Saturday, 23 February 2013 11:36

145 ዓመታት የፈጀ ትግልና ውጤቱ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ከሴባስቶፖል መድፍ እስከ ህዳሴ ሄሊኮፕተር
በሚፅፏቸውና በየመድረኩ በሚያቀርቧቸው ንግግሮች ላይ በሚያነሱት አነጋጋሪ ሃሳብ የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ “የክህደት ቁልቁለት” በሚል ርእስ በ1996 ዓ.ም ባሳተሙት መፅሐፍ ውስጥ፤ አገራችን ኢትዮጵያ አልላቀቅ ስላላት ችግር፣ ምክንያቱና አዙሪቱ እንዲህ ፅፈዋል፡-
“በ1860 አፄ ቴዎድሮስን ሊወጋ የመጣው በናፒየር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር የመጓጓዣ ዘዴው ከቴዎድሮስ ጦር የተሻለ አልነበረም፤ እንስሳት እየተጠቀመ ነው መቅደላ የደረሰው፡፡ በ1888 በአፄ ምኒልክ ዘመን የኢጣሊያ ጦር ኤርትራን በቁጥጥር ስር አድርጐ ትግራይን አቋርጦ አምባላጌ ሲደርስ መጓጓዣው ያው አጋሰስና አህያ ነበር፡፡ የአፄ ምኒልክም ጦር ከአምባላጌ እስከ አድዋ ያለውን የኢጣሊያ ጦር ያሸነፈው ከመሀል አገር በአጋሰስና በአህያ ያለውን ጭኖ ነበር፡፡ ከአርባ አመታት በኋላ በ1928 የኢጣሊያ ጦር በመሬት፣ በጦር መኪናና በታንክ፣ በሰማይ አውሮፕላን መርዙን እየዘራ ተመልሶ ሲመጣ፤ የአፄ ኃይለሥላሴ ጦር ወደ ማይጨው የዘመተው ያው እንደተለመደው አህያ እየነዳ ነበር፡፡
“በ1860 አፄ ቴዎድሮስን ሊወጋ ወደ መቅደላ ከመጣው የእንግሊዝ ጦር ጀምሮ እስከ ማይጨው ጦርነት (ማለት ከ1860-1928) አራት ትውልዶች ያህል በቅለዋል፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ የኢጣሊያና የእንግሊዝ ትውልዶች ምን ያህል መጥቀው እንደሄዱ መዘርዘር አስፈላጊ አይሆንም፡፡ የሚደንቀው ደግሞ የወያኔ ልጆች አዲስ አበባ ሲገቡ አህያ እየነዱ ነበር… የአዕምሮና የመንፈስ ኃይሉን የማይጠቀም ሕዝብ አህያ ከመንዳት ሊወጣ አይችልም”
ከጥንት እስከ ዛሬ በገጠር ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባም ለትራንስፖርቱ መቀላጠፍ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለው አህያ፤ የአገራችንን የችግርና የኋላቀርነት አዙሪት ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ሆኗቸዋል - ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፡፡ ፕሮፌሰሩ የእድገትና ለውጥ ፍላጐታቸው ገፍቷቸው ነው ይህን ያሉት፡፡ አህያን ከሸክም ነፃ አውጥቶ በላቀ የቴክኖሎጂ ትሩፋት የሚጠቀም ትውልድና አገር መፍጠር ቀላል የማይባል ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡
ላለፈው ትውልድ ልፋትና ድካም ቀጣዮቹ እውቅና ለመስጠት ንፉግ ሲሆኑ የሚመዘገበውም ለውጥ አዝጋሚና የቀጣይነት ችግር እንዳለበት ይታያል፡፡ በአገራችን የዘመናት ጉዞ ችግር ብቻ ሳይሆን እድገትም እንዳለ፤ የኢፌዲሪ የመከላከያ ቀንን ምክንያት አድርጐ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለ10 ቀናት የቆየው ትርዒት በብዙ ሰዎች ከመጐብኘቱም ባሻገር ብዙዎችን አወያይቷል፡፡
በኤግዚቢሽን ስለቀረበው ዝግጅት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ብዙ ስለተባለለት በአድናቂዎች የተሰጡትን ሐሳብ በመጋራት፣ ለመሆኑ እዚህ ደረጃ መድረስ እንዴት ተቻለ? ለሚለው ጥያቄ ካለፉት ዘመናት ጥረትና ድካሞች የተወሰኑትን ለማመልከት እሞክራለሁ፡፡

ሴቫስቶፖል - የኢንዱስትሪው መነሻ
አፄ ቴዎድሮስና የታላቁ መድፍ ታሪክን መነጣጠል የማይቻል የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡
ስለ ንጉሡ ታሪክና ሥራ አንስቶ የሚፅፍም ሆነ የሚናገር ሁሉ በደብረታቦር (ጋፋት) ስለተሰራውም ሴቫስቶፖል ማንሳቱ አይቀርም፡፡ “አፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚል ርእስ በተክለፃዲቅ መኩሪያ ተዘጋጅቶ በ1981 ዓ.ም የታተመው መፅሐፍ፤ አፄ ቴዎድሮስ ሴቫስቶፖልን ለትርዒት ማቅረባቸውን ሲጠቁም “ሰላምጌ እንደ ደረሱ እመቅደላ ላይ በእስረኝነት ያሉት ፈረንጆች መጥተው ይኸን መድፍ እንዲያዩ ጥሪ አደረጉላቸው፡፡” ይላል፡፡ እንግዲህ አገራችን የጦር መሳሪያን ለኤግዚቢሽን ማቅረብ የጀመረችው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡

አፄ ምኒልክ ያቋቋሙት የጥይት ፋብሪካ
ከዘመናቸው በቀደመ አስተሳሰባቸው የተነሳ በቅርብ የነበሩ ወገኖቻቸው ያልተረዷቸው አፄ ቴዎድሮስ፤ አገርና ሕዝብን ለማሳደግ እንዲሁም መንግሥትንና አስተዳደሩን ለማፅናት ስልጣኔ ቁልፍ መሆኑን በመረዳታቸው፣ የውጭ አገር ዜጐችን አስገድደው የጦር መሣሪያ ለማሰራት ሞክረዋል፡፡ ፈረንጆቹን እስከማሰር ያደረሳቸውም አውሮፓዊያን ዓላማዬን አልተረዱትም፤ ተገቢውን ያህል አላገዙኝም… በሚል ጫና ለማሳደርና አጋር ለማድረግ ነበር፡፡ የንጉሡ ዓላማ ባለመሳካቱ እስከ አፍንጫው በታጠቀው በናፒር ጦር ተሸነፉ፡፡
ለአፄ ቴዎድሮስ ውድቀት አንድ ምክንያት የሆነው የጦር መሣሪያ እጥረት ለአፄ ምኒልክም በተለይ በአድዋ ጦርነት ትልቁ ፈተናቸው ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ ችግሩን ተረድተውና ጊዜ ወስደው ወደ ጦርነቱ በመግባታቸው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊያንን ያኮራ ድል ለመቀዳጀት በቁ፡፡ በአድዋ ድል ማግስት በ1904 ዓ.ም የተቋቋመው የጥይት ፋብሪካ፤ የጦር መሣሪያ እጥረት ለመፍታት ታስቦ ቢሰራም በተለያዩ አገራት በተፈፀመ ተንኮልና ዳባ የፋብሪካው ሥራ መቋረጡን “ዝክረ ነገር” በሚል ርእስ በማህተመሥላሴ ወልደመስቀል ተዘጋጅቶ በ1942 ዓ.ም በታተመው መፅሐፍ ውስጥ ተገልጿል፡፡
የመጀመሪያው ወታደራዊ የሰልፍ ትርዒት
በ1944 ዓ.ም የታተመው “ፍሬ ከናፍር” አንደኛ መፅሐፍ፤ “ያራዳ ዘበኛ” አመሰራረትና ታሪክ መነሻው የሐረርጌ ሰዎች ናቸው ይላል፡፡ “ቱርኮች ከፈረንጆች፣ የሐረርጌ እስላሞች ከቱርኮች ተምረው ዶርያ የሚባል ዘበኛ በሐረር እንዳቆሙ፣ ልዑል ራስ መኮንን ለጃንሆይ አፄ ምኒልክ ቢያጫውቷቸው፤ “ወደዚህም ስደድልኝ” ብለዋቸው፣ እነዚያ ዶርያ የሚባሉ ዘበኞች በአዲስ አበባ በመጡ ጊዜ እንደዚህ ያለው የዘበኛ አኳኋን ቢቆም ሰው ሁሉ ተደነቀ” በዚህ መነሻነት በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያው ወታደራዊ የሰልፍ ትርዒት ለሕዝብ ቀርቦ የታየው በፍል ውሃ ሜዳ ነበር - በ1918 ዓ.ም፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ማሰልጠኛ በሱዳን
በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ የተጀመረው ዘመናዊ ጦር ሠራዊት የማደራጀትና የጦር መሳሪያ የመስራት ፍላጐት በታሰበው መልኩ ባለመፍጠኑ፣ አፄ ኃይለሥላሴን ለስደት የዳረገው የ1928ቱ የኢጣሊያ ወረራን ለመመከት፣ አርበኞች በየጫካው መሽገው ለአምስት አመታት መታገልን ጠየቃቸው፡፡ የአርበኞቹ ትግል በድል ወደመጠናቀቁ ሲቃረብ፣ አፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ወደ ሱዳን በመምጣት “ሶባ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጦር ትምህርት ቤት”ን በማቋቋም ኢትዮጵያዊያን ዘመናዊ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጋቸው “የባለታሪኮች ዳግም ስደት” የተሰኘውና በ1996 ዓ.ም የታተመው የአለማየሁ ኑሪ መፅሐፍ ይጠቁማል፡፡ በዚያ የጦር ትምህርት ቤት ሜ/ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መማራቸውም ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የጦር ሠራዊት አባላት በውጭ አገራት ዘመናዊ የውትድርና ስልጠና በመውሰድ የቆየ ታሪክ አላቸው፡፡ “ፍሬ ከናፍር” የተሰኘው መፅሐፍ፤ በ1903 ዓ.ም ግራዝማች ገብረዮሐንስ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ በውጭ አገር ሰልጥነው መምጣታቸውንና ወታደራዊ አለባበስና ሥነ ስርዓትን ለሌሎች ለማስተማር ፈር ቀዳጅ እንደነበሩ አስፍሯል፡፡
የሆለታ ጦር ትምህርት ቤት
በዘመናዊ የውትድርና ሥልጠናና የጦር መሳሪያ የተደራጀ በቂ የጦር ሰራዊት አለመኖር ለስደት የዳረጋቸው አፄ ኃይለሥላሴ፤ ኢጣሊያ ተባርሮ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ ካከናወኗቸው በርካታ ለውጥ አምጪ ተግባራት አንዱ የጦር ሠራዊቱን አቅም መገንባት ነበር፡፡ የሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በሱዳን “ሶባ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጦር ትምህርት ቤት” ገብተው ስልጠና ጀምረው የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች፣ በሆለታም ተጨማሪ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የሠራዊቱን አቅም የማጐልበት ሥራ ተጀመረ፡፡ በ1966 ዓ.ም ከየክፍለ ጦሩ ተውጣጥተው “ደርግ” በሚል መጠሪያ መንቀሳቀስ የጀመሩት መኮንኖች፤ በንጉሡ ዘመን የተነደፈው ትምህርትና ስልጠና ውጤት እንደሆኑም ይታወቃል፡፡
ሶሻሊዝምን ያመጣው የጦር መሣሪያ ችግር
አፄ ኃይለሥላሴ ለጦር ሠራዊቱ የሚሆኑ በርካታ የጦር መሣሪያዎች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ክፍያውን ፈፅመው ሳለ ነበር በወታደራዊው ኃይል ከስልጣን የመውረድ ዱብዕዳ የገጠማቸው፡፡ ንጉሡን የተካው ደርግ፤ የመንግሥትነት ስልጣን ይይዛል ብሎ ማንም አልገመተም፡፡ 120 አባላት ከነበሩት የመኮንኖች ስብስብም ከአንድ ሰው በስተቀር የአገሪቱ መሪ እንሆናለን ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም፡፡ “የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች” በሚል ርእስ በገነት አየለ የተዘጋጀው መፅሐፍ (1993 ዓ.ም) ውስጥ ደርግ ወደ መንግሥትነት እንዲለወጥ ትልቁን ሚና የተጫወቱት ኮሎኔል መንግሥቱ እንደነበሩ ጓደኞቻቸው የሰጡት ምስክርነት ይጠቁማል፡፡
ደርግ በምስራቁ የአገራችን ክፍል ተቀስቅሶ የነበረውን ጦርነት ለመመከት ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች ያስፈልጉት ነበር፡፡ ለዚህም ንጉሡ ክፍያ የፈፀሙበትን የጦር መሣሪያ ከአሜሪካ ለመረከብ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፤ ይሄን ጊዜ ነበር ደርግ ፊቱን ወደ ራሽያ ያዞረው፡፡ በዚያ አጋጣሚ ከጦር መሣሪያ ጋር አብሮ አገራችን የገባው ሶሻሊዝም፤ አገሪቱን ለፖለቲካዊ ምስቅልቅልና ለኢኮኖሚያዊ ድቀት ዳርጓት አለፈ፡፡

በደርግ ፖሊስ ሠራዊት የተሰሩት መኪኖች
ራሽያ፣ ኩባና የመን ከመሳሰሉት ሶሻሊስት አገራት የጦር መሳሪያ ብቻ ሳይሆን የወታደርም እርዳታና ትብብር ያገኘው የደርግ መንግሥት፤ በ1969 ዓ.ም በአገራችን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ የፈፀመውን የዚያድባሬን ጦር መክቶ ማሸነፈ ቻለ፡፡ ከዚያ በኋላም የደርግ ዋነኛ ትኩረት የጦር ሠራዊቱን አቅም ማጐልበት ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ የጦር ሠራዊቱ ለሰላምና ለአገር ዳር ድንበር መከበር ዘብ የሚቆም ብቻ ሳይሆን ለአገር እድገትና ልማት አስተዋፅኦ አድራጊ መሆኑን ለማሳያነት ከቀረቡት ሥራምች መካከል፤ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የወዳደቁ ቁሳቁሶችን በመገጣጠም ሠርተው ለአገልግሎት ያበቋቸው መኪኖች በተለየ ይታወሳሉ፡፡ በዘመኑ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አድናቆት የተቸራቸው መኪኖች የሰርቪስ አገልግሎት በመስጠት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ይታዩ ነበር፡፡
ለዛሬ ጠቃሚ የሆነው የደርግ ጅማሬ
በአገራችን እየተመዘገበ ስላለው የኢኮኖሚ እድገት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (አፈሩ ይቅለላቸው) በአንድ ወቅት ጋዜጠኞችን ጠርተው በቢሯቸው መግለጫ ሲሰጡ፤ በብረታ ብረት ኢንዱስትሪው በኩል ትልቅ ክፍተት እንዳለ ጠቁመው ነበር፡፡ የግል ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪው በመግባት ዘርፉን የማሳደግ አቅም እንደሌላቸው የተረዳው መንግሥታቸው፤ ደርግ ለጦር መሣሪያ ማምረቻ እንዲሆኑ አስቦ ያስመጣቸው ማሽነሪዎችን መጠቀም ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል በሚል እምነት፣ ተግባራዊ ሥራዎች መጀመራቸውን አመልክተው ነበር፡፡ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረውን የሠራዊት ቀን በዓል ምክንያት አድርጐ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ የታየው ተስፋ ሰጪ ሥራ፤ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትላንትም ብዙዎች የደከሙለት ዓላማ የደረሰበትን ደረጃ አመላክቷል፡፡
የአቶ አዲሱ ለገሰ ምስክርነት
የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን በተለያዩ ቦታዎች በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበር፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተላለፉት ፕሮግራሞች መካከል፤ በአማራ ክልል በአቶ አዲሱ ለገሰ የተመራው ስብሰባ ነው፡፡ በክልሉ የተለያዩ የህብረተሰብ አካላትና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በተገኙበት መድረክ መሪው አቶ አዲሱ ለገሰ ባደረጉት ንግግር፤ እንደ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ እስራኤል… ያሉት ታላላቅ የዓለም አገራት የኃያልነትና የጥንካሬ ምስጢር የመከላከያ ሠራዊቱ እውቀት፣ አቅም፣ ችሎታና ብቃት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን እውነት ደግሞ ከ145 ዓመታት በፊት አፄ ቴዎድሮስም ተገንዝበውት ነበር፡፡ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሳይፈቅድ ቀርቶ እንጂ ከዚህ ባጠረ ጊዜ ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ላይ መድረስ ይቻል ነበር፡፡ ጨርሶ ከሚቀር ግን ዘግይቶም ቢሆን መምጣቱ ተመራጭ ነው፡፡ ሆኖም ዛሬ የተገኙ ውጤቶችን ስናወድስ የትላንቱንና የትላንት ወዲያውን ከእነአካቴው ዘንግተን መሆን የለበትም፡፡
ለአገራችን የኢንዱስትሪ ጅማሮ መነሻ እንደሆነ ከሚነገርለት የአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ሴቫስቶፖል እስከ ዘንድሮው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን ለመድስ በርካታ አገር ወዳድና ባለራዕይ ዜጐች ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን ተገንዝበን ምስጋናና ውዳሴ ለሚገባቸው ሁሉ ምስጋናና ውዳሴ ማቅረብን መልመድ ያለብን ይመስለኛል፡፡ አገር በአንድ ትውልድ እንደማትገነባ ማወቅ ብልህነት ነው!!

 

Read 4382 times