Sunday, 03 March 2013 00:00

ሔንከን በ120 ሚሊዮን ዩሮ የቢራ ፋብሪካ ይገነባል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

ሔንከን ቢራ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ በ120 ሚሊዮን ዩሮ ለሚያስገነባው የቢራ ፋብሪካ ከትናንት በስቲያ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ፡፡
የበደሌ እና የሐረር ቢራ ፋብሪካዎችን በመግዛት የኢትዮጵያ ቢራ ገበያን የተቀላቀለው ሔንከን፤ በአዲስ አበባ ክልል ዙሪያ አቃቂ ቂሊንጦ በተባለው ሥፍራ ላይ በሚያስገነባው የቢራ ፋብሪካ በዓመት 1.5 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ቢራ እያመረተ ለገበያ ያቀርባል ተብሏል፡፡
በ18 ወራት ግንባታው ተጠናቆ ሥራውን ይጀምራል የተባለው ፋብሪካው፤ 120 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የሚሆንበት ሲሆን ዘመናዊና እጅግ የተራቀቁ መሣሪያዎች እንደሚኖሩትና ደረጃቸውን የጠበቁና ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ቢራዎችን እንደሚያመርት የሔንከን ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ማስተር ጆን ዶዮር በሥነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ፋብሪካ ለምርት ግብአትነት የሚያውለውን የብቅል ገብስ ለአራት ዓመታት ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ እርሻ ምርምር ኢንስቲቲዩት እና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር ከትናንት በስቲያ ተፈራርሟል፡፡ በዚህ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥና የስምምነት ፊርማ ላይ የተገኙት የሆላንድ የውጭ ንግድ ልማት ትብብር ሚኒስትር ሊላን ፕሎማን እንደተናገሩት፤ የመንግስትና የግሉ ዘርፎች በትብብር መሥራታቸው ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ትብብር ሁለቱንም ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሥራዎችን ያቀላሉ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው በአገራችን መገንባቱ በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጐች የሥራ እድል በመክፈት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቁመው 25ሺ የሚጠጉ አርሶ አደሮችም ለምርት ግብአት የሚውለውን የብቅል ገብስ በማምረት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፀዋል፡፡
ሔንከን ኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያን የቢራ ገበያ ከተቀላቀለበት እ.ኤ.አ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በደሌ ስፔሻል፣ በደሌ ሐረር፣ ሐኪም ስታውት እና ሐረር ሶፊ የተባሉትን ምርቶች ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡

Read 2276 times Last modified on Saturday, 02 March 2013 12:37