Saturday, 23 February 2013 10:53

ኢህአዴግ ቀጣዩን ሊቀመንበር ሊመርጥ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ዘጠነኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን ከወር በኋላ በባህርዳር ከተማ የሚያካሂድ ሲሆን በዚህ ጉባዔ ላይ የድርጅቱን ቀጣይ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበሩን በመምረጥ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ከትናንት በስቲያ በጽ/ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የግንባሩ ጉባዔ ዘንድሮ የሚካሄደው በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜው ሲሆን ቀጣይ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በምክር ቤቱ ከተመረጡ በኋላ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

“በመለስ አስተምህሮዎች ጠንካራ ድርጅትና የልማት ሃይሎች ንቅናቄ ለህዳሴያችን!” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል በተባለው ድርጅታዊ ጉባዔ፤ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚና በኢህአዴግ ምክር ቤት ውይይት ተደርጐበት የፀደቀው ረቂቅ ሪፖርት እንደሚፀድቅና አዲስ የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትም እንደሚሰየሙ አቶ ሬድዋን ተናግረዋል፡፡ ጉባዔው የግንባሩ መሥራችና እስከህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ድርጅቱን በሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሌሉበት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑንም አቶ ሬድዋን ገልፀዋል፡፡

ግንባሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልፈት የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት በተረጋጋ መንገድ መሙላቱን የጽ/ቤት ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በግንባሩ የጀመረው የአመራር መተካካት ሂደት በዘንድሮው ጉባዔ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሬድዋን፤ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ደረጃ በደረጃ የሚተካካበትና አዲሱ የአመራር ትውልድ ወደፊት የሚወጣበት እርምጃ እንደሚወሰድም ገልፀዋል፡፡ በጉባዔው ላይ ከአስራአምስት የውጭ አገራት የሚጋበዙ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉበትና በአጠቃላይ ከ2500 በላይ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ሬድዋን ተናግረዋል፡፡ የግንባሩ ዘጠነኛ ድርጅታዊ ጉባዔ መጠናቀቂያ ላይ የሚወጡት ውሣኔዎች አገሪቱ በቀጣዮቹ ሁለት እና ሁለት ዓመታት ተኩል የምትመራበት እንደሚሆንም አቶ ሬድዋን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡

Read 4243 times Last modified on Saturday, 23 February 2013 13:07