Print this page
Saturday, 23 February 2013 11:41

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(13 votes)

 

መልክአ ኢትዮጵያ - ፮

አትላንታ በቆየኹበት ጊዜ የኢትዮጵያውያን ባለውለታ እንደኾነ ወደሚነገርለት ሱፐር ማርኬት አቅኝቼ ነበር፡፡ደካልብ ፋርመርስ ማርኬት (Dekalb Farmers Market) ይባላል፡፡ ከ34 ዓመት በፊት ሮበርት ብላዛር (Robert Blazer) በተባለ እስራኤላዊ ተቋቁሞ እስከ አሁን በእርሱው ይመራል፡፡ ባለቤቱና አንድ ልጁም አብረውት አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ቀደምት የድርጅቱ አካል ናቸው፡፡ ቦታውን አሳጥረው ‹‹ፋርመርስ›› እያሉ ይጠሩታል፡፡
ሱፐር ማርኬቱ ግቢ ስንደርስ በተንጣለለው የመኪና ማቆሚያ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መኪኖች ተደርድረዋል፡፡ የሱፐር ማርኬቱን ስፋት አካቶ ማየት ስለማይቻል በሩቁ በቪላ ቅርጽ ዙሪያውን በዕንጨት የተሠራ ትልቅ መጋዘን ይመስላል፤ ነገር ግን ሱፐር ማርኬቱ በ14 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም ሙሉ ስፋት እንኳ 10 ሺሕ ካሬ ሜትር መኾኑን ልብ ይበሉ፡፡ ወደ መግቢያ በሩ ተጠግተን በስተግራ በኩል ረጅም አግዳሚ ወንበር ላይ በርካታ ሰዎች በተርታ ተቀምጠዋል፤የቆሙም አሉ፡፡ ከሩቅ ስመለከታቸው ዕቃ ለመግዛት ተራ የሚጠብቁ ሰዎች መስለውኝ ነበር፤ እየቀረብናቸው ስንመጣ ግን ሁሉም ማለት ይቻላል ኢትዮጵያውያን መኾናቸውን ለየኹ፡፡ ‹‹እንደዚህ ተራ ተጠብቆ ነው የሚገዛው? ደግሞ ደንበኞቹ በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው እንዴ?›› ስል ለሚኒ ማርኬት ባለቤቷ አስጎብኚ ዘመዴ መዓዛ ጥያቄ አቀረብኹ፡፡‹‹ሥራ ለመቀጠር የመጡ ናቸው፡፡ ፋርመርስ በየሳምንቱ ረቡዕ ሁልጊዜ ሰው ስለሚቀጥር ለመመዝገብ የመጡ ናቸው፤››
አለችኝ፡፡
በአትላንታ ኖሮ በፋርመርስ ያልሠራ ጥቂት ነው፡፡ ሌላ ቦታ ሥራ ሲጠፋ ፋርመርስ ስለማይጠፋ ከሌላ ቦታ ሲቀነሱ ተመልሰው ፋርመርስ ይቀጠራሉ፡፡ ‹‹እጅ ማፍታቻና አገር መላመጃ ነው፤›› ይሉታል፡፡ ለረዥም ጊዜ እዚሁ ቆይተው የሠሩም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ አግዳሚው ወንበር ላይ ተደርድረው ምዝገባ እስኪጀመር የሚጠባበቁትን የአገር ቤት ልጆች አልፈን በየሳምንቱ 100 ሺሕ ደንበኛ እንደሚያስተናግድ ወደሚነገርለት ሱፐር ማርኬት ዘለቅን፡፡
ሥራ ፈላጊዎቹ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ለ‹‹ፎርቹን›› የቢዝነስ ጋዜጣ በሪፖርተርነት ስሠራ የጎበኘኹትን ደብረዘይት ውስጥ የሚገኝ ‹‹ብሉናይል›› የተባለ የፕላስቲክ ፋብሪካ ሥራ ፈላጊዎች አስታወሰኝ፡፡ የፋርመርሱ ሥራ ፈላጊዎች ብሉናይል ካየኋቸው በቁጥር ይበዛሉ፤ የደብረዘይቶቹ ተራቸውን ይጠብቁ የነበረው ባገኙት ድንጋይ ላይ ቀምጠው ነው፤ የፋርመርሶቹ በሰዓት 180 ብር ከ50 ሳንቲም (9.50 ዶላር) ክፍያ ሲኾን የብሉናይሎቹ በወቅቱ ክፍያ በሰዓት 1ብር ከ04 ሳንቲም ክፍያ ለመሥራት የተሰለፉ ከመኾናቸው በቀረ በመልክ ተመሳሳይ ናቸው፡፡የብሉናይሎቹ ተስፈኞች የእነኝህን ክፍያ ቢሰሙ እንኳን በፋመርስ ደጅ በገሃነም ደጅም ለመሰለፍ እንደሚወስኑ ገመትኹ፡፡
የጅምላ መሸጫውን መጋዘን ጣራ ርቀት ለመገመት ይኹን ለማስረዳት በልኬት ካልኾነ ይከብዳል፤ በአጭሩ ጣሪያው በጣም ሩቅ ነው፡፡ ከላይ ወደታች ያልተንጠለጠለ የአንድም አገር የቀረ ሰንደቅ ዓላማ የለም፡፡ ‹‹በመላው ዓለም የሚገኝ ማንኛውም ምርት በፋርመርስ አይጠፋም›› የሚል መፈክር አላቸው፡፡ የኢትዮጵያን ባንዲራ ስመለከት ምናልባት ለኢትዮጵያውያኑ የድርጅቱ ሠራተኞች ማስታወሻ ተሰቅሎ ይኾናል የሚል ግምት አድሮብኝ ነበር፣ በኋላ ላይ የሐበሻ ጎመን፣ጊዮርጊስ ቢራና ቡና የኢትዮጵያ ምርት ስለመኾናቸው መግለጫ ተጽፎባቸው ስመለከት የባንዲራው መሰቀል በኩራት ቀብረር አደረገኝ፡፡
መዓዛ የሐበሻ ጎመን የኢትዮጵያ መሆኑ ተለጥፎበት፣ በዚያ ላይ ዋጋው ከሌሎቹ ሁሉ በዕጥፍ በልጦለ መጀመሪያ ጊዜ ባየችበት ቀን፣ጎመኑ ያለበት ቦታ ቆማ የሚያልፍ የሚያገድመውን የውጭ ዜጋ ሸማች እየጠራች፣ ‹‹እዩት የእኛ አገር ጎመን ነው፤….የኢትዮጵያ ጎመን እኮ ነው፤… ኦርጋኒክ ስለኾነ እኮ ነው የተወደደው፤›› እያለች ግብይቷን ጥላ እንደሞኝ ለሰው ስታሳይ እንደዋለች ነገረችኝ፡፡ በባዕዳን መካከል አገርን የሚያስጠራ ነገር ሲገኝ ሞኝ እንደሚያደርግ እኔም ዕድል ገጥሞኝ አይቼዋለኹ፡፡ ይኸውም የደረሰብኝ በቺካጎ ነው፡፡ ቺካጎ የሚገኘውን የአፍሪካ - አሜሪካ ሙዚየም ለመጎብኘት ከቡድኑ አባላት ጋራ በሄድኹበት ጊዜ ገና መግቢያው ላይ በሚታየው ነጭ ሸራ ላይ የተቀረጹ የግእዝ ፊደላት ተመለከትኹ፤ የኢትዮጵያም ታሪክ በአጭሩ ተጽፎ በመስተዋት ውስጥ ተሰቅሎ አነበብኹ፤ ‹‹እዩት የኢትዮጵያ እኮ ነው›› እያልኹ ሰዉን ሁሉ ሌላ ነገር አላስይዝ አላስጨብጥ ያልኁትን አስታወስኹ፡፡
በዓለም ሕዝብ ሁሉ ዘንድ ዝነኛ ለምትመስለን እምዬ ኢትዮጵያ ‹‹የት ነበር የምትገኘው?›› የሚል ጥያቄ መከተሉ ካገኘኋቸው ብዙዎቹ ነጮች የገጠመኝ ነበር፡፡ በአብዛኛው ግዛት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን እየኖሩ፣ የኢትዮጵያውያን ባህላዊ ምግብና መጠጥ ቤት፣ የቁሳቁስ፣ አልባሳትና ጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር መገኛዋ የት እንደኾነ ከሚያውቁት የማያውቁት ይልቃሉ፡፡ ይህ በኾነበት የሐበሻ ጎመን በምድረ አሜሪካ ከሌሎቹ በዋጋ ልቆ ሲገኝ ለአስረጅነት የሚሰጠው ኀይልና ምክንያት ያስፈነድቃል፤ መያዣ መጨበጫውንም ያሳጣል፡፡
የፋርመርስ ውስጠኛው ክፍል ልክ እንደውጪው ሁሉ በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች የተሞላ ነው፡፡ ከነጫጭ ጋዎን ጀምሮ እንደ ሥራ ምድባቸው የተለያየ ዐይነት ዩኒፎርም የለበሱ፣ኮፍያና ጓንት ያጠለቁ የአገሬ ልጆች በሥራ ተወጥረዋል፡፡ ውስጥ ለውስጥ ከሚነዱ ተሽከርካሪዎች ላይ ዕቃ ያወርዳሉ፤ ይጭናሉ፤ ይደረድራሉ፤ በጋሪ ይገፋሉ፤ ያጸዳሉ፤ ያሽጋሉ፤ ያስተካክላሉ፤ ደንበኞቻቸውን ያማክራሉ፡፡ ሁሉም ትኩረታቸውን በሥራቸው ላይ አድርገዋል፡፡ በቀዝቀዛው ከተማ በአንዳንዶቹ ግንባር ላይ ችፍ ያለ ላብ ይታያል፡፡ እርስ በርስ የሚተያይ ሰው የለም፡፡ ከቅርብ አለቃቸው በተጨማሪ እነርሱንም ገበያተኛውንም የሚቆጣጠር በርካታ ካሜራ ሊኖር እንደሚችል ገምቻለኹ፡፡
አብዛኞቹ መዓዛን ስለሚያውቋት ‹‹አዘሻል፤ይጫንልሽ?›› እያሉ ይጠይቋታል፡፡ ወደ ሱፐር ማርኬቱ የመጣችው ሰው ልታስጎበኝ በመኾኑ የሚጫን ዕቃ አልነበራትም፡፡ ‹‹ዛሬ በችርቻሮ ነው›› እያለች አሣሥቃ ትመልሳቸዋለች፡፡ ግብይቱ በአማርኛ ነው፡፡ ከአትላንታ ወጣ ብላ በምትገኝ ከተማ የዶክትሬት ዲግሪውን በመማር ላይ የሚገኘው የቀድሞው ጋዜጠኛ ጓደኛዬ ዳዊት ጋራ ፋርመርስን ካየኹት በኋላ ስለቤቱ ስንጨዋወት አንድ የእርሱ ጓደኛ፣ ‹‹ለምን ወደ ፋርመርስ ሄጄ እንደምሸምት ታውቃለኽ፤ ደኅና ዋላችሁ? ደኅና አመሻችኹ?ብዬ ገብቼ ማነሽ እንትናዬ ቂንጬ ይኖራል?ብዬ ጠይቄ የፈለግኹትን ነገር ገዝቼ ከተደረደሩት ገንዘብ ተቀባዮች ለአንዱ ከፍዬ ደኅና ዋሉ ወይም አመሰግናለኹ ብዬ ስለምወጣ በቃ ደስ ይለኛል፤››እንዳለው አጫውቶኛል፡፡
አስጎብኝዬ መዓዛ የቤቱ ደንበኛ ስለኾነች ማስጎብኘቱን ያስጀመረችኝ ከጅምላ መሸጫው ክፍል ነበር፡፡ በጥድፊያ እያለከለኩ ከውጭ ሲገቡ ያየኋቸው ሦስት ልጆች አንድ ጥግ ካለው ዕቃ ማስቀመጫ ሎከር ውስጥ የለበሱትን አውልቀው እያስቀመጡ የዩኒፎርም ጋዎን እያወጡ ይለብሳሉ፤የምሳ ዕቃቸውንም እዚያው ውስጥ ሲከቱ አየኋቸው፡፡ራቅ ብዬ ስለነበር በደንብ እንዲታየኝ ቀረብ አልኁ፡፡የአንዱን ክፍል ግድግዳ ግማሽ ያህሉን በያዘው የብረት ሎከር በእያንዳንዱ ላይ ስም ተጽፎበታል፡፡ጌታቸው፣ ተስፋዬ፣ሰላም፣ነጻነት፣መስፍን፣….አንድ የቀረ ኢትዮጵያዊ ስም የለም፡፡ አሁን በስያሜና አጠራር የጠፉ ስሞች ሁሉ መገኛቸው እዚያ መሰለኝ፤የቻልኹትን ያህል አነበብኹ፡፡ከጥቂት በስተቀር እንግዳ ስም አልገጠመኝም፤ የሎከሩ ባለቤቶች ከ90 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
ወደ ዋናው የሱፐር ማርኬቱ ክፍል (መቼም ስፋቱን በካሬ ሜትር ስለነገርኋችኁ ሱፐር ማርኬት ስል አጥብባችኹ እንዳትመለከቱት) ስንገባ አልፎ አልፎ ጥቁርና ነጭ ሠራተኞች ቢኖሩም ዐይኔ ከኢትዮጵያውያን በቀር አንድም ሰው ማየት አልቻለም፡፡ ቆይቼ እንደተረዳኹት ድርጅቱ ካለው ወደ 1000 የሚጠጋ ሠራተኛ ውስጥ 700 የሚኾኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ያለምንም ጥርጥር አንድ የማውቀው ሰው እንደማገኝ ርግጠኛ ነበርኹ፡፡
በገበያው ውስጥ በዓለም ላይ የሚገኝ የሚበላና የሚጠጣ ነገር ሁሉ በዚያ አለ፡፡ኢትዮጵያውያኑ ሠራተኞች የሽንኩርቱን ገለባ እያራገፉ አስተካክለው ይደረድራሉ፡፡የተለያዩ አትክልቶችን እየመዘኑ በላስቲክ እየቋጠሩ ያስቀምጣሉ፡፡ ቆሻሻውን ከሥር ከሥር ይጠርጋሉ፡፡ በአልፎ ሂያጅ ሰላምታ እየተለዋወጥን ተዟዙረን ጎበኘነው፡፡ አትክልት ቤቱ፣ሥጋ ቤቱ፣ጥራጥሬ ቤቱ፣መጠጥ ቦታው፣አበባ ቤቱ በሁሉም ዘንድ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ሱፐር ማርኬቱ ውስጥ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ብዛት ያየ በአገሩ ሰው የቀረ አይመስለውም፡፡
በትንንሹ ተቆራርጦ በስቴክኒ ዕንጨት ላይ የተሰካ የተለያየ ዐይነት ዳቦ ከፊት ለፊቷ ባለ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣ ስታስቀምስ ያየኋት ልጅ የሥራ ድርሻ ካየኋቸው ሠራተኞች በሙሉ ቀላሉ መሰለኝና ከቀማሾቹ እንደ አንዱ በመኾን ሰላምታ አቀረብኁላት፡፡ በፈገግታ ተቀበለችኝ፤ አዲስ መኾኔን ነግሬያት ሥራ ልቀጠር እንደፈለግኹና እንደርሷ ቀለል ያለ ሥራ እንዴት እንደሚገኝ ጠየቅኋት፡፡ ‹‹የእኔ ሥራ ቀላል መስሎሽ ነው?›› አለችኝ፤ በጥያቄዬ መጠነኛ መከፋት አስተዋልኹባት፡፡
‹‹መቆሙ ይከብዳል?›› አልኋት፡፡ ‹‹እዚህ የምቆመው ለአንድ ሰዓት ነው፤ አስቀምሼ ስጨርስ ወደ ውስጥ እገባለኹ፤››አለችኝ፡፡ ‹‹ወዴት?›› አልኋት ካለችበት ሳትንቀሳቀስ ቀናም ሳትል፣ ‹‹ከእኔ በላይ ያለው ፊልም ይታይሻል?›› አለችኝ፤ ቀና ብዬ አየኹት፤ 21 ኢንች በሚያህል ፍላት ስክሪን ቴሌቭዥን ላይ ዳቦ ከመጋገሩ በፊት ያለውን ሂደት ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከታች እስከላይ ነጭ ለብሰው ከቡኮው እስከ ጋገራው በሥራው ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡የልጅቷ ዋና ሥራ ማቡካትና መጋገር ነበር፡፡ ለማስቀመስ ወደ መሸጫው የምትወጣው ተራ ሲደርሳት በቀን ውስጥ ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው፡፡ ‹‹ለትምህርት መጥተሽ ካልኾነ በቀር አገር ቤት ጥሩ ሥራ ካለሽ እዚህ እንድትቀሪ አልመክርሽም፤ እኔ ከመጣኹ ሁለት ዓመቴ ነው፤ አሁን እንደ ድሮው አይደለም ይላሉ፤›› ስትል ምክር ለገሠችኝ፡፡ ከተል አድርጋም፣‹‹እዚሁ አገር ካልተማርሽ የምታገኝው ሥራ ሁሌም ዝቅተኛውን ነው፤›› አለችኝ፡፡
ወደ ሥጋ መሸጫው ተጠግተን ጉብኝታችንን ቀጥለናል፡፡ የበሬ፣የዶሮ፣የዓሣ፣ የተርኪ ብቻ የሌለ ዐይነት የሥጋ ዘር የለም፡፡ እንደጠረጠርኹት ስሜ ከኾነቦታ ተጠራ፡፡ የጠራኝን ሰው ማንነት ለማረጋገጥ ዐይኔ ተቅበዘበዘ፡፡ ፊት ለፊቴ ካለው የሥጋ ክፍል አንድ ወጣት እየሣቀ ወደ እኔ መጣ፡፡ነጭ በነጭ ለብሷል፡፡ ፕላስቲክ ቦቴ ጫማና ኮፍያ አድርጓል፡፡ጓንቱ በደም ተነክሯል፡፡‹‹ምስክር!›› በመገረም ጮኽ ብዬ ተጣራኹ፡፡እርሱም ዐይኑን ማመን አልቻለም የሞቀ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡
ምስክርን የማውቀው አዲስ አበባ ነው፡፡ሰፈሩ ኮተቤ አካባቢ ነው፤ ለቤተሰቦቹም አስቸጋሪ የሚባል ወጣት ነበር፡፡ ከ11 ዓመት በፊት ይመስለኛል በሰፈራቸው የቡድን ጠብ ፈጥረው ሲደባደቡ አንዱ ሕይወቱ ያልፋል፡፡ በዚያ ምክንያት ለብዙ ጊዜ ታስሮ ከተፈታ በኋላ እናቱ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኙት እኅታቸውጋ አስቀምጠውት ከእነ አስቸጋሪነቱ ከቤተሰቦቹ በሚደጎመው ገንዘብ ዝንጥ ብሎ ይኖር ነበር፡፡ ወደ አሜሪካ መቼ እንዳቀና ባላውቅም አዲስ አበባ እያለ ባጋጣሚ ባገኘኹት ቁጥር ‹‹አሜሪካ ልሄድ ነው››ይለኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
ምስክርን ዛሬ አገኘኹት፡፡ በእናቱ ጫንቃ ላይ የነበረው ያ ሁሉ አይበገሬነት ጠፍቶ በፋርመርስ ሥጋ ቤት አንገቱን ደፍቶ ሥጋ ቆራጭ ኾኗል፡፡ ምስክር የወጣበት የውስጠኛው ክፍል የገባው ሥጋ ተስተካክሎ እየተቆራረጠ ለገበያ የሚዘጋጅበትና የሥጋ ዘሮቹን ተከትለው የሚመጡትን ቆሻሻዎች ማጽዳት ነው፡፡ ምስክር በቆምንበት የተሻለ ኑሮ እየመራ ስለመኾኑ አጠር አጠር አድርጎ ነገረኝ፤ በሥራ ሰዓት ቆሞ ማውራት ብዙም አይፈቀድም መሰለኝ አድራሻውን ሰጥቶኝ እየተቻኮለ ወደ ውስጥ ገባ፡፡
የምስክርን የአሁኑን ትጋት ስመለከት አዲስ አበባ ሳለ ሌላው ይቅርና ካኔቴራውን እንኳ ራሱ አጥቦ እንደማያውቅ ሲያወሩ መስማቴን አስወስኹ፡፡ ኹኔታው ኢትዮጵያውያን ‹‹ጥረህ ግረኽ በወዝኅ ብላ›› የሚለው የመጽሐፉን ቃል የሚተገብሩት ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ብቻ ያስብላል፡፡ አይ አሜሪካ! እነ ምስክርን እንኳን ሥጋ ቆራጭ አደረገቻቸው፡፡ እናቱ ለደቂቃ ቢያዩት ስል ከልቤ ተመኘኹ፡፡
ፋርመርስ እውነትም የኢትዮጵያውኑ ባለውለታ ቤት ነው፡፡ ድርጅቱ ባይኖር ኖሮ ያ ሁሉ ኢትዮጵያዊ የት ይቀጠር ነበር? ስልራሴን ጠየቅኹ፡፡ግልጥ ባለው ሰፊ ክፍል ውስጥ ከፍ ባለው የገንዘብ መሰብሰቢያ ላይ ከባንኮኒያቸው ጀርባ ዙሪያውን የተቀመጡት ገንዘብ ሰብሳቢዎቹን ለመረጃ ይኾነኝ ዘንድ ቆሜ ቆጠርኋቸው፤ 50 ከሚኾኑት ገንዘብ ሰብሳቢዎች ውስጥ ከሦስቱ በስተቀር በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡መቼም በሥራቸው ጎበዝ ቢኾኑ እንጂ እስራኤላዊው ባለቤት ኢትጵያውያኑን እንዲህ አንድ ላይ ሰብስቦ የሚቀጥርበት ምክንያት አልታየኝም፡፡
በፋርመርስ የአገሬን ልጆች ጥንካሬ አየኹበት፤ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለማቆየት ባህር ማዶ ተጉዘው በሰው አገር ሥራ ሳይንቁ አጎንብሰው የታዘዙትን ይሠራሉ፡፡ ከሰዓታት በላይ የወሰደብንን ጉብኝት ጨርሰን ስንወጣ ባዶ የፕላስቲክ ምሳ ዕቃቸውን ይዘው የሚመለሱ በርካታ አማርኛ ተናጋሪ ሠራተኞች ጋራ ተላለፍን፡፡ እኒህ ደግሞ ድሬዳዋ የሚገኘውን የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ (ኮተኒ) ሠራተኞች አስታወሱኝ፡፡ ልዩነቱ አብዛኛዎቹ የፋርመርስ ሠራተኞች ምሳ ዕቃዎቻቸውን ይዘው የወረዱት ከመኪናዎቻቸው ውስጥ ነው፡፡ የኮተኒዎቹ በረጅሙ የመሥሪያ ቤታቸው አሮጌ ሰርቪስ አውቶብሱ በሙቀት ተፋፍገው፣ ፊታቸው በመስታወቱ ላይ እስኪጣበቅ ድረስ ተገፋፍተው እንደምንም በብታቸው ሥር ሸጉጠው ያደረሱት ምሳ ዕቃ መኾኑ ነው፡፡ በፋርመርሶቹ ምሳ ዕቃ ውስጥ እነ ቀዝቃዛ ሽሮ በጥቁር እንጀራ ቦታ እንደማይኖራቸውም ርግጠኛ ነበርኹ፡፡
በታላቋ አሜሪካ ሥራ መፈለግ አሳሳቢ ጉዳይ ይኾናል የሚል ግምት ስላልነበረኝ ለምሰማው ነገር እንግዳ ኾኜ ነበር፡፡ በተለይ እንደ ሆቴል፣ፓርኪንግ የመሳሰሉ ጉርሻ ያላቸው ሥራዎች በአብዛኛው የሚገኙት ‹‹በዘመድ ነው›› ሲሉኝ ‹‹ብቻ ከኛ አገር እንዳይኾን ልምድ የቀሰሙት›› ብዬ ነበር፤ ነገር ግን እንደሰማኹት አሜሪካን ከገጠማት የኢኮኖሚ አለመረጋጋት የተነሣ የሥራ ዐጥ ቁጥር ከፍ ብሏል፡፡ ከሦስትና አራት ዓመታት በፊት ሁለት ሥራ እንደልብ የሚገኘውን ያህል አሁን አንድ ሥራ ማግኘትም አስቸጋሪ ኾኗል ይላሉ፡፡ አልፎ አልፎ በርካታ ፈላጊ ባላቸው ሥራ ቦታዎች ላይ ሌላ ሰው እንዳይተኩበት ሰግተው ዕረፍት ከመውጣት እንኳ ታቅበው የሚሠሩ አሉ፡፡
በሌላ ገጽ በትምህርት ውጤታማ ኾነው በሞያቸው የሚሠሩ (professionals)፣በንግድ ዓለም ውስጥ ገብተው ውጤታማ የኾኑና በአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ያላቸው፣ ያየኋቸውም ዝናቸውንም የሰማኋቸው ስኬታማ የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ አትላንታ በጎበኘኹት ጫትና ሺሻ ቤት ውስጥ ስኬታማ ስለተባሉት ምሁራን ተነሥቶ ‹‹መማር ይጠቅማል አይጠቅምም›› በሚል የአምስተኛ ክፍል አማርኛ መምህሬ ጎራ ከፍለው ያከራክሩን የነበረው ዐይነት ክርክር በባለ ታክሲዎች ዘንድ ተነሥቶ ትምህርት ቀመሶቹና የመማር ፍላጎት ያላቸው በአንድ ጎራ ኾነው ስለመማር ጥቅም አሜሪካ የሚገኙ የተማሩ ሰዎችን ኑሮ፣የሥራ ዐይነት እየጠቀሱ ስለስኬታቸው በመዘርዘር ነገሮች አልመቻች ስላላቸው እንጂ መማር እንደሚፈልጉ ሽንጣቸውን ይዘው ሲከራከሩ ነበር፡፡
‹‹በአሜሪካ በተማረና ባልተማረ ሰው መካከል ምንም ልዩነት የለም፤›› በማለት ሲከራከር የነበረው ባለታክሲ፣ ‹‹እኔ እዚህ አገር ስመጣ አብሮኝ የመጣው ጓደኛዬ እኔ ከመጣኹ ጀምሮ እየሠራኹ ቢያንስ በዓመት እስከ 40 ሺሕ ዶላር ገቢ ሳገባ እርሱ ሲማር ሰባት ዓመት ፈጅቷል፡፡ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ሥራ ሲቀጠር እኔ ከማገኘው ገቢ የተሻለ ሲከፈለው አላየኹም፤ እንዲያውም የተማረበትን ዕዳ ስለሚከፍል እኔ በገቢ እበልጠዋለኹ፤›› በማለት ሲከራከር ሰምቼዋለኹ፡፡ ስለ ዶክተሮችም አንሥቶ፣ ‹‹እነሱም ቢኾኑ በጥቂት ገቢ ነው ሊበልጡን የሚችሉት፤ እሱንም ወጥረን ከሠራን እኩል ነን፤ እነርሱ ከሚገዙበት ሱፐር ማርኬት ገዝተን እንበላለን፤ ልጆቻችንን አንድ ዐይነት ወተት አጠጥተን አንድ ዐይነት ዳይፐር እናደርጋለን፤ እነርሱ ከሚገዙበት ገዝተን እንለብሳለን፤ እነርሱ በሚኖሩበት ቤት እንኖራለን፤ አብዛኛው የአኗኗር ቅጣችን አንድ ዐይነት ነው፤ እነርሱም አገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቻውን ይረዳሉ እኛም እንረዳለን፤ ማነው የተማረን ብቻ ስኬታማ ያደረገው?›› በሚል ሲሟገት ነበር፡፡ ‹‹እንዲያውም ዶክተሮቹና የተማሩት እዚህ መጥተው በነጻነት ሺሻቸውን እያጨሱ አይዝናኑም፤ እኔ ደግሞ እዝናናለኹ፤››በማለት ሲሣለቅ ነበር፡፡ በርግጥ ባለታክሲው እንዳለው በገቢያቸው ምክንያት የምግባቸው ዐይነት ተመሳሳይ ቢኾንም በተማሩበት ሞያና ባገኙት የሥራ ዘርፍ ላይ ተሠማርተው በሚሠሩት መካከል የኑሮ ልዩነት አለ፡፡
አብዛኞቹን የሚወክለው የሥራ ዘርፍ በኢትዮጵያውያን ሬስቶራንት ውስጥ መስተንግዶና ወጥ ቤት፣የምሽት ጭፈራ ቤቶች ውስጥ መጠጥ ቀጂነትና መስተንግዶ፣ በካፌ፣ በኤርፖርት ውስጥ በሚገኙ ፈጣን ምግብ መሸጫዎች ውስጥ አስተናጋጅነት፣ ምግም አዘጋጅነትና ገንዘብ ተቀባይ፣በተለያዩ ቦታዎች በሽያጭ ሠራተኝነት፣ ፓርኪንግ፣ ነዳጅ ማደያ፣ ሆቴል ውስጥ ከጥበቃ እስከ ጽዳት፣ሙዚየም ውስጥ ጽዳት፣መኪና ማከራያ ውስጥ መኪና አጠባ፣ የተለያዩ የንግድ ቦታዎች በሽያጭ ሠራተኝነት፣ታክሲ፣ሊሞዚን፣የከባድ መኪና አሽከርካሪ፣አዛውንቶችን መንከባከብ፣ፋብሪካ….. እንዲህ ያሉት ሥራዎች በበርካታ በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ሲሸፈኑ ያየኋቸው ናቸው፡፡
እንደ ነርሲንግ ሆምና ሆም ኬር ያሉ የአዛውንቶች መንከባከቢያ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ክፍያው ከሌሎቹ ሥራዎች የተሻለ እንደኾነ ይናገራሉ፤ሥራው ግን አስቸጋሪ ነው ይሉታል፡፡ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በቦታው ላይ ካልታዩ በስተቀር ሥራቸው ምን እንደኾነ መናገር አይፈልጉም፡፡ በጣም ካልተቀራረቡም በግምት ካልኾነ አንዱ የአንዱን ሥራ አያውቅም፡፡
እንደኔ ከአገር ቤት የሄደ ከኾነ ከጓደኝነትና ከዝምድና በቀር የተዋወቅኹትን ሰው ሁሉ ሥራውን ዐውቃለኹ ማለት ዘበት ነው፡፡ ስለነርሲንግ ሆም ለማወቅ ጥረት በማደርግበት ወቅት በደንብ ትነግርሻለች በሚል ቨርጂኒያ ውስጥ ያገናኙኝን አንዲት ልጅ እያጨዋወትኹ ስጠይቃት ‹‹ነርስ ነኝ›› አለችኝ፡፡ ‹‹በጣም ጎበዝ፣ ተምረሽ ነው?›› ብዬ ስጠይቃት፣ ‹‹ኮርስ ወስጄ ነው›› ስትል በአጭሩ መለሰችልኝ፡፡ በመልሷ መርካት ስላልቻልኹ ዙሪያዋን ብዞራትም አልኾነልኝም፡፡ በመጨረሻ ‹‹መድኃኒት ነው የምሰጠው አለችኝ፤›› ተስፋ ቆርጬ ልተዋት ስል ኾን ብላ በምሳ ሰበብ ያገናኘችኝ ዘመዴ ‹‹በናትሽ ንገሪያት›› ብላ ልታግባባት ስትሞክር፣ ‹‹ስሚ እኔ የአሮጊትና የሽማግሌ ዳይፐር የቀየርኩበትን ጊዜ ከዕድሜዬ ላይ እንዳልኖርኁት የምቆጥረው አስቀያሜ ጊዜ ስለኾነ እንኳን መተረክ ማስታወስ አልፈልግም፤›› ስትል አምርራ ተቆጣች፡፡
እኔም የልጅቷ ምሬት የገባኝ ፍሎሪዳ ፔንሳኮላ ውስጥ በአንድ የፊሊፒንስ የአዛውንቶች መከባከቢያ ቤት ውስጥ ያገኘኋት ኢትጵያዊት ወጣት ናት፡፡ አዛውንቶቹን ከማጫወት፣ተረት ከማውራት፣ከማብላት፣ልብስ ከመቀየር፣የእግር መንገድ አብሮ ከመጓዝ. . . የባሰባት የጠዋት ተረኛ ገቢ ኾና ሌሊት ያደሩበትን ዳይፐር መቀየር ነው፤ እሱን ስታስታውሰው ያንገፈግፋታል፡፡ (ይቀጥላል)

Read 5907 times Last modified on Friday, 15 March 2013 07:32