Sunday, 03 March 2013 00:00

በኢንዲያን ኢንተርናሽናል ት/ቤት የተማሪዎች ወላጆች ቅሬታ አቀረቡ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 8 በሚገኘው ኢንዲያን ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች፤ ት/ቤቱ የሚያስከፍለው ክፍያና የሚሰጠው አገልግሎት አይመጣጠንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡ “የትምህርት ቤቱ ግቢ ስፋት ለተማሪዎቹ ብዛት አይመጥንም፤ በቂ የመጫወቻ ቦታም የለውም” የሚሉት ወላጆች፤ ክፍሎቹ በኮምፖርሣቶ የተከፋፈሉ ናቸው፤ የህፃናት ማረፊያ መኝታ የለውም፣ ግቢው አቧራና ቆሻሻ ነው” በማለት ት/ቤቱ ዘረፋና ማጭበርበር እየፈፀመባቸው እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በዓመት ከሚከፍሉት ከ10ሺህ ብር በላይ ክፍያ በተጨማሪ የስቴሽነሪ 1050 ብር እንጠየቃለን ያሉት ወላጆች፤ ክፍያውና ልጆቻቸው የሚያገኙት አገልግሎት ፈጽሞ እንደማይመጣጠን ይገልፃሉ፡፡
መጀመሪያ ላይ ቦታው ለትምህርት ቤት አይመጥንም የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን የገለፁት አንዲት ወላጅ፤ የተሻለ ቦታ እስኪገኝ በጊዜያዊነት የሚቆይ ነው የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውሰው፤ ሆኖም ት/ቤቱ ሳይቀየር ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመቱን እንደያዘ ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ኢንተርናሽናል ነው ቢባልም የተሟላ መጽሐፍ እንኳን የለውም፤ ለምን እንዳልተሟላ ስንጠይቅም፤ “ብራችሁ አቅሙ ስለወደቀ ከህንድ መጽሐፍ ማስመጣት አልችልም” የሚል ምላሽ ከህንዳዊው የት/ቤቱ ባለቤት ከሚስተር አብርሃም እንደተሰጣቸው እኚሁ ወላጅ ገልፀዋል፡፡
ከካችአምና ጀምሮ የሰባትና የአምስት ዓመት ህፃናትን እያስተማሩ እንደሚገኙ የነገሩን ሌላዋ ወላጅ፤ የህፃናቱ ሽንት ቤት ንጽህና የለውም እያሉ በርካታ ወላጆች ቅሬታ በማሰማታቸው ልጆቻቸውን ለመውሰድ ወደ ውስጥ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልፀው፤ ትምህርት ቤቱ በር ላይ ከጫፍ እስከጫፍ ገመድ ታስሮ ህፃናቱ በገመድ ስር እየሾለኩ ወላጆቻቸው ጋ እንደሚደርሱ ተናግረዋል፡፡
ከሁለት ወር በፊት የትምህርት ቤቱን ባለቤት በተጠቀሱት ችግሮች ዙሪያ ማነጋገራቸውን ያስታወሱት ወላጂቱ፤ ከባለቤቱ ያገኙት ምላሽ “ትምህርት ሚኒስቴር ይጠይቀኝ” የሚል እንደነበር ገልፀዋል፡፡ “ትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ የለውም፤ የወላጅ ስብሰባም ተጠርተን አናውቅም” ያሉት ሌላዋ ወላጅ፤ አስተማሪ በየጊዜው በመቀያየር ልጆቻቸውን ለስነ - ልቦና ጫና እንደዳረጉባቸው ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ህፃናቱን ለመውሰድ የሚመጣው ሰው ማንነት ሳይረጋገጥ ልጆቻችን ከግቢ ይወጣሉ ሲሉ አማረዋል፡፡ “እኔ በሌለሁበት ልጄ ከጐረቤት ሰው ጋር ሄዳ፣ ልጄ የታለች ብዬ ስጠይቅ አናውቅም ተብዬ ራሴን እስከመሳት ደርሼ ነበር” ሲሉ ብሶታቸውን የገለፁት እኚሁ ወላጅ፤ አንዲት የክፍል ተወካይ አስተማሪ ስትቀር ሌላ እንደማይተካና ወላጅ እስኪመጣ ህፃናቱ አቧራና ፀሐይ ላይ ያለ ረዳት እንደሚቀመጡ ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩን ለወረዳውና ለክፍለ ከተማው ትምህርት ቢሮ ማመልከታቸውን የጠቆሙት ወላጆቹ፤ ት/ቤቱ ከወረዳውም ሆነ ከክፍለ ከተማው አቅም በላይ እንደሆነ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት የትምህርት ቤቱ ሃላፊዎች፤ በበኩላቸው አንዳንዶቹ ችግሮች መኖራቸውንና ቦታውም ምቹ አለመሆኑን አምነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወላጆችን በመሰብሰብና ኮሚቴ በማቋቋም አፋጣኝ የማሻሻያ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኪዳነማርያም ህንፃ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ በወላጆች ቅሬታ መሠረት ትምህርት ቤቱን ለመጐብኘት በተደጋጋሚ ወደ ስፍራው ቢሄዱም “ፈቃዱን የሰጠው ትምህርት ሚኒስቴር ይጠይቀው እንጂ ክ/ከተማ ምን አገባው” በሚል ጥበቃዎች መግባት እንደከለከሏቸው ተናግረዋል፡፡ ሃላፊው አክለውም፤ ጉዳዩ ከአቅም በላይ በመሆኑ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እርምጃ እንዲወስድ ደብዳቤ መፃፋቸውን ጠቅሰው፤ የትምህርት ቢሮው እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱን ገልፀዋል፡፡

Read 2609 times