Saturday, 23 February 2013 11:04

ዶ/ር ዮናስ አድማሱ፣ የሥነ ፅሁፍ ንድፈ ሃሳብ ቀማሪ

Written by  ገዛኸኝ ፀ.
Rate this item
(2 votes)

ጋሼ ዮናስ በፅህፈት ሥራ የጥንቁቅነት የመጨረሻ መለኪያ ነው
የአንድን ኮማ ( ‚) እጣፈንታ ለማሳወቅ የተሟገተ ትጉህ መምህር…

ፈር መያዣ፡- ባለፈው ሳምንት በታዋቂው የሥነ ፅሁፍና የቋንቋ ሊቅ በዶ/ር ዮናስ አድማሱ ሕይወት ዙሪያ አንድ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር፡፡ ተከታዩ እነሆ! የእስከዛሬ አንቱታዬን ትቼ፣ “አንተ” እያልኩ ነገረ ወጌን ማርቀቄም፣ የዶ/ር ዮናስ የኪነጥበብ ሰውነት የመገናኛ ብዙሃን ከለመደውና ከሚፈቅደው የአነጋገር ዘልማድ ጋር እንደሰመረ እንዲፀና ከማሰቤና ከመትጋቴ እንጂ፣ ከአጉል ድፍረቴ እንዳልሆነ ዛሬም በትህትና ልገልፅ እፈልጋለሁ…

የጠፋች ኮማ (,) ፍለጋ
ዶ/ር ዮናስ የራሱን የፅሁፍ ሥራ ሲሰራም ሆነ የሌሎች ሥራዎች ሲያነብ፣ ጊዜውን ብቻ ሳይሆን፣ ህይወቱንም የሚከፍል ይመስላል፡፡ የጥንቃቄ ደረጃው መለኪያ የለውም። ለድህረ ምረቃ ተማሪዎቹ፣ የክፍል ውስጥ ገለፃውንና ፎቶ ኮፒ አድርገን እንድናነብ ከሚያዘን መፃህፍት በተጨማሪ “ዳረጐት” ብሎ የሚሰጠን ማስታወሻ ምን ያህል በጥንቃቄ እንደሚያዘጋጀው ተማሪዎቹ በደንብ እናውቃለን፡፡ አንድ ገፅ የማስታወሻ ፅሁፍ እንኳ ቢሆን፣ አንድ የፊደል ወይም የሥርዓተ ነጥብ ግድፈት፣ ወይም የተዛነፈ አጠቃቀም ካየ ወረቀቱን መልሶ ይሰበስብና እንደገና አስተካክሎ አትሞ ይሰጠናል፡፡
የተማሪዎቹን ወረቀት ሲያርምም፣ ልቅም አድርጐ ነው፡፡ አንዲት ኮማ (,) የማያሳስቱ እረፍት አልባ ዐይኖቹ፣ ከማስገረም አልፈው ያስቀኑናል፡፡ ብዙ ጊዜ ዐይኖቹ፣ የአዛውንት ምሁር ዐይን ስለመሆናቸው እንጠራጠራለን። የእኛ የወጣቶቹ ዐይኖች የጋሼን ያህል የሰሉና የተካኑ አይደሉም፤ ይህን የምናረጋግጠው፣ በወረቀቶቻችን ላይ በቀይ ብእር አዥጐርጉሮ የሚሰጠንን እርማት፣ እንደሱ በወጉ ለቅመን ማየትና ማስተካከል እያቃተን፣ በአንድ ፊደል ወይም ምልክት ሳይቀር ተደጋጋሚ እርማት ሲያደርግልን በማየታችን ነው፡፡
የጋሼን ህልፈተ ህይወት ከሰማን በኋላ፣ ተማሪዎቹ እየተደዋወልን በቤት ሥራዎቻችን፣ በፈተናዎቻችንና በመመረቂያ ወረቀቶቻችን ላይ የፃፈልንን እርምት እያነበብን በትዝታ ስናወጋ ነው የሰነበትነው፡፡ አንድ ለድህረ ምረቃ ከተሰራ የመመረቂያ ወረቀት ላይ እንዲህ ብሏል፡፡ አጥኚው ተማሪ “ዓ.ም” ብሎ ከፃፈው ከወረቀቱ የመጀመሪያ ገፅ ላይ፣ “ከ ‘ዓ’ በኋላ . [ነጥብ] አድርገህ ‘ም’ ምን በደለና ነፈግኸው! በነገራችን ላይ ይህ ያንተ ወይም የመሰሎችህ ብቻ ሳይሆን የመላው ሀገር በሽታ ነው!” የሚል የእርምት አስተያየት ሰፍሯል፡፡
ጋሼ ዮናስ፣ በሚያርማቸው ወረቀቶች ላይ ተደጋጋሚ ስህተት ሲያጋጥመው፣ “ኧረ በህግ! ባዛኚቱ የሽማግሌ ዐይኔን አጠፋችሁት… መርቅነህ ነው እንዴ? እግዜኦ ያንተ ያለህ!...” የሚሉ ለእርማቱ አፅንኦት መስጫ፣ ማባያ (“ካ” ይጠብቃል) ቃላት ያክላል፡፡ እኛ ታዲያ ወረቀቶቻችንን ሲመልስልን ምን እንደፃፈብን ለማየት እንቸኩላለን፡፡ እርስ በርሳችን እየተያየን እንሳሳቃለን፤ ውጤት የተፃፈበትን የወረቀታችንን ጠርዝ ታዲያ ብዙ ጊዜ አናሳይም፡፡ በነገራችን ላይ ጋሽ ዮናስን ከሌሎች ትጉህ መምህሮቻችን ለየት የሚያደርገው፣ ሁሉንም የመልመጃና የፈተና ወረቀቶች አርሞ ይመልስልናል፤ ሌሎቹ ግፋ ቢል ሊያሳዩን ይችላሉ እንጂ፣ ወረቀቶቹን አይመልሱም ነበርና፡፡
በወረሀ ግንቦት 2002 ዓ.ም አካባቢ አንድ የድህረ ምረቃ ተማሪ አንዲት ኮማ(,) ጠፍታው የስድስት ኪሎ ግቢን ማመስ ይጀምራል፡፡ የጠፋችው ኮማ እንዲፈለግ ቀጭን አካዳሚያዊ ትእዛዝ ያስተላፈው ደግሞ ጋሼ ዮናስ ነበረ፡፡ ጉዳዩ እነዲህ ነው፡- የዶ/ር ዮናስ ተማካሪ የሆነ የድህረ ምረቃ ተማሪ፣ የመመረቂያ ወረቀቱ ላይ የGillbert Hight የንድፈ ሀሳብ መፅሐፍ ከሆነው “The Power of Poetry” (1960) ላይ በቀጥታ አንድ አንቀፅ ጠቅሦ ኖሯል፡፡ ጋሼ ታዲያ፣ ይኼን የእንግሊዝኛ ጥቅስ ያነብና “ይህቺን ኮማ[,] ከየት አመጣሃት?” ብሎ ይጠይቃል። ጓደኛችን ደግሞ፣ ከመፅሐፉ በቀጥታ የጠቀስኩት ነው ይላል፡፡ ጋሼ ወዲያው ቆጣ ይልና “እዚህ ላይ ኮማ አይገባም… አንተ ስትገለብጥ ነው የተሳሳትከው…” ይለዋል፡፡ ተማሪውም በትክክል መገልበጡ ይናገራል፡፡
ጋሼ ዮናስ ወዲያው መፅሐፉን አምጣው ይለዋል፡፡ ተማሪ ደንግጦ የእውቀት ቀለም ተመጥኖ ከሚጠመቅባትና በወጉ ከሚጠጣባት ከጋሼ ቢሮ ውልቅ ይላል፡፡ ወዲያው፣ ከኬኔዲ ቤተመፃህፍት ተውሶ የመለሰውን መፅሐፍ ውለዱ ማለት ይጀምራል፡፡ መፅሐፉን ሌላ ተማሪ እንደተዋሰው ይነገረዋል። ከሁለት ሳምንት በኋላ ሌሎች እርማቶችን አስተካክሎ ወደ ጋሼ ቢሮ ብቅ ይላል፡፡ ጋሼም የተማሪውን ወረቀት ይቀበልና ያሰናብተዋል፡፡ ተማሪው ሃምሳ ሜትር ያህል ሳይርቅ ጋሼ ደውሎ፣ ይጠራና፣ “ኮማዋስ? መፅሐፉስ?” ይለዋል፡፡ ጓደኛችን የጋሼን አስታዋሽነትና ጥንቁቅነት እየረገመ፣ መፅሐፉ እንዳላገኘው ይገልፃል፤ ወዲያው ጋሼ፣ “ይኸው በዚህ አለንጋ ሾጥ ሳላደርግህ ይዘህልኝ ውጣ!” ይለዋል - የምር ተናዶ፡፡
ጓደኛችን በጋሼ ዮናስ ብቻ ሳይሆን፣ በመፅሐፉ መሰወር ተናዶ ወደ ኬኔዲ ያመራል፡፡ የተባለው መፅሐፍ መመለሱ ሲነገረው፣ በደስታ ሰከረ፤ ወዲያው ግን ከመደርደሪያ ሼልፉ ላይ እንደሌለ ተረጋገጠ፡፡ የቤተ መፃህፍቱን ሠራተኞች ተማፀነ፡፡ ፍለጋው ጦፈ - መፅሐፉ ግን አልተገኘም፡፡ በበነጋው ፈልገው እንደሚቆዩት ተነግሮት ሄደ፡፡ በበነጋው ጧትም መፅሐፉ አልተገኘም፤ ጓደኛችን በንዴት “እኔ’ኮ አንድ ኮማ ጠፍታብኝ እሷን ለማሳየት እኮ ነው… አንዲት ኮማ እኮ ናት የምፈልገው…” እያለ እንባ ሲተናነቀው፣ አብረነው ያለን ጓደኞቹም፣ የቤተመፃህፍቱ ሠራተኞችም በድንገት በሳቅ ተንከተከቱ፤ “ምን ያስቃል ዶክተር ኮማዋን ፈልገህ ካላመጣህ ከፊቴ እንዳትቆም ብሎኛል… ዘንድሮ እኮ ተመራቂ ነኝ… አሁን በአንድ ኮማ…” እያለ ሲንቆጫቆጭ ሌሎቹ ሳቃቸውን ለቀቁት…
ጓደኛችን ከእኛ ተለይቶ ወደ ኬኔዲ ቤተመፃህፍት ሃላፊ ቢሮ ሄደና ክስ ጀመረ፡፡ አሁን የመፅሀፉ መጥፋት የምር ጉዳይ ሆነ… ቤተመፃህፍቱም ታመሰ… ምን አለፋችሁ ከሁለት ሳምንት በኋላ መፅሐፉን ይዞ ወደ ጋሼ ዮናስ ቢሮ እስከሄደበት እለት ድረስ፣ አጥኚው ከስጋት፣ እኛ ከፍካት፣ ጋሼ ደግሞ ከትጋት አልተለየንም ነበር… የጠፋችው ኮማ ጉዳይ ቅንጣት ያህል ግነት የሌለበት እውነተኛ ገጠመኝ መሆኑን ለአንባቢዎች በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ…
የዶ/ር ዮናስ አድማሱ የታተሙ ጥናቶችን በወፍበረር
ጋሼ ዮናስ ለጽሁፍ ያለው ጥንቃቄ እዚህ ከምገልጸው በላይ መሆኑን በትሁትነት መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ፣ ‹‹እንዲህ ነው›› የተባለ ሁለት ጊዜ ብቻ ታትሞ የተቋረጠ የተማሪዎች መጽሔት መስራችና የኤዲቶሪያል ቦርድ ጸኃፊ እንደነበረ እ.ኤ.አ. ሚያዚያ16 ቀን 1964 የታተመው ‹‹News and Views›› የተባለው የተማሪዎች ጋዜጣ መዘገቡ ይታወቃል፡፡ ጋሼ ዮናስ በ1954ዓ.ም. አካባቢ በ‹‹ቴዎድሮስ›› ተውኔት ላይ መተወኑን፣ በ1962 ዓ.ም. የጥላሁን ገሰሰን ሙዚቃ ከባንድ ጋር ሲጫወት ብዙዎችን የሚያስደምም ድምጽና ችሎታ ያለው መሆኑ ወዘተ.፣ ነፍሱ ለጥበብ የተገዛች ሊቅ መሆኗን ያስመሰክራል፡፡ የዛሬ ጥንቁቅነቱም መሰረት ያለው መሆኑን የሚጠቁሙ ይመስለኛል፡፡
ለዚህ ነው፣ ‹‹በኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት›› እና በሌሎች የምርምር መጽሄቶች ላይ አይቀሬ አርታኢና ተርጓሚ የመሆን ተፈላጊነት ያገኘው፡፡ በርግጥ፣ ‹‹ዳረጎት›› እያለ የሚዘጋጅልንን ምርጥ የማስተማሪያ ጽሁፎች በአንድ ላይ መልክ አሲዞ፣ በስሙ አንድ እንኳ የማስተማሪያ መጽሐፍ ሳያሳትምልን በማለፉ ግን፣ የምንቆጭ ተማሪዎቹ ብዙ ነን፤ ባይሆን ጥልቀት ባላቸው የምርምር ጽሁፎቹ ክሶናል እንላለን እንጂ፡፡ ዋና ዋና ጥናቶቹንም እንደሚከተለው በአጭር በአጭሩ ለማስተዋወቅ ልሞክር፡፡
ዮናስ፣ <<Journal of Ethiopian Studies>> የጥናት መጽሔት ላይ <<On the State of Amharic Literary Scholarship>> (June, 2001) በተባለ ጥናቱ፣ ቀደም ሲል የተነሱ የውጭ ሃገር አጥኚዎች የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍ ሥራዎችን “መርምረው” የስነ ምግባር ሰባኪነታቸውን (Didactism) እና እውነታዊ (Realistic) አለመሆናቸውን እንደ በቀቀን እየተቀባበሉ ማወጃቸውን ወዘተ. የሞገተበትና የአማርኛ ስነ-ጽሁፍ የራሱ የአነባበብ ሥልት እንዳለው ያስተነተነበት አቅም፣ የአማርኛ ሥነጽሁፍ ንድፈሀሳብ አፍላቂነቱን የሚያጸናለት ይመስለኛል ፡፡ ይህን ጥናት በሌላ ጊዜ ሌሎች ደፋር ‹‹ሀያሲያን›› ካነሷቸው ነጥቦች ጋር በትይዩ እያናበብኩ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡
ዮናስ አድማሱ፣ “The Image of the Hero in an Early Amharic Panegyric: Towards a Discourse of Empire” በሚል ርዕስ <<Proseeding of the First International Symposium on Ethiopian Philology ›› (2004) ላይ በታተመ ጥናቱ፣ አንድ የውዳሴ ግጥም ላይ ተወስኖ ባቀረበው ትንታኔና ፍካሬ፣ በጊዜው ተፈጥሮ የነበረውን ነባራዊ ምስል አሳይቷል፡፡ የወቅቱን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የማስረፅ ሥልትንና የማህበራዊ ኑሮ ፍልስፍናን፣ በጨረፍታም ቢሆን አመላክቷል፡፡
ዶ/ር ዮናስ፣ ከሰራቸው የጥናት ወረቀቶች በብዙዎች የሚታወቀው፣ “የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ፅሁፍ መፅሔት” ልዩ እትም (ቁ.10፣ 1992) ላይ የታተመው “ ‘አስረኛንኩዋ?’ ሀዲስ አለማየሁና የማህበራዊ ሂስ ስልታቸው” የሚለው ነው። ጋሼ ዮናስ በዚህ ጥናቱ፣ “ፍቅር እስከ መቃብር” ብዙዎች እንደሚሉት የፊውዳል ሥርዓቱን አስከፊነት ማጋለጥ ነው ከሚለው የተለመደ ጭብጣቸው በተለየ መንገድ፣ የተለያዩ የንባብ አሀዶችን ዋቢ አድርጐ የመፅሐፉ ጭብጥ “የሰብዕና መንጠፍ” (dehumanization) እንደሆነ አስተንትኗል፡፡ ይህ ሂሳዊ መጣጥፍ፣ በጥናት አካሂያድ ብቻ ሳይሆን በጭብጥ ግኝቱም አዲስነት እንዳለው ይታወቃል፡፡
“Callaloo” በተባለ የሥነ ጽሑፍ መጽሐፍ ላይ “What where they writing about anyway? Tradition and Modernization in Amharic Literature” በሚል ርዕስ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ በሁለት ደረጃ (Phase) በመክፈል፣ የትሁቶቹን የእነ ህሩይን ወልደስላሴ እና የተስፈንጣሪ ለውጥ ፈላጊዎቹን የእነ ዮሐንስ አድማሱን ዘመን ሥራዎችና የጭብጣቸውን የትኩረት አቅጣጫ ዳስሷል፡፡
ዮናስ ፣ የ“ጦቢያ”ን የመጀመሪያ የአማርኛ ልቦለድነት በማጽናት፣ የእነ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሣን “ተረት ነው” ትችት ለማክሸፍ ከአስተነተነበት የምር ጥናታዊ ወረቀቱ መካከል፣ “Silent is not Golden” (1995) በተባለ የጥናቶች መድበል ውስጥ ፣ ከእነ ዶ/ር ታዬ አሰፋ ጋር የታተመለት፣ “The First Borne of Amharic Fiction; A Revaluation of Afewerk’s Tobbya” የተባለው ተጠቃሽ ነው፡፡
“Narrative Ethiopia; A panorama of National Imaginary” (1995) የተባለው የዶክትሬት የምርምር ስራውም፣ ”ጦቢያ”ን እና ሌሎች የነገስታት አወዳሽ ተራኪ ግጥሞችን በማስተንተንና በመፈከር ያንጸባረቁትን ሀገራዊ ምስል በወጉ አርቅቆበታል፡፡ ጋሼ ዮናስ ከነዚህ የታተሙ ጥናታዊ ሥራዎቹ ሌላ በተለያዩ መጽሔቶች (ለምሣሌ በ”ጦቢያ”) የተለያዩ ሥነጽሑፋዊ ሀቲቶችንና ፍካሬዎችን አስነብቧል፡፡ በአለን ካፕላን የተጻፈውን መጽሐፍ፣ “አቅምና ብቃት ማዳበር” በሚል ርዕስ ተርጉሞ በስሙ ታትሞለታል። ብዙዎቹ ወዳጆቹና ተማሪዎቹ እንኳ በማያውቁት በዚህ የትርጉም መጽሐፉ፣ ታዲያ፣ የቋንቋ ብቃቱን በሚገባ እንዳሳየበት መመስከር የሚቻል ይመስለኛል፡፡

Read 6954 times