Sunday, 03 March 2013 00:00

ዓለም ላይ ኮሜዲ የሰሩት አምባገነኑ የኡጋንዳ መሪ - ኢዲ አሚን!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(7 votes)

“ዲሞክራሲ የሚሰራው አውሮፓ ውስጥ ነው!” - ኮሎኔል መንግስቱ ኀ/ማርያም
ከሰሞኑ እጄ የገባውን የሰባት አምባገነን መሪዎች ቃለምልልስ የያዘ Talk of The Devil የተሰኘ መፅሃፍ ያዋሰችኝ ለዚህ አምድ ተስማሚ የሆኑ ፖለቲካዊ ግብአቶችን ዘወትር የምታቀብለኝ የሥራ ባልደረባዬ ናትና በናንተ በውድ አንባቢያን ስም ምስጋናዬን እንዳቀርብላት ፍቀዱልኝ (ባትፈቅዱም ማመስገኔ አይቀርም!) በነገራችሁ ላይ በጣልያናዊው ጋዜጠኛ ሪካርዶ ኦሪዚዮ የተሰናዳው ይሄ መፅሃፍ፤ የአፍሪካ አምባገነኖችን ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካም ወጣ ብሎ የፖላንድን፣ የምዕራብ ጀርመንን፣ የዩጎዝላቪያንና ሌሎችንም አገራት አምባገነን መሪዎች ታሪክ በቃለምልልስና በትረካ ያቋድሳል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይሄን መፅሃፍ ስታነቡ ትንሽ መፅናናታችሁ አይቀርም፡፡ ለምን መሰላችሁ? “ለካስ አምባገነኖች ያሉት በአፍሪካ ብቻ አይደለም” ትላላችኋ! በእርግጥ ይሄ እስከዛሬ በአምባገነኖች የደረሰብንን ከሰብአዊነት ውጭ የሆነ ጭቆናና በደል በምንም አይነት መንገድ የሚያጠፋው እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ግን በቃ ትፅናናላችሁ! በየትኛውም ዓለም የነበሩና አሁንም ያሉ አምባገነኖች የቱንም ያህል ቢንጠራሩ የአፍሪካዎቹ አቻዎቻቸው ላይ ፈፅሞ ሊደርሱባቸው እንደማይችሉ ብነግራችሁስ? (በሌላ ሳይሆን በዝርፊያና በጭካኔ ማለቴ ነው!) ከመቅፅበት መፅናናታችሁ እንደጉም በንኖ ይጠፋላ! ምን ይደረጋል--- እውነቱ ግን እንዲያ ነው! 
እንዴ ዋናውን ጉዳይ ሳልነግራችሁ --- በዚህ የአምባገነኖች መፅሃፍ ውስጥ በዚምባቡዌ ላለፉት 20 ዓመታት በጥገኝነት የኖሩት የቀድሞው የአገራችን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኀ/ማርያም ታሪክም ተካትቷል፡፡ አምባገነኖች አምባገነንን ያስጠጋሉ እንዲሉ--- መንጌን ያስጠጓቸው የዚምባቡዌው አምባገነን መሪ (እርጅናና ህመም ተጫጭኗቸዋል!) አዛውንቱ ሮበርት ሙጋቤ ናቸው፡፡ የመፅሃፉ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሪካርዶ ኦሪዚዮ ግን አንድ ስጋት አለው- ሙጋቤ ከሥልጣን የወረዱ እለት ኮሎኔሉን ምን ይውጣቸዋል የሚል፡፡ (የአምባገነኖች አምላክ አለ እንዴ?) ለጊዜው ግን መንግስቱ በዚምባቡዌ ገጠር ቀመስ (suburban) ከተማ የመሬት ባለቤት ሆነዋል - በ150ሺ ዶላር በልጃቸው ስም መሬት በመግዛት! እናም ድሮ የናፈቁትን መሳፍንትነት የማታ ማታ አሳክተዋል ባይ ነው - የአምባገነኖችን ድርሳን የከተበው የጣልያኑ ጋዜጠኛ፡፡
በነገራችሁ ላይ አብዛኞቹ አምባገነን መሪዎች ከድሃ ቤተሰብ የተገኙ ናቸው፡፡ አብዛኞቹም ከድህነት ለማምለጥ ሲሉ ውትድርና ገብተዋል፡፡ ውትድርና ገብተው ግን አልቀሩም፤ በመፈንቅለ መንግስት የየአገሮቻቸውን የሥልጣን መንበር ይዘዋል፡፡ (ኢዲ አሚንና መንጌ ይጠቀሳሉ!)
እንግዲህ በመፅሃፉ ውስጥ ከተካተቱት አምባገነኖች መካከል ለዛሬ ላወጋችሁ የመረጥኩት የኢዲ አሚንን ታሪክ ነው፡፡ እውነት ለመናገር Talk of The Devil የተባለውን ይሄን የአምባገነኖች ታሪክ የያዘ መፅሃፍ እስከማነብ ድረስ ስለቀድሞው የኡጋንዳ አምባገነን መሪ - ሃምሳ አለቃ ኢዲ አሚን ብዙ የማውቅ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? በእሳቸው ዙሪያ የተሰሩ ጥናታዊ ፊልሞችንና የተፃፉ ድርሳናትን ስላነበብኩ ነው፡፡ ለካስ የኢዲ አሚን ታሪክ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ (እናንተ በዓለም ላይ ቀላል ቀልደዋል እንዴ!) ሰው በሊታ (cannibal) እንደሆኑ የሚነገርላቸው ኢዲ አሚን፤ የሰው ሥጋ ጨው ጨው ይላል በሚል ሰብዓዊነት የራቀው ንግግራቸውም ይታወቃሉ፡፡
በጭካኔያቸው ወደር አይገኝላቸውም፡፡ የመንግስት ባለሥልጣኖቻቸው ከሥልጣን መባረራቸውን የሚሰሙት በቴሌቪዥን በሚሰጡት መግለጫ ነበር፡፡ የዓይኑን ቀለም ያልወደዱትን የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ዜጋ ለማስገደል አፍታም አይፈጅባቸውም የሚባሉት አሚን፤ በተመሳሳይ ወቅት ከነበሯቸው ሦስት ሚስቶቻቸው መካከል አንደኛዋ ያረገዘችውን ፅንስ በማስወረዷ ሁለት እግሮቿን ያስቆረጡ አረመኔ ናቸው፡፡ በዚህም ቢበቃቸው ጥሩ ነበር፡፡ እሳቸው ግን የተቆረጡት እግሮቿ ተመልሰው እንዲሰፉላት ሃኪሙን አዘዙት፡፡ ተፀፅተው ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ተጨማሪ ጭካኔ አምሯቸው ነው፡፡ እናም የሴትየዋ እግሮች ተዟዙረው እንዲሰፉ ትዕዛዝ አስተላለፉ - የግራው ወደቀኝ፤ የቀኙ ወደግራ፡፡ (አያችሁልኝ የጭካኔያቸውን መጠን!)
ኢዲ አሚን፤ ከዓለም አገራት ጋር በነበራቸው ኮሜዲ የመሰለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ይታወቃሉ፡፡ በለንደን የመጀመርያውን መንግሥታዊ ጉብኝት ያደረጉት አ.ኤ.አ በጁላይ 1917 ዓ.ም ነበር፡፡
ስሙ መንግሥታዊ ጉብኝት ይባል እንጂ ታሪኩስ ሌላ ነው፡፡ ኢዲ አሚን ለንደን የገቡት ሳይጠበቁ ነው- ድንገት! ስለጉብኝታቸው ለእንግሊዝ መንግሥት አላሳወቁም፡፡ ከአውሮፕላን እንደወረዱም ከእነአጃቢዎቻቸው ሆቴል ውስጥ ነበር ያረፉት፡፡
በመንግስታዊ ፕሮቶኮል መሰረትም በነጋታው ከንግስቲቱ፣ ከጠ/ሚኒስትር ኤድዋርድ ሂዝና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰር አሌክ ዳግላስ-ሆም ጋር ምሳ መጋበዝ ነበረባቸው፡፡ በቡና ሰዓት ላይ ታዲያ ንግስቲቱ ለኢዲ አሚን ጥያቄ አቀረቡ - “ሚ/ር ፕሬዚዳንት፤ የድንገተኛ ጉብኝትዎን ምክንያት እስቲ ይንገሩኝ”
አሚን መልስ ለመስጠት አፍታም አልፈጀባቸውም “ንግሥት ሆይ፤ እቃ ለመግዛት ፈልጌ ነው --- ኡጋንዳ ውስጥ 14 ቁጥር ጫማ ማግኘት እንዴት አስቸጋሪ መሰለሽ!” (ከኡጋንዳ አውሮፕላን ተሳፍሬ የመጣሁት ጫማ ለመግዛት ነው እያሉ ነው!!) ይሄኔ ንግሥቲቱ ምን ይበሉ? የፕሬዚዳንቱን አባባል እንደ ቀልድ ሊቆጥሩት ወደዱ! (ሌላ ምርጫ አልነበራቸውማ!) አሚን ወደ አገራቸው ኡጋንዳ መመለሻቸው ሲደርስ ግን ምክር ቢጤ ተለገሳቸው - መንግሥታዊ ጉብኝት ከመደረጉ በፊት ለአገሩ መንግስት ቀደም ብሎ ማስታወቅ እንደሚገባ፡፡
እቺን ይዘው አገራቸው የገቡት አሚን፤ ሌላ ጊዜ ለንደን መሄድ ያምራቸዋል፤እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 1975 ዓ.ም ላይ፡ እናም ፕሬዚዳንቱ ለቤኪንግሃም ቤተመንግሥት የሚከተለውን ደብዳቤ እንደላኩ ሬዲዮ ካምፓላ አስታወቀ፡፡
የእኔዋ ውድ ንግሥት፡-
በዚህ ዓመት ኦገስት 4 ለንደን ለመምጣት አስቤአለሁ፡፡ ይሄን ደብዳቤ የፃፍኩትም በቆይታዬ ወቅት የሚያስፈልጉኝን ነገሮች አንዳችም ነገር ሳይጓደል ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ እንድታገኚ ነው፡፡ በተለይ የምግብ ነገር ያሳስበኛል፤ ምክንያቱም በአስፈሪ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ እንደሆናችሁ አውቃለሁና፡፡ በተጨማሪም ስኮትላንድ፣ አየርላንድና ዌልስን መጐብኘትና የእናንተን ኢምፔሪያሊስታዊ ጭቆና ከሚዋጉት አብዮታዊ መሪዎች ጋር መገናኘት ስለምሻ ይሄንኑ እንድታመቻችልኝ እፈልጋለሁ፡፡
አያችሁልኝ… እኚህን አምባገነን! መንግሥታዊ ጉብኝት ለማድረግ በቅድምያ ለአገሩ መንግስት ማስታወቅ ያስፈልጋል የሚለውን ምክር መተግበራቸው እኮ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ አሚን የእንግሊዟን ንግስት ኤልዛቤት “ሊዝ” ሲሉ በማቆላመጥ በፃፉላቸው ቴሌግራም “እውነተኛ ወንድ ማግኘት የምትፈልጊ ከሆነ አገሬን ትጐበኚ ዘንድ እጋብዝሻለሁ” ብለዋቸው ነበር፡፡(እሳቸው ማንን ሊፈሩ?!) ደፋሩ አሚን የንግስቲቱ አገር ከገባችበት አስከፊ የኢኮኖሚ ድቀት ለማውጣት “አንድ መርከብ ሙሉ አትክልት” ወደ ብሪቲሽ መላካቸውን በሬዲዮ አስነግረዋል (ሲተረተሩ እኮ ነው!) በቅኝ ግዛት ዘመን በአገራቸው የነበረው የስኮትላንድ ጦር ሠራዊት አባል በመሆን ውትድርናን የተቀላቀሉት አሚን፤ መንግሥታዊ ጉብኝት በማያደርጉ ጊዜ ቴሌግራም መላክ ያስደስታቸው ነበር ይባላል፡፡
(ለስንቱ አገራትና መሪዎች እንደላኩ አልነግራችሁም!) በአሜሪካ የወተርጌት ቅሌትን ምክንያት በማድረግ ለፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን የላኩት ቴሌግራም እንዲህ ይላል - “አገርህ ካልተረዳችህ ቀጥ ብለህ ወደሚወድህ አባትህ አሚን ዘንድ መምጣት ትችላለህ፡፡ ሁለቱም ጉንጮችህ ላይ ስሜሃለሁ” በስተመጨረሻም እንዲህ የሚል ምክር ቢጤ አስፍረዋል - “የአገር ሰላምና መረጋጋት አደጋ ውስጥ በሚገባ ጊዜ እንደአለመታደል ሆኖ ብቸኛው መፍትሄ የተቃዋሚዎችን መሪዎች ማሰር ነው” (እንደ አገራቸው ኡጋንዳ ማለታቸው ነበር!) ለወቅቱ የሶቭየት ህብረትና የቻይና መሪዎች - ሊዎኒድ ብሬዥኔቭ እና ማኦ ትሴ-ቱንግም ተከታዩን ቴሌግራም ልከዋል፡- “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰለሶቭየት ህብረትና ቻይና ብዙ እያሰብኩና እየተጨነቅሁ ነው፤ ደስተኛ ሆናችሁ ማየት እፈልጋለሁ፤ ግንኙነታችሁ የወዳጅነት ዓይነት አይደለም፤ አስታራቂ ከፈለጋችሁ ላገለግላችሁ ዝግጁ ነኝ” (የጠየቃቸው እኮ የለም!) በዮም ኪፑር ጦርነት ወቅት ደግሞ ለእስራኤል መንግሥት በላኩት ቴሌግራም - “ሽንፈታችሁን ተቀብላችሁ ትጥቅ እንድትፈቱ አዝዤአለሁ” ብለው ነበር - (እንደልቡ የነበሩት አሚን!)
ቱርክ ሳይፕረስን በወረረች ማግስት ለቱርክ መንግሥት እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ፡- “ወታደራዊ እቅዳችሁንና የወረራውን ፊልም መመልከት እችል ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ጦር ሰራዊቴ በደቡብ አፍሪካ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በሚነሳ ወቅት ይጠቅመኛል” ቀልድና ቁምነገራቸው የማይለየው አምባገነኑ መሪ ፤ የጦር ሰራዊታቸው በደቡብ አፍሪካ ላይ ለሚሰነዝረው ጥቃት ወታደራዊ ልምምድ ያደርግ ዘንድ ታንዛንያን እንዲወር ትእዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡
ይሄኛው ግን ህይወታቸውን ሊያሳጣቸው ነበር፤ እድሜ ለሊቢያው አምባገነን መሪ ሙአመር ጋዳፊ እንጂ! አ.ኤ.አ በአፕሪል 1979 ዓ.ም በታንዛንያ ጦር ሠራዊትና በኡጋንዳ አማፅያን ከመገደል የተረፉት ጋዳፊ በላኩላቸው የግል አውሮፕላን ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ ኢዲ አሚን ከአብዛኞቹ አምባገነን መሪዎች በአንድ ነገር ይለዩ ነበር፡፡ በማስመሰል ማንም አያማቸውም፤ ሁሉን ነገር ፊትለፊት በመናገር ነበር የሚታወቁት፡፡ በሙስና ሲወነጀሉ እንኳ ፈፅሞ አላስተባበሉም (ሃቀኛው አሚን!) “አገር መምራት ትልቅ ቢዝነስ እንደመምራት ነው፤ ዳጐስ ያለ ደሞዝ ለራስህ መሸለም አለብህ!!” ነበር ያሉት - እንደ አፍሪካ አምባገነኖች ሳይሸፋፍኑ!! የዛሬውን ፖለቲካዊ ወግ ከመቋጨቴ በፊት በዚሁ የአምባገነኖች መፅሃፍ ውስጥ ጋዜጠኛ ሪካርዶ ኦሪዚዮ፤ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ጋር ካደረገው ቃለምልልስ ጥቂት መስመሮች ተርጉሜ ላስነብባችሁ ወደድኩ - ለቅምሻ ያህል፡፡
“ወደ አዲስ አበባ እመለሳለሁ ብለው ያስባሉ?”
“ኢትዮጵያን ከህይወቴ አስበልጬ እወዳታለሁ ”
“የሚቆጭዎት ነገር አለ?”
“አለ እንጂ! በአፍሪካ እጅግ ጠንካራውን ጦር ሰራዊት አቋቁሜ ነበር፤ በዓለም በአደረጃጀቱ ምርጥ የሚባል ፓርቲም መሥርቼአለሁ፤እናት ልጇን ከአደጋ እንደምትከላከለው ሁሉ እኔም የአገሬን ዳር ድንበር ተከላክዬአለሁ፤ግና ምን ያደርጋል--- ሁሉም ነገር ከንቱ ሆነ”
“በዲሞክራሲ ያምናሉ?”
“ዲሞክራሲ የሚሰራው አውሮፓ ውስጥ ነው፤ የአፍሪካ ባህል የተለየ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን ተመልከት፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አምጥተናል ይላሉ፤ ነገር ግን በትክክል ያመጡት ጎሰኝነትን ነው፤ሁሉም የተደራጀው በፓርቲ ሳይሆን በጎሳው ወይም በሃይማኖቱ ነው - በሱዳን፣ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ፣ በኮንጎ፣ በኬንያ--- በሁሉም ቦታ እንደሚታየው፡፡ በዚህ የተነሳ ዓለም ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀው ጦርነት በአፍሪካ ውስጥ መከሰቱ አይቀርም፡፡ አስከፊ የጎሳ ጦርነት!”
በመጨረሻ ጋዜጠኛው፤ አምባገነን መሪዎቹን ያሉበት ድረስ ሄዶ (ተመላልሶ ማለት ይሻላል) ለማነጋገር ያሳለፈውን ውጣ ውረድ በከተበበት የመፅሃፉ መግቢያ ላይ እንዲህ ይላል- “አምባገነኖቹ የሚናገሩት እውነት ይሁን አይሁን አላውቅም (አንዳንዶቹን ጉዳዮች ማለቱ ነው) ይቅር እንላቸው አንላቸው እንደሆነም እንኳ የማውቀው ነገር የለም ፤በእርግጠኝነት ማድረግ የምንችለው አምባገነኖቹን ማጥናት ብቻ ነው፡፡
ምናልባት ይሄ ጥረት ስለራሳችን የላቀ ግንዛቤ እንድናገኝ ያግዘን ይሆናል” እውነቱን እኮ ነው! እነኢዲ አሚንም ሆኑ መንግስቱ ኃ/ማርያም፤ እነቦካሳም ሆኑ ሚሎሶቪች ከሌላ ፕላኔት የመጡ አይደሉም - ከራሳችን ጉያ የወጡ እንጂ፡፡ እናም ስለአምባገነን መሪ የሚደረግ ጥናት ሁሉ አምባገነኑ የወጣበትን ህብረተሰብ የበለጠ ለመገንዘብ ይጠቅመናል በሚለው እንስማማለን፡፡ ዋናው መፍትሄ ግን አምባገነንነትን ማጥፋት ነው፡፡ ሳይንቲስቶች ጉዳዬ ቢሉት እኮ ማጥፊያ መላ አያጡለትም - በክኒን ወይም በመርፌ መልክ አሊያም በቀዶ ጥገና ሊሆን ይችላል፡፡

Read 4242 times