Saturday, 16 February 2013 13:30

ሽማግሌው እና የአትክልት ቦታው

Written by  ነቢዩ ስዩም
Rate this item
(0 votes)

የሆስፒታሉን አፀድ፣ አፀድ ካደረጉት ዛፎች ላይ የሰፈሩ ወንድ፣ ሴት እና ፍናፍንት አእዋፋት በህብር ያዜማሉ፣ ይንጫጫሉ፡፡
“ማድመጥ፣ በሰሚ ንቃት ተወሰነ
ማየት፣ በአድማስ ጥጋት ተጋረደ…” እያሉ፡፡
ግቢው ሁሌ ጅምር በሆነ ግንባታ እንደባተለ ነው፡፡ ሁሌ መቆፈር፣ አሸዋና ጠጠር መገልበጥ፣ አሮጌ የሆኑትን ህንፃዎች ማፍረስ… ይሄ ሁሉ የሚያስነሳው አቧራ!
ከጐረቤት ወፍጮ ቤት ከሚለቀቅ በርበሬ ከጨቆነው ወፍራም አየር እና መግቢያውን ከያዘው አትክልት ቦታ ካሉ አበቦች የአባላዘር ብናኝ ጋር እየተጋመደ አየሩን ይገዛል፤ ሜዳውን አቋርጦ፣ እንግዳ መቀበያውን ሞልቶ፣ ከበሽታው ውጪ ሌላ ፈላጊ የሌለውን ባይተዋር እንግዳ ከሰርኑ ጋር እየተላፋ ተጠምጥሞ ይቀበላል፡፡ ከአቧራነት አድጐ አስም ይሆናል፡፡ አይን ማዝ ይሆናል፡፡ ንጥሻ ይሆናል፡፡ በተደናገረ ስበት ተጐትቶ ከወለሉ ጋር ይጣበቃል፡፡ በኋላ በፅዳቶች ተጠርጐ ሊወጣ፡፡ የመኝታ ክፍሎቹን መስታወት ያደበዝዛል፡፡ በኋላ በአስታማሚዎች መሃረብ ተገፎ ሊነሳ፡፡በዚህ ፍዝ ሂደት የፍዘቱ አካል የሆነ ቤተኛ ፊት ያላቸው አዛውንት ቅፅሩን አልፈው ገቡ፡፡ የሆስፒታሉ የቀድሞ አትክልተኛ ናቸው፡፡ እድሜ ሳይሆን አይንማዝ ነው የቀነሳቸው፡፡ አንድ ቀን እንደ ሁልጊዜያቸው ለግቢው ውበት ደፋ ቀና እያሉ ከታመሰው አካላቸው ውስጥ የተወለደ ዘልዛላ ጥላ እንደ ተንኮለኛ ደመና ጀንበራቸውን ጋረዳት፡፡
የዛሬው አመጣጣቸው ታዲያ ይሄን ሁለት ወር ሙሉ ቤት ያዋላቸውን ህመም ሊታከሙት ነው፡፡ እድሜ የቧጠጠው ቀይ ፊት አላቸው፡፡ መቧጠጡ የተወው ጠባሳ ግንባራቸው ላይ ይደምቃል እንጂ… ትላልቅ ጆሮዎች፣ የተንደላቀቀ አፍንጫ፣ ከየጉድጓዳቸው በስሱ የሚንቦጫረቁ ጭላጭ ኩሬዎች መስለው የሚንጨለጨሉ አይኖች አሏቸው፡፡
መግቢያ በሩን ተከትሎ ቶንሲላም ጉሮሮ የመሰለ፣ ሰማያዊ ቀለም የተቀቡ ጣውላዎች ያጠሩት፣ ከሁለት እርምጃ በላይ ስፋት የሌለው መንገድ እስከ ዋናው ህንፃ ድረስ ያለ መዛነፍ ተያይዟል፡፡ ሽማግሌው በሩን እንዳለፉ የስጋትም፣ የተስፋ መቁረጥም አይነት ምት ባለው አካሄድ ሳያላምጡ እንደ ዋጡት እኩይ ጉርሻ ያን “ቶንሲላም ጉሮሮ” እያወኩ ወደ “ጨጓራው” አመሩ፡፡
በመንገዱ ግራ እና ቀኝ የተዘረጋው መስክ፣ ያለፉትን ሰላሳ አመታት የተጠበቡበት ስዕላቸው ነው፡፡ ድንገት ለወራት ቢርቁት ግን የልምላሜ ውቃቢ ርቆት፣ ጋኔን ቆፍሮ በተከላቸው አመዳም ሙጃዎች እና በየሙጃዎቹ መሃል በተሰገሰጉ ስም አልባ አረሞች ተወሮ ቢያገኙት ውስጣቸውን ተስፋ መቁረጥ ገዛው፡፡ ከአይናቸው ሞራ ይልቅ የእድሜያቸውን እኩሌታ የገበሩለት “ውበት” መና ሲሆን ማየት ብርሃን የሚያስገባውን የህልውና ሽንቁራቸውን ደፈነው፡፡
የሙጃዎቹ አውራ የሆነ ፈርጣማ ሙጃ ከግንዱ ላይ አፍ አጐንቁሎ ያሽሟጥጣቸው ገባ፡፡
“እህ ሽሜው ተጠናግረህ ተመለስክ አይደል? ድሮም ብዬህ ነበር፡፡ እስቲ ያደላህላቸው አበቦች ምን ጠቀሙህ? ብናኛቸው አይኖችህን አጠፋቸው እንጂ” ብሎ ሲጨርስ፣ ሚሊዮን የሙጃ አፎች በሽሙጥ ተንከተከቱባቸው፡፡
የሽማግሌው ልቦናም በአንደበታቸው ማልጐምጐም በኩል እንዲህ እያለ ለሽሙጡ ይመልስ ጀመር፡፡
“ዝም በሉ እናንተ የእፉኝት ምሽጐች፡፡ አይኔ እያየ፣ ክንዴን ሳልንተራስ በዚህ ሁሉ በሽተኛ እይታ ላይ አትሰለጥኑም፡፡ ደሞ እንደ አበቦቹ እንዳያችሁ ትሻላችሁ?! እነሱ እኮ እንደ እናንተ አባላዘራቸውን በንቦች ተንቆ ለነፋስ አይገብሩትም፣ ከተመልካች አይኖች ጋር ለመዳራት ንፉጐች አይደሉም” ይሄን እያልጐመጐሙ ኩታቸውን አጣፍተው፣ ያቺን ድንክ አጥር ተሻግረው የቀረባቸውን ሙጃ ይነቅሉ ገቡ፡፡ እጃቸው የገባን ዘለላ ሁሉ ሲነቅሉ ቆይተው አንድ የሚድፈነፈን ድምፅ “አበቦቹን! ሰውዬ አበቦቹን ጨረስካቸው” ብሎ አቋረጣቸው፡፡
እሳቸውን የተካው ወጣቱ አትክልተኛ ድምፅ ነበር፡፡ እሳቸውን ሲያይ ትንሽ ደንግጥ እንደማለት ብሎ ከስራቸው የተከመረውን የአበባ ነዶ እና የሽማግሌውን ገፅ እያፈራረቀ ተመለከተ፡፡ ፊታቸው ላይ ከባድ ሰቆቃ አነበበ፡፡ አለሙ እንደተናደበት ሰማይ ያለ እንባቸው ከሞጨሞጩት አይኖቻቸው እንደ ስስ አቧራ ተነስቶ፣ ከታችኛው ሽፋሽፍቶቻቸው አፋፍ ላይ ወፈረና እየተድፈጠፈጠ ይወርድ ጀመር፡፡ ይሄን ሲያይ አዲሱ አትክልተኛ ደነገጠ፡፡ የአንጋፋው ሰቀቀን ከአድማስ አድማስ ተነጥፎ “ወደፊቱን” ሁሉ እንደ ዱብዳ ላጲስ ደልዞ ያዘበት፡፡
ሽማግሌው መንዘፍዘፉ ጋብ ሲልላቸው ኩታቸውን ከጣሉበት አንስተው፣ እያልጐመጐሙ ካርድ ወደሚወጣበት የህንፃውን ግድግዳ ፊንጢጣ አድርጋ ወደ በቀለች “ኪንታሮት” ክፍል አመሩ፡፡
ጥልቁ ህሊናቸው እንዲህ እያዜመ፡-
“ኮሪደሩን የመላው ይሄ መንጋ ማቃሰት
ግቢውን ያጠረው ይሄ አብይ መከሰት
ካሞገገው ጉንጬ፣ ከበረደው ልቤ እስኪ ምን ኖሮት ነው?
ልቤን የሚፈትሽ፣ ጉንጬን የሚሞዥቅ”
ብሎ በጠየቀ
የልቤ ወስጥ በረዶ ቀልጦ ያይኔን ባህር መላው
የፊቴን እንግዳነት፣ የብቻነቴን አፀድ መወዳጀት አረከሰው
አመክንዮ ሆኖ እንጂ…
ማቃሰትን ለህመሙ የሚያስተምር ማነው?
ለጥያቄው ምላሽ ይሄ መሆኑን ባምን
አይኖቼን ያን ሰሞን በርካሽ ሸጥኳቸው
ጥያቄዬን ሁሉ “መላሽ ነኝ” ባይ አፍ አባብሎ ዋጣቸው
“የሻረውም ከሳ፣ የከሳውም ሞተ” ከሆነ ተረቱ
እኛም እንሙትና እነሱም ይረቱ
***
ከሁለት ወር በኋላ…
ሽማግሌው አትክልተኛ ድሮ አበቦቹን ይኮተኩቱ በነበረበት ሰዓት ፊታቸውን የምትሸፍነው አይነት ፀዳል ከባቸዋለች፡፡ የሆስፒታሉ በረንዳ ላይ ቆመው ግቢውን ቃኙት፡፡ አንድ አይናቸው በፋሻ ተሸፍኖ፣ አንዱም ባልደረቀ ቁስል ሽፋሽፍቱ እንደ መገልበጥ ብሎ፡፡ ኩራት የሳንባቸውን አየር ተመስሎ ቁና ሆኖ ወጣ፡፡
“ግቢውን ጥሩ ይዘኸውማል አይደል’ንዴ ጃል?!!” አሉት በጐማ የአትክልት ቦታውን ውሃ ሲያጠጣ ወደነበረው ተተኪያቸው እየተጠጉ፡፡ መለስ ብሎ አያቸውና መሽቆጥቆጥ በገራው ልሳን “አመሰግናለሁ” አላቸው፡፡
“ስራው ቀላል መስሎሃል! ብታውቅ አትክልተኝነት ለሰማይ ቤትም ሁነኛ ስራ ነው፡፡ የገነትን መስክ ውበት ማን ይጠብቅ መስሎሃል? እኛው ነን፡፡ ሌላ ሌላው ከረፈፍማ ሲዘምር ነው እሚውል” ብለውት ኩፈሳ በዳበሰው እርምጃ ወደ መውጫው በር አመሩ፡፡
አዲሱ አትክልተኛ በቀኝ እጁ ያን ሰላላ ጐማ እንደያዘ ቆሞ፣ ደስ እያለው በአይኑ ሸኛቸው፡፡ እድሜ ገፍትሮት እሳቸውን ሲሆን የዚህ ወግ አዋቂነትና ኩራት ባለቤት እንደሚሆን እየተሰማው፡፡
ግቢው ከወትሮው ጭር ብሏል፡፡ ጐረቤት ያለው ወፍጮ ቤት ጁምሃን አስመልክቶ ተዘግቷል፡፡
እነዛ ተንጫጪ፣ ዘማሪ አእዋፍትም “እሽ” ባይ የሌለውን የወፍጮ ቤት ጥሬ እየለቀሙ ማዜሙን ረስተውታል፡፡ የቀን ሰራተኞቹም ምሳ እንደወጡ አልተመለሱም፡፡
ያ ተአምረኛ አቧራ ብቻ ዝቅ ብሎ እየበረረ በየኮሪደሩ ተኝቶ ያናውዛል፡፡ “ወፌ ቆመች”ን እያዜሙ ሃያል የሚያደርጉት እስኪመጡ፡፡
የሽማግሌው ንቃት የማያነበው ጉራንጉር ንቃትም በሰለሞን ወለሎ* ቅርፅ እንዲህ እያለ ይቀኛል፡፡
ዳገት፣ ሽቅብ የታየ ቁልቁለት
ቁልቁለት፣ ቁልቁል የታየ ዳገት
መገልበጥ፣ ተገልብጠው ያዩት መቆም
መቆም፣ ቆመው ያዩት መገልበጥ
መሆኑን ስላመንኩ…
ጉብታዬን ንደው ሜዳቸው ያድርጉት
መንበሬን ደልድለው ሞቶ የሚወለድ
እውነታቸውን ያስርጉበት፡፡
*ዘበት እልፈቱ (ወለሎታት)
1991 ዓ.ም ሰለሞን ደሬሳ

Read 2010 times