Saturday, 16 February 2013 13:04

“ጫካ ውስጥ ካሉት ሁለት ጅግራዎች ይልቅ በእጅ ያለችው ወፍ ትሻላለች”

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

    ግርማ በዳዳ - ከጅማ እስከ ደቡብ አፍሪካ
ግርማ በዳዳ ላለፉት ሃያ ሁለት አመታት ብዙ ነገሮችን ለመሆን፣ ብዙ ነገሮችን ለማድረግና ብዙ ነገሮችም እንዲኖሩት በህልሙም በእውኑም ሲመኝ ኖሮአል፡፡ ከእነዚህ እጅግ በርካታ ምኞቶቹ ውስጥ አንዷ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ አሁን ከህልም ተራ ወጥታለች፡፡
ደቡብ አፍሪካ አሁን ለግርማ ተራ ምኞትና የህልም እንጀራ አይደለችም፡፡ አሁን በእጅ የምትዳሰስ፣ በዓይን የምትታይና በጆሮ የምትሰማ ሆናለታለች፡፡
ደላላው ቪዛ የተመታበትን ፓስፖርቱንና የአውሮፕላን ትኬቱን ሲሰጠው በማግስቱ “በዝነኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ” ሽው እልም ይልባትና ሁሉም ነገር እውን ይሆናል፡፡ ያኔ “እሰይ ስለቴ ሰመረ!” የሚለውን ዘመን የጠገበ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ዜማ ሞቅ አድርጐ እየዘፈነ የሚችለውን ዳንኪራ ማስነሳት ብቻ ነው፡፡ በዚህ ታላቅ ምኞቱና በምኞቱ እውን መሆን መካከል ባለው ቀጭን መስመር ላይ ተደንቅሮ፣ የበለጠ ቀልቡንና ልቡን የነሳው ግን ከደላላው ጋር የተቀጣጠሩባት ሰአት አልደርስ ማለቱ ብቻ ነበር፡፡
ግርማ በህይወቱ ቀጠሮ እንዲህ ረዝሞበት፣ አንዱ ደቂቃ አንድ ድፍን ቀን ሆኖባት አያውቅም፡፡ ከወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጠና በተቀጣጠሩባት ካፌ አካባቢ ላይ ታች እያንዣበበ ሰአቱን አሁንም አሁንም ቢመለከትም ፈቅ የሚለው በጥቂት ደቂቃዎች ብቻ እየሆነበት መረጋጋት አቃተው፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ታዲያ ጊዜን መቆጣጠር፣ ጊዜን እርሱ እንደፈለገው ወደፊትና ወደ ኋላ መዘወር የሚያስችል አንዳች የተለየ መለኮታዊ ሀይል በኖረኝ ብሎ በእድሜ ዘመኑ ከተመኛቸው ህልቁ መስፈርት ከሌላቸው ምኞቶች የተለየውን ምኞት የተመኘው፡፡
ዳቦ ሁሌም ቢሆን ወደ መሬት የሚወድቀው ማር በተቀባበት ጐኑ ነው እንደሚባለው፣ ግርማ የቀጠሮው ሰአት እንዲያጥርለትና በፍጥነት እንዲደርስለት በእጅጉ አጥብቆ ቢመኝም ጊዜ የሚጓዘው ግን እንደ ሰዎች ምኞትና ፍላጐት ሳይሆን በራሱ ዛቢያ ላይና በራሱ የተፈጥሮ ኡደት ብቻ ነውና ከደላላው ጋር በዚያች ትንሽዬና ጠባብ ካፊቴሪያ የተገናኙት ያው የቀጠሯቸው ሰአት እንደ ደረሰ ብቻ ነበር፡፡
ደላላው ያዘዘውን ሻይ ፉት እያለ የግርማን ጉዳይ ለማስጨረስ የገጠመው ከፍተኛና እልህ አስጨራሽ ትግል ለከፍተኛ ወጪ ስለዳረገው ኪሳራ ላይ ቢወድቅም የገባለትን ቃል ለመጠበቅ ሲል ብቻ በኪሳራም ቢሆን ጉዳዩን አስጨርሶላት እንደመጣ በሰፊው ተረከለት፡፡
ግርማ ግን ቀልቡን ሰብስቦና ተረጋግቶ ማዳመጥ አልቻለም፡፡ የቀረበለትን ሻይ ሳይቀምስ በማንኪያው ብቻ እየተጫወተ የሚያስበው ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ከች ስለሚልባት ደቡብ አፍሪካ ብቻ ነበር፡፡ አንዳንዴ ቀና ብሎ ደላላውን ሲያየው ያስበው የነበረው ደግሞ “ይሄ ደላላ አሁን ይሄን ሁሉ ነገር ከሚንዘባዘብልኝ ለምንድን ነው ዝም ብሎ ፓስፖርቴንና ትኬቴን የማይሰጠኝ?” እያለ ነበር፡፡
ግርማ ከዚህ ሀሳቡ ድንገት የባነነው፣ ደላላው ምንም እንኳ ያን ያህል ቢጥርና ከፍተኛ ገንዘብ ቢያወጣም የደቡብ አፍሪካ መግቢያ ቪዛ ማግኘት እንዳልቻለ ሲነግረው ነበር፡፡ ግርማ የብራ መብረቅ የወረደበት ያህል ክው ብሎ በመደንገጡ ቃል መተንፈስ እንኳ አልቻለም፡፡ አፉን በሰፊው ከፍቶና አይኑን ደላላው ላይ ተክሎ ቀረ፡፡
ግርማ አለመጠን መደንገጡን ያስተዋለው ደላላው አንገቱን ወደፊት አስግጐና የግርማን ሁለት እጆች ይዞ ያገኘው ቪዛ ወደ ዚምባቡዌ የሚያስገባ ብቻ እንደሆነና ዚምባብዌ ከደረሰ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያስገባው ሰው እንዳዘጋጀለት በመግለጽ ሊያረጋጋው በሞከረ ጊዜ ነበር፡፡
ግርማ የደቡብ አፍሪካ ጉዞው በድል ተጠናቀቀ ብሎ እርግጠኛ በሆነበት የመጨረሻዋ ደቂቃ፣ ደላላው የነገረው ነገር ጨርሶ ያልጠበቀውና ያልገመተው ስለሆነበት የደነገጠው ድንጋጤ ከባድ፣ የሰማውም ስሜት እጅግ መራራ ነበር፡፡ ደላላው በግራም ይሁን በቀኝ ብሎ ደቡብ አፍሪካ እንደሚያስገባው እየነገረም እየማለም ትንሽ ካረጋጋው በሁዋላ ግን ቻይናዎች “ለስህተት ትንሽ ባዶ ቦታ ይኑርህ፡፡” የሚሉትን አባባላቸውን አስታውሶ እሱኑ ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ቻይናዎች ይህን የሚሉት የሰው ልጅ ከስህተቱ ይማራል የሚለውን የዘመናት አነጋገር አሻሽለውት ነው፡፡
ግርማም “እኔ ነኝ ወይስ ደላላው ለስህተት ትንሽዬ ክፍት ቦታ ያኖርነው?” እያለ ማሰላሰል የጀመረው “ስህተት የሰራነውና ከስህተታችንም መማር ያለብን እኔ ነኝ ወይስ ደላላው?” የሚለውን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በማሰብ ነበር፡፡
ደላላው ቀደም ብሎ እንዳስረዳው ያለምንም ችግር ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚያስገባው፣ ካልፈለገም ደግሞ የዚምባብዌ የመግቢያ ቪዛ ላገኘበት የድካም ዋጋውን አስቦ ተራፊውን ገንዘብ ሊመልስለት እንደሚችል ፍርጥም ብሎ ሲነገርው፣ ግርማ ልቡ በመንታ መንገድ ላይ ቆሞ መዋለል ጀመረ፡፡
“እሺ ዚምባብዌ ድረስስ ሄድኩ! ከዛ በሁዋላስ እንዴት ነው? ምኑን ከምን አደርገዋለሁ?” አለው ግርማ፡፡
“ነኧገይ ነመቢያኮቲ” (ስማኝማ ያገሬ ልጅ ለማለት ነው) ያለው እድል ሁለት ነው ብዬሀለሁ፡፡ ዚምባብዌ ከደረስክ በሁዋላ የእኔ ጓደኞች ይቀበሉህና ወደ ደቡብ አፍሪካ በመኪና ያሻግሩሃል፡፡ ለዚህ ተጨማሪ ወጪ ድንቡሎም አታወጣም፡፡ አይ ካልክ ደግሞ የቪዛና የድካሜ ወጪ ይታሰብና የተረፈ ገንዘብ ካለ እመልስልሃለሁ፡፡ ዚምባብዌ ከደረስክ በሁዋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ራስህን ችለህ በራስህ ወጪ ትገባለህ፤ ካላስ! ምርጫው የራስህ ነው” አለው ደላላው፤ ውሳኔህን አሁኑኑ ንግረኝ በሚል አይነት ከተቀመጠበት እንደመነሳት እያለ፡፡
ግርማ የሚተርፍ ገንዘብ ካለ ተቀብሎ ምኑንም ከማያውቀው ሀገር ዚምባብዌ ተነስቶ በራሱ ጥረት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ከመሞከር ይልቅ ደላላው ያቀረበለትን የመጀመርያውን አማራጭ አምኖ መቀበል የተሻለ እንደሆነ ቀልቡ ቢነገርውም፣ ዝም ብሎ በቀላሉ ተስማማ እንዳይባል ብቻ ከደላላው ጋር “ከሄድኩ በሁዋላ እዚያ ከማላውቀው የሰው ሀገር ላይ ብትከዳኝስ? ገንዘብህን እንደሆነ አንዴ ቆጥረህ ወስደሀል እኮ!” እያለ መከራከር ጀመረ፡፡
ደላላው የተሠማራበት የድለላ ስራ ባለው ለየት ያለና አስቸጋሪ ባህሪ የተነሳ ሁሌም ቢሆን በሰዎች ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ ስላደረገው ውስጡን የቅሬታ ስሜት ቢሰማውም በግል የሞራል አቋሙ፣ በሚከተለው ሀይማኖት የስነምግባር መርህና አብሮ አደጐቹ የሀገሬ ልጆች ለሚላቸው ሰዎች ባለው ልዩ የቅርበትና የወገንተኝነት ስሜት የተነሳ የገባውን ቃል እስከመጨረሻው ድረስ እንደሚጠብቅ የአምላክን ስም ደጋግሞ እየጠራ በመሃላ አረጋገጠለት፡፡
ግርማ ደላላውን ያመነውና ልቡም ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ የተረጋጋው ግን ስለማለለት ሳይሆን የገባውን ቃል ሳይጠብቅ ቢቀርና ግርማ በማያውቀው የባዕድ ሀገር ለእንግልትና ለአደጋ ቢጋለጥ፣ ወሬው የፈለገውን ያህል ቢዘገይ እንኳን መቼም ቢሆን መሰማቱ ስለማይቀር ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ስለሚያውቅ፣ በተጨማሪም በእንዲህ ያለ ሁኔታ ወደ ውጪ ሊልካቸው የሚችል ሌሎች ሰዎችን ስለማያገኝ፣ ከዚህ አይነቱ ስራው ውጪ እንደሚሆን ከነገረው በሁዋላ ነበር፡፡
ለደላላው የእምነት ነገር በእርግጥም ልክ “የአይነ ስውር ሚስት በኩልና በሜካፕ መኳኳል አያስፈልጋትም፡፡” እንደሚባለው አይነት ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የቱንም ያህል በኩልና በሜካፕ ተጊያጊጠን ያማርንና የተዋብን መስለን ብንቀርብ የማታ ማታ እውነተኛው መልካችን ተገልጦ መታየቱ መቼም ቢሆን እንደይቀር በሚገባ ያውቀዋል፡፡ እናም ለግርማ እንዲህ ብሎ የነገረው ከምሩ ነበር፡፡ የልብ እምነቱና የተግባር አቋሙ ይሄና ይሄው ብቻ ነበረ፡፡ ይህ ጉዳይ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ከተጠናቀቀ ከሶስት ቀናት በሁዋላ ግርማ በዳዳ ቤተሰቦቹንና ወዳጅ ዘመዶቹን ተሰናብቶ ወደ ሀራሬ ዚምባብዌ አቀና፡፡ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ ድረስ አብራው በመሄድ በለቅሶ እየተነፋረቀች የሸኘችው ፍቅረኛው አበበች ብቻ ነበረች፡፡
ሀራሬ እንደደረሰ ጂማ ከተማ ውስጥ ተወልደው እንዳደጉና የደላላው ዘመዶች መሆናቸውን የነገሩት ሁለት ወጣቶች ደላላው በነገራቸው መረጃ መሠረት አውሮፕላን ማረፊያው ድረስ በመምጣት ሲቀበሉት አይኑን ማመን አቅቶት ነበር፡፡ ደላላው በእርግጥም የእምነትና የአቋም ሰው ነበረ፡፡ የገባውን ቃል ጠብቆና አክብሮ በቃሉ ተገኝቷል፡፡
የተቀበሉት ሁለቱ ወጣቶች ይዘውት በመጡት ነጭ ማዝዳ ፒክአፕ መኪና አሳፍረው በሀራጌ ከተማ ሰሜን ምስራቅ ጠርዝ አካባቢ በሚገኘው በርካታ የሰርቪስ ክፍሎች ባሉት ባለአንድ ፎቅ ቤት ውስጥ አሳረፉት፡፡ ቤቱ የመኖርያም የንግድ መጋዘንም አድርገው የሚገለገሉበት ነበር፡፡ ግርማ በዚህ ግቢ ውስጥ አንድ ሳምንት ለሚሆን ጊዜ አብሯቸው ሲቆይ ሁለቱ የጅማ ልጆች እሳት የላሱ ዲታ ነጋዴዎች መሆናቸውን ተገንዝቧል፡፡ ይህም ሁኔታ እሱም እንደ እነሱ ለመሆን ያለውን ከፍተኛ ጉጉት አለመጠን እንዲቀሰቀስና እንዲጨምር ስለአደረገው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚገባበትን ቀን ያራቀበት ሲሆን ትዕግስትም አሳጥቶት ነበር፡፡
ሀራሬ ደርሶ እነሱ ጋር ካረፈ ከዘጠኝ ቀናት በሁዋላ ግን ልክ እንደ እሱ ሁሉ ከአዲስ አበባ፣ ከደብረ ማርቆስ፣ ከባህር ዳርና ከሁመራ መጥተው ሀራሬ የሚኖሩ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ከተቀበሏቸው አስራ አንድ ወንዶችና አራት ሴት ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድ ቶዮታ ሚኒባስ ተሳፍሮ ዚምባብዌን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ወደምታዋስነው የድንበር ከተማ ዝቪሻቫኔ ተጓዘ፡፡
የደቡብ አፍሪካን ድንበር ጨለማን ተገን በማድረግ ከተሻገሩ በሁዋላ ልዊዝ ትሪቻርድንና ቤላቤላ የመሳሰሉትን የደቡብ አፍሪካ ከተሞች በማቋረጥ የደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ፕሪቶሪያ ለመግባት ቻለ፡፡
(ይቀጥላል)

 

Read 1791 times