Saturday, 16 February 2013 13:08

ዝክረ ሰማዕታት ዘየካቲት አሥራ ሁለት

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው የ1928 ዓ.ም ወረራ፣ ከአርባ ዓመታት አስቀድሞ በዐድዋ ላይ የደረሰባት አሳፋሪ ሽንፈት የበቀል እርምጃ ነው፡፡ ወራሪው ፋሺስት ለዚህ ጦርነት ያሠለፈው ሠራዊት ብዛትና የታጠቀው መሣሪያ መጠን ሲታይ ኢጣሊያ ለመፋለም የተዘጋጀችው እኩያዋ ከሆነ አውሮፓዊ ኃይል ጋር እንጂ፣ የሠለጠነ ወታደር፣ መሣሪያም ሆነ ተሸከርካሪ ከሌለው ድሀ አፍሪካዊ አገር ጋር የሚደረግ አይመስልም ነበር፡፡ይህ በፋሺስት በኩል የተደረገ የመሣሪያና የሠራዊት ጋጋታ አሳፋሪው የዐድዋ ሽንፈት እንዳይደገም ታስቦበት በጥንቃቄ የተሰናዳ የዓመታት ዝግጅት ውጤት ነበር፡፡ ሙሶሊኒ እ.ኤ.አ መጋቢት 8 ቀን 1935 ዓ.ም ለምሥራቅ አፍሪካ የኢጣሊያ ጦር አዛዥ በጻፈው ደብዳቤ ‹‹. . . በጥቂት ሺህ ሰዎች እጥረት ምክንያት የዐድዋን ድል አጣነው፤ ያንን ስህተት ዛሬ አንደግመውም›› ብሎ ነበር፡፡


ፋሺስት ኢጣሊያ በደቡብ፣ በምሥራቅና በሰሜን አቅጣጫዎች ኢትዮጵያ ላይ ለከፈተው ለዚህ ጦርነት፤ 360 ሺህ የኢጣሊያና የቅኝ ግዛት ወታደሮች፣ 50 ሺህ መንገድ የሚገነቡ ሰራተኞችን፣ አምስት መቶ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች፣ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ታንኮች፣ 6500 ካሚዮኖችና ሞተር ሳይክሎች፣ ሶስት ሚሊዮን ቶን የሚመዝን የጦር መሣሪያ፣ 30 ሺህ የጭነት እንስሳት፣ አሠልፎ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ፋሺስቶች በዓለም የተከለከለ የኬሚካል ጦር መሣሪያ የፈሪ በትርን ተጠቅመው የጅምላ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ፋሺስቶች በገፍ የቀረበላቸውን የጥፋት መሣሪያ ሁሉ በመጠቀም ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያንን ሳይለዩ በመንገዳቸው ያገኙትን ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ እየረመረሙ አዲስ አበባ ከተማ ገብተው ግንቦት 1 ቀን 1928 ዓ.ምኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቄሣር ግዛት መሆንዋን ዓለም ይወቅልን አሉ፡፡
ፋሺስቶች በነበራቸው የመሣሪያና የሠራዊት ብልጫ ኢትዮጵያን በጉልበት ቢይዙም ክንዳችንን ሳንንተራስ አገራችንን ፋሺስት አይገዛውም ያሉ የኢትዮጵያ አርበኞች በዱር በገደል ተሠማርተው፣ የፋኖ ውጊያ በመክፈት እንዲሁም በጠላት ንብረትና መገናኛ ላይ አደጋ በመጣል በወራሪው ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሲያደርሱበት ቆይተዋል፡፡

ጠላት የገጠመው የፋኖ ውጊያ ባለመደው መልክዓ ምድር እና ሕዝብ ውሥጥ እንደመሆኑ ለመከላከል ባለመቻሉ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ወራሪዎቹ ራሳቸው በተለያየ ጊዜ ካዘጋጇቸው ሪፖርቶች ለመረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ጊዜ አንጻራዊ ሠላም አላቸው ከሚባሉት የአገሪቱ ክፍሎች መካከል በከፍተኛ ሠራዊትና መሣሪያ ይጠበቅ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ይገኝበት ነበር፡፡ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት በፋሺስቶች ላይ በድንገት የተጣለ አንድ አደጋ ያስከተለው ጉዳት፤ የዳር አገር ብቻ ሳይሆን መሐሉም ጭምር ከአርበኞች ጥቃት ነጻ ሊሆን ያልቻለ ከባቢ መሆኑን ያስመሰከረ ሆነ፡፡ ይህ ከባድ አደጋ በፋሺስቶች ላይ ሲደርስ ጠላት ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቄሣር ግዛት አካል ሆናለች ብሎ ካወጀ አንድ ዓመት እንኳን አልሞላውም ነበር፡፡
በፋሺስቶች ላይ ከደረሱ ጥቃቶች መካከል ምንጊዜም ሲታወስ የሚኖረው የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው የገነተ ልዑል ቤተመንግሥት (አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ) ውሥጥ የተጣለው አደጋ ነው፡፡
በኢጣሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ወኪል አገረ ገዢ የነበረው ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ፣የኔፕልስ ልዕልት ልጅ መውለዷን ምክንያት በማድረግ በቤተመንግሥቱ ለድሆች ምጽዋት ለመስጠት ስለፈለገ የከተማው ድሆች እንዲሰበሰቡ አዝዞ፣ ሶስት ሺህ የሚሆኑ ምንዱባኖች በቅጥሩ ውሥጥ ተኮልኩለው ነበር፡፡ ለእያንዳንዱ ደሀም ሁለት የማርትሬዛ ብር እንዲሰጥ ተወስኖ ነበር፡፡
በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ራሱ ጀነራል ግራዚያኒ፣ የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርል እንዲሁም ታላላቅ የኢጣሊያ ሹማምንት ተገኝተው ነበር፡፡


እኩለ ቀን ሲሆን ግራዚያኒ በቤተ መንግሥቱ መግቢያ ደረጃ ላይ ሆኖ ለተሰበሰበው ሕዝብ ዲስኩር ማሰማት እንደጀመረ በግቢው በር በኩል ሁለት ቦምቦች ተከታትለው ፈነዱ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ የፈነዳው ቦምብ ግን ከፍተኛ የፋሺስት ኢጣሊያ ባለሥልጣናት ከተቀመጡበት መካከል አረፈ፡፡ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች አራት ተጨማሪ ቦምቦች ተወርውረው ፈነዱ፡፡ማርሻል ግራዚያኒ ጀርባውን ቆስሎ ወደቀ፣ የኢጣሊያ አየር ኃይል አዛዥ የነበረው ጀነራል አውሬሊዮ ሊዮታ ቀኝ እግሩንና ቀኝ ዐይኑን አጣ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጉይዶ ኮርቲሲ እና ሌሎች ኢጣሊያውያን እንግዶች በፈንጂው ተጎዱ፡፡ ፍንዳታው ጋብ ሲል ከንቲባ ኮርቴሲ ከወደቀበት ተነስቶ የተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ላይ በማነጣጠር የመጀመሪያውን ጥይት ተኮሰ፤ የፋሺስት ፖሊሶችም ምሣሌውን በመከተል ሶስት ቀን የሚቆየውንና መላውን ከተማውን ያዳረሰውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከዚያው ከቤተ መንግሥት ውሥጥ ጀመሩ፡፡
በደረሰበት የፈንጂ አደጋ ማርሻል ግራዚያኒ በ350 ፍንጣሪዎች ቆስሏል፡፡
የካቲት 12 ቀን ስለ ደረሰበት አደጋ ግራዚያኒ ለኢጣሊያ ቅኝ ግዛቶች ሚኒስትር ባስተላለፈው ቴሌግራም ‹‹ ዛሬ ጠዋት በ5 ሠዓት ግቢ ተገኝቼ ነበር፡፡
ታላላቅ መኳንንት፣ የኦርቶዶክስና የእስልምና ሀይማኖት መሪዎች ሁሉ ተሰብስበው ነበር . . . 6 ሠዓት ሲሆን አሥር የብሬዳ የእጅ ቦምቦች ካልታወቁ ሠዎች ተጣሉብን፡፡
በዚህም ምክንያት ሠላሳ ሰዎች ቆሰሉ፡፡ በኔ መቁሰል ምክንያት አገሪቱን የተከበሩ ፔትሬቴ እና ጀነራል ጋሪባልዲ እንዲጠብቁ አድርጌአለሁ፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ ጸጥታም አላፊ አድርጌያቸዋለሁ›› ብሏል፡፡ ግራዚያኒ በሌላ ጊዜ ወደ ሮማ ባስተላለፈው ቴሌግራሙ የተደረገበትን የመግደል ሙከራ አስመልክቶ ሲጽፍ ‹‹የተጣለብኝ ቦምብ ቢያንስ 18 ይሆናል፡፡
አሳባቸው ባንድ ፈንጂ እኔን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም የመንግሥቱ ባለሥልጣኖች ጠራርጎ ለማጥፋት ነበር . . .
በተጣለብኝም ቦምብ 250 ፍንጥርጣሪ ብረቶች ከገላዬ ወጥተዋል፡፡ እነዚህንም ፍንጣሪዎች ለታላቅ መታሰቢያነት አስቀምጫቸዋለሁ›› ብሏል፡፡
ለዚህ በግራዚያኒ እና በሌሎች የፋሺስት ኢጣሊያ ባለሥልጣኖች ላይ ለተጣለ አደጋ የኢጣሊያ ፖሊሶች (ካራቢኔሪ)፣ ባለ ጥቁር ሸሚዞችና ወታደሩ የሰጡት ምላሽ ከማጥቃት ወሰን፣ ከውጊያ ደንብ እና ከጭካኔ ገደብ ያለፈ አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ ነበር፡፡ በጊዜው አዲስ አበባ ውሥጥ ይሠራ የነበረ ዶክተር ላዲስላስ ሳቫ የተሰኘ ሀንጋሪያዊ ሐኪም የተመለከተውን የፋሺስቶች የግፍ ሥራ እንዲህ አስታውሶ ነበር:-
‹‹ምን ዓይነት አጨካከን ነው? ደም እንደ ውሃ ሲፈስ በየመንገዱ ላይ ያየሁት የዚያን ጊዜ ነው፡፡ የወንዶች፣ የሴቶችና የልጆች ሬሳ በያለበት ተኝቷል፡፡ ወዲያው ከባድ የቃጠሎ ጭስ ተነስቶ ከተማዋን አጨለማት፡፡ የሕዝቡ ቤት ከተፈተሸ በኋላ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ ቤቱ በእሣት ይቃጠላል፡፡ ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም በቤንዚንና በዘይት ይጠቀሙ ነበር፡፡

ሰዉ እሣቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየስ ይገድሉታል . . . መኪናዎች እየዞሩ ሬሣ ያነሳሉ፡፡ ባለ ጥቁር ሸሚዞች ወደ ኢጣሊያ ባንክ እየገቡ ሌሊት የሠረቁትን ብርና ወርቅ ያስቀምጣሉ፡፡ ዘረፋው በቤት ውሥጥ ብቻ አልነበረም፡፡ ከሚገድሏቸው ሴቶች አንገትና ጆሮ ላይ የሚገኘውን ወርቅ ሁሉ ይወስዱ ነበር . . . ሕክምና በምሠራበት ቦታ ብዙ ኢጣሊያኖች ይመጡ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ኢጣሊያዊ ምን ያህል ሰው እንደገደለ በኩራት ይናገራል፡፡ አንዳንዶች 80 ገደልኩ ሲሉ ሌሎች 100 እንደገደሉ ይናገራሉ፡፡ አንድ ኢጣሊያዊ ብቻ እያዘነ እኔስ የገደልኩት ሁለት ሰው ብቻ ነው ሲል ሰምቼዋለሁ፡፡ . . . የማልረሳው ነገር፤ ግድያው እንዲቆም በተደረገበት ጊዜ ታላቁ ግራዚያኒ ለሕዝብ በማዘን ግድያው ይቁም ብለዋል ተብሎ የተነገረው ነው፡፡ ግሩም አዘኔታ!››
ዐርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ቀትር ላይ በግራዚያኒ ላይ ቦምብ የወረወሩት አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ኤርትራውያን ወጣቶች ናቸው፡፡ የዚህ አደጋ ቀያሽ ሆኖ የሚቆጠረው አብርሃ ደቦጭ እና ጓደኛው ሞገስ አስገዶም የኢጣሊያ ወረራ ሲጀመር አዲስ አበባ በሚገኘው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አብርሐ ደቦጭ ቀደም ብሎ የኢጣሊያ ቋንቋ ተምሮ ስለ ነበር ከወረራው በኋላ አዲስ አበባ ባለው የፋሺስት ፖለቲካ ቢሮ ተቀጥሮ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አብርሃ ደቦጭ ይህ ስራው የፋሺስቶችን የግፍ አገዛዝና የዘር መድልዎ አሠራር በቅርብ ለማወቅ ስላስቻለው ጉዳዩን ከሞገስ አስገዶም እና ስብሐት ከተባለ በጀርመን ቆንስላ ከሚሰራ ጓደኛው ጋር ይወያይበት ነበር፡፡

ይህ ሁኔታም በፋሺስቶች ላይ እንዴት አደጋ መጣል እንዳለባቸው እንዲያውጠነጥኑ አድርጓቸዋል፡፡ አብርሐ ደቦጭ ወደፊት ላቀደው ጸረ ፋሺስት ጥቃት እንዲረዳው በባዶ እግሩ ከአዲስ አበባ 10 እና 15 ኪሎሜትሮች እየወጣ በጫካ ውስጥ ፈንጂ ለመወርወር የሚያስፈልገውን ልምምድ ያከናውን ነበር፡፡
አብርሐ ደቦጭ የቤት ዕቃዎቹን ሸጦ ባለቤቱን ደግሞ ወደ ደብረ ሊባኖስ ወስዶ በማስቀመጡ በፋሺስቶች ላይ አደጋ የሚጥልበትን ቀን አስቀድሞ የሚያውቀው ይመስላል፡፡ አብርሐ ደቦጭ በዚህ ዝግጅት ላይ እያለ ግራዚያኒ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ድሆችን በመጥራት ምጽዋት ለመስጠት መወሰኑ ተሰማ፡፡ የካቲት 12 ቀን አብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከእንቅልፋቸው የነቁት ማልደው ሲሆን፣ የፋሺስት ኢጣሊያን ባንዲራ የሚኖሩበት ቤት ወለል ላይ በጦር ሰፍተውና የእጅ ቦምቦቻቸውን አዘጋጅተው ወደ ገነተ ልዑል ቤተመንግሥት አመሩ፡፡ በሥፍራው እንደደረሱም ወደ ዒላማቸው በድንጋይ ውርወራ ርቀት ያህል ቀረብ ካሉ በኋላ አመቺ ጊዜ ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ስድስት ሰዓት ሆኖ ማርሻል ግራዚያኒ ንግግር ማድረግ ሲጀምር አከታትለው የእጅ ቦምቦችን ወረወሩበት፡፡ ፍንዳታው ያስከተለው ረብሻ ከመረጋጋቱና ፋሺስቶችም የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት፣ አብርሀ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በቤተ መንግሥቱ የጓሮ በር ሹልክ ብለው ለመውጣት ችለዋል፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የተጣለውን አደጋ ተዋናዮች አብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም መሆናቸውን ተረድቶ ስለነበር ‹‹አማጽያኑን›› ለሚይዝ ማንኛውም ሰው የ10 ሺህ ሊሬ ሽልማት እንደሚሰጥ አውጆ ነበር፡፡ አብርሃምና ሞገስ ግን መላውን የአዲስ አበባ ነዋሪ ያብረከረከው ጅምላ ጭፍጨፋ ሳይነካቸው ከመናገሻ ከተማው በሰላም ወጥተው ደብረ ሊባኖስ ለመድረስ ችለው ነበር፡፡ በዚያ ከደረሱ በኋላ በራስ አበበ አረጋይ ከሚመሩት የሸዋ አርበኞች ጋር መቀላቀላቸው ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ ኤርትራውያኑ ወጣቶች ከኢጣሊያኖች ጋር ይሠሩ ስለነበረ የሸዋ አርበኞቹ እምነት ስላልጣሉባቸው ወደ ሱዳን ለመሄድ ፈቃድ ጠይቀው እንደተሰናበቱ ታውቆ ነበር፡፡

ሁለቱ ወጣቶቹ በጎጃም በኩል አድርገው ወደ ሱዳን ለመግባት ጥቂት ሲቀራቸው በድንበር አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡ የየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ጅምላ ጭፍጨፋ ከደረሰ ከአራት ዓመታት በኋላ ለብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደት፣ ስቃይና እልቂት ምክንያት የነበረው የፋሺስት ኢጣሊያ የግፍ አገዛዝ የሚያከትምበት ጊዜ መጣ፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው እንደ አውሬ የሚታደኑብት የጨለማ ጊዜ አልፎ ግፈኞቹ ፋሺስቶች በተሸናፊነትለኢትዮጵያ አርበኞችና ለእንግሊዝ ሠራዊት እጃቸውን የሚሠጡበት ጊዜ ሲደርስ እውነተኛው የነጻነት ደወል በመላው ኢትዮጵያ አስተጋባ፡፡የወደቀውና የተዋረደው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከአምስት ዓመታት በኋላ እንደገና በኩራት ከፍ ብሎ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ሲውለበለብ፤ የፋሺስት ባንዲራ፣ የፋሺስት የቀበሮ እና የአሞራ አርማና ሐውልት እየተቀደደ እና እየተነቀለ የትም ተጣለ፡፡
አዲሱ የነጻነት ዘመን የተጀመረውም በአምስቱ የጠላት ወረራ ዓመታት ለውድ አገራቸው ነጻነትና አንድነት ሲፋለሙ የወደቁ ወይም ተይዘው በግፍ እየተገደሉ እንደ ጉድፍ የትም የተጣሉ ኢትዮጵያውያን አጽም በክብር በማሳረፍ ነበር፡፡ አብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶምም ተገድለው የተጣሉበት በዳር አገር ያለ ሥፍራ በጠቋሚ ስለታወቀ አጼ ኃይለ ሥላሴ የወጣቶቹ ቅሪተ አካል ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን እንዲመጣ አድርገው፣ ኦፊሴላዊ የቀብር ሥርዓት እስኪደረግለት ድረስ አጽማቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል በጊዜያዊነት እንዲቀመጥ ተደርጎ ነበር፡፡
እሁድ ሚያዝያ 23 ቀን 1941 ዓ.ም ጧት የአብርሓ ደቦጭን እና የሞገስ አስገዶምን አጽም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመውሰድና በዘላቂነት በክብር የማሳረፍሥነ ሥርዓት ተጀመረ፡፡ የሁለቱን አርበኞች ቅሪተ አካል የያዘው ሣጥን የህይወት መስዋዕትነት በከፈሉበት በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሸፍኗል፡፡
ከአምስቱ ዓመት ጸረ ፋሺስት የአርበኝነት ውጊያ መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት ራስ አበበ አረጋይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ በሚደረገው ጉዞ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ አጀቡ የካቲት 12 ቀን ለተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ የቆመው ሐውልት አጠገብ ሲደርስ በመቆም አክብሮቱን ገልጾ አለፈ፡፡
አጽሙና የተከተለው ብዙ ሺህ ሕዝብ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲደርስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ፊታውራሪ ደምሴ እና የኢትዮጵያ እና የኤርትራ አንድነት ማሕበር ሊቀመንበር አቶ ክፍለ እግዚ ይህደጎ የአብርሐ ደቦጭን እና የሞገስ አስገዶምን ጀብዱ የሚያወሳ ንግግር አድርገው ሲጨርሱ፣ አቡነ ፊልጰስ ጸሎት አድርገው የሥነ ሥርዓቱ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
አብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በጊዜው በኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ሥር ከነበረችው ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የነጻነት አየርን ተንፍሰው፣ ጊዜው የፈቀደውን ዘመናዊ ትምህርት ያለ አድልዎ ለመከታተል ችለዋል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ኤርትራውያን ከኢጣሊያ ጎን ተሰልፈው ከፋሺስቶች ያልተናነሰ ጥቃት በኢትዮጵያውያን ላይ በሚያደርሱበት ጊዜ፤ አብርሐ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ግን ከአገራቸው ሸሽተው የመጡት የኢጣሊያ የግፍ አገዛዝ ቀንበሩን በባለውለታቸው ኢትዮጵያ ላይ ሲጭን መመልከት ባለመቻላቸው፣ በፋሺስት መሪዎች ላይ ይህንን ከባድ አደጋ እንዲጥሉ አድርጓቸዋል፡፡
ወጣቶቹ በቤተ መንግሥቱ የጣሉት አደጋም ፋሺስቶች በኢትዮጵያ ሰፍኗል ያሉት ጸጥታና ሰላም የይስሙላ እንደነበረ ለመላው ዓለም ከማሳየቱም በላይ ለኢጣሊያውያን የዳር አገሩ ብቻ ሳይሆን መሐሉም ጭምር አደገኛ መሆኑን ያሳዩበት ተጨባጭ ምሳሌ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ ለዚህ አደጋ በፋሺስቶች በኩል የተሰጠው ምላሽ ፍጹም ጭካኔ የተሞላበት ቢሆንም፤አብርሐም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የጣሉት አደጋ በአምስቱ ዓመት ጸረ ፋሺስት ትግል መዘክር ውሥጥ በጠላት አመራር ላይ በቅርብ የደረሰ ብርቱ ጥቃት ተደርጎ ስለሚወሰድ ታሪክ ለዘላለም ሲያስታውሰው ይኖራል፡፡

 

Read 4410 times