Print this page
Sunday, 03 March 2013 00:00

የኮንዶምኒዬም ልዩ ኮታ ለመንግስት ሰራተኞች! ልዩ ኮታው… ለፓርቲ አባላት መሆኑ ነው?

Written by  ቶማስ
Rate this item
(3 votes)

ቢሆንስ ምን ችግር አለው? “ህዝብ” ናቸዋ!
ችግር ቢኖረውስ የት ይደረሳል? ዝም ነው!
ብዙዎቻችን ፈቅደን ያስጀመርነው አይደል!
የመንግስት ሰራተኞች ከሌላው ዜጋ የበለጠ የኮንዶምኒዬም ኮታ እንደሚመደብላቸው ባለፈው ቅዳሜ እለት ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲናገሩ በጣም ነበር የገረመኝ። የመንግስት ሰራተኞች ከሌላው ዜጋ በምን ይበልጣሉ? በርካታ የፓርቲ አባላትን ስላሉበት ነው ልዩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው? አይን ያወጣ አድልዎ መስሎ ስለሚታየኝ ነው የተገረምኩት፤ የደነገጥኩት። ረጋ ብዬ ሳስበው ግን፤ ለካ ያን ያህልም አስገራሚ አይደለም። “ኧረ ጉድ!” የሚል ሰውም አላጋጠመኝም። ደግሞም አዲስ የተፈጠረ ነገር የለም። የመንግስት ችሮታ፣ ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ የአገራችን ባህል ነው። 
የድሮ ነገስታት፣ በነሱ ፊት ከሌላው ሰው በልጦ ለታያቸው “አገልጋይ”፣ ልዩ ድጋፍ ያደርጉ ነበር። “አገር ያቀና”፣ “በታማኝነት ያገለገለ”፣ “በትውልድ ሃረጉ የከበረ”፣ “በእምነቱ የፀና” … በሚሉ የተለያዩ ሰበቦች መሬት ይሰጡታል፤ መተዳደሪያ ገቢ የሚያገኝበት ግዛት ይሸልሙታል። እንደፈቃዳቸውም፣ ላሰኛቸውና ስሜታቸውን ለነካው ሰው ወይም ተወዳጅነትን ያስገኛል ብለው ሲያስቡ ለመንገደኛ ሁሉ ምፅዋት ለመስጠት እጃቸውን ይዘረጋሉ። አልያም፣ “ስጠው” ብለው የግምጃ ቤት ተቆጣጣሪውን ያዝዙታል። አልያማ ንጉስነታቸውና መንግስትነታቸው ምኑ ላይ ነው?
በእርግጥ ነገሥታት መሬት ጠፍጥፈው አይሰሩም። ማሳ አርሰውና ብረት ቀጥቅጠው መተዳደሪያ ገቢ አያመርቱም። ግን ችግር የለውም። ያው፤ ከአንዱ ዜጋ መሬት ነጥቀው ለሌላው ይሰጣሉ። ዜጎችን እያስገበረ መተዳደሪያ ገቢ እንዲያገኝ፣ ከወንዙ ማዶና ከተራራው ወዲህ ያለውን ግዛት ሰጥቼሃለሁ ይሉታል። ትንሽ ቆንጥረው ለተወሰኑ ዜጎች በምፅዋት ያከፋፍላሉ። “ለተቸገረ የሚያበሉ የድሃ አባት” ተብለው ይወደሳሉ - ከተወሰኑ ዜጎች ከወሰዱት ግብር እና ከነጠቁት ንብረት ቆንጥረው ስለሰጡ። ለነገሩ “የዜጎችን ንብረት እየነጠቁ” መባል የለበትም። የአገሬው ንብረት ሁሉ የንጉሡ ወይም የመንግስት ስለሆነ። ደርግ የዜጎችን ንብረት የወረሰውም በዚሁ ሂሳብ ነው።
አሁንስ ቢሆን፣ መንግስት ከአምራች ዜጎች በተለያዩ የግብር እና የታክስ አይነቶች አማካኝነት ገንዘብ የሚወስደው፤ የዜጎች መብት ለማስከበር ነው እንዴ? ፖሊስና ፍርድ ቤት ለመሳሰሉ የህግ እና የፍትህ አካላት የሚሰበሰበው ግብር ኢምንት ነው። ይልቅ አብዛኛው ገንዘብ የሚውለው፤ “ለልማት” ነው። ለምሳሌ ኮንዶሚኒዬም ገንብቶ ለማከፋፈል። ዜጎች ባዋጡት ገንዘብ ልክ፣ ኮንዶሚኒዬም የሚያገኙ ቢሆን ኖሮ፣ በገበያ ህግ ይከናወን ነበር - በከፈልከው መጠን ጥቅም ማግኘት። መንግስት የኮንዶሚኒዬም ግንባታ ውስጥ የሚገባበት ምክንያት አይኖርም ነበር። ከአንዱ ዜጋ ገንዘብ ወስዶ ለሌላው መስጠት ግን፣ በገበያ ህግ ሊፈፀም አይችልም። በመንግስት ሃይል እንጂ።
ታዲያ ኮንዶሚኒዬም የሚያስገነባ መንግስት ፤ ለመንግስት ሰራተኞች ልዩ ኮታ እመድባለሁ ቢል ያስገርማል? ከአንዱ ወስዶ ለሌላ የመስጠት ስልጣን፣ የአገራችን ነባር ባህል ነው፤ አዲስ የተፈጠረ ነገር የለም። ደግሞም፣ እስካሁን የተቃውሞ ድምፅ የሚያሰማ ሰው አላየሁም።
የመንግስት ሰራተኞች በህግ ፊት… (ማለቴ በመንግስት ፊት) ከሌላው ዜጋ ልቀው ቢታዩና ልዩ ኮታ ቢመደብላቸው ተገቢ ነው እያልኩ አይደለም። ተገቢ የሚሆንበት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የለም። እንዲያውም፣ ሙሉ ለሙሉ በተሳሳተ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ መጥፎ ውሳኔ ነው። “ሁሉም ዜጋ በህግ ፊት እኩል ነው” የሚለውን የህግ የበላይነት መርህን በግላጭ የሚጥስ ውሳኔ ቢሆንም፣ ያን ያህልም ተቃውሞ የሚያጋጥመው አይመስለኝም። ነገር የተበላሸው፣ የኮንዶምኒዬም የኮታ ምደባ ላይ ሳይሆን፣ ገና ድሮ ከታች ከመሰረቱ ነው። “መንግስት በዜጎች ምርትና ንብረት ላይ የማዘዝ ስልጣን ሊኖረው ይገባል” የሚል ለግለሰብ ነፃነት ዋጋ የማይሰጥ አስተሳሰብ ነው የችግሩ መንስኤ። መንግስት፣ ከአንዳንድ ዜጎች ንብረት ወይም ገንዘብ የመውሰድና ለሌሎች ዜጎች የመስጠት ስልጣን እንዲኖረው ብዙ ሰዎች የሚፈልጉ መሆናቸው ነው ዋናው ችግር። ለግለሰብ ነፃነት ዋጋ ሳንሰጥ፤ “የህግ የበላይነት ተጣሰ፤ አድልዎ ተፈፀመ” ብለን መቃወምና መከራከር ለውጥ አያመጣም።
“አገራዊ መግባባት” - ከአበበ ገንዘብ ወስዶ ኮንዶምኒዬም ለከበደ
ለጥበቃ ደሞዝ የሚከፈለው ባለጠመንጃ፣ የማስገደድ ሃይል ስላለው፣ ከሃላፊነቱ ውጭ ድንገት ተነስቶ፣ የመንደሩ ነዋሪዎች ላይ አዛዥና ተቆጣጣሪ ለመሆን ቢወስን፤ ከእርስዎ የስራ ውጤትና ምርት (ማለትም ከንብረትዎ) ላይ ሲሶውን ነጥቆ ለጎረቤትዎ ኮንዶሚኒዬም ሰርቶ ቢሰጥ ተገቢ ነው? ከወር ገቢዎ 30 በመቶ፣ እንደገና በየእለቱ 15 በመቶ መውሰድ አልበቃ ብሎት “ ለወደፊት ህይወትህ ስለማስብልህ በወር ከገቢህ ሌላ 5 በመቶ እየወሰድኩ አስቀምጥልሃለሁ” ቢልዎ፤ በእሺታ ይቀበሉታል? “የመንደሩን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መምራትና መቆጣጠር መብቱ ነው” ብለው ይስማሙለታል? ወይስ፣ “ይሄማ እብደት ነው” ብለው ይቃወሙታል? መቼም፣ እያንዳንዱ ሰው፣ የራሱ ሃሳብና አቋም ላይ ወይም የራሱ እምነትና ሃይማኖት ላይ እንጂ በሌላ ሰው ሃሳብና ሃይማኖት ላይ መብት እንደሌለው ያውቃሉ። በዚያው ልክ፣ “እያንዳንዱ ሰው፣ በራሱ ምርትና ንብረት እንጂ በሌላ ሰው ምርትና ንብረት ላይ ስልጣን የለውም” ብለው ለነፃነትዎ ይከራከራሉ? የሃሳብና የንብረት መብትዎን ለማስከበር ይጥራሉ? ለግለሰብ ነፃነትና መብት ትልቅ ክብር ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ ማለት ነው።
ባለጠመንጃው፣ የዝርፊያ ድርጊቱ እንደ ቅዱስ ተግባር እንዲቆጠርለት የማመካኛና የሰበብ መአት ሊደረድር ይችላል። “ንብረታችሁን የምወስድባችሁ፤ የድሆችና የአቅመ ደካሞች አለኝታ ስለሆንኩ ነው”፣ “ለመንደራችን ልማትና ለፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ግንባር ቀደም ተቆርቋሪ ነኝ”፣ “ራዕይ ይኑራችሁ፤ በኔ አመራርና በመንደሩ ነዋሪዎች ንቁ ተሳትፎ ወደ አዲስ የህዳሴ ምዕራፍ እንሻገራለን” … እያለ ይሰብካል። ግን ባለጠበንጃው ብዙ ብዙ ቢናገር እንኳ በፕሮፓጋንዳው ተማርከን፣ “የዝርፊያና የንጥቂያ መብት አለው” ብለን እንገብርለታለን? መንግስት ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈፅም ግን፤ “የአገሪቱን ኢኮኖሚ መምራትና መቆጣጠር የመንግስት መብት ነው፤ ተገቢ ስልጣን ነው” ብለን ብዙዎቻችን ተቀብለናል። እያንዳንዱ ሰው በምርቱና በንብረቱ ላይ የማዘዝ ነፃነትና መብት የለውም እንደማለት ነው። ለግለሰብ ነፃነትና መብት ክብር የለንም ማለት ነው።
መንግስት ባሰኘው መጠንና ደረጃ፣ በዜጎች ምርትና ንብረት ላይ ዋና አዛዥ መሆን እንደሚገባው ብዙዎቻችን አምነን ተቀብለናል። ብዙዎቻችን እንስማማበታለን። አንዳንድ የማያስማሙና የሚያወዛግቡ ጥቃቅን ጉዳይች ይኖራሉ። የትእዛዙ ክብደትና የንጥቂያው መጠን፣ የንጥቂያ ሰለባዎቹና የንጥቂያ ተቋዳሾቹ ማንነት… ፓርቲዎችን እያወዛገበ ፖለቲከኞችን እንደሚያከራክር አይካድም። “የመንግስት ስልጣን ላይ ማን ይቀመጥ?” ከሚለው ጥያቄ ጋር ተያይዞም፣ የባለስልጣኑ ማንነት ላይ ላንግባባ እንችላለን። እገሌ ይንገስ፣ እገሌ ይግዛ እያልን እንነታረካለን። የገዢው ፓርቲ ማንነት ላይ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ያኛው ፓርቲ እና ይሄኛው ፓርቲ ስልጣን ለመያዝ የተቀናቃኝነት ሽኩቻ ይኖራል። መጋጨትና መጠፋፋትም ይከሰታል። እንዲያም ሆኖ በመሰረታዊው ሃሳብ ላይ ሙሉ ለሙሉ ይስማማሉ። መንግስት፣ በዜጎች ምርትና ንብረት ላይ የማዘዝ፣ እንዲሁም ከአንድ ዜጋ ገንዘብ ነጥቆ ለሌላ የመስጠት ስልጣን ሊኖረው እንደሚገባ፣ ሁሉም ፓርቲዎችና አብዛኞቹ ዜጎች ያምናሉ - “አገራዊ መግባባት” ልትሉት ትችላላችሁ።
የመንግስት ኮንዶምኒየምና የግለሰብ ነፃነት አይጣጣሙም
“መንግስት ኢኮኖሚውን መምራትና መቆጣጠር አለበት” መባሉ፣ አዲስ ሃሳብ አይደለም። ጥንታዊ ሃሳብ ነው። እንዲያውም፣ የዜጎች ምርትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ሃሳብና አቋማቸው፣ ወይም እምነትና ሃይማኖታቸውም በመንግስት ቁጥጥር ውስጥ ነበር።
“በዜጎች ሃይማኖትና በዜጎች ኢኮኖሚ ውስጥ፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነትና የበላይነት”፤ የአገሪቱ ባህል ነው - ለበርካታ ምዕተአመታት የነገሰና ስር የሰደደ ክፉ ባህል። “ሃይማኖትና መንግስት መነጣጠል አለባቸው” የሚለው አስተሳሰብ የሚያስፈልገውም፣ በሌላ ምክንያት ሳይሆን የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት ለማስከበር ነው - መንግስት የሰዎችን ነፃነት የመጣስ ስልጣን እንዳይኖረው ለመገደብ።
“ማንኛውም ሰው በራሱ ሃሳብና በራሱ ሃይማኖት ላይ ሙሉ ነፃነት አለው። ማለትም ማንኛውም ሰው (በተለይ ደግሞ ይህንን ነፃነት እንዲያስከብር ለጥበቃ ጠመንጃ የታጠቀው የመንግስት ባለስልጣን)፣ በሌላ ሰው ሃሳብና ሃይማኖት ላይ ቅንጣት ስልጣን የለውም” የሚል ቁም ነገር ይዟል - የሃይማኖትና የመንግስት መነጣጠል። የሃይማኖት ነፃነትን ያካተተ የሃሳብ ነፃነት እንዲከበር ከፈለግን፤ ለግለሰብ ነፃነት በፅናት የምንቆም ከሆነ፤ ልናከናውናቸው ከሚገቡ ተግባራት መካከል አንዱ፤ ሃይማኖትና መንግስት እንዲነጣጠሉ ማድረግ ነው። መንግስትና ኢኮኖሚ እንዲነጣጠሉ ማድረግስ?
እንግዲህ፣ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምርትና ንብረት ላይ ሙሉ ነፃነት አለው። ማንኛውም ሰው (በተለይ የንብረት መብትን እንዲያስከብር የጥበቃ መሳሪያ የታጠቀው የመንግስት ባለስልጣን)፣ በሌላ ሰው ምርትና ንብረት ላይ ቅንጣት ስልጣን የለውም” ከተባለ፤ መንግስትና ኢኮኖሚ ተነጣጥለው የነፃ ገበያ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ መስፈን አለበት ማለት ነው። መንግስት፤ ለፖሊስ፣ ለፍርድ ቤትና ለመከላከያ ሃይል ስራዎች ከሚያስፈልገው ገንዘብ በላይ ከዜጎች አንዲት ሳንቲም መውሰድ አይችልም ማለት ነው። የታክሲዎችን የጉዞ መስመር በበላይነት የማዘዝ ስልጣን አይኖረውም፤ የዋጋ ቁጥጥር አያውጅም፤ በሁለት አመት ስራ ይጀምራል የተባለ ፋብሪካ ለመትከል 10 አመት ሙሉ ገንዘብ አያባክንም። ኮንዶሚኒዬም እያስገነባ ኮታ አይደለድልም… በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ እጁን አያስገባም። ለምን? የግለሰብ ነፃነት እንዲከበር ነዋ። እያንዳንዱ ሰው፣ በራሱ ምርትና ንብረት ላይ ነፃነት ካለው፤ መንግስትና ኢኮኖሚ መነጣጠል ይኖርባቸዋላ። አይደለም እንዴ?
ብዙ ሰዎች ይህንን መስማት አይፈልጉም። በአጋጣሚ ቢሰሙ እንኳ፣ “ይሄማ ሊሆን አይችልም፤ ቅዠት ነው” ብለው ያጣጥሉታል። ለነገሩ፣ ከ50 አመታት በፊትስ፣ “ሃይማኖትንና መንግስትን መነጣጠል ቅዠት ነው” ተብሎ ይታሰብ አልነበር? ከምር ስናየው ግን ለካ ቅዠት አይደለም። በኔ ሃሳብና ሃይማኖት ላይ ሌላ ሰው ምን ያገባዋል? መንግስትስ ምን ያገባዋል? ይልቅስ፤ “እኛ ባዘዝንህ መንገድ ብቻ አስብ፣ መንግስት ባወጀልህና በፈቀደልህ መንገድ ብቻ እመን” ስንባባል ነው፤ ቅዠት የሚሆነው። መንግስት፣ በዜጎች ሃሳብና ሃይማኖት ላይ የበላይ አዛዥ ሲሆን፤ ወይም ጣልቃ ሲገባ፣ በዚያው መጠን የእያንዳንዱ ሰው የሃሳብና የሃይማኖት ነፃነት ይጣሳል። የመንግስት የበላይነትና የሰዎች ነፃነት አብረው ሊሄዱ አይችሉምና።
ኢኮኖሚ ላይም ተመሳሳይ ነው። ወይ፤ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምርትና ንብረት ላይ ነፃነቱ ይከበራል - በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ የካፒታሊዝም ስርዓት ማለት ነው። አልያም የግለሰብ ነፃነትን የሚያንቋሽሹ ሶሻሊስቶች እንደሚሉት፤ መንግስት ያሻውን ያህል ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር “መብት” ይኖረዋል። የግለሰብ ነፃነትና የመንግስት የበላይነት ተቃራኒዎች ናቸው - አብረው ሊሄዱ አይችሉም። ታዲያ፣ ሁለቱንም ሃሳቦች መርምረን፣ ትክክለኛውን ለይተን መምረጥ እንዴት ያቅተናል? ብዙ ሰዎች ለመመርመርም ሆነ ለመምረጥ አይፈልጉም። ሶሻሊዝም “ትክክለኛና ቅዱስ ሃሳብ” እንደሆነ እያመኑ፤ በተግባር ግን ከተቃራኒው ከካፒታሊዝም ጋር እየቀየጡ ለማስኬድ ይመኛሉ። ለምን?
ማምረትና መንጠቅ ሲቀየጡ፤ አምራቹ ይከስራል
በአንድ በኩል፣ ትክክል ነው ብለው የሚያምኑበት የሶሻሊዝም ሃሳብ ጎጂና አጥፊ ይሆንባቸዋል። ለምሳሌ፣ ደርግ በሞከረው አቅጣጫ፣ የሰው ንብረት እየተወረሰ ወደለየለት ሶሻሊዝም መጓዝ ያስፈራቸዋል። ለምን አይፈሩ! እልቂትንና ረሃብን ቢፈሩ አይፈረድባቸውም። ስለዚህ በከፊል ብቻ እየተገበሩ ሙሉ ለሙሉ ያምኑበታል። በሌላ በኩል፣ ስህተት ነው የሚሉት የካፒታሊዝም ሃሳብ ጠቃሚና አልሚ ሲሆን ያዩታል - ፍፁም ሳያምኑበት በከፊል ይተገብሩታል። ለእምነታቸው ሲሉ ሶሻሊዝምን በከፊል መተግበር፤ ለኑሮ ያህል ደግሞ ካፒታሊዝምን በትንሹ መተግበር!
ከሶሻሊዝም ወይም ከካፒታሊዝም፣ ትክክለኛውን መርጠው ለምን ሙሉ ለሙሉ አይተገብሩትም? …ትክክለኛውና ጠቃሚው ሃሳብ የትኛው ነው? “ሶሻሊዝም… ካፒታሊዝም… እያልን ኢዝም ብንዘረዝር ዳቦ አይሆነንም። ቲዎሪ ሌላ ተግባር ሌላ!” ብለው ከጥያቄው ለማምለጥ የሚሞክሩ ይኖራሉ። ማሰብ አይጠቅምም ማለታቸው ነው። ጥያቄውን ትርጉም አልባ የቃላት ምርጫ ሊያስመስሉት ቢሞክሩም፤ ቁምነገሩን መሰረዝ አይችሉም። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምርትና ንብረት ላይ ነፃነት አለው? ወይስ በመንግስት ትእዛዝ ስር ነው? … ይሄው ነው የካፒታሊዝምና የሶሻሊዝም ጥያቄ።
የቅይጥ ስርዓት አፍቃሪዎች እንዲህ ብለው ይመልሳሉ፡ “ይሄኛውን ወይም ያኛውን መምረጥ አያስፈልግም። ጥቁር እና ነጭ እያደረግን ማየት የለብንም። ይሄኛው ትክክል ነው፤ ያኛው ስህተት ነው እያልን ፅንፍ ድረስ አንሂድ” በማለት ይሰብካሉ። “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ንብረት ላይ ነፃነት አይኑረው አይባልም፤ ይኖረዋል…” በማለት ይነሱና፤ የግራጫ መንገድ ስብከታቸውን ሲያሳርጉ “መንግስትም በሰዎች ንብረት ላይ የማዘዝ (ኢኮኖሚውን የመምራትና የመቆጣጠር) ስልጣን ይኖረዋል” ብለው ይደመድማሉ። “ስለዚህ የግለሰብ ነፃነት እንዲከበር በፅናት መከራከር ስህተት ነው?” ብሎ የስብከቱ ማሳረጊያ ከስበከቱ መነሻ ጋር እንደሚቃረን የሚነግራቸው ሰው ቢመጣ አይሰሙትም።
እንዲያውም፤ በተቃራኒ ሃሳቦች ውስጥ መንቦራጨቅና መጨቅየት የመራቀቅ ምልክት እንደሆነ አስመስለው ለማቅረብ ይሞክራሉ - ሃሳቦችን አጥርቶ ለማየትና ለማሰብ መሞከር የአላዋቂነት ምልክት። “በጥቁርና በነጭ ማሰብ የለብንም። የግለሰብ ነፃነትን ማክበር ተገቢ እንደሆነ እንቀበል፤ መንግስት የህዝብን ፍላጎቶች የማሟላት ሃላፊነትም አለበት። ስለዚህ የግለሰብ ነፃነትን የሚጥስ የመንግስት ስልጣንም ተገቢ እንደሆነ መማመን አለብን” በማለት ያብራራሉ (ብርሃንን አጥፍተው ያጨልማሉ ቢባል አይሻልም?)
ለመሆኑ፤ መንግስት የህዝቡን የኢኮኖሚ ፍላጎት ለምሳሌ የምግብ፣ የልብስና የመኖሪያ ቤት ፍላጎቶችን ማሟላት አለበት ወይ? … “አዎ፤ ማሟላት አለበት፤ ይሄማ ትክክለኛ ሃሳብ ነው” ይላል ብዙ ሰው። መንግስት እንዴት አድርጎ፣ ከየት አምጥቶ ነው የሚያሟላው? መቼም፣ በራሱ ጥረት አርሶ፣ በራሱ ገንዘብ ፋብሪካ አቋቁሞ፣ በራሱ የአእምሮ ችሎታ ቴክኖሎጂ ፈጥሮ፣ ህዝብን የሚያበላና የሚያጠጣ፣ የሚያለብስና ቤት የሚሰጥ መንግስት የለም። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም፤ ዛሬ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እንዲህ አይነት መንግስት ታይቶ አይታወቅም። ወደ ፊትም ሊታይ አይችልም።
የሚያርስ፣ የሚፈበርክና የፈጠራ ችሎታ ያለው ሰው፤ ስልጣን አያስፈልገውም። የስራውን ውጤት ለሌሎች መስጠት ከፈለገ፤ መስጠት ይችላል። የታረሰውን፣ የተፈበረከውንና የተፈጠረውን የስራ ውጤት ከአንዱ ወስዶ ለሌላ ለመስጠት ግን ስልጣን ያስፈልጋል - የማስገበር፣ የመዝረፍ ወይም የመውረስ ስልጣን። ንብረቱ እንዲዘረፍ፣ እንዲወረስ ወይም በግብር እንዲነጠቅ አስደናቂ ፍላጎት የተጠናወተው ህዝብ ካለ፤ በእርግጥም የህዝቡን ፍላጎት የሚያሟላ መንግስት ለማግኘት አይከብድም። “ይሄማ ፀጉር ስንጠቃ ነው። ይሄማ አጉል መፈላሰፍ ነው” … ብለን እንለፈው? ለስንት ዘመናት እንዲህ አድበስብሰንና ሸፋፍነን ስናልፈው ኖረናል። እስቲ ለለውጥ ያህል ገለጥለጥ አድርገን እንየው።
“መንግስት የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት አለበት” ስንል፤ “መንግስት ከአንዳንድ ዜጎች ሃብትና ገንዘብ እየወሰደ ለሌሎች ዜጎች ይስጥ” ማለታችን አይደለምን? ብዙ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙም ሊያስቡበት አይፈልጉም። በእምነት የተቀበሉት “ትክክለኛ ሃሳብ”፣ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይሆናል ብለው ስለማይጠብቁ፤ በተግባር መንግስት ከነሱ ገንዘብ ወስዶ ለሌሎች ይሰጣል ብለው አያምኑም። “ትክክለኛው ሃሳብ” በከፊል ተግባራዊ ቢሆን እንኳ፤ መንግስት ከሌሎች ሰዎች ገንዘብ ሲወስድ፤ “እኛ ተቀባይ፣ ተጠቃሚና ተቋዳሽ እንሆናለን” ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። መንግስት ኮንዶሚኒዬም ቤቶችን እየሰራ ለህዝብ ያዳርሳል ሲባል በደፈናው፤ “ትክክለኛ ሃሳብ፤ ቅዱስ አላማ ነው” ብለው ብዙ ሰዎች ድጋፋቸውን የሚገልፁት፤ በተቻለ መጠን፤ “ከእድለኞቹ መካከል እንደሚካተቱና ተቋዳሽ እንደሚሆኑ” በማመን ነው። ካልሆነም ደግሞ፤ “ለኮንዶምኒዬም ግንባታ ሃብታቸውን ከሚገብሩት ሰለባዎች መካከል ላለመካተት” ተስፋ ያደርጋሉ።
የኮንዶሚኒዬም ተቋዳሽ መሆን ነውር ነው?
መንግስት “ኮንዶሚኒዬም እገነባለሁ፣ አከፋፍላለሁ” ብሎ ከዜጎች ግብር ይሰበስባል። ግብር መክፈል ግዴታ ከሆነ፤ ገንዘብ ከተወሰደብህ አይቀር፤ ከኮንዶሚኒዬም ክፍፍሉ ተቋዳሽ ለመሆን መሞከር ምን ነውር አለው? “የግለሰብ ነፃነትን የሚጥስ ቢሆንም፤ ለጊዜው ምንም ማድረግ አይቻልም። የግብር ህግም ይሁን በኮንዶሚኒዬም ዙሪያ የወጡ ህጎች፣ ሁሉንም ዜጋ ያለአድልዎ የሚያስተናግዱ ከሆነ፤ ቢያንስ ቢያንስ የህግ የበላይነት መርህ ይከበራል ማለት ነው። የህገመንግስቱ አንቀፅ 25 እንዲህ ይላል።
አንቀፅ 25፡ ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም አይነት ልዩነት ሳይደረግ፣ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በዚህ ረገድ፣ በዘር፣ በብሄር፣ በብሄረሰብ፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፓለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው።
ግብር የሚሰበሰበውና የኮንዶምኒዬም ክፍፍል የህግ የበላይነትን በማክበር የሚከናወን ከሆነ፤ ትልቅ ቁምነገር አይደለም እንዴ? ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው የሚለው የህግ የበላይነት መርህ ትክክለኛ መርህ አይደለም እንዴ? ትክክለኛ መርህ ነው። ነገር ግን፤ የህግ የበላይነት፣ የእያንዳንዱን ሰው መብትና ነፃነት ለማስከበር ካልዋለ ምን ዋጋ አለው? እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምርትና ንብረት ላይ ነፃነቱ ሊከበር ይገባል የሚለውን መርህ ስናፈርስ ከርመን፤ “መንግስት የህዝብን ፍላጎት ማሟላት አለበት” በሚል ሰበብ የግለሰብ ነፃነት ትርጉም እንዲያጣ ካደረግን በኋላ፤ “ለህግ የበላይነት” በፅናት የምንቆምበት ሃይል ሊኖረን አይችልም። ለዚህም ነው፤ በኮንዶሚኒየም ስርጭት ላይ፤ ለሴቶች ልዩ ተጨማሪ ኮታ ይመደብላቸዋል የሚል “ህግ” ሲወጣ፤ “ይሄማ የህግ የበላይነትን ያጠፋል” ብሎ የሚቃወም ሰው ያልተገኘው።
መጀመሪያ የግለሰብ ነፃነትን አድበሰበስነው - “መንግስት የህዝብን ፍላጎት ማሟላት አለበት” በማለት። መገበርን፣ ዝርፊያንና ንጥቂያን ተቀብለን፣ ከዝርፊያው ውስጥ መቋደስን ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ አመንን። ሁሉም ሰው በእኩል አይን መታየት አለበት አልን። ቢያንስ ቢያንስ የህግ የበላይነት ይከበራል በሚል። ነገር ግን፣ ከግለሰብ ነፃነት ተለይቶ ለብቻው የተነጠለ የህግ የበላይነት… ብዙም ትርጉም የለውም። “ለሴቶች ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋል” ተብሎ የህግ የበላይነት ሲጣስ በዝምታ የታለፈውም በዚሁ ምክንያት ነው። የህግ የበላይነት የይስሙላ መርህ ሆኖ አረፈው። አሁን ደግሞ፤ “የመንግስት ሰራተኞች ከሌላው ዜጋ የላቀ ልዩ ኮታ ይመደብላቸዋል” ተብሎ ተወሰነ። ምን ማለት ይቻላል? ዝም ነው።

Read 3635 times