Saturday, 23 February 2013 11:53

የግርማ ተስፋው ባለ“እሾህ” ግጥሞች!!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

“ሁላችንም የየራሳችንን ዳገት በየቀኑ እንወጣለን” እንደ በገና አውታር፣…ልብ የሚነዝሩ፣…ሆድ የሚያባቡ፣…ስሜት የሚነሽጡ ናቸው - የግርማ ተስፋው ግጥሞች፡፡ “መጀመሪያ” ብሎ መግቢያው ላይ ከተጠቀመበት የህይወት ማንጸሪያ ላይም የወደድኩለት ነገር አለ፡፡ “ሁላችንም የየራሳችንን ዳገት በየቀኑ እንወጣለን፡፡”
በማለት አንድ አዛውንት የራስ ዳሸንን ዳገት ሲወጡ ከተናገሩት የምሬት ንግግር ጋር ያነጸረበት መንገድ የሚመች ነው፡፡
“የጠፋችውን ከተማ ሃሰሳ” በሚል ግርማ መጽሃፍ ማውጣቱን ስሰማ ያው በግጥም ላይ ከሚቀልዱት አንዱ ይሆናል በሚል ችላ ብዬው ነበር፡፡ ምክንያቱም እኛ ሃገር መጣጥፍ የጻፈ ሁሉ ደራሲ፣ጋዜጣ ላይ ስንኞች ያስነበበ ሁሉ ገጣሚ ነው የሚል ዘውድ ሲደፋለት እያየን ነው፡፡ የፈጠራ ስራ ክብር ከመጣጥፍ እኩል እስከመታየት ደርሷል፡፡

ግና ኤድጋር ስፔየርን ጨምሮ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ታላላቅ መምህራንን ለጥበብ የመወለድ እውነትን ማጣጣም ያቃታቸው ብዙ ናቸውና ግርማንም ከዚሁ ተርታ መድቤው ነበር፡፡ ምክንያቱም ግጥም ይዞ ወዲያ-ወዲህ ሲል አላየሁትም ነበርና!! ይሁንና ለግርማ የነበረኝን ግምት ከገጽ-ገጽ ስሻገር እየቀየርኩ ሄጃለሁ፡፡ግርማ የ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረ ሲሆን አሁን ውጭ ሀገር በስደት የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
ከግርማ ግጥሞች ብዙዎቹን ወድጃቸዋለሁ፤ያ ብቻ አይደለም ተመስጨባቸዋለሁ፡፡ በተለይ ተፈጥሮን ለማንጸሪያነት እየተጠቀመ በፈጠረው ውበት ተደምሜያለሁ፡፡ ሰማይን….ደመናን…ትዝታን…ክዋክብትን ወዘተ ወደ ምደር አውርዶ እንደ መጽሃፍ ገልጦ፣አቅርቦ አሳይቶናል፡፡ ስሜታችንን እንደ ድስት ገልብጦ ሽንኩርት አቁላልቶበታል፡፡
በባለሁለት መስመርዋ ግጥም ብጀምር ደስ ይለኛል፡፡ እነዚህን ግጥሞች ያነበብኩት ጎልፍ ክለብ ያሬድ ከሚባል የግጥም፣የንባብ ወዳጅ ጋር ነበረና፤”በናትህ ስማ!” እያልኩ ድምጽ እያወጣሁ ነበር ያነበብኩት፡፡ በግጥም የመጀመሪያ ንባብ የሚፈጠር ስሜት አይታመንም ይላሉ የዘርፉ ሊቆች፡፡ እኔ ግን ደግሜ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ ግሩም ነው - እፁብ ድንቅ!
ቀጣዩ ግጥም “ነገረ እስር” በሚለው ግጥሙ ስር ካሉት ግጥሞች ቁጥር አምስት ላይ ያለ ነው፡፡
አገሩ ታሠረ
እስር ቤት መቀለስ እንደድሮው ቀረ፡፡
እጅግ የገረመኝ - አንገቴን ያስነቀነቀኝ ግጥም ነው፡፡ በሁለት ስንኞች አገር ማነቃነቅ!!...በጣም ልብ ይነካል፡፡ ግርማ ይህችን ግጥም ብቻ እንኳ ጽፎ በቃኝ ቢል ትልቅ ገጣሚ ነው፡፡ በጣም ትልቅ የምናብ ኃይል የታየበት ግጥሙ ነው፡፡ ትልቅ አይን!...እያንዳንዱ ሰው በየራሱ ቤት ከታሰረ ወህኒ ቤት ምን ይሰራል?…ሃሳቡ ከተጠፈነገ የሰው ልጅ ሌላ እስር ቤት ለምን ያስፈልገዋል?ኦ ግርማ!... ጀፈርሰን 3ኛ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆኖ ሲመረጥ እንዲህ ብሎ ነበር፡-“I have sworn upon the altar of God eternal hostility against any form of tyranny over the mind of man.” በሰዎች አእምሮ ላይ የሚጫን የአምባገነኖች ጫና የሚያስጠላ ነገር ነው፡፡ከመግደልም አይተናነስምና መሰዊያ ላይ ባልምልም ግርማና ጀፈርሰንን እደግፋለሁ!!
ብቻ ይህቺ የግርማ ግጥም እንደ እንቁላል ተፈልፍላ በሰማይ ሊያበር የሚችል አቅም ያላት ናት፡፡ ልብ ብሎ ላነበባት፡፡ሰንሰለት የማይታይበት፣ሰሚ ያጣ አልቃሽ ከሆንን ቆየን፤የቁም እስረኛ ሆነን ይሆን? መንግስታችንም ገጣሚ ዳዊት ጸጋዬ እንዳለው መናገር እንጂ መስማት አልችልም ስላለ ይለወጣል ብለን በጉጉትና በተስፋ የምንጠብቀውን እንኳ አስከፍቶናል፡፡
“ተራራ እናትና በር” (ርዕሱ ለግጥም የማይመች ቀውላላ ቢሆንም)
በር በሌለው ጎጆ፤በተራራው ጫፍ ላይ
አለች ምስኪን እናት፤ማዶ ማዶ እምታይ፡፡
ከተራራው ቆርባ፤ከጋራው ተላምዳ
እያማከረችው የዘመንዋን ፍዳ፤
ምስክር ማን አለ? የተመለከተ
ሳይዘጋ ሲኖር የጎጆዋ በሩ እንደተከፈተ፤
ምልዔል ደረሰ መመለስ ወግ ሳይኾን
በሄዱት ልጆቿ ሃሳብዋ ሳይሰክን፤
ልጆቿም አልመጡ፣በሩም አልተዘጋ
እንባዋም አልቆመ፣ሌሊቱም አልነጋ፡፡
ይህ ግጥም ተምሳሌታዊ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ግን ሆድ ያባባል፤እንደ ሁዳዴ የበገና ዜማ አንጀት ያላውሳል፤በተለይ ለስደተኞች፡፡ እግር ላላቸው ሳይሆን ሃገር ከሆድ ያለፈ ትርጉም እንዳለው ለሚገባቸው፡፡ ለመቃጠል…ለማሰብም…ሆድ ሳይሆን ህሊና ያስፈልጋል፡፡ ግርማ ለኔ ከአድማስ ባሻገር የሚያማትር ዓይናማ፣በሳል፣ስል ነፍስ ያለው ያገር ልጅ ነው፡፡ሃሳቦቹ የተንጠለጠሉባቸው ተራራዎች ራሳቸው ግዙፎች ናቸው፡፡ በከበረው ሃሳብህ ምክንያት አክብሬሃለሁ፡፡ ሸጋ ልብ ወገን ወዳድ፣የነጻነት ጥማት ከግጥሞችህ ውስጥ ይፈልቃልና ብራቮ ብያለሁ!!
“የቃየን ፉከራ”ሌላው ለዳሰሳዬ የመረጥኩት ግጥም ነው፡፡
ለቃየን ውላጆች ጀግና መኾን ማለት
መሸለል፣መፎከር፣“ዘራፍ-ዘራፍ” ፉጨት፡፡
መንገዱን የሳተ ዐይኑን ያልገለጠ ደቦል ገደሉና፤
ተው ጋሜ ሽለላ፣ፉከራ ቀረርቶ
“ትመታ እንደኹ ምታ…”
እንደ ማስመሰል ሳግ በውሸት ተሰርቶ
እንጀራው ሲጋገር ባሰት እርሾ ቦክቶ፡፡
ይህ ነው ዝማሬያቸው
የከንቱነት ክብር የቃላት ኳኳታ
የሰውነት ሽሽት የወናነት ሆታ፡፡
የአንበሳ ደቦል ገድሎ አደባባይ ላይ መፎከር እንዴት ነውር እንደሆነ በተለይ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ሩቅ አይመስለኝም፡፡ የአድዋ ድል ጀግኖች ዛሬ ጀግና አይደላችሁም ብንባል ወይም እኛ ራሳችንን ጀግና ነን? ብለን ብንጠራጠርም ቢያንስ ትርጉሙ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ የጀግንነት መጀመሪያው እውነት መናገርና ለእውነት ዋጋ መክፈል ነው፡፡
በአደባባይ እውነት መናገር የቻለ ሰው ጀግንነት ይጎድለዋል ማለት አይቻልም፡፡ ብዙዎቻችን ሆዳችንን ስንከተል፣ነጻነታቸውን የሚጠይቁ ጥቂት ሰዎች አሉን፡፡ብዙ ችግሮቻችንም የወናነት ናቸው፡፡…ጋንዲን እየጠቀስን፣ግን እንደ ሂትለር እንኖራለን፤እንደ ሊንከን እያወራን እንደ ሞሶሎኒ ጦር እንስላለን፡፡
“ቤልማ”
ማዶ ማዶ ማየት ቁጥር 3 እነሆ፡-
ማደጎ እንደሰጡት እንደ አሳዳጊ አልባ፣
ዝናም እንደሻተ
ሰኔ እንደራቀበት እንደ ዱር አበባ፣
ምኞት ነው ቀለቤ
እንባ ነው ማዕዴ
ትካዜ ነው ምግቤ፡፡
አይመስለኝም ነበር፤ሰው ብቻ እሚመንን
ለካ ሃገር ሲከፋው፤ትካዜ ሲወርሰው
ይሸሻል ከጀማው፤ይደበቃል ከሰው፡፡
ሰኔ የራቀበት አበባ ከኛ አይብስም- እኛ ነጻነት ተርበናል፡፡ ነጻነት ምን እንደ ሆነ ከሶስት መቶ አመታት በፊት ጀፈርሰን የጻፋቸው ደብዳቤዎች ይነግሩናል፡፡ እኛ ግን ዛሬም በነጻነት መናገር የሰማይን ያህል እየራቀን ነው፡፡ በገዛ ሃገራችን አንገታችንን መድፋት ግድ ሆኖብናል፡፡ ቀደም ሲል እንዳየነው ዓይነት የግጥም ስሜት ቢኖረውም ይኸኛው የሚለየው ሃገር መሸፈቱ፣ሃገር መደበቁ ነው፡፡ ወይም ሃገር ገዳም መግባቱ!! ይህ ደግሞ የልብ መመነን ሊሆን ይችላል፡፡ ማን ያውቃል!!
“ፈጣሪን ምስረታ”
ሸንጎ ተመካክረው ጉባኤ ዘርግተው
ያሳመኑኝ ሰዎች እግዜር ሞቷል ብለው፡፡
“የዓለም መሠረት፣የሰው ልጅን መሪ
አልፋና ዖሜጋ አድራጊ ፈጣሪ፤
የነገ ፍጻሜ፣የትናንት ጀማሪ
እኛ ነን ስላሴ መሰረቱን ሰሪ፡፡”
ሲሉ ወንጌል ጻፉ፡፡
ድንጋዩን ዳቦ ብለው ስለሚነግሩን ዋሾዎች ታሳያለች - ግጥሟ፡፡
የግርማ ግጥሞች ባብዛኛው ሃገራዊ ብሶቶች ናቸው፡፡ እውነትም ይህንን ማየቱ ነው - አንዱ አድናቆቴ፡፡ ሃገር የመውደድ አባዜ አለበት፡፡ ከጥቂት ትሩፋን አንዱ ነው - ገጣሚው!
ስለፍቅር ደግሞ እንዴት ጻፈ? ብለን እንጠይቅ፡፡ መቼም ፍቅር በትግልም በጦርነትም ውስጥ የሚወለድ ምትሃት ነውና አይቀርም፡፡ ”ምሽትና ፍቅር” በሚለው ግጥሙ እንዲህ ብሏል፡-
ተያየን በምሽት፣በአዲሳባ ሌሊት
በሐምሌ ደመና፣በድቅድቁ ጽልመት፡፡
ብርሃን ንፉግ ነው፣ኮከብ ይደብቃል
ምሽቱ ግን ቸር ነው፣ጨረቃን ያመጣል፡፡ (“ያመጣል”የሚለውን “ያደምቃል”ቢለው ምቱ ጠንከር ባለ!!”
ደግ አይበረክትም፣ደመናውም ቀንቶ
ጋረደው ሰማዩን፣እንደጥጥ ባዘቶ፡፡
በንጋቱ ጮራ፣የሄድሺው አንቺዬ
ምሽት ተማምኜ፣በእሱ ተስፋ ጥዬ፤
በሬ መች ተዘጋ፣ትመጫለሽ ብዬ፡፡
ከዕፀ በለስ ዕጣው ድርሻ ለቆረሰ
የመገንገን ውርስ ቀድሞ ለቀመሰ፤
ምን ባልንጀራ አለ? ከምሽቱ ሌላ
ለሄዋን መንታ ልብ የሚፈልግ መላ?
እንደጋኔን ጠሪ፣ምሽት ተጓድኜ
በውድቅት ሌሊት፣ወንዝ መሐል ኾኜ፡፡
አነበንባለኹ በማላውቀው ዜማ
የሰወረሽ ጋኔን ጩኸቴን ቢሰማ፡፡
ይህንን መዘርዘር፣መተንተን አያስፈልግም፡፡ በየልባችሁ ትርታ አዋድዱት፡፡ ግጥሞቹ የዜማና የምት ችግርም የለባቸውም፡፡ ስርዓተ ነጥቦችንም በሚገባ ተጠቅሟል፡፡አንዳንድ ግጥሞቹን ባንድ ሙሉነት ውስጥ መንቶና፣ሶስቶን በመገጣጠም አበጅቷቸዋል፤ተያያዥ አድርጎ በንዑስ ክፍሎች መከፋፈሉም አንባቢ ሳይሰለች እንዲያጣጥም ያደርገዋል፡፡ብቻ ግርማ ሞገስ ያለው ሆኗል፡፡
ይልቅስ አሳዛኝና አናዳጅ ጉድለቶቹ አጨራረስ ላይ የሚታዩ ናቸው፡፡ መዝጊያ ላይ ብዙ ግጥሞች ተበላሽተዋል፡፡ እግራቸው እንደተቀቀለ ፓስታ ተጥመልምለዋል፡፡ እውነት ለመናገር በአርትዖት የሚስተካከሉ ጥቂት የማይባሉ ግጥሞች አሉ፡፡…ግን በቸልታ ወይም ባለማጣጣም የተበላሹ ግጥሞች ብዙ ናቸው፡፡ሲያናድዱ!! ለምሳሌ- ላፈቀረ መንፈስ…ጀግንዬ…ውዳሴ ገበሬ…ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ “የጠፋችውን ከተማ ሃሰሳ” ጠንካራ አጥንት ያላቸው ጭብጦች የያዘ፣አድማስ የሚተረክክ፣ልብን የሚቆፍር እውነት ያረገዘ፣የግጥም ለዛውን ሳይተው ቁም ነገር የሚተርክ ውበታም የግጥም መድበል ነው!!...ገጣሚውን በድጋሚ ብራቮ ብያለሁ!!

Read 11478 times