነው አብዱልአዚዝ፡፡
የከተማዋን ብቸኛ አልጋ ኪራይ የምታገኘው “ኬሮ ቡና ቤት” ነው፡፡ …ትዝ ይለኛል እዚያች ቤርጐ አባ ኬሮን ተከትዬ እንደገባሁ ማገሩ ላይ ሁለት አይጦች ስመለከት ሰቀጠጠኝ፡፡ ድንጋጤዬን አይተው አይዞህ “ቤርጐ ስናከራይ ከድመት ጋር ነው” ብለውኝ ወደል ድመት አስከትለው መጡ፡፡ “አነር የሆነ ድመት ነው፤ እራትህን ስትበላ ቅንጥብጣቢ ስጋ ብታመጣለት በቅንነት ያገለግልሃል”
…ወጣ ብዬ እራቴን በላሁ፡፡ ለድመቱም ሙዳ ሥጋ ይዤ ተመለስኩ፡፡
ሥጋውን እንደወረወርኩለት ዋጥ ስልቅጥ አድርጐ አይኑን እኔው ላይ አቁለጨለጨብኝ፡፡ አስተያየቱ ተከታዩን ምግብ ፍለጋ ይመስላል፡፡ ማሾውን አጥፍቼ ተኛሁ…መብራትስ? አልከኝ አብዱልአዚዝ…እዚያች የጠረፍ ከተማ መብራት የለም…የቧንቧ ውሃ የለም፡፡
…እንትን የለም፡፡ ብቻ የሌሉ ነገሮች ተቆጥረው አያልቁም፡፡ የሚቀረና ሽታ አጥወለወለኝ፡፡ እነ ቅማል፣ ትኋን…ጨለማን ተገን አድርገው አካሌ ላይ ተርመሰመሱብኝ፡፡ እንቅልፍ እንቢ አለኝ፡፡ “መጠጥ ብቀማምስ ለእንቅልፍ፤ …ጠጣ…ጠጣ አለኝ መንፈሴ…ምን ችግር? አለኝ ኪሴ”
ወደ ቡና ቤቱ አመራሁ፡፡ በርጩማ ላይ ተሰይሜ በደሌ ስፔሻል መጐንጨት ጀመርኩ፡፡ ከጐኔ አባ ኬሮ ያለማቋረጥ የምጽዓት ቀን ስለመቃረቡ…እግዚአብሔር ስለመቆጣቱ…መልአክት ስለማኩረፋቸው …ሲናገሩ መስማቱ በዛች ፀጥ ረጭ ባለች ምሽት ስለ ህይወት እና ፍፃሜዋ እያሰብክ ሳትወድ መቆዘምህ አይቀሬ ነው፡፡ አራት በደሌ ስፔሻል ላፍ አድርጌ ወደ ቤርጐዋ ተመለስኩ፡፡ እነ ትኋን፣ ቅማል…የመጠጡ ሽታ አለርጂ ሆኖባቸው ነው መሰል፣ ጫፌን ሳይነኩኝ ድብን ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡ ውድቅት ላይ አንዲት አይጥ ከኮርኒሱ ቁልቁል ጭንቅላቴ ላይ ዱብ! አለችብኝ፡፡ ቆሌዬ፣ ስካሬ ተገፈፈ፡፡ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ፡፡ ማሾ አበራሁ፡፡ የአይጥ መንጋ ይተራመሳል፡፡ ሙዳ ስጋ የበላው ድመት ያለ ሃሳብ እንቅልፉን ይለጥጣል፡፡ ልቀሰቅሰው ጫማዬን ብወረውርበት “ሚያው” ብሎ አንቃብቆ አይኑን እኔ ላይ አጉረጠረጠብኝ፡፡ ድመቱ ለእኔ ያሳየው ንቀት የልብ ልብ የሰጣቸው አይጦች ኮርኒሱን ቀውጢ አደረጉት፡፡ ላይ ታች ቱር! ቱር! ይሉ ጀመር፡፡ በእውነት ነው የምልህ አብዱልአዚዝ… ድመቱ ከአይጦቹ ይልቅ እኔን በጥላቻ ያየኝ ነበር፡፡…
…የዛች ቤርጐ ጣጣ በዚህ የሚያበቃ አይደለም - የታይፈስ ሰለባ ልትሆን ትችላለህ፡፡ ታይፈስ በሰውነት ቅማል ይተላለፋል፡፡ ቤርጐዋ ካላት ብዝኃ የቅማል ክምችት በታይፈስ የመያዝህ ዕድል የሰፋ መሆኑን በአጽዕኖት አረጋግጥልሃለሁ፡፡
እመት ቅማሊት መረቅ የሆነውን ትኩስ የወጣትነት ደምህን ስትመጥ፣ እግረ መንገዷን በሽታውን ታስተላልፍብሃለች፡፡ እዚያች ከተማ ሕክምና አገኛለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ …ትኩሳት …የጉሮሮ መቁሰል… ቁርጥማት… ከተፈራረቁብህ በኋላ የልብ ምትህ ይቀንሳል፡፡
ልብህ እንደመቆምም እንደመምታትም እያለች ትንተፋተፋለች፡፡ የነርቭ መዛባትን ተከትሎ በቀጥታ ወደ ቁም ቅዠት ዘው ብለህ ትገባለህ፡፡ በአልጋህ ዙሪያ ሰዎች ከበውህ “ይተርፋል ማለት ዘበት ነው፡፡
እዚህ ይቀበር ወይንስ ሬሳው ወደቤተሰቦቹ ይላክ” በሚል ሲከራከሩ ስትሰማ የበለጠ ትቃዣለህ፤ ትቀባዥራለህ፡፡ ወፈፍም ያደርግሃል፡፡ ያኔ ስድብ ትጀምራለህ “እኔ ሬሳ! - በቁማችሁ ተገንዛችሁ ግብአተ መሬታችሁ ያልተፈፀመ ህያው ሬሳዎች! አብዱላዚዝ ያን ስድብህን በመቅረፀ ድምጽ ተቀድቶ ዳግም ብትሰማው በሐፍረት ያሸማቅቅሃል፡፡ ደግነቱ ፈጽሞ በሕይወት የመትረፍ እድል ስለሌህ አንዳችም የሚያሸማቅቅህ ነገር የለም፡፡ ለሦስት ቀን እየወራጨህ ጠመዝማዛውን የሰመመን ቅዠት መንገድ ከተጓዝክ በኋላ ህሊናህን ስተህ ወደ ግራ በሚወስደው መንገድ ትታጠፋለህ፡፡ ያ መንገድ የሞት መንገድ ይባላል፡፡
ዝንተ ዓለም የሰው ልጆች የሚመላለሱበት ማለቂያ የሌለው መንገድ፡፡ ፀጥ፡፡ ረጭ፡፡ ጭጭ፡፡ ዘለዓለማዊ ፍጻሜ፡፡ ሞት፡፡ …እንዴ አብዱልአዚህ እየተንቀጠቀጥክ እኮ ነው! እንዲህም በአንዴ ተስፋ አትቁረጥ፡፡ ተስፋ ለመቁረጥ ገና በቂ ጊዜ አለህ፡፡
ውድ አንባቢያን…አብዱልአዚዝ ነኝ - በታይፈስ ጦስ ዳግም ይችን ምድር ተሰናብቻለሁ፡፡ ሬሳዬ የት ይቀበር በሚል ሰዎች እያንባረቁ ሲጨቃጨቁ አይሰማችሁም…ያ! ያላህ…ወደዚህ ወፈፌ የላከኝ አጐቴ ሆይ ነፍስህ አይማር…
…የምትመደብበት ቢሮህ ተጋሪህ አቶ ምንዳዬ ይባላል፡፡ የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ ነው፡፡ ከድህነቱ ጋር የማይሄድ ቦርጭ ባለቤት ነው፡፡ በደሞዝ ማግስት ብድር በመውሰድ የሚቀድመው የለም፡፡ ደሞዙ እንደ ፔንኪለር ታብሌት ለ24 ሰዓት ብቻ ነው የሚያገለግለው፡፡ አይፈረድበትም፡፡ 12 ልጆች አሉት - አንድ ደርዘን በለው፡፡ በቤቱ ስታልፍ 12 ልጆች፣ ባል፣ ሚስት… ገበታ ቀርበው ሲመገቡ ብታይ አቶ ምንዳ ማህበር አልያም ሰንበቴ እያወጣ እኔን ሳይጠራኝ በለህ እንዳትቀየመው፡፡
ለዚህ ሰው ድንቡሎ እንዳታበድረው፡፡ የእኔ 300 ብር ቀልጣ ቀርታለች - እኔ ስላበደርኩት 300 ብር ደጋግመህ አንሳበት፡፡ በመስሪያ ቤቱ ስብሰባ ላይ ከሆነ ጉዳይ ጋር አያይዘህ የ300 ብር ባለ እዳ ስለመሆኑ ጣል አድርግበት፡፡ ለነፍስ አባቱም በጐን ሄደህ ገንዘብ የሃጢያት ስር ስለመሆኑ፣ የብድር ገንዘብ ደግሞ የሐጢያት ስር ብቻ ሳይሆን ሥራ ሥር ሆኖ በእሱና በቤተሰቡ ስለሚደርሱ የመርገምት አይነቶች እንዲሰብኩት… ብሬን እንዲያስመልሱልኝ… አለበለዚያ ከሰማይ መብረቅ! …ከምድር በእሳተ ጐመራ ፍንዳታ ከነቤተሰቡ እምሽክ እንደሚል…
…ወደ ሥራ አስኪያጁ ቢሮ እናምራ… ወደ ውስጥ ለመግባት የፀሐፊዋን ክፍል ታልፋለህ፡፡ ፀሐፊዋ ወደ 50ዎቹ አጋማሽ የምትመገት ሴተ ላጤ ናት፡፡
የሚገርምህ በየወሩ ፔሬድ ላይ ነኝ በሚል ፈቃድ ጠይቃ ትወጣለች፡፡ ካረጠች 10 አመት ያስቆጠረች ሴትዮ ወሯ በገባ በሦስተኛው ቀን ሳታስተጓጉል ፈቃድ መውጣቷ የተፈጥሮን ምፀት ያሳያል፡፡ …እንዲህ ያለ ነገር እንኳን ብዙም አይጠቅምህም - ለጠቅላላ እውቀትህ ያህል ነው፡፡
የፀሐፊዋን ይሁንታ ጠይቀህ የሥራ አስኪያጁን ቢሮ በር ታንኳኳለህ - ልጅ እግር ተላላኪ በሩን ከፍቶ ብቅ ይላል፡፡ ካውያ ራስ ነው፡፡ አባቱ በዚህ መስሪያ ቤት በተላላኪነት 30 አመት አገልግለዋል፡፡ አባቱ ሲሞቱ ልጁ በአባቱ የሥራ መደብ ቅጥር ፈፅሟል፡፡ ይህ ተላላኪ የመስሪያ ቤቱን ሠራተኛ እያንዳንዷን ሚስጥር ያውቃል - ከምን ተበላ እስከ ምን ተፈሳ፡፡ እናም የሰማውን ወሬ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ እንደ ፀበል ረጭቶ እንደፀዲቅ አቃምሶ ይጠብቅሃል፡፡
አብዱልአዚዝ ፊት እንዳታሳየው፡፡ ከዚህ በተረፈ ይህ ተላላኪ ትንሽ ሲቀማመስ የአባቱን የሆዳምነት ታሪክ ይተርክልሃል፡፡ የበሬ ታፋ፣ ሽንጥ… ሲጥ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ይህን እምብርት የለሽነታቸውን አንጋፋ የመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች እውነት መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡
በዚህም በኩራት ሲጀነን ታየዋለህ፡፡ የአባቱ ሆዳምነት የኩራቱ ምንጭ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ “አባቴ ከርሳም ነበር!” ብሎ ነገር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው… አጋሰስ አባቱ በሕይወት ዘመናቸው “በቃኝ …ጠግቤያለሁ” የሚለውን ቃል አንድም ጊዜ ትንፍሽ ሳይሉ ለህልፈት በቅተዋል፡፡ የሚናዘዙት ሃጢያትም ሆነ ገንዘብ ስላልነበራቸው ለልጃቸው ያወረሱት 5 ብር እዳ ያለባት የወርሃዊ የእድር መክፈያ ካርድ…
…ምን ላይ ነበርኩ አብዱልአዚዝ… አዎ አንተ በር ላይ ነህ፡፡ የተላላኪው እንደ ጥይት የሾለ ግንባር በቅርብ ርቀት ተደቅኖብሃል፡፡ አንተን ከማስገባቱ በፊት ለአለቃው ወንበሩ ላይ እንዲቀመጥ ምልክት ይሰጠዋል፡፡ በዚያች ቅፅበት ሥራ አስኪያጁ እግሩ ግድግዳ ላይ… ጭንቅላቱን ወለል ላይ ተዘቅዝቆ የራስ ምታቱን እያስታመመ ሊሆን ይችላል፡፡
የመስሪያ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ በ40ዎቹ አጋማሽ የሚገመት ነው፡፡ ሥራና ሠራተኛን አይወድም፡፡ ሚስት የለውም፡፡ ልጅ የለውም፡፡ ግድ የለውም፡፡
ህይወት የታከተው፡፡ ሁሉን ነገር የሚከውንለት ተላላኪው ነው፡፡ ቢሮው የሥራ ገበታው ሳይሆን ጫት መፈረሻው ነው፡፡ ለስልቹ አለቃ ጫት ቀንጥሶ የሚያጐርሰው …ሲጋራ ለኩሶ የሚያስበው… እንደ ገመምተኛ አንገቱን ቀና አድርጐ ውሃ የሚያጠጣው ያ ተላላኪ ነው፡፡ ሽንቱ ቢወጥረው ከቢሮው ወጥቶ መሽናት ስለሚታክተው ያን ግንባሩ እንደ ጥይት የሾለ ተላላኪ ጠርቶ “ሽንቴን ውጥር አድርጐኛል - ሽናልኝ” የሚል ከውሃ የቀጠነ ትእዛዝ ሊሰጠው ይችላል፡፡
ከመሰላቸቱ የተነሳ ልብሱን አውልቆ መተኛት ስለሚታክተው፣ ጠዋት ኮትና ሱሪው የተወቀጡ ይመስል ሁሌም እንደተጨማደዱ ነው፡፡ ይህንን ጨምዳዳ አለባበሱን ከጨምዳዳ ፊቱ ጋር ስታየው አስቂኝ የካርቱን ስዕል ሆኖ ያርፈዋል፡፡
አለቃህ እንደመናፍስት በአንድ ጊዜ የተለያዩ ቦታዎች ይከሰታል፡፡ እንደሰው በምድር ተራምዶ ይምጣ እንደ ሸረሪት ከጣራ ይውረድ ዱካውን ሳያሰማ አጠገብህ ተቀምጦ፣ እንደ እንቁራሪት ወጣ ወጣ ባሉ አይኖቹ ትክ ብሎ ያፈጥብሃል፡፡ በተለይም ብርጭቆ መሳይ መነፅሩን አድርጐ ሲቃኝህ አንጀት፣ ልብና ኩላሊትህን ዘክዝኮ የሚያይብህ ይመስልሃል፡፡
ማታ ስላየኸው የስቃይ ህልም ሊነግርህ ይችላል፡፡ አይኑን ሳይነቅል “ማታ ጠጥተህ ነበረን?” ሲል የጉበትህን በአልኮል መታወክ በዓይኑ በብረቱ እያየ የሚጠይቅህ ስለሚመስልህ፣ አትዋሸው - የጠጣኸውን የጂን መጠን በስፍር… የጋፍከውን ቢራ በሊትር ተናዘዝለት፡፡ አፍታም ሳይቆይ “መጠጥ ጠጥቶ የሥራ ገበታ ላይ በመገኘት…” የሚል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይፅፍብሃል፡፡ ለእኔ ከመጠጥ ጋር የተያያዙ ወደ አራት ማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች ደርሰውኛል፡፡ ከሱስ ነፃ ለመውጣት አስቤ፣ የሰብስታንስ ሕክምና ለመከታተል አማኑኤል ስገባ፣ እነዚያን በመጠጥ ጦስ የተፃፉብኝን አራት ደብዳቤዎች ከግል ታሪኬ ጋር አያይዤ በማቅረቤ “ይህማ ሰርቲፋይድ ሰካራም ነው” በሚል ቅድሚያ አልጋ ይዤ ለመታከም ችያለሁ፡፡ ያደለው ለተሻለ ሥራና ደመወዝ ዶክመንቱን ሲያቀርብ፣ እንደ እኔ ዓይነቱ የሰው ከንቱ ቀምቃሚነቱን በሰነድ አስደግፎ የማቅረቡ ነገር የሕይወትን ምፀት ያሳያል፡፡ አንዳንዶች በስኬት ይራመዳሉ…ሌሎች በውድቀት ይጋደማሉ…አብዱልአዚዝ ዱኒያ የምትሏት የዓለም ሃገር እንዲህ ናት፡፡ እዚህ ከገባሁ ወር አለፈኝ፡፡ ይሔ ሳይኮቴራፒ …ግሩፕ ቴራፒ ቅብርጥሲዮ የሚባለው አልተመቸኝም፡፡ ከሱስ ነፃ እወጣለሁ ብዬ አላምንም፡፡ እንኳን በ30 ዓመቴ በ300 ዓመቴም መጠጥ የማቆም አልመስልህ እያለኝ ነው፡፡
አለቃህ ገና እንዳየኸው የምትገረመው በጥርሱ ነው፤ ከጥግ እስከ ጥግ የተሸራረፉ ናቸው፡፡ ሰውየው እንጀራ ተመጋቢ ሳይሆን ብርጭቆ ቆርጣሚ ይሆን እንዴ ያስብልሃል፡፡ እንደበረዶ የነፁ ሽርፍርፍ ጥርሶቹን አንተን እያየ ከገለፈጠብህ አለቀልህ፤ በአንተ ላይ ያሴረው ሴራ ፍሬ አፍርቶ ጐምርቶ መከራን ልትጐነጭ ጥቂት ጊዜያት ስለመቅረታቸው እንደማስጠንቀቂያ ደውል ቁጠረው! የሚደርስብህ ዱብዳ አለ ‘ግፋ ቢል ደመወዝ ቢቆረጥብኝ ነው፤ ወይም ከሥራ መሰናበት ነው’ በሚል እንደ ተራ ነገር እንዳታየው፡፡
ይሄማ ቀላል ነው፡፡ ምን መቅሰፍት እንደሚወርድብህ ከአለቃህ እና ከሰይጣን በቀር ማንም አያውቅም፡፡ ምናልባትም በብቸኛው የከተማዋ ጠንቋይ እንጀራ ለመግባት እቅድ እንዳለህ ጠንቋዩን አሳምኖ፣ በጠንቋዩ ጀሌዎች አንገትህ በጐራዴ ሊቀነጠስ ይችላል፡፡
ምናልባትም በሽብርተኝነት ፈርጆህ ከመንግስት ያልጠበቅኸው መቅሰፍት ሊወርድብህ ይችላል፡፡ በተገላቢጦሽም የመንግስት ሥራህን እንደሽፋን በመጠቀም ፀረ-ሽብርተኛ ሚሽን እንዳለህ ለጽንፈኞቹ አቀሳስሮብህ፣ በሰርጐ ገቦች በላውንቸር ከነቤትህ ዶግ አመድ መሆን አለ፡፡ እንዴ አብዱልአዚዝ እየተንቀጠቀጥህ እኮ ነው! እንዲህ በአንዴ ተስፋ አትቁረጥ፤ ተስፋ ለመቁረጥ ገና በቂ ጊዜ አለህ ብዬህ አልነበር ወይንስ ሳልልህ ያልኩህ መሰለኝ፡፡ ውድ አንባቢያን አዚዝ ነኝ…እነሆ ዶግ አመድ ሆንኩኝ…በጐራዴ የተቀላው አንገቴስ? ጭንቅላቴ ቁልቁል እየተንከባለለ ሲያስካካ አይታያችሁም? አሃሃሃ…
ያ አላህ…ሰውየው ሊያሳድብኝ ነው፡፡ ወደዚህ ወፈፌ የላከኝ አጐቴ ነፍስህ አይማር፡፡
አብዱልአዚዝ ውበትን የማድነቅ ፍላጐቱ ካለህ ዘወትር አርብ በ10፡00 ሰዓት ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ብቅ በል፤ አለቃህ ጫቱን እየጐሰጐሰ…ተርዚናውን ወጥሮ የሲጋራው ጢስ ቢሮውን ሰማያዊ የደመና ካባ አልብሶት፣ በፍንጭት ጥርሱ ምራቁን ጢቅ ጢቅ! እነዚያ ጫት ንክር ሃምራዊ አረንጓዴ የምራቅ ዘንጐች እንደቀስት ተወንጭፈው ብሩህ ሰማያዊውን የሲጋራ ጭስ ደመናን ሰንጥቀው …በመስኮት ከገባችው ጀንበር ጋር የቀስተ ደመና ህብር ፈጥረው ምትሀታዊ ውብ የቀለማት ትእይንት ፊትህ ድቅን ይላል፡፡
አብዱልአዚዝ፤ ቢያንስ ይህንን ከጢስ አባይ ፏፏቴ ጋር ሊነፃፀር የሚችል ውብ ትዕይንት ለማየት ወደዚያች የአገር ጠርዝ እንድትሄድ በአጽንኦት እመክርሃለሁ፡፡

Read 4317 times
More in this category: « ዝንቅ ፍለጋ »