Sunday, 03 March 2013 00:00

መኢአድ በአባላትና ደጋፊዎቼ ላይ የሚደርሰው የመብት ረገጣ ተባብሷል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በሃገሪቱ ሶስት ክልሎች በሚገኙ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ ላይ መፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ትላንት በፅ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው በመግለጫው፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል እንዲሁም በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች እና ዞኖች ውስጥ ነዋሪ በሆኑ አባሎቹና ደጋፊዎቹ ላይ ከመንግሥት የስራ አስፈፃሚ አካላት የተለያዩ የመብት ረገጣዎች እንደተፈፀሙባቸው ጠቁሟል።
የመኢአድ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወንድማገኝ ደነቀ፤ በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቡለን ወረዳ በኩቺ ቀበሌ፣ ባሩዳ ቀበሌ፣ በጭራቆ ቀበሌ፣ በአዲስ አለም ቀበሌ፣ በአይደሉ ቀበሌ፣ በኢፃር ቀበሌ እና በማጣ ቀበሌ በድምሩ ወደ 2500 የሚደርሱ የአማርኛ ተናጋሪ አርሶ አደሮች ከ18 አመት በላይ ህጋዊ በሆነ የመሬት ባለቤትነት ፍቃድ የያዙትን መሬት ለቀው እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አንዳንድ ተፈናቃዮችም በፌደራል ፖሊስ እና በአካባቢው ሚሊሽያ በጭነት መኪና ወደ ጐንደር፣ ጐጃም እና ሸዋ አካባቢዎች እንዲሄዱ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ የመኢአድ አመራር አባላት ላይ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረገባቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በሚገኙ የፓርቲው የአካባቢው ተጠሪዎች እና አባላት ላይ የእስራት እንዲሁም የእርሻ መሬት ንጥቂያ እንደተፈፀመባቸው፤ በአማራ ክልል በሚገኙ የፓርቲው አመራር አባላት ላይም ድብደባ እና የእርሻ መሬት ንጥቂያ መፈፀሙን የፓርቲው መግለጫ ያመለክታል፡፡
ፓርቲው በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት ለማስቆም በየደረጃው ላሉ ለየአካባቢው የመንግሥት ተጠሪዎች አቤቱታ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ ሊሰጠው እንዳልቻለ አቶ ወንድማገኝ አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ፓርቲው በዛሬው እለት የሚከበረውን የአድዋ በአል ምክንያት በማድረግ በፅ/ቤቱ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና አባላቱ በተገኙበት የአድዋ በአል መታሰቢያን እንደሚያከብር ገልጿል፡፡

Read 2326 times