Saturday, 23 February 2013 11:55

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(5 votes)


መጣች
መጣች
እቴ መጣች
መጣች
ውዴ መጣች
መቼ ሄዳ ቀረች
መቼ ከእጄ ወጣች
አምቼ ሳልጨርስ
ተመልሳ መጣች!
ሄደች ብዬ ሳማት
ውል እያፈረሰች
እንባ ሆና መጣች
አይኔ ስር ፈሰሰች
ስትሄድ እያየኋት
ከአይኖቼ እየራቀች
የእንባ ጅረት ሆና
አይኔ ስር ፈለቀች!
ወለላ
የእኔ ወለላ
ሄደች ስል
ሆነች የሌላ
መጥታለች
ዙራ በመላ
ዘለላ
የእኔ ዘለላ
የራቀች መስላ
አይኔ ስር
መጣች በመላ
ሰርታብኝ
የእንባ ዘለላ
እኔው ልፈር እንጂ
አንቺ ምን በወጣሽ
ሄደች ብዬ ሳማሽ
ዞረሽ በአይኔ መጣሽ
ሄዳለች እያልኩኝ
በሩቅ ስናፍቅሽ
ዞረሽ በአይኔ መጣሽ
ከቶም ሳልጠብቅሽ
የእንባ ኩሬ ሆነሽ
ቀድቼ እማልዘልቅሽ
ሌት ተቀን ብጨልፍ
ዘለለት ብጠልቅሽ
አይንሽም ጥርስሽም
ሳቅሽም ለዛሽም
እቴ ሁለመናሽ
እያየሁ ሲርቀኝ
ምን ይውጠኝ ብዬ
ሲጠበኝ ሲንቀኝ
የገባሽልኝን
ቃልሽን አክብረሽ
እንባ ሆነሽ መጣሽ
በአይኔ ቦይ አሳብረሽ
ትታኝ ሄደች ብዬ
ከአጠገቤ ርቃ
አምቼ ሳልጨርስ
ክሴን ሳላበቃ
ስትሄድ እያየኋት
ከጐኔ እየራቀች
እምባ ሆና መጥታ
አይኔ ስር ፈለቀች
ጥላኝ ሄደች ስላት
ውድዬ ጨክና
በደም ስሬ በኩል
መጣች ቁስል ሆና
እኔም እንዳይከፋኝ
ሌላም እንዳይከፋኝ
ስውር ቁስል ሆነች
በጣቴ እማላካት
በሩቅ ስፈልጋት
ሳያት አሻግሬ
ፀፀት ሆና መጥታ
ገባች በደም ስሬ
ይሄውና ጥርስሽ
ሁሌ እሚናፍቀኝ
ይሄውና ሳቅሽ
ያየሁት ሲርቀኝ
ይሄው ሁለመናሽ
ቀርቶ እሚያስጨንቀኝ
ከደም ስሬ ገብቶ
እየተናነቀኝ
መጣች ተመልሳ
ትታኝ ሄደች ስላት
የጐን ውጋት ሆና
ዋግምት የማይነቅላት
የኔ ቃል አክባሪ
የኔ መልከመልካም
መጣች ተመልሳ
ሆናኝ ልብ ድካም!

 

Read 5606 times