Saturday, 23 February 2013 11:06

የዝንጀሮ ልጅ፤ ቅቤ ተቀብተህ ና ቢሉት፤ ቅቤ ቢኖር ያባቴ ታፋ ይህን ይመስል ነበር ወይ? አለ”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በኢትዮጵያ በ1920ዎቹ የነበረው ታሪክ ዛሬ ሲያስቡት ተረት ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ የጦር-ባላባቶች፤ ሰው ኃይለሥላሴ የሚባል (ራስ ተፈሪም የሚባል ስም አለው) አንድ ወጣት በአሰርታት ዓመታት ውስጥ መሪ ሊሆን ማኮብኮቡን ሰሙ፡፡ ይሄ ጭምት መሳይ ዝምተኛ ሰው አገሪቱን የመቆጣጠር አቅም እንደሚኖረው ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ሆኖም በ1927 ዓ.ም ኃ/ሥላሴ እያንዳንዱ በየተራ እንዲመጣና ታማኝነታቸውን በመግለፅ መሪያቸው መሆኑን እንዲያረጋግጡ አዘዘ፡፡
አንዳንዶች በጥድፊያ፣ አንዳንዶች ፈራ-ተባ እያሉ ትእዛዝ ሲፈፅሙ፤ የሲዳሞው ደጃዝማች ባልቻ ግን አሻፈረኝ አለ፡፡ ኃይለሥላሴ በተለመደው የጨዋና ግትር ዘዴው፤ ባልቻ እንዲመጣ ተማፀነው፡፡ ባልቻም “እታዘዛለሁ ግን በፈለኩት ጊዜ ነው የምመጣው፡፡ በተጨማሪም 10,000 ጦር ይዤ ነው ከአዲስ አበባ ወጣ ብዬ እምጠብቀው” አለ፡፡
ኃ/ሥላሴም፤ “ስለክብርህ የፌሽታ ግብዣ ላደርግልህ አስቤአለሁና፤ ተጋበዝልኝ” አለ፡፡ ባልቻ ግን ታሪክን ጠንቅቆ ያውቃልና የቀደሙት የኢትዮጵያ ነገሥታትና መሳፍንት ግብዣን እንደወጥመድ ሲጠቀሙበት እንደኖሩ ተገንዝቧል፡፡ ነቄ ነው፡፡ መታሰርም ሆነ መገደል የሚከተለው ከግብዣ በኋላ ነው፡፡
ደጃዝማች ባልቻ የግብዣውን ዓላማ እንደተረዳ ለመጠቆም “የምመጣው 600 ክብር ዘበኞቼን ይዤ ነው” አለ፡፡ ኃ/ሥላሴ ግን “እንዲህ ያሉትን ጀግኖችህንማ ማስተናገድ ለእኔ ክብር ነው” ሲል መለሰ፡፡
ባልቻ ክቡር ዘቦቹን ግብዣው ላይ እንዳይሰክሩና በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ አዘዘ፡፡ ግብዣው ቦታ ሲደርሱ ኃ/ሥላሴ ታይቶ የማይታወቅ አቀባበል አደገ፡፡ ባልቻ “ማምሻውን ወደ ጦር ሰፈሩ መመለስ አለብኝ፤ አለበለዚያ ጦሬ አዲስ አበባን እንዲወርር አዝዣለሁ” አለ፡፡ ኃ/ሥላሴ ባለመታመኑ እንዳዘነ በመግለፅ፤ ይልቁንም ከግብሩ በኋላ የሚዘፈነው ዘፈን የሲዳሞን ጦረኛነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን አደረገ፡፡ ባልቻም ኃ/ሥላሴ የፈራና ለማይረታው ወታደሩ እጁን የሰጠው መሰለው፡፡
ከሰዓት በኋላው ሲገባደድ ባልቻና ወታደሮቹ ነጋሪት እያስጐሰሙ ወደ ጦር ሠፈራቸው አመሩ፡፡ ከሳምንታት በኋላ አዲስ አበባን መውረር እንደሚችል አሰበና ባልቻ ኃ/ሥላሴ እንግዲህ ቦታው ወይ ዘብጥያ ወይ ሞት ነው” አለ፡፡
ሆኖም ባልቻ ወደ ጦር ሠፈሩ አካባቢ ሲደርስ አንድ የተሳሳተ ነገር መኖሩን ተገነዘበ፡፡ አንድም ድንኳን የለም፡፡ የሚታየው ጭስ ብቻ ነው፡፡ አንድ የዐይን ምስክር የሆነውን ሁሉ አስረዳው፡- የኃ/ሥላሴ ጦር ባሳቻ መንገድ መጣ፡፡
የመጣው ግን ሊዋጋ አልነበረም፡፡ ኃ/ሥላሴ በዘምቢል ወርቅና ብር አጭቆ የላከው ጦር ነው፡፡ የባልቻን ወታደሮች መሣሪያ ሁሉ በወርቅና በብር ገዛ፡፡ እምቢ ያሉ ተያዙ፡፡ በጥቂት ሰዓት ውስጥ የባልቻ ጦር መሣሪያውን አስረከበ፡፡ ባልቻ ወደ ደቡብ 600 ወታደር ይዞ ለመሸሽ ቢፈልግም ያ መሣሪያ የወሰደባቸው የኃ/ሥላሴ ወታደር መንገዱን ገትሮ ይዟል፡፡
ወደ አዲስ አበባ እንዳያቀና ሌላ ጦር መንገዱን ገድቦታል፡፡ እንደቼዝ ተጨዋች ዙሪያውን ተከበበ፡፡ ባልቻ ለመጀመሪያ ጊዜ እጁን ሰጠ፡፡ በኩራትና በአጉል ምኞት የሠራው ኃጢያት ስለፀፀተው ወደ ገዳም ሊገባ ተስማማ፡፡ ያለ አንዳች የጥይት ድምፅ ኃ/ሥላሴ ደጃዝማች ባልቻን አስወገደ፡፡
የሲዳሞው ደጃ/ባልቻም ወደ ገዳሙ ከመግባቱ በፊት፤
“የተፈሪን ጉልበት አትናቁ፡፡ እንደ አይጥ ይድሃል፡፡ ሆኖም የአንበሳ ጥርስ ነው ያለው!” አለ፡፡
***
በግብዣ ከመጠመድ ይሰውረን! የሌሎችን ጉልበት ከመናቅ አባዜ ያድነን፡፡ የራስን አቅም የዓለም መጨረሻ ነው ብሎ ከማጋነን ይሰውረን! የመስተዋት መስኮቱን ጭሳማ የማድረግ ጥበብ ያለው አለቃ ወይም የፖለቲካ መሪ፤ ጭሳማውን ቀለም የበለጠ ባጠቆረው መጠን፣ የበለጠ እንዳናየው እያደረገ መሆኑን አንርሳ፡፡ “ጦርነቱን ከማወጅህ በፊት ድልን ተቀዳጅ” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ እቅድህን አታሳውቅ፡፡ ስለእቅድህ ከመፎከር ተጠንቀቅ ነው ነገሩ፡፡ ባላንጣህ እቅድህን እንዳያውቅ ባደረግህ ቁጥር የድልህ መጠን ይበልጥ እየሰፋ ይመጣል፡፡ ስለእቅድህ በፎከርክ ቁጥር ግን ስኬትህን እያራቅህ ነው የምትሄደው፡፡ የሞቀ ከተማ እያሰብን መጨረሻችን ገዳም የሚሆነው ሥር-ባልሰደደ ድል ስንኩራራና ሌሎች ስለእኔ ምን ያስባሉ ብለን ሳንጠይቅ ስንቀር ነው፡፡
በቡድናዊ ስሜት አለመጠመድና አለመጨፈን ለአገርና ለህዝብ የሚበጅ አካሄድ ነው፡፡ ምክንያቱም አስተሳሰባችንን እያጠበብን የቡድናዊ ስሜት ተገዢ ስንሆን ደባንና ሴራን የሙጥኝ ወደማለት እንገባለን፡፡ ያ ደግሞ አደገኛ ነው፡፡
የሦስተኛው ክፍለ - ዘመን ህንዳዊ ፈላስፋ - ካውቲላ፤
“በዓላሚ ቀስተኛ፣ የተሰደደ ቀስት
አለው አጋጣሚ፣ ወይ ሊገል ወይ ሊስት፡፡
ግን በስል-ጭንቅላት፣ ሤራ ከተሳለ
ህፃንም ይገድላል፣ እናት ሆድ ውስጥ ያለ፡፡”
የሚለን ለዚህ ነው፡፡
ሌላው የአገር ጉዳይ ግልብ - እውቀትን መከላከል ነው - ባልበሰለ አዕምሮ ዘራፍ ማለትን፡፡ ያለፖለቲካዊ ብስለት ፖለቲከኛ ነኝ ማለትን፡፡ መላው ዓለም እውቀት ሆኖ ሳለ የአዕምሮን በር ዘግቶ፣ የእኔ እውቀት ብቻ ነው ገዢ ብሎ ማሰብ ክፉ አባዜ ነው፡፡ ከሳጥኑ ውጪ (Out of the box እንዲሉ) ለማየትና ለማስተዋል አለመቻል፤ የሌሎችን ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆንን ያስከትላል፡፡ ያ ደግሞ ብዙ አለመግባባቶችን ይወልዳል፡፡ “ከመርገምት ሁሉ የከፋው መርገምት ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት” ይለዋል ባለቅኔው፡፡ ወጣቱ፤ መሰረታዊ እውቀት፣ ጥልቀትና ብስለት፣ ከዚያም ስክነትና ጥበበኛነት እንዲኖረው ለማድረግ ብርቱ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ አዋቂው ራሱን እንዳያጥርና እንዳይገድብ፣ ልምዱን እንዲያጋራ መንገድ መክፈት ያሻል፡፡
ለሁሉ የህይወት ዘርፍ ፖለቲካዊ ትርጉምና አንድምታ ሰጥተን አንችለውም፡፡ መሰረታዊ እውቀት፣ ከኑሮ የምንቀስመው ልምድና ከባህል ያበለፀግነው የአእምሮ ሀብት የህይወትን ትርጉም ለማየት በዋናነት መሣሪያዎቻችን ናቸው፡፡ ይህንንም ለመቀበል እውነተኛ የህዝብ ፍቅር ያስፈልጋል፡፡ እውነተኛ የህዝብ ፍቅር የራስን ጥቅም መሰዋትን ይጠይቃል፡፡
“ህዝብን በመጠቀም የራስን ግብ ለመምታት ያለው ዘዴ በጉልበትና በማጭበርበር የሚደረግ ነው፡፡ ይልቁንም የህዝብ ፍቅር አንዱ መሣሪያ ነው ይላሉ ጠበብት፡፡ ያ ግን ፀሀይ እስኪወጣ መጠበቅን ይጠይቃል፡፡ ህይወት ደግሞ እያንዳንዷን ቅፅበት ትፈልጋለች” ይላል ጐይቴ፡፡
ካለፉት የወረስነው፣ ወይም የወረስን የመሰለንን ነገር ልብ ብለን እንመርምር፡፡ ለህዝብ ሰጥተነዋል ያልነውን ነፃነት፣ የኢኮኖሚ ብልፅግና፣ ፍትሕ-ርእዕ፣ ዲሞክራሲና እኩልነት እንመርምር፡፡ ስትራቴጂ በነደፍን፣ መመሪያ ባወጣን፣ ሪፖርት ባቀረብን ቁጥር ምን ያህል ለህዝብ ጠቀመ? ከሚለው ማንፀሪያ አኳያ እናስተውለው፡፡ መለስ ብለን፤ ያለምነውን ነገር፣ እጅ-ካስገባነው ነገር እናወዳድር፡፡ አለበለዚያ፤ የማታ ማታ “የዝንጀሮ ልጅ ቅቤ ተቀብተህ ና ቢሉት፤ ቅቤ ቢኖር ያባቴ ታፋ ይህን ይመስል ነበር ወይ” አለ እንደሚባለው እንዳይሆን እናስብ፡፡

Read 5012 times