Sunday, 03 March 2013 00:00

40 የፍሳሽ ቆሻሻ ማንሻ መኪናዎች ሊገዙ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ውሃና ፍሳሽ በ6 ወራት 187 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን 40 የፍሳሽ ቆሻሻ ማንሻ መኪናዎችን ግዥ ሊፈጽም ነው፡፡ ይህም በባለስልጣን መ/ቤቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነና ከዚህ ቀደም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መኪኖችን ብቻ ይገዛ እንደነበር ተገልጿል፡፡ በፍሳሽ ቆሻሻ ማንሳት ሥራ ላይ የሚሰማሩ በቂ መኪኖች ባለመኖራቸውና የህብረተሰቡ ፍላጐት ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ የአርባ መኪኖች ግዥ ለመፈፀም መታሰቡን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዓለም ባዬ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለፀው፤ በስድስት ወራት ውስጥ 187.15 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ በአሁኑ ወቅት በከተማው ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የውሃ እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን የገለፁት የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰግድ ጌታቸው፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ለህብረተሰቡ በቂ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ቀን ከሌት እንሠራለን ብለዋል፡፡
በባቡር መሥመር ዝርጋታው ሰበብ የሚነሳውንና በ1947 ዓ.ም የተሰራውን 8.5 ኪ. ሜትር ርዝመት ያለውን የውሃ መስመርና ትልቅ የውሃ ማከፋፈያ ቱቦ በማንሳት በአፋጣኝ ቀይሮ ለአገልግሎት ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የውሃ ቱቦዎቹና ልዩ ልዩ መሣሪያዎች በቻይና አገር እንዲመረቱ ተደርጐ ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ የውሃ መስመር ዝርጋታው እስከሚጠናቀቅም በጊዜያዊ መስመር ህብረተሰቡ ውሃ ለማግኘት እንዲችል ለማድረግም እየሰራን ነው ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

Read 3512 times