Sunday, 03 March 2013 00:00

የመቀሌ ጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነብይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

“ፊዚክስ ከግሪክ ፍልስፍና የመጣ ነው”
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጆኪም ሔርዚግ፤ ንግግር ፊዚክስን ከማውቀው በላይ እንዳውቀው ያደረገኝ ነው፡፡ እነሆ፡-
“ዛሬ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በርካታ የሥራ ባልደረቦቼን በማየቴ ደስታና ኩራት ይሰማኛል፡፡ ውድ ዶክተር ሙሉጌታ በቀለ፤ የኢትዮጵያ ፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር ሊቀመንበር፤ ውድ አቶ ገብሬ፤ የትግራይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ተወካይ፤ ውድ የሥራ ባልደረቦቼና ውድ ተማሪዎች! እንኳን ደህና መጣችሁ!” ብለው ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ የትግራይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮን ጨምሮ ሌሎች ስፖንሰሮችን አመስግነዋል፡፡ ከዚያም በንግግራቸው ላይ “በዛሬው፤ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አኳያ 70% አዲስ ገቢ ተማሪዎቻችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተማሪዎች ናቸውና ፊዚክስ ማራኪ ትምህርት መሆኑን፣ ለየዕለት ህይወት ፊዚክስ ሁሉንም ባለይዞታዎች ማሳተፍ ተገቢ መሆኑን ማስመር ለሳይንሱም ለሀገሪቱም ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ የማንኛውም አገር ትልቅ እሴታዊ ሀብት ሰዎች ናቸው፡፡ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ የሥራ ፍቅር ያላቸውን ሰዎች በማሰባሰብ፤ የመተባበርን መንፈስ እያሰረፁ በተለያዩ ዲሲፕሊን መካከል ያለን መረዳዳት መፍጠር፤ በጋራ የምንጠቀምበት ዕውቀትም ወደ ጋራ ዕሴት የሚያመራበትንና ያ ደግሞ ወደ ጋራ ወዳጅነት የሚሄድበትን ስኬታማ ዘዴ በመጠቀም ህብረተሰብን የተሻለ ነገ እንዲኖረው ማድረግ ዋና ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
በመቀጠልም፤ “ታዲያ ይሄ ሁሉ በሁሉም ወገን በሚከፈል ኮስታራ መስዋዕትነትና የመኖርና ኀብረት የመፍጠር ፍላጎትን በማበልፀግ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ የሚሰጠን አንድምታ ፍቃደኝነትን ማወጅን ነው፡፡ ማለትም በዚህ አገር ምርምርንና ፊዚክስን ማስተማርን በንቃት በማሳደግና በማስፋፋት እንዲሁም ዕውቀትንና ልምድን በማደርጀት እንዲሁም በማዳበር ከሙያና ከሙያው ዲሲፕሊን ባሻገር ድልድይ እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡
“ፊዚክስ በአዳዲስና ከንድፈ-ሀሳብ በሚመነጩ የቴክኖሎጂ ግኝቶች አኳያ ታላቅ ፋይዳ ያለው አስተዋፅዖ ያደርጋል” በማለት፤ “አስረጅ ይሆነን ዘንድ በኤሌክትሮ ማግኔቲዝም ወይም ኒኩሊየር ፊዚክስ-መር በሆነ መንገድ ለእድገት አዲስ ግብአተ-ምርቶችን በመለገስ ዘመናዊውን ህብረተሰብ እንደ ቲቪ፣ ኮምፒዩተር፣ የቤት-ውስጥ ቁሶችን እንዲሁም የኑክሊየር መሣሪያዎችን በመፍጠር ረገድ ሥር-ነቀል ለውጥ የሰጠና ያስታጠቀ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ “የቴርሞዳይናሚክስ እመርታ ለኢንዱስትሪ ሥርዓት በር ከፋች መሆኑንና የሚካኒክስ ማደግ ለካልኩለስ ሂሳብ መበልፀግ ያደረገውን አስተዋፅኦ ማስተዋል ይበቃልም” ብለዋል፡፡
“የተፈጥሮ ፍልስፍና ሥርወ-ምንጩ ግሪክ ነው - በጥንታዊ ዘመን (650-480 ከክ.ል.በፊት)፡፡ ያኔ እንደታለስ ያሉ ቅድመ-ሶቅራጥስ ፈላስፎች ልዕለ-ተፈጥሮ፣ ሃይማኖታዊ ወይ አፈ-ተረታዊ ገለፃዎችን ተቃወሙ፡፡ ለተፈጥሮአዊ ክስተት ተሟገቱ፡፡ እያንዳንዱ ክንዋኔ ተፈጥሮአዊ ምክንያት አለው አሉ፡፡ በምክንያትና በምልከታ ላይ የተመረኮዙ ጉዳዮችን ለማስረዳት ተነሱ፡፡ ሆኖም ገና ቤተ-መከራ ጋ አልደረሱም ነበር፡፡ ምነው ቢሉ የቤተ-ሙከራ ሥራ ለምዕተ-አመታት የተወገዘ ነበርና ነው፡፡ ያኔ ዓለም በሁለት ተከፍሎ ነበር፡፡ በአንድ ወገን የጉልበት ሥራ ሙያተኞች ያልሆኑ የተማሩ ጠቢባን አሉ፡፡ በሌላ ወገን መሀይም የሆኑትና የማሰብ ሥራ የማይፈቀድላቸው ባሪያዎች አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ የቤተ-ሙከራ ሥራ ማሰብም መሥራትም እንደሚያስፈልገው ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም፤ በ16ኛውና በ17ኛው ክ/ዘመን የመጣው የአብራሄ-ህሊና ዘመን እስከተከሰተ ድረስ ለዕድገት ጎታች ሆኖ የነበረው በባሪያ የጉልበት ሥራ ላይ የተመረኮዘው የግሪክ ህብረተሰብ ነበር፡፡
“ክላሲካል ፊዚክስ የተባለው የጥንቱ የጠዋቱ ፊዚክስ፤ የተለየ ሳይንስ ሆኖ የተገኘው የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ አውሮፓውያን የቤተ-ሙከራንና የብዛት-ምጣኔ ዘዴን (Experimental and quantitative methods) በመጠቀም ዛሬ ሕግጋተ-ፊዚክስ (Laws of physics) የተባሉትን ሲያገኙ ነው፡፡ ኬፕለር፣ ጋሊሊዮ እንዲሁም፣ በተለይ፣ ኒውተን የተለያዩትን የእንቅስቃሴ ህግጋት አገኙና አዋህደው ለመጠቀም ቻሉ፡፡ በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን የኃይል ምንጮች ጥያቄ ሲበራከት ምርምርና የምህንድስና ጥበብ እያበበ መምጣቱ ለቴርሞዳይናሚክስ፣ ለኬሚስትሪና ለኤሌክትሮ-ማግኔቲዝም አዳዲስ ህግጋት መፈጠር ምክንያት ሆነ፡፡
“ዘመናዊው ፊዚክስ (አዲሱ የፊዚክስ አቅጣጫ) በማክስ ፕላንክ የኳንተም ንድፈ - ሃሳብ (Quantum theory) እና በአይነስታይን “ሪሌቲቪቲ” ንድፈ - ሃሳብ ተጀምሮ በአብሪ-ሳይንቲስቶቹ በሐይዘንበርግና በሽሮዲንገር ኩዋንተም ሜካኒክስ የቀጠለ ነው፡፡
“ፊዚክስ፤ በብዙ አቅጣጫ ስናየው፤ ከጥንቱ የግሪክ ፍልስፍና የመጣ ነው፡፡
ለምሳሌ ታለስ የተባለው ሳይንቲስት የቁስ አካልን ባህሪ ለማወቅ ያደረገውን የመጀመሪያ ሙከራ፤ የዲሞክራተስ አንድ ቁስ አካል ወደማይለወጥ የአተም ደረጃ ሊወርድ ወይም ሊያንስ ይችላል የሚል ድምዳሜ፤ ወይም ክሪስታሊን ፈርማመንት ላይ የሚያተኩረው እሳቤ ማስረጃ ይሆኑናል፡፡
“በ19ኛው ክ/ዘመን ፊዚክስ፤ ከፍልስፍናና ከሌሎቹ ሳይንሶች ተለይቶ የሚታይ ዲሲፕሊን መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገባ፡፡ ፊዚክስ እንደሌሎቹ ሳይንሶች ሁሉ የሳይንሳዊ ዘዴን በበቂ ለመግለጽ በፍልስፍና ሳይንስ ላይ ይንተራሳል፡፡ ሳይንሳዊ ዘዴ ቅድመ -ምክንንና ድህረ-ምክንን እንዲሁም የአንድን ንድፈ ሃሳብ ፋይዳ በሚመለከት የምንገለገልበትን ቤይሲያን ኢንፈረንስ (Bayesian inference) የሚባል ዘዴ ይጠቀማል፡፡ ይሄ ደግሞ መላምትን በመሠረቱ ማፍረስ የማስፈለጉን ጽንሰ-ሀሳብ ያካትታል፡፡ “የፊዚክስ ማደግ የጥንቶቹን ፈላስፎች ብዙ ጥያቄዎች መልሷል፡፡ ሆኖም በርካታ ጥያቄዎችንም አንስቷል፡፡ በፊዚክስ ዙሪያ ያለው ፍልስፍና ባለሁለት ፈርጅ ነው፡፡ አንደኛው ተፈጥሮአዊ ፍልስፍናን መሠረት ያደረጉና የቦታ፣ የጊዜና የዲተርምኒዝም ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ ሌላው ሜታፊዚካዊ አመለካከትን የተንተራሰውና ኢምፔሪሲዝምን፣ ናቹራሊዝምንና ሪያሊዝምን የሚያካትተው ሳይንስ ነው፡፡”
የአርስቶትልም በፊዚክስ ላይ ያነጣጠረ መጽሐፍ እንቅስቃሴን ለመተንተንና ለመተርጐም የሞከረው ከፍልስፍና ምልከታ ነጥብ ሲሆን አያሌ ፈላስፎች የየራሳቸውን የተፈጥሮ ፍልስፍና እንዲያጐለብቱ አነቃቅቷል፡፡ እስከ 18ኛው ክ/ዘመን ፊዚክስ የተፈጥሮ ፍልስፍና ነው ይባል ነበር፡፡ ዛሬም የፍልስፍና ዶክተር (ፒ ኤች ዲ) የሚል ማዕረግ ለሳይንቲስቶች ለፊዚክስም እንደምንሰጥ ልብ በሉ፡፡
“ፊዚክስ የመጣው ከግሪክ ቃል ነው፤ትርጉሙም “ተፈጥሮ ፊዚዝ” ማለት ነው፡፡ ፊዚክስ የተፈጥሮ ፍልስፍናና የተፈጥሮ ሣይንስ አካል ሲሆን ቁስ - አካል በጊዜና ቦታ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የሚያጠና ሳይንስ ነው፡፡ የኃይል እና የጉልበት አጠቃቀም (energy and force) በተጓዳኝ የያዘ ጥበብ ነው፡፡ በሰፊው ስናየው የተፈጥሮ አጠቃላይ ትንታኔ ነው፤ ይህም ዩኒቨርስ (ሁለንተናዊው ዓለም) እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡
“ፊዚክስ ከጥንታዊ የአካዳሚ ዘርፎች አንዱ ነው፡፡ ምናልባትም አስትሮሎጂን (ሥነ - ከዋክብትን) ከጨመርን አንጋፋው ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ሚሌኒየሞች ፊዚክስ ከኬሚስትሪ፣ ከሂሳብ ቅርንጫፎችና ከባዮሎጂ ጋር የተፈጥሮ ፍልስፍና አካል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በ16ኛውና በ17ኛው ክ/ዘመን በተካሄደው ሳይንሳዊ አብዮት ወቅት የተፈጥሮ ሳይንሶች የጥናትና ምርምር መርሀ ግብር እየሆኑ መጡ፡፡
ፊዚክስ ከብዙ ተዛማጅ ዘርፎች (ዲሲፕሊኖች) ምርምሮች ጋር እንደ ባዮፊዚክስ፣ እንደኳንተም ኬሚስት ካሉት ጋር ከመዛመዱ አኳያ ስናየው ግዴታ ይህ ወሰንህ ይህ ዲካህ የሚባል አልሆነም/አይደለም፤ አዳዲስ የፊዚክስ ግኝት ሃሳቦች መሠረታዊ የሳይንስ ሜካኒዝምን ያብራራሉ፡፡ እንደ ሂሳብና ፍልስፍና ላሉ መስኮችም አዲስ ጥርጊያ ጐዳና ይከፍታል፡፡
ከዚህ ጉባዔ የሚጠበቀው
ዕውቀትና ልምድን መጋራት
የጥናት ፍሬዎችንና አዳዲስ ፕሮጄክቶችን መጨመር
ፊዚክስን በማስተማር ረገድ ያጋጠሙ ችግሮችን መለየት
የፊዚክስን ከሪኩለም ማሻሻል ነው ”
በዚህ መንፈስ 7ኛው የፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር ጉባዔ ስኬታማ እንዲሆንና ተሳታፊዎቹ ፍሬያማ የሃሳብ፤ የጽንሰ ሃሳብና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እመኛለሁ፡፡”
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ “በኢትዮጵያ ለፊዚክስ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት፣ የፊዚክስ ዕድገት በአንድ ደረጃ እንዲያድግ፣ ለሀገሪቱ ፋይዳ ያለው ነገር እንዲሆን ምኞታቸውን ገልፀው፤በመጨረሻም፤“ዘላቂ ልማት/ዕድገት ማለት በቀጥተኛውና ትክክለኛው መንገድ ተከታታይ ዕድገት መያዝ ማለት ነው” ያሉ ሲሆን “ይህ ጉባዔ ዘላቂ የፊዚክስ ዕድገት ለዓለም ዓቀፍ ዕውቀት ፋይዳ፣ ለሀገራዊ ኢኮኖሚና በጠቅላላም ለሀገሪቱ ጥቅም እንዲያመጣ ብርቱ ምኞቴ ነው” ብለዋል፡፡

Read 3058 times