Saturday, 23 February 2013 10:58

ቤተክህነት የከሰሰቻቸው አራት ጋዜጠኞች ቃላቸውን ሰጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያሪክ፤ መሠረተ ቢስ መረጃዎችን በማስተላለፍ ህዝቡን ለማደናገር ይሠራሉ በማለት ክስ የመሠረተባቸው አራት ጋዜጠኞች ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ቃላቸውን ሰጡ፡፡
በስልክ ከፖሊስ በደረሳቸው ጥሪ መሠረት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቀርበው የተከሳሽነት ቃላቸውን የሰጡት የ “ሎሚ” መጽሔት፣ የ “ሊያ” መጽሔት፣ የ“አርሂቡ” መጽሔት እና የ “የኛ ፕሬስ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች ፎቶግራፍ እና አሻራቸው ተወስዶ በዋስ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
የ“ሎሚ” የ “ሊያ” እና የ “አርሂቡ” መጽሔት ዋና አዘጋጆች ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ለፖሊስ ቃል የሰጡ ሲሆን የ “የኛ ፕሬስ” ዋና አዘጋጅ ሃሙስ የካቲት 14/2005 በቀረበበት ክስ ዙሪያ ቃሉን ሰጥቷል፡፡
የየኛ ፕሬስ ጋዜጣ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ስዩም ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ካሣሁን ወ/ዮሐንስ ላይ “ሲኖዶስ ተከፋፍሏል” እና “ስደተኛው ሲኖዶስ መግለጫ አወጣ” በሚሉ ርዕሶች በወጡ ዘገባዎች ክስ ቀርቦበታል፡፡
የ“አርሂቡ” መጽሔት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ካሣሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በታህሳስ ወር እትም ቁጥር 40 ላይ “አቡነ ማቲዎስና አቡነ ሣሙኤል ተፋጠዋል” በሚል ባወጣው ዘገባ ክስ እንደረቀበባቸውና ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አበራ የተከሳሽነት ቃሉን መስጠቱን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ማክሰኞ የተከሳሽነት ቃላቸውን እንደሰጡ የገለፁልን የ“ሎሚ” መጽሔት ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ታዬ ዋና አዘጋጇ ወ/ት ብዙአየሁ ጥላሁን በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች ለቀረበባት ክስ ቃሏን ከሠጠች በኋላ የመኪናቸውን ሊብሬ አስይዘው በዋስ እንደተለቀቀች ተናግረዋል፡፡
ዋና አዘጋጇ “መንግሥት በሃይማኖት ሃይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገባም” የሚለውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ፣ ህዝብ በመንግስትና በቤተክርስቲያን አመኔታ እንዳይኖረው የሚያደርግና ህዝብን ለአመጽና ለሁከት የሚያነሳሳ ጽሑፍ አትማ አሠራጭታለች የሚሉ ክሶች የቀረቡባት ሲሆን ለሁሉም ክሶች ቃሏን መስጠቷን አቶ ግዛው ገልፀዋል፡፡
የ“ሊያ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ አማረ በበኩላቸው፤ ስለ ጉዳዩ ዋና አዘጋጇ ብዙም የምታውቀው ስለሌለ እሣቸው የተከሳሽነቱን ቃል እንደሰጡና በክስ ዝርዝር መግለጫው ላይም ከሳሽ ሆነው የቀረቡት አቡነ ናትናኤል መሆናቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። መጽሔቱ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቀጣይ እጣ ፈንታ ምንድነው?” በሚል በቁጥር 19 እትሙ ባቀረበው ዘገባ ክስ እንደቀረበባቸውም አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የጥር 25 ቀን 2005 እትም “ጠቅላይ ቤተክህነት በአራት የሚዲያ ተቋማት ላይ ክስ መሠረተች” በሚል ርዕስ በወጣው ዜና ላይ የተከሰሱት የሚዲያ አባላት ሃሳብ ሳይካተት በመዘገቡ ቅሬታ እንደተሰማቸው የሚዲያ ባለቤቶችና ስራ አስኪያጆች ገልፀዋል፡፡ ጋዜጣው ዘገባውን ሲያጠናቅር የእኛን ሃሣብ ማካተት ነበረበት የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ሚዲያው እርስ በእርስ የመተባበር መንፈስን መፍጠር እንደሚገባው አስታውቀዋል፡፡

 

Read 4388 times Last modified on Saturday, 23 February 2013 13:08