Saturday, 23 February 2013 12:01

ከደፈሩ አይቀር እንደ ዳዊት!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(2 votes)

የጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴና የእስራኤል አምባሳደሯ አስገራሚው ቃለምልልስ!
የዛሬ ሦስት ሳምንት ያቀረብኩትን ጽሑፍ አንብበው ደስ ያልተሰኙ አቶ ዳዊት የተባሉ የእየሩሳሌም ነዋሪ በሳምንቱ ቅዳሜ ታትሞ በወጣው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “የአቶ አልአዛር የቤተእስራኤሎች ጽሑፍ ተጋኗል” በሚል ርዕስ ትችታቸውን አቅርበዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ጽሑፎችን ለማቅረብ ዋነኛው ምክንያቴ አሁንም ድረስ በአለም አቀፍ ደረጃ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆነው በእስራኤላውያን የህክምና ባለሙያዎች ታቅዶና ሆን ተብሎ በቤተእስራኤላውያን እናቶች ላይ የተፈፀመው ማህፀናቸውን የማንጠፍ ጭካኔና ዘረኝነት የተሞላበት የወንጀል ድርጊት ነው፡፡
አቶ ዳዊት ያቀረቡትን ትችት ተጋኗል የሚል ርዕስ ስለሰጡት እኔ ያጋነንኩትን አብርደውና በእውነተኛ ሚዛኑ ልክ አስገብተው እኔ ማየትና መገንዘብ ያልቻልኩትን በማሳየት አዲስ እውነት ያስጨብጡኛል፤የቤተእስራኤላውያኑን ጉዳይ እኔ ስጽፈው ምናልባት ስሜት ተጭኖኝ አሊያም በወገንተኝነት ልቤ አድልቶላቸው ከሆነም እውነታውን በማቅረብ ልክ ልኬን ነግረው አደብ ያስይዙኛል በሚል ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ አቶ ዳዊት ባቀረቡት ትችት ግን ምንም እንኳ እኔን አጋነኸዋል ብለው ቢወቅሱኝም፣ እንደ አዲስ መረጃ ቆጥረው ባቀረቧቸው ማስረጃዎች ሁሉ እኔ ያነሳኋቸውን ዋና ዋና የቤተእስራኤላውያን ችግሮች በማመናቸው ባልጠበቅሁት መንገድ ቢሆንም ደስታዬን ወግ አልነፈጉትም፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ካቀረቧቸው ትችቶች ውስጥ የእኔን አቋም የበለጠ ለማስረዳት ይረዳኝ ዘንድ ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ብዬ የመረጥኳቸውን ጥቂት ጉዳዮች በተሻለ ለማብራራት እፈልጋለሁ፡፡
ቤተእስራኤላውያኑን ከእስራኤል የድሩዚም ማህበረሰብ ጋር ያነፃፀርኳቸው ለእስራኤል መንግስት ያላቸውን ታማኝነት እንደነውር በመቁጠር ጨርሶ ለማጣጣል አይደለም፡፡ ይልቁንስ ቤተእስራኤላውያን በእስራኤል መንግስትም ሆነ በተቀረው የእስራኤል ማህበረሰብ ዘንድ እየደረሰባቸው ያለውን ችግር ለመንግስት ባላቸው ክብር የተነሳ ብቻ አሜን ብለው መቀበላቸው ተገቢ እንዳልሆነና ለችግሩ ፈጣሪዎች ያልተገባ ድርጊት “እሰየው ደግ! እንኳንም አደረጋችሁብን” የሚል የይሁንታ ቡራኬ መስጠት መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ የእስራኤል ድሩዞች ለእስራኤል መንግስት ታማኝ መሆናቸው አስገራሚ ነገር የለውም፡፡ ለምን ቢባል የእስራኤል መንግስት እንደ አናሳ ማህበረሰብ ቆጥሮ ሳይሆን በሁሉም ነገር አቀማጥሎ ስለያዛቸው ነው፡፡ የመንግስትን አያያዝ በተመለከተ እንኳን እኔና አቶ ዳዊት ይቅርና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ናታንያሁም ቢሆኑ ቤተእስራኤላውያንን ከእስራኤል ድሩዞች ጋር ደፍረው ማወዳደር አይችሉም፡፡ አሃ! ልዩነቱ እኮ የሰማይና የመሬት ያህል ነው!
“ሁለቱን ህዝቦች ያመሳሰሉት በመንግስት ላይ አመጽ ባለማንሳታቸው ወይስ ወደ ኢትዮጵያ መልሱን ባለማለታቸው ይሆን? ደግሞስ ይህን ያህል የሚያማርር ምን ነገር ተገኝቶ ነው?” በሚል አቶ ዳዊት ያቀረቡት ስሞታ ዋነኛ መነሻው፣ ከወራት በፊት ወደ እስራኤል የገቡ ጥቁር እንግዳ በመሆናቸው አሊያም ደግሞ የእስራኤል መንግስትም ሆነ የተቀረው የእስራኤል ማህበረሰብ የፈለጉትን ቢያደርጉኝም ሆነ ያሻቸውን ግፍ ቢፈጽሙብኝ ጫንቃዬ መሸከም ይችላል፡፡ እነሱንም እንደ ተሳሳቱ በደለኞች አድርጌ አልቆጥራቸውም ብለው የወሰኑ በመሆናቸው ነው ብዬ በትልቁ እጠረጥራቸዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ከሁለቱ ውጭ የሆነ ሰው ያን ሁሉ ግፍና በደል እለት በእለት እየቀበለ፣ እንዲህ ያለ ደፋርና ነጭ ውሸት ይሰነዝራል ብሎ ለመገመት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡
እንዴ! በዘመቻ ሙሴ አማካኝነት በ1984 ዓ.ም መጨረሻና በ1985 ዓ.ም መጀመሪያ ባሉት አራት ወራት ወደ እስራኤል የገቡት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያን የብራ መብረቅ የወረደባቸውና የዘረኝነት መድልኦ ሰለባ በመሆን፣ ሰብአዊ መብታቸው የተደፈረውና ሰብአዊ ክብራቸው በአስከፊ ሁኔታ የተንቋሸሸው እግራቸው የተስፋዋ ሀገራችን ያሏትን የእስራኤልን መሬት ገና እንደረገጠ እኮ ነው! ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሰላሳ አመታት በእስራኤል የሚኖሩ ቤተእስራኤላውያን የሚያማርር ብቻ ሳይሆን መፈጠራቸውን የሚያስጠላና ለቁጥር የሚያታክት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖማያዊና ማህበራዊ ችግሮች ሲፈራረቁባቸው ኖረዋል፡፡
ምናልባት አቶ ዳዊት በወቅቱ እስራኤል ውስጥ ስላልነበሩ አያውቁት ይሆናል እንጂ በሺ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያን የተሸከሙትን ፈርጀ ብዙ ችግር እንዲሁም የዘረኝነት መድልዎና ጥቃት መቋቋም እያቃታቸው ለተቃውሞ አደባባይ የወጡበትና “ወደ መጣንበት” ማለትም “ወደ ኢትዮጵያ እንመለሳለን” ያሉበት የተለያዩ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በ1985 ዓ.ም በሊቀ ራባይ አቭርሃም ሻፒራና ሞርዶካይ ኢልያሁ የሚመራው የእስራኤል የራባዮች ጉባኤ፤ ቤተእስራኤላውያን የመታደስ ጥምቀት (ሚክላህ) እንዲጠመቁ፤ወንዶች አዲስ የግርዘት ስነስርአት እንዲፈጽሙ፣ የቤተእስራኤል ቄሶች ደግሞ ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ስነስርአት መምራትና ማስፈፀም ከመጀመራቸው በፊት ስልጠና መውሰድ እንደሚገባቸው ጥብቅ ድንጋጌ በማውጣት፣ ይህን ድንጋጌ ካልፈፀሙ በቀር እንደ አይሁዳዊ ህዝብ መቆጠር እንደማይችሉ በማስታወቅ፣የብራ መብረቅ ባወረደባቸው ወቅት ከሰሜን እስራኤል ተነስተው ወደ ቴልአቪቭ የቤንጉርየን አውሮፕላን ማረፊያ ረጅም ጉዞ በማድረግ “ይህን ያወጣችሁትን ዘረኛ ደንብ ሰርዙልን፡፡
አለበለዚያ ወደመጣንበት መልሱን” በማለት ከፍተኛ የምሬትና የተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ ይህ ድርጊት ከተፈፀመ ድፍን ሃያ ስምንት አመታትን በማስቆጠሩ ፋይሉ አርጅቷል ተብሎ የቆሻሻ ማቃጠያው ምድጃ ሲሳይ ሆኗል ብለው ቅንጣት ታህል እንኳ ስጋት ሊያድርብዎት አይገባም፡፡ “ጉግልን” ቢጠይቁት ከጋዜጣ እስከ መጽሐፍ ድረስ ያሉትን ሁሉንም አይነት መረጃዎች በደንብ አሰናድቶ ያቀርብልዎታል፡፡ አቶ ዳዊት በጽሑፋቸው “ጠቅላላ ቤተእስራኤላውያንን ያነሳሳ በ1996 ዓ.ም ለሜጌን ዴቪድ (የእስራኤል ቀይ መስቀል) የለገሱት ደም በመደፋቱ የተነሳ ካደረጉት ተቃውሞ ውጪ ያን ያህል የተጋነነ ነገር አልታየም፡፡” በማለት የገለፁት ሃሳብ “ከደፈሩ አይቀር እንደ ዴቪድ” እንድል አድርጐኛል፡፡ እውነት ለመናገር እንዲህ ያለ ነገር በግልጽ ለዚያውም በጋዜጣ ላይ መፃፍ የሚቻለው ልክ እንደ አቶ ዳዊት “በሻምፒዮንስ ሊግ” ደረጃ የሚገኝ ደፋር ሰው ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ የአቶ ዳዊት ድፍረት ምንጩ ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ የእውቀት ማነስና ነጭ ውሸት፡፡ አቶ ዳዊት የቤተእስራኤላውያንን የመኖሪያ ሰፈሮች በተመለከተ የእስራኤል የኮንስትራክሽንና ቤቶች ሚኒስቴር ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የሚያወጣቸውን መረጃዎች እንዲያው ላመል ታህል አንድ አፍታ ገረፍ ገረፍ አድርገውት ቢሆን ኖሮ ወይንም ደግሞ ከ1988 ዓ.ም እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ ባሉት ስድስት አመታት ውስጥ በኪርያት መላኺ፣ በኪርያት ጋትም ሆነ በአፉላና፣ በፆር ይሁዳ አካባቢዎች ነዋሪ ቢሆኑ ኖሮ አንድ ኪሎ ብርቱካን ወይም አንድ ኪሎ ሽንኩርትና ቲማቲም ለመግዛት የት ድረስ በእንዴት ያለ አኳኋን መሄድ ያስፈልግ እንደነበረ፣ የቤተእስራኤላውያንን ልጆች ተቀብሎ ለማስተማር ፈቃደኛ የሆነ ትምህርት ቤት በእንዴት ያለ ሁኔታ ይገኝ እንደነበረ (ለነገሩ ዛሬም ድረስ የብዙዎቻችን ችግር ነው) በመጠኑም ቢሆን ለመረዳት ያስችልዎት ነበር፡፡
አቶ ዳዊት የቤተእስራኤላውያንን የመኖሪያ ቤት ግዢን በተመለከተ በጽሑፋቸው በዝርዝር ያቀረቡት መረጃ ከአንዱ በቀር ሌላው ማንም በግልጽ ሊያረጋግጠው የሚችል አሪፍ ማስረጃ ነው፡፡ ይሁን እንጂ “የሚገዙት ቤት ማብሰያ፣ መታጠቢያና፣ መፀዳጃ ክፍሎችን ሳይጨምር ሶስትና ከሶስት ክፍል በላይ ነው፡፡ እውነት ለመናገር አብዛኛው አዲስ ገቢ ኢትዮጵያውያን (ቤተእስራኤሎች) ቤት ለገዙበት ብድር በወር ለባንክ የሚከፍሉትን ሶስትና አራት ቀን ሰርተው ያገኙታል፡፡” በሚል ያቀረቡልን መረጃ፤ እሳቸው ብቻ የሚያውቋት እስራኤል የምትባል ሌላ ሁለተኛ ሀገር ካልኖረች በስተቀር በመካከለኛው ምስራቅ ግብጽ፣ ሶሪያና፣ ሊባኖስ የሚያዋስኗትና እኔም ሆነ የተቀረው አለም ዛሬም ድረስ በምናውቃት በዛሬዋ እስራኤል ያሉትን ነገር ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ እሳቸው ያሉት ምናልባት ለነጭ እስራኤላውያን ሊሰራ ይችላል፤ ለ“ኩሽሞቹ” (ባሪያዎቹ) ቤተእስራኤላውያን ግን ጨርሶ በቀላሉ የሚሳካ ነገር አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የእስራኤል የውህደት ሚኒስቴር፣ የኮንስትራክሽንና የቤቶች ማኒስቴር እንዲሁም የአሚዳር ቢሮዎች ቋሚና አይነተኛ ምስክሮች ስለሆኑ ወደ እስራኤል መሄድ የቻለ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ማረጋገጥ የሚችለውን ተራ ሃቅ እንዲህ በድፍረት ለመካድ አይመችም፡፡
አቶ ዳዊት በጽሑፋቸው፤ ቤተእስራኤላውያን በብዛት ተከማችተው የሚኖሩባቸውንና እንደ አብነት የጠቀስኳቸውን አፉላን፣ ኪርያት መላኺንና፣ ኪርያት ጋትን የመሳሰሉ ከተሞች ሳይሆን ሰፈሮችንና ነዋሪዎችን በሚገባ ለማወቅ ጉግልን ጠይቀው ቢሆን ኖሮ ከእኔ ይልቅ አቶ ዳዊት የበለጠ በተጠቀሙ ነበር፡፡ ይህን ቀደም ብለው አድርገውት ቢሆን ኖሮም በሌለ እውቀት በድፍረት ብቻ ከመፃፍ መቆጠብ የሚያስችል እርጋታና የጥሞና ጊዜ ያገኙ እንደነበር እገምታለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ዳዊት “ጉግልን” እንድጠይቅ ያዘዙኝ እኔን ስለሆነ “ጉግል” አሰናድቶ ካቀረበልኝ በርካታ ማስረጃዎች ውስጥ Myers – JDC –Brook dale Institute የተሰኘ የእስራኤል ተቋም፣ በእስራኤል የሚኖሩ ቤተእስራኤሎችን በተመለከተ በጁን ወር 2012 ዓ.ም ባወጣው መረጃ፣ በመኖሪያ አካባቢያቸውና በመኖሪያ ቤት ይዞታቸው፣ በትምህርት፣ በስራ ደረጃ፣ በደመወዝ አከፋፈል፣ በሀብት መጠን፣ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ህፃናትና ወጣቶች መጠን ወዘተ የመጨረሻ ዝቃጭ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ያሳያል፡፡
ማአሪቭ የተሰኘው ታዋቂ የእስራኤል ጋዜጣ ዲሰምበር 11 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው እትሙ፣ በ2012 ዓ.ም በመላ እስራኤል ከሚገኙት አስር ሺ እስራኤላውያን የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎች መካከል አስራ ሶስቱ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች (ቤተእስራኤሎች) መሆናቸውን “ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ፈፅሞ አስመዝግበውት የማያውቁት ድንቅ የስኬት ታሪክ ነው” በማለት ዘግቦታል፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ፡፡ በመኖሪያ ቤት ባለቤትነት፣ በስራ እድልና በደመወዝ አከፋፈል ደረጃ፣ በሀብት መጠን ወዘተ ቤተእስራኤላውያን ያስመዘገቡት የስኬት ታሪክ እየተባለ በመገናኛ ብዙሃን የሚሞዘቅለት ይሄ ነው፡፡
በርካታ ሚሊዮን እስራኤላውያን ከእየሩሳሌም ቀጥሎ ሁለተኛዋ ታላቅ ከተማና የእስራኤል የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የትምህርትና፣ የቱሪዝም ዋነኛ የልብ ትርታ በሆነችው በቴልአቪቭ ከተማ እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ በሺ የሚቆሩ ቤተእስራኤላውያንም በዚች ከተማ ውስጥ በነዋሪነት ተመዝግበው አታካቹን የእለት ተዕለት ኑሮአቸውን ይገፋሉ፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ዳዊት ቤተእስራኤላውያኑ የቴልአቪቭ ከተማ ታዋቂና እጅግ ዘመናዊ ዝነኛ የመኖሪያ ሰፈሮች ከሆኑት ከራማትጋንና ከዲዚንጐፍ ሰፈሮች ይልቅ በፔታህቲክቫና በጾር ይሁዳ ሰፈሮች ውስጥ ለመኖር የመረጡበትን ትክክለኛ ምክንያት ሊያስረዱን ቢችሉ እጅግ በጣም በተደሰትን፡፡
ለቅሶ ለመደራረስ፣ ቡና ለመጠራራት፣ አሊያም ጠበል ጠዲቅ ለመቅመስ ወዘተ እንዲመቻቸው ብለው ነው የሚል መልስ እንደማይሰጡን ግን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ፀሃፊው ቤተእስራኤላውያን ላለፉት ሰላሳ አመታት የተጋፈጡትን እጅግ አስቸጋሪ የእለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታና በቅድስቲቱ ሀገራቸው ድንገት እንደጉም የበነነውን ተስፋቸውን ጨርሰው ባይክዱትም፣ መልከጥፉ አስቀያሚ የሆነችውን ጦጣ በተራ አንባሬ ጭቃ ቀባብተው ለማስዋብ እንደመሞከር ያለ ከባድና እልህ አስጨራሽ ነገር ግን ጨርሶ ያልተሳካ አጉል ሙከራ ባደረጉበት ጽሑፋቸው ውስጥ ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ ደግሞ እስራኤላውያን ለቤተእስራኤላውያን ያወጡላቸውን “ኩሽም” ወይም “መሸጦ ባሪያ” የሚለውን የቅጽል ስምን የተመለከተው ነው፡፡
ነጭ አሜሪካውያን በጥቁር አፍሪካ አሜሪካውያን ላይ ያላቸውን የዘር ጥላቻ ለመግለጽ “ኒገር” ወይም “መሸጦ ባሪያ” እያሉ ይጠሯቸው ወይም ይሰድቧቸው እንደነበረው ሁሉ ነጮቹ እስራኤላውያንም በጥቁር ቤተእስራኤላውያን ላይ ያላቸውን የዘር ጥላቻ ለመግለጽ “ኩሽም” ወይም “መሸጦ ባሪያ” እያሉ እንደሚጠሯቸው ፀሃፊው አሳምረው እያወቁ (በእርግጥ በእየሩሳሌም የሚኖሩ ከሆነ ወይም ለጥቂት ሳምንታትም እንኳ ቢሆን ኖረው የሚያውቁ ከሆነ አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ “ኩሽም” ወይም “መሸጦ ባሪያ” ተብለው እንደተሰደቡ ምንም ጥርጥር የለኝም) ነጮቹ እስራኤላውያን ቤተእስራኤላውያኑን “ኩሽም” የሚሉን ወይም መሸጦ ባሪያ እያሉ የሚጠሩን “እኛ ሀበሾች የኩሽ ልጆች ስለሆንና የሙሴም ሚስት ኩሺ ስለነበረች” ነው ብለው ሊያስረዱን መሞከራቸው የእውቀት አልባ ድፍረታቸው መገለጫና የጽሑፋቸው ዋነኛው ኮሜዲ ነው፡፡
የሆኖ ሆኖ አቶ ዳዊት ከዚህ በላይ ያነሳሁዋቸውን ጉዳዮች በጥሞና ተመልክተው ቃል እንደገቡልን በሌላ ጊዜ ቤተእስራኤሎች እንዴት ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ወገናቸው የችግር ምንጭ እንደሆኑ ሊያስረዱን ሲጽፉ ብዙ ጥናትና ምርምር ማድረግ ሳያስፈልጋቸው፣ በየእለቱ በአይናቸው በብረቱ የሚታዘቡትን የቤተእስራኤላውያን ጠቅላላ የኑሮ ሁኔታ መቀባባትና ማድበስበስ ሳያስፈልግ “አካፋን አካፋ” ለማለት ይደፍራሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
በ2012 ዓ.ም የጃንዋሪ ወር መግቢያ ላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪና በአንድ የእስራኤል የፓራትሩፐር ሻለቃ ጦር ውስጥ የአንድ ጓድ አዛዥ የሆነው ቤተእስራኤላዊው አቪ ተሰራ፣ በኪርያት ማላኺ ከተማ ያዕቆብ ቫክኒን የተባለ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ኮንትራክተር፣ በቆዳው ቀለም የተነሳ የመኖሪያ ቤት አፓርትማ አልሸጥልህም እንዳለው በይፋ አስታወቀ፡፡ ከሁለት ቀናት ቆይታ በሁዋላ በጃንዋሪ ሁለት ቀን ምሽት ላይ ደግሞ Channel -2 የተሰኘው የእስራኤል የቴሌቪዥን ፕሮግራም የኪርያት ማላኺ ሰፈር ነዋሪ የሆኑ እስራኤላውያን ለቤተእስራኤላውያን ቤት ላለመሸጥና ላለማከራየት ሲማማሉ የሚያሳይ ፊልም በግልጽ አስተላለፈ፡፡ ሴፕቴምበር 1 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ በአራት ህፃናት ሴት ቤተእስራኤላዊ ተማሪዎች ላይ በፔታህ ቲክቫ የመኖሪያ ሰፈር የሚገኘው ኒርአፂዎን የተባለው ትምህርት ቤት ያደረሰባቸውን የዘር መድልዎ በመቃወም ሶስት መቶ የሚሆኑ ቤተእስራኤላውያን የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ነበር፡፡
በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተገኝተው ንግግር ካደረጉት የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣኖች አንዱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልመርት “ኢትዮጵያውያን አይሁዶች የመበደል ስሜት ተሰምቷቸው፣ ተጐዳን ብለው አቤት ማለታቸው ሲያንሳቸው ነው፡፡” በማለት ሲናገሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዚፒ ሊቭሂም በበኩላቸው “ይህ ችግር በእነዚህ አራት ህፃናት ሴት ተማሪዎች ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን መጤዎች ስራ በመቅጠርና የመኖሪያ ቤት በማከራየት በኩልም ቁልጭ ያለና የለየለት ዘረኝነት አለ፡፡” ሲሉ እውነታውን በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ በጃንዋሪ 27 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ የደረሰባቸው የዘር መድልዎና ጥቃት ያንገሸገሻቸው ቤተእስራኤላውያን “እኛም እንደ እናንተ ሰዎች ነንና እባካችሁ ለአንድ አፍታ እንኳ አዳምጡን” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በማንገብ በሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ወጡ፡፡ ከራሺያ የፈለሱት የመጤዎችና የውህደት ሚኒስትሯ ሶፋ ላንድበር ግን የቤተእስራኤሎችን ብሶት ሰምተው የመፍትሔ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ “ኧረ ተው ግፍ ፍሩ! ይህን መንግስት ምን አድርግ ነው የምትሉት? እንዴ እስካሁን ላደረገላችሁ ነገር ሁሉ ተመስገን በሉ እንጂ!” በማለት አምርረው ተቆጧቸው፡፡
የተከበረው የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጐንደር ተወልደው ያደጉትን ቤተእስራኤላዊቷን ወይዘሮ በላይነሽ ዝቫዲያን በኢትዮጵያ የእስራኤል ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አድርጐ መሾሙን ባስታወቀበት ጊዜ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቪግዶር ሊበርማን ባደረጉት ንግግር “ይህ ሹመት ዘረኝነትን ለመዋጋት የተሰጠ መልዕክት ነው፡፡ በተለይ የእስራኤል ህብረተሰብ በኢትዮጵያውያን የቤተእስራኤል ማህበረሰብ ላይ የሚደረገውን ዘረኝነት እየተዋጋ ባለበት ባሁኑ ወቅት ይህ ሹመት የተለየ ጠቀሜታ አለው፡፡” ነበር ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት የተከበሩ ወይዘሮ በላይነሽ ዝቫዲያ ባለፈው ሰሞን በፋና የኤፍ ኤም ራዲዮ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ከ“አይሁዳዊው” ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ጋር አስገራሚ ቃለምልልስ አድርገው ነበር፡፡ አምባሳደር በላይነሽን እንግዳው አድርጐ ያቀረባቸው የፕሮግራሙ አዘጋጅ ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ፣ የአለም የመገናኛ ብዙሀንና አንዳንድ የሀገር ውስጥ ጋዜጦች በቤተእስራኤላውያን ላይ የዘረኝነት መድልዎ ደርሶባቸዋል እያሉ “ያለ አንዳች ተጨባጭ ማስረጃም ይሁን መረጃ እንዲሁ ከመሬት ፈጥረው በሚያናፍሱት የሀሰት ዘገባ” እጅግ አድርጐ እንዳዘነም፣እንደተናደደም በሰፊው ካብራራ በኋላ “የተከበሩ አምባሳደር፣ እንዲያው ለመሆኑ ዘረኝነት የሚባል ነገር እስራኤል ውስጥ አለ እንዴ?” የሚል ጥያቄ እንደዘበት አቅርቦላቸው ነበር፡፡ አምባሳደር በላይነሽ ሲመልሱም “ኧረ እቴ ከየት መጥቶ! የሚዲያ ሰዎችና አንዳንድ ፖለቲከኞች ያለ አንዳች ተጨባጭ ማስረጃ እንዲሁ አማረልኝ ብለው የሚያስወሩት ዝባዝንኬ ነው” ብለዋል፡፡
የተከበሩ አምባሳደር በላይነሽ ጉዳዩን በእርግጠኝነትና በግንባር ከሚያውቁት ሰዎች ግንባር ቀደም ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ችግሩ ግን አሁን የእስራኤል መንግስት ለዘረኝነት መድልዎ መልስ ይሰጡ ዘንድ የሾማቸው ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ የተለየ መልስ ቢሰጡ በአምባሳደርነት የስልጣን ወንበራቸው ላይ አንዲት ቀን እንኳን እንደማይቆዩ እሳቸውም እኛም በሚገባ እናውቃለን፡፡ እናም ለአምባሳደር በላይነሽ ይቅርታ ልናደርግላቸው እንችላለን፡፡
ችግሩ የ”አይሁዳዊው” ጋዜጠኛ የአለምነህ ዋሴ ነገር ነው፡፡ በቤተእስራኤላውያን ላይ የሚፈፀመውን የዘረኝነት መድልዎ ለምን መካድ እንደፈለገ የሚያውቁት እሱና ፈጣሪ ብቻ ናቸው፡፡ እኛ ግን ቢያንስ አንድ ነገር እናውቃለን፡፡
አለምነህ ዋሴ እንደአምባሳደሯ የሚሳሳለት ስልጣን ከእስራኤል መንግስት አልተሰጠውም፡፡

Read 8008 times