Saturday, 23 February 2013 11:12

በፍርሃትና በጩኸት እንደ እያሪኮ ግንብ የምፈርስ አይደለሁም”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

(ወ/ሮ ሙሉ ሠለሞን፤ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት)

በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ኢምፖርት ኤክስፖርትና የችርቻሮ ኮርፖሬሽን ውስጥ ነው ስራ የጀመሩት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፀሐፊነት አገልግለዋል በቢዝነስ ቢኤ ዲግሪ፣ በኢንቫይሮመንትና ዴቨሎፕመንት ማስተርስ ያላቸው ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፤ አሁን ደግሞ በሊደርሺፕና ኢንተርፕሪነርሺፕ ፒኤችዲያቸውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ “ራይት ቪዥን” የተባለ ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉ፤የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በንግስተ ሳባ ሆቴል በነበራቸው ቀጠሮ በሥራና ተመክሮ፣ በስኬትና ፈተና፣ በህይወትና ራዕያቸው ዙሪያ ያደረገችው ቃለምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንትነት ያደረጉት ውድድሩ እንዴት ነበር? 
በመሠረቱ ምክር ቤቱን ቀደም ብዬም አውቀዋለሁ፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ ቻምበርን በዳይሬክተርነት አገልግያለሁ፡፡ በበጐ ፈቃደኝነት በተለያዩ ማህበራት ውስጥም ሰርቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የራሴ ስራ ላይ ላተኩር ብዬ ባሰብኩበት ሰዓት ነው ወደዚህ ውድድር የገባሁት፡፡ አዲስ አበባ ቻምበር ዳይሬክተር የሆንኩት በከፍተኛ ድምጽ ተመርጬ ነው፡፡ እንደውም ፕሬዚዳንት እንድሆንም ብዙ ግፊቶች ነበሩ፡፡ ሆኖም በግሌ የምመራቸውና የምሠራቸው በርካታ ነገሮች ስለነበሩ በወቅቱ ጥያቄውን አልተቀበልኩም፡፡
የሆነ ሆኖ እኔ የአዲስ አበባ ቻምበር ዳይሬክተር ሆኜ ከ1997 ምርጫ ጋር ተያይዞ በተከሰተው ቀውስ ከሱቆች መዘጋትና ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር በተገናኘ ፈታኝ ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ ሱቆችን ከማስከፋት ጀምሮ አጠቃላይ የንግዱ ማህበረሰብ ወደቀድሞው መረጋጋትና የንግድ ሥርዓት እንዲገባ፣ነጋዴው በራሱ ካጠፋ እንዲጠየቅ፣ነገር ግን ድርጅቶቹ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የማድረግ ፈታኝ ወቅት አሳልፈናል፡፡ ያ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡
ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የተወዳደርኩት ያለ አንዳች ተቃውሞ ሲሆን እንድወዳደር ፈርመው ነው የኔን ስም የላኩት፡፡ ነገር ግን እኔ ብዙ የራሴ ሥራ አለኝ፡፡ የአዲስ አበባውን አገልግያለሁ፡፡ ያላገለገሉ ስላሉ እነሱ ይወዳደሩ ብልም ጫናው በዛ፡፡ ምናልባት አንድም ሁለትም አመት አገልግለሽ ብትተይው ይሻላል፣ይሄ ሁሉ ሰው ያለ አንዳች ተጣባባቂ አንቺን አምኖ ሲያወዳድር እንዴት እምቢ ትያለሽ--- የሚል ጫና በረታና ተወዳደርኩኝ፡፡ በዚህ ደግሞ ሌላ ጫና ገጠመኝ፡፡
ምን ዓይነት ጫና?
ምን መሰለሽ? የበፊቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ መቀጠል ይፈልጉ ነበር መሠለኝ ከየአቅጣጫው በስልክ ዛቻና ማስፈራሪያው በዛ፡፡ በአካልም መጥተው አርፈሽ ተቀመጪ፣ ቦታውን ስለሚፈልጉት ከውድድሩ ራስሽን አግልይ ያሉኝ ነበሩ፡፡ በስልክም የማላውቃቸው ሰዎች “አርፈሽ ልጆችሽን አሳድጊ” ይሉኝ ነበር፡፡ ማንነታቸውን ግን አይገልፁም፣ እኔ ደግሞ በጩኸትና በፍርሃት እንደ እያሪኮ ግንብ የምፈርስ አይነት ሰው አይደለሁም እና ጉዳዩ የበለጠ እንድፀና አደረገኝ፡፡ ለምሣሌ ሚዲያ ተቋሙንም የጋዜጠኞችንም ሥም መጥቀስ ባልፈልግም ሴት ጋዜጠኞች ማበረታታት ሲገባቸው ያቀርቡልኝ የነበረው ጥያቄ የንቀትና የማስፈራራት አይነት ነበር፡፡
እስቲ ከእርስዎ ጋር የተወዳደሩትን ሰዎች ይንገሩኝ----
ለውድድር የቀረብነው አራት ሰዎች ነን፡፡ አንደኛው ተወዳዳሪ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ናቸው፡፡ አባልነታቸው አዲስ አበባ ቢሆንም ከአዲስ አበባ አልተወከሉም፡፡
ህጉም የሚለው ካለሽበት ክልል ተወክለሽ ነው የምትወዳዳሪው፣ካለሽበት ክልል ተወክለሽ ግን የትኛውም ክልል ሊመርጥሽ ይችላል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ የተጠቆሙት ከሌላ ክልል ነበር፣ይህም የምርጫው ቀን ጭቅጭቅ አስነስቶ ነበር፡፡ ሌላው ጌታቸው አየነው ከአማራ ክልል ነበር፣ሶስተኛው የማላውቀው ሰው ነበር - ለውድድሩ አልቀረበም፣ እኔ አራተኛ ነኝ፡፡ ለምክትል ፕሬዚዳንትነትና ለቦርድ አባልነት የሚወዳደሩም ነበሩ፡፡ ለውድድሩ ንግግር ስናደርግ ከአማራ ክልል የመጣው ራሱን አገለለ (ሪዛይን አደረገ)፣ አንደኛው መጀመሪያውኑም አልመጣም፣ ስለዚህ እኔና አቶ ኢየሱስ ወርቅ ብቻ ቀረን፡፡ እዛ ውድድር ላይ ቀድሞ የተሠራ ሥራ እንደነበር ፍንጮች ነበሩ እናም በሻይ ሰዓት “እናንተ በቃ ሴት አትመርጡም አይደል” እያልኩ እቀላልድ ነበር፡፡
ቀደም ብሎ የተሠራው ስራ ምንድን ነው?
እሣቸውን ለመምረጥ ተማምለው የመጡ እንደነበሩ መረጃ አለኝ፣በአንደበታቸውም ይህንኑ የነገሩኝ አሉ፡፡ የሆነ ሆኖ እኔ እዚህ ተወዳድሮ በመመረጥ እንጂ በሌላ ሌላው አላምንም፣ መሆንም የለበትም፣ ስለዚህ ውድድሩ ቀጠለ፡፡ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ተጀምሮ 10፡00 ሰዓት ማለቅ የነበረበት እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ማለቅ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጫናና ፍትጊያ ነበር፡፡ ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚፈልጉ ሰዎችም ነበሩበት፡፡ የሆነ ሆኖ እርሳቸው ንግግር አድርገው ሲጨርሱ እኔ በተራዬ ንግግር ካደረግኩ በኋላ አብላጫው ሰው ፊቱን ወደኔ አዞረ፡፡
ድምጽ ተቆጥሮ አሸናፊው እስከሚነገር ከአንድ የማላውቃቸው የክልል ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጋር ስናወራ “እኛ አንችን አናውቅሽም ስለዚህ የምናውቀውን ለመምረጥ ስምምነት ነበረን፡፡ ነገር ግን ንግግር ስታደርጉ ሁሉም ወዳንቺ ተገለበጠ” አሉኝ፡፡
ሌሎችም እንዲሁ ወንዶችም ሴቶችም ንግግሬን እስኪሰሙ አቋማቸው የእኒህ ሰውዬ አይነት እንደነበር ነግረውኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ያሸነፍኩት፡፡ እኔ 132፣ እሣቸው 62 ድምጽ ነበር ያገኘነው፡፡
ምን አይነት ንግግር ቢያደርጉ ነው መራጮችን መማረክ የቻሉት?
እኔ የተናገርኩት ብዙ ከባድ ንግግር አይደለም፡፡ ምን አልኩ መሰለሽ? “እኔ እንደ ድሮ ፓርላማ - መንገድ አሠራላችኋለሁ፣መብራት አስገባላችኋለሁ አልልም፡፡ ከአዲስ አበባም ልመረጥ ከሌላም ልወከል ለላከኝ ክልል ወይም ቻምበር ሳይሆን ለሁላችሁም የኢትዮጵያ ማህበር አባላት በቀናነት አገለግላለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ከተወከለች ለእኛ ትሠራለች ለዚህኛው ወገን በቅርበት ትሠራለች የሚል የተከፋፈለ ሃሳብ ካላችሁ አትምረጡኝ፡፡ ለእውነትና ለሃቅ ፊት ለፊት የምጋፈጥ ስለመሆኔ ታውቃላችሁ” ከዚህ በላይ ብዙ መናገር አላስፈለገኝም ነበር፡፡
የሃላፊነት ቦታው ግን እስካሁን ድረስ ከሽኩቻ እንዳልፀዳ ይነገራል------
በፊት የነበሩ ሰዎች መቀጠል ነበረብን የሚል ቁጭት አለ፣ አሁንም የሷን ስራ እናበላሻለን ይላሉ፣ የኔ ሳይሆን የመንግስትና የህዝብ ስራ ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ ይሄ ነገራቸው የበለጠ እንድንሰራ ያደርገኛል እንጂ አያሰንፈኝም፡፡
የድሮ ሰው ምቀኛ አታሳጣኝ የሚለው ለምን ይመስልሻል፡፡ ሰው ሲቃወምሽ አንዳንዴ ስህተትሽንም ትመለከቻለሽ፣በጭፍን ጥላቻ የሚያወራብሽም ከሆነ ዘግተሽው ስራሽን ትቀጥያለሽ አለቀ፡፡ በወሬ ጊዜያቸውን ባያባክኑ ግን ደስ ይለኛል፡፡ እኛ በአሉባልታ ጊዜ እንድናባክን ይፈልጋሉ፣እኛ ለወሬ ጊዜ የለንም አለቀ፡፡ ሥራ ላይ ነን፡፡ ለውጥ ላይ ነን፡፡
አሸንፈው ሃላፊነቱን ሲረከቡ በቅድምያ የጠበቅዎት ስራ ምን ነበር? እስካሁንስ ምን አከናወኑ?
ብዙ ሊስተካከሉ የሚገቡ ሥራዎች ሊጠብቁሽ ይችላሉ፡፡ አንድ አገርኛ አባባል ልንገርሽ፡፡ የዱሮ ባሎች የመጀመርያ ሚስት ፈትተው ሌላ ሚስት ሲያገቡ፣ አዲስ የተገባችው ሴት የመጀመሪያዋ የሠራችውን መደብ አፍርሳ ከዛ የባሰ የተበላሸ መደብ ትሠራለች ይባላል፡፡ እሷ ያንን የምታደርገው ከጀመሪያዋ የተሻልኩ ነኝ ለማለት ነው፡፡ እኔ እንደ አዲሷ ሚስት ያለ አመለካከት የለኝም፡፡ አዲስ የተመረጡት የቦርድ አባላትም ጭምር፡፡ እከሌ በነበረበት ጊዜ ይህን አላደረገም ይህን አበላሽቷል ብሎ የማጣጣል ፍላጐትም ሃሳቡም የለንም፡፡ በነበረው አሠራር ጥሩ ነው ያለውን እንቀጥልበታለን፡፡
የተበላሹ ካሉ እያስተካከልን የመሄድ ሃሳብ ነው የነበረን፡፡ በጣም የሚገርምሽ የምርጫው ዕለት እኔ ሳሸንፍ ህዝቡ “ሳዳም ወረደ፤ጋዳፊ ወረደ” እያሉ ሲጨፍሩ ሊቀመንበሩ ማስቆም አልቻሉም ነበር፡፡ እኔ ድምጽ ማጉያውን ተቀብዬ “ከእኔ ጋር መስራት የምትፈልጉ ከሆነ እንዲህ አይነት ንግግር አልፈልግም፡፡ እኔ የሠላም አምባሳደር ነኝ፤ በሠላምና በፍቅር ነው መስራት የምፈልገው፡፡ የሚሠራው ሰው ይሳሳታል ያጠፋል፤ ያም ቢሆን እስከዛሬ ያገለገለ ሰው መመስገን እንጂ መሰደብ የለበትም፤አሁኑኑ ይህን አይነት ስድብና ጭፈራ ካላቆማችሁ ትቼ እሄዳለሁ” ስል ሁሉም በአንድ ጊዜ ፀጥ አሉ፡፡
ይታይሽ “ሳዳም ጋዳፊ ወረደ” የሚሉት እሳቸው ባሉበት ነው፤ የሠራ ሰው በፍፁም መሰደብ የለበትም፡፡ በእለቱ እኔ ምን አልኩኝ፤“ድግስ ደግሰን ጋብዘን ሸልመንና አመስግነን እንሸኛቸዋለን” ይህንንም አድርገናል፤ሚኒስትሮች ባሉበት ራት ጋብዘን፤ ለቦርዶቹ ደረት ላይ የሚደረግ የቻምበሩ አርማ ያለበት ወርቅ ሸልመን ነው የሸኘናቸው፡፡
ሥራውን ሲጀምሩት በጣም ፈታኝ የሆነብዎ ምን ነበር?
በጣም ፈታኝ የምለው ስራ በኢትዮጵያና በአዲስ አበባው ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች መካከል ጠብ ነበር፡፡ ጠላትነታቸው ደግሞ ለ40 ዓመታት ሥር የሰደደ ነው፡፡ እኔ ወደ ኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ስመጣ ሁኔታው በጣም የከፋ ነበር፡፡ ብቻ ምናለፋሽ ጥሩ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ሰዎች የሁለቱን ቻምበሮች ጉዳይ እንዳትነኪ፤ ዝም ብለሽ ቀጥይ ይሉኝ ነበር፡፡
የጠባቸው መንስኤ ምንድን ነው?
አንዱ የሚያጣላቸው የህንፃው ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው የስራ መመሳሰል ነው፡፡ ለምሣሌ አዲስ አበባ ቻምበር ይህን ይሠራል፤የኢትዮጵያ ይህን ይሠራል እየተባባሉ፡፡ ተባብረውና ተቻችለው መስራት ሲችሉ ይበጣበጡ ነበር፡፡ እኔ ለጉዳዩ እልባት ለማግኘት ስሞክር፤ሁለቱን ቻምበሮች ለማስታረቅ እንዳትሞክሪ፤የህንፃውን ጉዳይ እንዳትነኪ እባላለሁ፡፡ እኔ ደግሞ መስራት ካለብኝ ሠላምና የረጋ መንፈስ ባለው ሁኔታ ነው የምሠራው፡፡ ይህን አትንኪ ያንን አታንሺ የሚባለውን ነገር አላመንኩበትም፤እስከመቼ ነው ሳትነኪ የምትኖሪው? ችግርን ቀርበሽና ተጋፍጠሽ እንጂ በመፍራትና በመሸሽ መፍትሔ አታመጪለትም፡፡
ከቦርድ አባላት ጋር ተነጋግሬ ይህን ጭቅጭቅና ጠብ ፈትተን በሠላማዊ መንገድ መስራት አለብን በሚል ብዙ ሥራዎች ተሠሩ፡፡ መጀመሪያ ኮሚቴ አቋቋምኩኝ፤የሚጣሉበትን ነገር አጣራን፤ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ሲያቀርብ የሚበጣበጡ ሰዎችን ኮሚቴ ውስጥ በመክተት ገለልተኛ የሆኑ ሰዎችንም ጨምሬ በሠላማዊ መንገድ ተነጋግረን ችግሩን ፈታን፡፡ አንድ ወር ተኩል ባልሞላ ጊዜ ነው ችግሩ የተፈታው፡፡
የህንፃውን ጉዳይ በተመለከተ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በደብዳቤ ባሳወቁት መሠረት፤ “አዲስ አበባ ቻምበር በባለቤትነት ይዞት አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች የክልል ቻምበሮች እንዲገለገሉበት፤የራሳቸውን ህንፃ እያሰሩ ሲወጡ ቀሪው ለኢትዮጵያ ቻምበር እንዲሆንና እያከራየ እንዲጠቀም እንዲሁም የክልል ቻምበሮችን እንዲያጠናክርበት ይሁን” በሚል ተስማምተን አሁን በፍቅርና በሠላም ብዙ ነገሮችን በጋራ እንሠራለን፡፡ አሁን እንደውም እኛ ስራ ሲበዛበን አዲስ አበባ ቻምበሮችን አግዙን እንላለን፤ እኛም እነሱን እናግዛለን፡፡ እንደ ዱሮው መገለማመጥና የጐሪጥ መተያየት ፈጽሞ ተወግዷል፡፡ በአመት ሁለት ጊዜ የመገናኛና የመሰብሰቢያ ፕሮግራም ሁሉ አዘጋጅተው እርስ በእርስ ይገባበዛሉ ይጨዋወታሉ፡፡
ከመንግስት ቢሮዎችና ከንግዱ ጋር ከተገናኙ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር ያላችሁ የስራ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ከ10 እና ከ15 ዓመት በፊት ሲለፋበት የኖረን ጉዳይ ነው፤ አሁን እኛ በተሳካ ሁኔታ እየሠራን ያለነው፡፡ ለምሣሌ ከንግድ ሚኒስቴር፣ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ወዘተ ስንተዋወቅና አብረን መስራት እንፈልጋለን ስንል ሁሉም እውነት አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም ንግድ ምክር ቤት ከመንግስት ጋር አብሮ መስራት አይፈልግም የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ እኛ ግን ከመንግስት ጋር የመስራት ጽኑ ፍላጐት አለን፡፡ ምክንያቱም ህግና ፖሊሲ የማያወጣው መንግስት ነው፡፡ ህግና ፖሊሲ ከሚያወጣ መንግስት ጋር አብሮ አለመስራት ደግሞ መልካም አይደለም በሚል ተነጋግረን፣ ከእነርሱ ጋር ሁለትና ሶስት የምክክር መድረኮች አካሂደናል፡፡ ይህን በብሔራዊም በክልልም ደረጃ አድርገነዋል፡፡ ከተመካከርንባቸው ውስጥ የወደብ ዕቃ ማንሳት ጉዳይ፣ ህዝቡ የተጯጯኸበት የንግድ ምዝገባ ጉዳይ፣ የታክስ አከፋፈልና የመሳሰሉት ላይ ተወያይተን አሁን ህጉን ሊያሻሽሉት ነው፡፡ ለምሣሌ ከጉምሩክ ጋር ባካሄድነው ውይይት ከመንግስት ጋር ይጣላሉ ተቀባይነት አያገኙም ሲሉን፣ መንግስት 98 በመቶውን የኛን ሃሳብ ተቀብሏል፡፡ ከላይ በጠቀስኩልሽ በታክስ አከፋፈል፣ በወደብ ዕቃ አነሳስ፣ በንግድ ምዝገባና በበርካታ ጉዳዮች ለንግዱ ማህበረሰብም ሆነ ለመንግስት ይጠቅማሉ ባልናቸው ሃሳቦች ላይ ነው መንግስት 98 በመቶ ሃሳባችንን የተቀበለው፡፡ “ያልተጠበቀ የመንግስት አቋም” ተብሎ ተወድሷል፡፡ በአጠቃላይ ያተኮርነው ለንግዱ ህብረተሰብ ምቹ የንግድ ከባቢን የመፍጠር ስራ ላይ ነው፡፡
አገሪቱ ውስጥ የተለያየ ፍላጐትና ባህሪ ያላቸው ነጋዴዎች አሉ፡፡ የንግዱን ማህበረሰብ የማስተዳደሩ ጉዳይ ምን ይመስላል?
እኛ የአገሪቱ የንግድ ማህበረሰብ ጥሩ ስነ - ምግባር ያለውና ታማኝ እንዲሆን የማንቃት፣ በተሳሳተ መንገድ የሚጓዙ ካሉ ወደ መስመር የመመለስ፣በሰዓቱ ግብር እንዲከፍሉና በንግድ ሥራ የሀገራቸውን መልካም ገጽታ እንዲገነቡ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ እርግጥ ነው በርካታ ነጋዴዎች አሉ፣የተለያየ ባህሪ መኖሩም አይካድም፣ ነገር ግን በመልካም አቀራረብና አዎንታዊ መንፈስ በተሞላበት ሁኔታ ችግሮቻችንን እንፈታለን፡፡
የነጋዴውን ጥቅም በማስከበርና ከመንግስት ጋር ቅርርብ እንዲኖር የበኩላችንን እያደረግን ነው፡፡
አባላቱ በርካታ ቢሆኑም ነጋዴውን በመቅረብና በማነጋገር በቀላሉ ጤናማ በሆነ መንገድ መምራት ይችላል፡፡
በደርግ መንግስት ተወርሶ የነበረው ህንፃችሁ ተመልሶላችኋል፡፡ ሆኖም አዲስ ህንፃ ለማስገንባት ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የቦታ ጥያቄ ማቅረባችሁን፣ምን ያህል ቦታና የት ቦታ እንደምትፈልጉ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ አሳውቁን ማለታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ያሁኑ ህንፃ እያለ ሌላ መገንባት የፈለጋችሁት ለምንድን ነው? ህንፃውን የምትገነቡበት ገንዘብ ከየት የሚገኝ ነው? ምን አይነት ህንፃስ ለማስገንባት አሠባችሁ?
ህንፃውን የማስመለስ ሥራ ረጅም ጊዜ ወስዷል፡፡ ከአስራ አምስትና አስራ ስድስት ዓመት በላይ ማለት ነው፡፡ ይሄ ህንፃ የተሠራው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሳይመሠረት በፊት ነው፤ አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በሚል የተሠራው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ቻምበር ይመለስልኝ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ቻምበርም ይመለስልኝ የሚል ደብዳቤ ሲያስገባ ቆይቷል፡፡ በኋላ ግን እኛ ምን አልን ---- የሚመለስ ከሆነ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአዲስ አበባ ይመለስ የሚል አቋም ላይ ደረስን፡፡ በዚህ ሁኔታ መንግስት ህንፃውን ሲመልስ ኢትዮጵያ ቻምበር በባለቤትነት ይያዘውና መጠቀሙን አብረው ይጠቀሙ ሲል፤ አዲስ አበባ ደግሞ ኢትዮጵያ ቻምበር ሳይፈጠር የራሴ ነበር ይላል፡፡ ይሄው ይጠቀሙ ሲል አዲስ አበባ ደግሞ ኢትዮጵያ ቻምበር ሳይፈጠር የራሴ ነበር ይላል፡፡ ይሄ ጭቅጭቅ በነበረበት ወቅት እኛ በጭቅጭቅ ጊዜም ገንዘብም ከምናባክን ለአንዳችን ተመልሶ በጋራ ለምን አንጠቀምም፤ ከዚያስ ለምን የራሳችንን ህንፃ አንሰራም በሚል የአዲስ አበባው ንግድ ምክር ቤት ቦታ ጠይቆ ስራ ጀምሯል፡፡
እኛም ቦታ የጠየቅነው ለዚህ ነው፡፡ ህንፃው ከሁለት ዓመት በፊት ከተመለሰ በኋላ ግን ተከፋፍሎ በሠላም መጠቀም አልተቻለም፡፡ ስለዚህ እኛ ተመካክረን መንግስትን የወሰነውን ተግባራዊ ወደማድረግ ሄድን፡፡
ምክንያቱም መንግስት በዚህ በዚህ መልኩ ይጠቀሙ የሚል መመሪያ አስቀምጧል፡፡
አዲሱን ህንፃ ለመገንባት የታሰበበት ዋናው ምክንያት በየሀገሩ ሄደን የንግድ ምክር ቤት ቢሮዎችን ስንጐበኝ የምናያቸው ከእኛ ጋር ፈጽሞ አይገናኙም፡፡ የእኛ በጣም ያሳፍራል፡፡ የውጭዎቹ የአብዛኛዎቹ ቢሯቸው ህንፃው ራሱ ቤተ - መንግስት ነው የሚመስለው፤የእኛ ግን ከ60 እና 70 ዓመት በፊት የተሠራ ህንፃ ነው፡፡ እንደውም ያኔ ባለራዕይ ሆነው ይሄን ሰሩ እንጂ አሁን ያለበት ሁኔታ እንኳን ከአለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤቶች ከክልል ምክር ቤቶች ጋርም መወዳደር አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባን ቦታ ጠይቀናል፡፡ አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የስብሰባ አዳራሽ፣ ቢሮዎች በአጠቃላይ የትኛውም አለምአቀፍ ሰው ቢመጣ አንገታችንን ቀና አድርገን የምናስገባበት መሆን መቻል አለበት፡፡ አሁን የአገራችን ኢኮኖሚ እያደገ ስለሆነ ብዙ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ እየመጡ ነው፡፡ ሲመጡ ደግሞ ንግድ ምክር ቤቱን ያነጋግራሉ፡፡ ያኔ የእኛ ቢሮ እንዲህ የሚያሳፍር ከሆነ ልክ አይመጣም፤ስለዚህ ቦታውን ሊሰጡን ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ሁሉም ክልሎች ቦታ ተሰጥቷቸው ንግድ ምክር ቤት እንዲሠሩ እያልን ነው፡፡ የድሬዳዋው ንግድ ምክር ቤት ህንፃ እንዲመለስ ደብዳቤ መንግስት ጽፏል፤አፈፃፀም ነው የቀረው፡፡ በሌላ በኩል የንግዱ ማህበረሰብ ድምጽ እንዲሰማና ትኩረት እንዲያገኝ የአባላት ማብዛት ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ተሠርቷል፡፡ ለምሳሌ ትግራይ 16ሺህ ደርሷል፡፡ ደቡብም አማራም የአባላት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ ጠንካራ ስራ ሠርቶ አባላትን በከፍተኛ ሁኔታ ላበዛ ክልል ሽልማት እንሸልማለን ብለን ሁሉም በፉክክር በጥሩ ሁኔታ እየሠራ ነው፡፡ አሁን የምንጠይቀው መሬት በከተማ ውስጥ ሆኖ ስፋቱም ምክንያታዊ የሆነ ነው፡፡
መጀመሪያ ለቢሮ ነው የምንጠይቀው፡፡ ከዚያ በኋላ አለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽን የምናሳይበት ከከተማ ውጭ ቦታ መጠየቃችን አይቀርም፡፡
ቻምበር አካዳሚ ለማቋቋም ሀሳብ እንዳላችሁ ሰምቻለሁ፡፡ ምንድነው የሚሰራው? ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ቢሰጡኝ----
ቻምበር አካዳሚ የሚለውን ስም አስጠንተናል ቻምበር አካዳሚ ከሚባል በቀላሉ “ሊደርሺፕ ኢንተርፕሪነርሺፕ ኤንድ ማኔጅመንት ሴንተር” እንዲባል ተስማምተናል፡፡ አመራርን፣ ስራ ፈጠራን እንደዚሁም ሥራ አመራርን አካትቶ ከተቋቋመ የላቁ ሰዎችን - መሪዎችን፣ የቦርድ አመራሮችን፣ የአገር መሪዎችን ወዘተ ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም የሚያሰለጥን የልቀት ማዕከል ሊሆን ይችላል፡፡ ሥራ ፈጠራ ላይ በተለይ የሚያሰለጥን በቂ ተቋም የለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች ችግር ከመፍራት ይልቅ መፍትሔ ፈጣሪ እንዲሆኑና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያዳብሩ ማስተማር የሚችል ማዕከል ይሆናል፡፡ በማኔጅመንትም በኩል አገራችን ላይ ጉልህ የማኔጅመንት ችግር አለ፡፡ ስለዚህ ሰዎች በብቃት የመምራትና የማስተባበር ችግርን አስወግደው የላቀ ብቃት የሚያገኙበት ይሆናል፡፡ ይህንን ስንልም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ነው፡፡ ለምሣሌ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከውጭ ሁሉ መጥተው የሚሠለጥኑበት ሆኗል፡፡ ራዕይ ባላቸው ሰዎች ነው አየር መንገዱ ለዚህ የደረሰው፡፡ አሁን የእኛን ሃሳብ የሚያጣጥሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን በእርግጠኝነት ዕውን እናደርገዋለን ብለን እናስባለን፡፡
በአሁን ሰዓት የመጀመሪያዋ ሴት የኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅተዋል፤ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ሃሳብስ የለዎትም?
(ሣ…ቅ) እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ ፖለቲከኞች ናቸው ለስልጣን ተነሳስተው የሚሄዱት፡፡ እኔ እዛ ወጥቼ ባልመራም በየትኛውም ቦታ ላይ መሪ ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሣሌ እኔ ጥሩ ሃሳብ አምጥቼ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራ ላይ ካዋለው እኔ ነኝ የመራሁት ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ አንቺ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለማርያም ጥሩ ሃሳብ አቅርበሽ ሥራ ላይ ካዋሉት የመራሽው አንቺ ነሽ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚያዩት ወንበር ላይ መቀመጡን ነው፤ እኔ ግን የምፈልገው ስራ መሠራቱን ነው፡፡ አንቺ ከልብሽ ከሠራሽና ከተንቀሳቀሽ አንቺ ባትፈልጊም ስራው ይፈልግሻል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ጥያቄ ገፍቶ ቢመጣስ አልፈልግም ትያለሽ?
አዎ እምቢ እላቸዋለሁ፡፡ ለምን መሠለሽ? እናንተ ምሩ፤ እኛ ከኋላ እናሠራለን እላቸዋለሁ፡፡ እኔ ፖለቲከኛ ስላልሆንኩ ነው፡፡ እዛ ቦታ ላይ መቀመጥ ያለባቸው ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ባለፈው ለምንድነው ፖለቲካ ውስጥ የማትሳተፊው ሲለኝ ነበር፡፡ እኔ ግን የፖለቲካውን ቼዝና ዳማ ጨዋታ አልችልበትም፡፡ እኔ ፊት ለፊት የምናገር ሰው በመሆኔ የፖለቲካውን ድራማ አልችልም ብዬ መልሼለታለሁ፡፡
ይሄ የብቃት ጉዳይ አይደለም፤ሞክሮ መውደቅም ይቻላል፡፡ ለአንድ ሰው ዋናው ነገር የተቀመጠበት ቦታ ሳይሆን በቀናነት ባለበት ቦታ መስራት መቻሉ ነው፡፡ ቀና ሰው ስለሆንሽ ችግር አይገጥምሽም ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ችግርና እንቅፋት አለ፡፡ ያንን እንቅፋት ረግጠሽ አንቺ ወደ ላይ ከፍ ማለት ነው ያለብሽ፡፡
አንዳንዱ የአንዱን ትከሻ ረግጦ ራሱ ከፍ ማለት ይፈልጋል፡፡ እኛ እንኳን ባለንበት ቦታ ብዙ ጫና አለ፡፡
እኔ አሁን ስራውን የቀጠልኩት ለችግርና ለመከራ ስለማልበገር ነው፡፡ እንቅፋት እኮ ከኖርማሉ መሬት ከፍ ያለ ነው፤ስለዚህ እዛ እንቅፋት ላይ ስትቆሚ የባሰ ከፍ ትያለሽ፡፡ ለዚህም ነው እኔ ከመከራ በላይ ነኝ ብዬ የማምነው፡፡
የቤተሰብ ሃላፊነት አለ፣ የስራ ሃላፊነት አለ፣ አሁን ደግሞ ለፒኤችዲ እየተማርሽ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ሃላፊነት በአንድ ላይ መወጣት አይከብድም? እንዴት እየተወጣሽው ነው?
ይሄ የጊዜ ጉዳይ ነው እንግዲህ፡፡ አንዳንዴ በቻምበሩ በኩል በሙያሽ ከምትሠሪው በተጨማሪ በርካታ ስራዎች ይመጣሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ዛሬ ነፃ ነኝ ብለሽ ስታስቢ ያላሰብሻቸው ሥራዎች በፀሐፊዋ በኩል ይቀርቡልሻል፡፡
አለም አቀፍ ስብሰባ መምራት፣ የተለያዩ ሪሴፕሽኖች ላይ መገኘት የመሳሰሉት ለምሣሌ በአንድ ምሽት ሶስት ሪሴፕሽን ላይ እንድትገኚ ይፈለጋል፡፡ እኔ አንዱ ጋ ሄጄ ሌላው ጋ አንድ የቦርድ አባል ስልክ፣ ለምን ፕሬዚዳንቷ አልመጣችም ይላሉ፡፡ ስለዚህ አንዱ ጋ ቶሎ ግንባሬን አስመትቼ ሌላው ጋ ደግሞ እሮጣለሁ፡፡ ቻሌንጁ ብዙ ነው ግን ቁርጠኛ ከሆንሽ የማይሰራ የለም፡፡
ብዙ ጊዜ በዕቅድ እንቀሳቀሳለሁ፣ነገር ግን እቅዴን የሚያበላሹ ነገሮች ይመጣሉ፣አቻችሎ መሄድ ነው፡፡ እቤት ውስጥ እኔ ከሌለሁ የቤት ሠራተኛ አበላሽታ የምትጠብቅሽ ነገር ይኖራል፣የቤቴን መበላሸት ግን ከአገር ጉዳይ አላስቀድምም፤ ወደ መንግስት ሥራ እሄዳለሁ፤የትምህርቱም ጉዳይ በዚህ መልኩ ነው የሚሄደው፡፡ እኔ በትምህርት ልምዱ ስላለኝ ክላስ ሳልከታተል የምሠራቸው ስራዎች አሉ፡፡
ቃለምልልሱን ከማጠናቀቃችን በፊት ስኬት ለእርስዎ ምን ማለት እንደሆነ ቢነግሩኝ----
ስኬት ማለት ሰው የፈለገውን መሆን መቻል ነው፡፡ አንድ ሰው ስኬት ብሎ የሚያስበው በ10 ደቂቃ 100 ሜትር መሮጥ ሆኖ በሳምንትም ሆነ በ10 ደቂቃ ከጨረሰ ስኬት ነው፤ ግን ያ የስኬቱ መጨረሻ ሊሆን አይገባም፡፡ ከዛ የተሻለ ስራ ለመስራት መነሳት አለበት፡፡ አንድ ሰው ግቡ ጋ ሲደርስ ስኬት ነው፡፡
ግን የስኬቱ መጨረሻ መሆን የለበትም ብዬ ነው የማምነው፡፡
እኔ ሁሌም ችግርን መከራን አሸንፋለሁ፡፡ ለሌላ ስኬት እዘጋጃለሁ፡፡ በአጠቃላይ ለእኔ ስኬት ቀጣይነት ያለውና መሆን የምትፈልጊውን መሆን ማለት ነው፡፡

Read 7396 times