Saturday, 23 February 2013 11:52

ስለቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ከተነገረው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“----አቶ ዮፍታሄ ንጉሴን የማውቃቸው ከቀኝ ጌትነታቸው በኋላ መምህር ከነበሩበት ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት እድገት ቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ይባል ወደነበረው ዲሬክተር ሆነው በመጡበት ጊዜ፣ ከሰሩአቸው ትያትሮች አንዱ ላይ የሕፃን አክተር ሆኜ ስተውን ነው፡፡ “ሶረቲዮ”፣ “የኛማ ሙሽራ”፣ “ቦረናና ባሌ በጣልያን ወረራ ጊዜ” በሚሉትና በሌሎችም በአክተርነት ሰርቻለሁ፡፡
ከጣሊያን ወረራ በኋላ ጃንሆይ ሲመለሱ አቶ ዮፍታሄም ተመልሰው የድሮ ተማሪዎችን በመሰብሰብ “አፋጀሽኝ” የተባለውን ትያትር በቤተመንግሥት ለማሳየት ሐምሌ 16 ቀን 1933 ዓ.ም ትያትሩ እንዲታይ ተማሪዎች ሲሰበሰቡ እኔም ካለሁበት ተሰብስቤ “አፋጀሽኝ”ን (ሴት ገፀ ባህርይ) ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡
ከዚያ ጊዜ በኋላ አልተለየሁአቸውም፡፡ በኋላም ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት በነበሩበት ጊዜ እኔም በዚያው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የመዝገብና የፐርሶኔል ሹም በነበርኩበት ጊዜ አለቃዬ ስለነበሩ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አልተለያየንም፡፡ የእሳቸውን ታሪክ በመጠኑም ቢሆን እንድገልፅ በመታደሌ እድሌን አመሰግናለሁ፡፡“ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ምን አይነት ፀባይ ነበራቸው፤ ታጋሽ ናቸው፣ ቁጡ…? ትእግስተኛ፣ አዋቂ፣ ሁሉንም በእርጋታ የሚመሩ ነበሩ፡፡ ጠባያቸው ይሄ ነው፡፡ አሁን ስለጠባያቸው ሳይሆን የምናገረው ስለ ስራቸው ነው፡፡ “አፋጀሽኝ”ን ከሰራሁ በኋላ “ዓለም አታላይ” የሚለውን የመድረክ ትያትራቸውን ራሴ ዓለም አታላይ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ከኔ ጋር የሰራው ይድነቃቸው ተሰማ ያራዳ ኮረዳ ሆኖ ሰርቷል፡፡
ዮሐንስ ወዳዘጋጀው ታሪካቸው ልምጣ፡፡ እኔ አቶ ዮፍታሔ ከሞቱ በኋላ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት “አፋጀሽኝ” ትያትር ለማዘጋጃ ቤት አክተሮች እንዳስጠናና እንዳሳይ ታዘዝኩ፡፡
እነ ተስፋዬ ሳህሉን፣ እነ… ሁሉን ላስታውስ አልችልም፡፡ እነሱ እነሱን ሰብስበው ይኼን ትያትር አስጠንቼ አሳይቻለሁ፡፡ እንግዲህ ትያትሩን አስጠንቼ ባሳየሁበት ጊዜ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አሁን ለመጀመርያ ጊዜ አደባባይ የወጣ ታሪካቸውን እኔ ለጉባኤው ገልጬ ነበር፡፡ ያ የገለጥኩት ታሪክ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተፃፈ፤ በጊዜው፡፡ ትያትሩ ተደነቀ፡፡ እንደገና እነሱም እየደጋገሙ አሳይተውታል፡፡
(የ95 ዓመቱ አዛውንት አቶ በለጠ ግርማ በባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ የተዘጋጀውና በወንድማቸው በዶ/ር ዮናስ አድማሱ የአርትኦት ሥራው የተሰራለት “የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ አጭር የህይወቱና የፅሁፉ ታሪክ” መፅሐፍ ሰሞኑን በተመረቀበት ወቅት ከተናገሩት የተወሰደ)

 

Read 4768 times