Saturday, 23 February 2013 11:08

“አላህ መኖሩን በምን ታውቃለህ? ቢለው፤ ያላሰብኩት ቦታ ሲያውለኝ፤” አለ ወሎ

Written by  ነብይ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

የመቀሌ ጉዞ ማስታወሻ 

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ኮሌጅ ቅጽር ግቢ ለመቀሌው የኢትዮጵያ የፊዚክስ ባለሙያዎች ማህበር 7ኛ ጉባዔ እየተንቀሳቀስን እንደነበር ነው ያለፈውን የጉዞ ማስታወሻዬን ያቆምኩት፡፡
“እባካችሁ ቶሎ እንውጣ፡፡ ገና እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ጐማ እንቀይራለን!” አለ አጋፋሪው የፊዚክስ ባለሙያ፡፡ እኔ፤ አንድ ነገር ሆዴ ገባ፡፡ የእንግሊዝ ነገር ሁሌ ይገርመኛልና “ሆሆ! ይሄ እንግሊዝ መቼም አይለቀንም” አልኩኝ፡፡ አንግሎፎን (Anglophone) የሆነው የመማሪያ ቋንቋችን (የትምህርት አፍ -መፍቻችን) እንግሊዝኛ መሆኑ፤ አንዱ እንግሊዞችን እንዳልረሳ ያደረገኝ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንግሎፎን ሆኜ በእንግሊዝ - አፍ ተምሬ፣ ለምን እንደሆን በማላውቀው ምክንያት እነዚህ እንግሊዞችኮ ብዬ ከጀመርኩ ምሬቴ አይጣል ነው፡፡ አንዳንዴ am I transcending from Anglophone to Anglophobe? (ከእንግሊዝ -አፍ ተናጋሪነት ወደ እንግሊዝ - ጠልነት እያደግሁ ነው እንዴ?) እላለሁኝ፡፡

እንግሊዝን ማሰቤ ዕውነቴን ነው፡፡ አንዳንዴ ግዴም ይመስለኛል፡፡ ምነው ቢሉ፤ የአስኳላ ትምህርት አፍ - መፍቻ ቋንቋ እንግሊዝኛ መሆኑ፣ ዊንጌት ት/ቤት በእንግሊዙ ጄኔራል ስም መሰየሙና መለስ ዜናዊን ጨምሮ አያሌ የሀገራችን የፖለቲካ ሰዎችና ምሁራን የዚሁ ት/ቤት ፍሬዎች መሆናቸው፤ በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በአፍንጮ በር መውጪያ በኩል ይገኝ የነበረው የተመረጡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለዩኒቨርሲቲ የሚያዘጋጀው prince Bede Mariam Laboratory School (የልዑል በዕደማርያም ላቦራቶሪ ት/ቤት)
የእንግሊዞች መሆኑና ከዚያም እነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስንና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን፣

አያሌ የኢህአፓ መሪዎችን፤ እንዲሁም እንደ አለምሰገድ ገ/አምላክ (የኢህአዴግ አመራር የነበረውን)፣ አበበ ተ/ሃይማኖትን (የአየር ኃይል አዛዥን)፣ ፃድቃን (የጦ/ኃ/ጦ አዛዥ)፣ ገብሩ አሥራት (የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት) ወዘተ…ዓይነት የፖለቲካ ሰዎችንና ምሁራንን ያፈራ ት/ቤት በመሆኑ አይረሴ ነው፡፡ እኔም እዚያው ነበርኩ፡፡
(እኔም እዚያው ነበርኩ ስል ማርክትዌን ትዝ አለኝ፡፡ እንዲህ አለ፡- “እገሌ የተባለው ታላቅ ደራሲም ሞተ፡፡ እገሌ የተባለው የስነጽሑፍ ሰውም ሞተ… እያለ ታላላቅ ደራሲዎችን ይደረድር ይደረድርና “እኔም ጤና አይሰማኝም!” ብሎ ይደመድማል”)
እንደ ሳንፎርድ ት/ቤት ያለ (ውድም ቢሆን) ምርጥ ምርጥ ተማሪዎችን ያፈራ ት/ቤት የእንግሊዞች መሆኑም እንግሊዝን እንዳስብ ያደርገኛል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁሌ የማነሳት እትዬ ዓባይ አለች፡፡

ዘመዳችንም ሠራተኛችንም ናት/ነበረች - አጐቴ ቤት፡፡ አራት ኪሎ፡፡ እንደ ሠራተኛ ተቀጥራ ከመኖር ብዛት ዘመድ ሆነች፡፡ እትዬ ዐባይ አጭሩ ስሟ ነው - ዐባይነሽ ነው ድፍን - ስሟ፡፡ ማቆላመጡን ስናበዛው እትዬ አቡም እንላታለን፡፡ ጠጅ በጣም ትወዳለች፡፡ አንድ ማስረጃ፡- አጐቴ ማዕድን ሚኒስቴር (ማይጨው አደባባይ) አስቀጥረዋት ነበር፡፡ ላቦራቶሪ ጽዳት ነው ሥራዋ፡፡ ታዲያ የላስቲክ ወተት በየቀኑ ይሰጣታል (ነብሱን ይማረውና የሾላ ወተት 0.40 ሣንቲም ነበር ያኔ) ኬሚካል እንዳይመርዛት ተብሎ ነው (ደጉ ጊዜ!) እሷ ሆዬ ያቺን የላስቲክ ወተት ታመጣና አራት ኪሎ፤ “ይገባዋል ጠጅ ቤት (እሱንም ነብሱን ይማረው)” ሄዳ በጠጅ ትቀይረዋለች፡፡ ጠጅ ከወደዱ አይቀር እንዲህ ነው!
እትዬ ዐባይ ጠጅ መውደድ ብቻ ሳይሆን ታውቃለች፡፡ የአጐቴ ቤት ጠጅ ቀማሽ ነች! የዕውነት ታውቃለች! የአጐቴ ሚስት በአዘቦትም ሆነ በድግስ ቀን ጠጅ ሲጥሉ፤
“አቡ፤ ነይ እስቲ ቅመሺው?” ይሏታል፤ ከመሥሪያ ቤት ስትመለስ፡፡ ትቀምሰዋለች፡፡ “ምጣ - ሞጣ” ብላ ታጣጥምና፤
“አቤት! አቤት! እንግሊዝ የሆነች ጠጅ ነች!” ትላለች፡፡
እትዬ ዐባይ እንግሊዝን እንዳልረሳ ካደረጉኝ ሰዎች አንዷ ናት፡፡ እንደ እትዬ ዐባይ አባባል እንግሊዝ መሠሪ፣ ውስጥ ውስጡን ቦርቧሪ፤ ምስጥ፣ እየጣፈጠ ገብቶ ሥራውን የሚሠራ እንደማለት ነው፡፡ እንደው አስብ ቢለኝ ነው፡፡
እንግዲህ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ጐማ ቀይረን ወደመቀሌ መጓዝ ነው!! ጐማ እስኪቀየር ከጐኔ ከተቀመጠው ከመቱ የመጣ ፊዚሲስት ጋር ከአውቶብሱ ወርደን ቡና ስንጠጣ፤ ለመተዋወቂያ ጊዜ አገኘን፡፡ በፊዚክስ ማስተርስ ዲግሪውን ሠርቷል፡፡ ሁለት ቀን ከመቱ ተጉዞ ለፊዚክሱ ጉባዔ ነው የመጣው፡፡
የደከመው ይመስላል፡፡ የመቱው ኮሌጅ የፊዚክስ መምህር ነው፡፡ የመቱው ፊዚሲስት የምለው ስሙን ከጠራሁ ጽሑፌ የሚጠብብኝ ስለሚመስለኝ ነው፡፡ አስተማሪዎቹን አቃለሁ፡፡ እኔ በጣም የምቀርበው ሰው ለሱ አድቫይዘሩ (መካሩ) ነበር፡፡
“መቱን ያውቁታል?” አለኝ
“አላውቀውም” አልኩት፡፡
“መቱ ስትሄዱ ለጥ ያለ ሜዳ ሆኖ በግራም በቀኝም ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ነው - የቡና ደን ነው”
“ኦ ወደ ትግራይ ስንዘልቅ ደሞ የተለየና ተቃራኒ ቀፅታ ነው የምናገኘው፡፡ ትግራይ ሄደህ ታውቃለህ?” አልኩት ተራዬን፡፡
“እስከደብረ ብርሃን ነው የማውቀው”
“ታየዋለህ፡፡ ሰንሰለታማ ተራራ፣ አቀበት ቁልቁለት፣ ዋሻ፣ የአላማጣ ጠመዝማዛ ገደልና ተረተር… ኦ ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮልሃል፡፡ ዱሮ አንድ የአክስቴ ልጅ ምን ይል ነበር መሰለህ ‘አገሬን እወዳለሁ ማለት ብቻ አይበቃም ዞር፣ ዞር ብሎ ማየት ያስፈልጋል’
“አሪፍ አባባል ነው እርሶስ ከየት ነዎት?” አለኝ ተራውን፤ ስለኔለ ለማወቅ፡፡
“አዲስ አድማስ የሚባል ጋዜጣ ታውቃለህ?”
“በደምብ!”
“የዚያ ዋና አዘጋጅ ነኝ!”
“ኧረ እባክዎት?!” የድንጋጤ ቅልፄ አለ ድምፁ ውስጥ፡፡ ይህን ድንጋጤ መገለጫውን ያገኘሁት፤ በኋላ ወደኛ መቀመጫ የመጣ ትንሽ ፈጣንና ዘርዘር ያለ ወጣት፣ የህይወት ታሪኩን በሰፊው ሲተርክልኝ፤ የመቱው ልጅ ሰምቶ፤” ጋዜጠኛ መሆንዎትን ስለማያውቅኮ ነው እንዲህ የሚለፈልፈው” አለኝ ወደ ጆሮዬ ዘመም ብሎ፡፡
ወይ ጉድ! ጋዜጠኛን እንዴት ነው ሰው የሚያየው? ብዬ በሆዴ መጀመሪያ ስንተዋወቅ “እረ እባክዎ!” ያለኝ ለምን እንደሆነ የገባኝ፤ ጋዜጠኛም፣ ሣይንቲስትም፣ ፖለቲከኛም ሆነ ሃይማኖተኛ፤ ከሁሉ አስቀድሞ ሰው ሆኖ ሲያወራ ነው እኔ ደስ የሚለኝ፡፡ ከጋዜጠኝነትም ይልቅ እንደተጓዥ ደራሲ ማሰብ የበለጠ ህይወትን ሳያሳይ አይቀርም፡፡
ቡና ጠጥተን ወደ አውቶብሳችን ተመለስን፡፡
ምሣ ደብረ ሲና ሆነ፡፡
ደሴ የገባነው በጣም መሽቶ ነው፡፡ ጠዋት ስንነሳ ማርፈዳችን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ሰው መኝታ ፍለጋ በጭለማ ሻንጣውን ይዞ መዟዟር ነበረበት፡፡ እኔ እንደ እንግድነቴ ከተያዙ ሆቴሎች አንዱ ጋ አረፍኩ፡፡
ወዳጄ ሙሉጌታ የእሥር ቤት አብሮ አደጌ አሊያም አብሮ - ታሠሬ ነው፡፡ Inmate እንደሚሉት ፈረንጆቹ፡፡ አረፍ ብለን ቢራ እንጠጣለን ብዬ ሳስብ ወደኔ መጥቶ፤
“ገና ጣጣችን አላለቀምኮ!” አለኝ ረጋ ባለው ትሁት ልሣኑ፡፡
“ምነው?” አልኩት፡፡
“አውቶብሳችን ማደሪያ አላገኘም፡፡ ይህን ቦታ ፈልገን ማሳደር የእኔና ያንተ ኃላፊነት ነው”
“ታዲያ የት እንጠይቅ”
“ምናልባት ፖሊስ ጣቢያው ደጃፍ”
“እንሞክራ”
በማህል፤ ያረፍንበትን ሆቴል ዘበኛ “እዚህ ማሳደር ይቻላል ወይ?” ብለን ጠየቅነው፡፡
ዘበኛውም፤ “እዚህ አይቻልም፡፡ ግን ሹፌራችሁ ጠመመ እንጂ ብዙ መኪኖች የሚያድሩበት የመንግሥት ግቢ አለ ብዬ ነግሬው ነበር” አለና ቦታውን ስሙን ነገረን፡፡ አንድ ጠቋሚ ልጅ ያዘን ወደተባለው ግቢ ሄድን፡፡ አውቶብሱ ረጅም በመሆኑ ግቢው ውስጥ ቦታ እስኪያስተካክል ዘበኛው ወደኔ ጠጋ አሉ፡፡ ወፈር ያለ ካፖርት ለብሰዋል፡፡ ጠና ይበሉ እንጂ ጠንካራ ናቸው፡፡
“አቦ፤ ከወዴት ነው የመጣችሁት?” አሉኝ በወልኛ ቅላፄ ‘ቦ’ን ረገጥ አድርገው፡፡
“ከአዲሳባ”
“ወየት ነው ምትሄዱ?”
“ወደመቀሌ፡፡ አንድ ጉባዔ አለ - እዛ ልንሳተፍ ነው”
“ከምን መሥሪያ ቤት ናችሁ?”
“ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ”
“አይ! ዩኒቨርሲቲ እንኳን ገንዘብ የላቸውም፡፡ አንድ ሠላሳ ብር ቢከፍሉኝ ይበቃቸዋል!” አሉ፡፡
ገረሙኝ፡፡ ዋጋ የሚጠይቁት በግልጽ ነው፡፡ ስለመንግሥት ሠራተኞች የራሳቸውን ግንዛቤ ወሰዱ፡፡ ዋጋቸውን ተናገሩ፡፡ አለቀ፡፡
“ሰውዬው የሻይ ይፈልጋሉ መሰለኝ!” አልኩት ለወዳጄ፡፡
ጠራቸውና ቦታውጋ ላደረሰንም፤ ለእሳቸውም የደንቡን ሰጣቸውና እፎይ ብለን፤
“አሁን እራት እንፈልግ” ተባባልን
ወደከተማው ማህል ገብተን ራት ጠየቅን፡፡ “ደህና ምግብ የት ይገኛል፤ ጐበዝ?”
“የሆቴል ስም ነገሩን፡፡
“የትጋ ነው?”
“ከፍ በሉና፤ እዚያ አደባባይጋ አጠፍ በሉ ወደቀኝ” ስንደርስ አንዱን ጠየቅነው፡፡
“ኦ በዛችጋ ዝቅ በሉ”
ዝቅ አልን፡፡ ሌላ ሰው ጠየቅን፡፡
“ትንሽ ዝቅ በሉ - ያ መብራት ይታያችኋል?” አለ በጣቱ እያሳየ፡፡
“ይሄ ነገር ስናውቀው የበለጠ ይርቃል እንዴ?” እየተባባልን እየሳቅን ወረድን፡፡
ደርሰን ክትፎ አዘዝን፡፡ ሆቴሉ፤ ባንድ ወገን ናይት ክለብ፣ ባንድ ወገን ምግብ ቤት ነው፡፡ ዳንሰኛ የሚመስሉ ሚኒ የለባበሱ ሴቶች ይመላለሳሉ፡፡ ቢራ አዘን በሰፊው ጨዋታ ቀጠልን፡፡ መሻሽቷል ሳይታወቀን፡፡
ከሆቴሉ ወጥተን ወደ መኝታችን ስንጓዝም ጨዋታችን ደርቷል፡፡ ከጥንት እስከዛሬ ነው ሁሌ ርዕሳችን!
አስፋልቱ ዳር የምናያቸው ጐዳና አዳሪዎች ያሳዝናሉ፡፡ ብዛታቸው ይገርማል፡፡ መንገዱ ጭር እያለ፣ የሚንቀሳቀሰው ሰው ቁጥር እየሳሳ ሄደ፡፡ ወዳጄ ተጠራጥሮ፤
“ሆቴላችን በዚህ ነው እንዴ?” አለኝ፡፡
ለካ መንገድ ስተናል!
ተመልሰን ዋናውን መንገድ ይዘን ሆቴላችንን አገኘነው፡፡ በጨዋታችን መስህብ ድካሙ አልተሰማንም ነበር፡፡
ጠዋት ከትላንት ተምረናልና በአልጋ ፍለጋ የተቀጣው ሁሉ በጊዜ አውቶብሱ ላይ ሰፈረ፡፡ መንገድ ቀጠልን፡፡
አውቶብሱ ላይ የአዳር ወሬ መጣ፡፡
“እኛ ያደርንበት አሪፍ ነበር” አለ አንዱ፡፡
“የእኛም ጥሩ ነበር” አለ ሌላኛው
አንደኛው ግን “እኔ ጉድ ነው የገጠመኝ!” አለ፡፡
“ምን አጋጠመህ?”
“ቁጭ ብለን 11 ሰዓት ሆነ!”
“እንዴት?”
“ከታች ናይት ክለብ ነው - ዳንስና ሙዚቃ ጆሮህን ይበጥስሃል፡፡ ከላይ አልጋ ነው - ኖርማሊ ለአጭር ጊዜ አረፍ የሚባልበት አልጋ ነው - እንዳፈጠጥን 11 ሰዓት ሆነ ነው የምላችሁ”
እኛ ያጋጠመን ደግሞ የሚደንቅ ነው፡፡
“እንዴት?”
“አንዷን አዳር ይቻላል ወይ?” ብዬ ጠየኳት፡፡
“ዴቦ ነው ያለው” አለችኝ
“ምንድነው ዴቦ?” አልነው ሁላችንም፡፡
“እኔም አላወኩም ነበር፡፡ በኋላ ነው ያስረዱኝ፡፡ ለካ ዴቦ ስትል ደቦ ማለቷ ነው፡፡ ደቦ በነሱ ምንድነው መሰላችሁ? ሴቶቹ በአንድ ክፍል ብዙ ሆነው ያድራሉ፡፡ እናንተም የምትፈልጓትን ልጅ ይዛችሁ እዛው ትደመራላችሁ!”
“ይሄ አዲስ ግኝት ነው! እኔ ደሴ ነው የተማርኩት! እንዲህ ያለ ቃል ሰምቼም አላውቅ” አለ አንዱ ደሴ - አደግ ምሁር፡፡
ወልዲያ ቁርስና ምሣ - “ቁምሣ” (Branch) በልተን ጉዞ ወደ መቀሌ ሆነ፡፡ ሁላችንም መንገዱን አናውቀውም ማለት ነው፣ ወይም ረስተነዋል መሰለኝ፣ ረዘመብን፡፡ ይሄን ያህል ኪሎ ሜትር ቀረን የሚለው የሂሳብ ስሌት - ይሰላል… ይሰላል… ይሰላል - መቀሌ አልተገኘም፡፡ ያ ሁሉ የፊዚክስ ምሁር ሂሳቡን አላገኘውም፡፡
ትዝ ይለኛል፤ አንድ ጊዜ አንድ ሹፌር ወደ አፍዴራ ሲወስደን እንደዚሁ መንገዱ በጣም ይረዝምብናል፡፡ የሰው ዘር ሳናይ በዚያ በሙቀት በበረሃው ማህል እየተጓዝን ታከተን፡፡
“ኧረ ይሄ አፍዴራ የት ነው ያለው?” አለ አንዱ ተጓዣችን፡፡
ይሄኔ ሹፌራችን፤ “ኧረ አፍዴራ ቀርቶ አገር ባገኘን” አለ፡፡
መቀሌ ሳንደርስ እየመሸ ነው፡፡ የምሁራኑ የሂሳብ ሥራ ቀጥሏል፡፡ “30 ኪ.ሜ ነው አላላችሁም?” ይላል አንዱ፡፡
ሌላው “አረ 20 ኪ.ሜ ነበር የተባለው?”
“ኧረ ወደ ጐንደር እንዳይሆን የምንሄደው፤ ሹፌር?”
“መቀሌ እንዲህ በቀላል የሚደረስ መስሏችኋል እንዴ?”
አንዱ፤ “አዲ…የሚል ከተማ አልፈናል” ይላል፡፡
ሌላው፤ “ባክህ መቀሌ ብዙ “አዲ” ነው ያላት”
ወጣቶቹ ሂሣቡን ትተው ፌዝ መረጡ! ለካ ምሁርም ሲመረው ምሬት ትቶ ፌዝ ይጀምራል፡፡
(ይቀጥላል)

 

 

Read 3790 times