Saturday, 16 February 2013 13:18

“ምን…አለና ነው!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

“እግርህ እስኪነቃ ብትሄድ እኔን የመሰለች አታገኝም”
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ጣልያኖች ምን ይላሉ አሉ መሰላችሁ…“የቼዝ ጨዋታ ሲጠናቀቅ የወታደሩም የንጉሡም ጠጠሮች የሚከተቱት አንድ ሳጥን ውስጥ ነው፡፡”
እናማ…አንድ ሳጥን ውስጥ እንደምንገባ እየዘነጋን ለራሳችን የማይገባ የተጋነነ ግምት እየሰጠን እንዳይሆን፣ እንዳይሆን የሚያደርገን በዝተናል፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ዘንድሮ አስቸጋሪ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ምን መሰላችሁ… ለራሳችን ከልክ በላይ የሆነ ቦታ የምንሰጥ ሰዎችን ማስታመሙ!ከዚህ በፊት ያነሳትን አንዲት ነገር ልድገማትማ…ሰውየው ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ የተከበሩ ምሁር ናቸው፡፡ ታዲያላችሁ… የሆነ ‘ግሮሰሪ’ ውስኪያቸውን እየገጩ ሳለ አጠገባቸው እየጠጣ ከነበረ ታዋቂ ድምጻዊ (የምር ታዋቂ) ጋር በሆነ ነገር ይጋጫሉ፡፡ እናላችሁ ታዋቂው ድምጻዊ የራሱን ስም እየጠቀሰ “እንዴት እኔ ማን እንደሆንኩ አታውቅም!” ምናምን ነገር እያለ ‘ሲያብድ’ ፕሮፌሰሩ “ማነህ ኳስ ተጫዋች ነህ…” ምናምን ሲሉት ጦዘ ይባላል፡፡
እናማ…“እኔ ማን እንደሆንኩ እንዴት አታውቅም… አይነት ነገር እየበዛ አይመስላችሁም! ገና የዳገቱን አንድ ሀምሳኛ የሚሆነውን እንኳን ቧጥጠን ከፍ ሳንል ተራራው ጫፍ ላይ የደረስን የሚመስለን ቁጥራችን እየበዛ ነው፡፡
ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…እዚህ አገር ሚጢጢ የሆነች አድናቆትም በማይሆን ሁኔታ እየተባዛች “ጥሩ ሥራ ነው፣ በርታ/በርቺ…” የሚለውን አስተያየት ሁሉ የስኬት ጫፍ አድርገን እየወሰድን በሁሉም ነገር በተዋጣላቸው ሰዎች ብዛት የሚስተካካለን ያለ አይመስልም፡፡ እንደ ልብ በየዓረፍተ ነገሩ የሚሰገሰጉት ቅጽሎች ብዛት በእውነትና በህልም መካከል ያለውን መስመር እያጠፉት በምንሠራቸው ሥራዎች እየተሻሻልን እንዳንሄድ እያደረጉን ነው፡፡
እሷዬዋ በጣም ቆንጆ ነኝ ባይ ነች፡፡ ቆንጆ አይደለችም ባዮችም ብዙ ናቸው፡፡ እሷም… “አንድ ሰው ቆንጆ ነሽ ቢለኝ ምን ሀጢአት አለው?” ብላ ስትጠይቅ አንዱ ምን ብሎ መለሰላት መሰላችሁ…“ቆንጆ ነሽ ማለት ሀጢአት ብቻ ሳይሆን እንዲህ የሚለው ሰው ሀሰተኛ ምስክርነት በመስጠት ወንጀለኛ ነው” ብሏት አረፈ፡፡ ለነገሩ እዚህ አገር የቁንጅና ምልክታችን ነጮቹ ያወጧቸው መለኪያዎች ናቸው፡፡ እናማ፣ በእነሱ መለኪያ…
አፍንጫ ጎራዳ ከወደደልህ
እኔም አፍንጫዬን ልጎረድልህ፣
ብሎ ዘፈን አይሠራም፡፡ ልክ ነዋ… አፍንጫ ጎራዳነት በፊልም ላይ ዋና ገጸ ባህሪይ ሆኖ ለመጫወት አይሠራማ! “እንዴት ያለች ጉርድርድ ያለች ደመ ግቡ መሰለችህ…” ምናምን ማለት አይሠራማ! (የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የዚህ አገር የፊልም ‘ፍልስፍና’ አንዳንዴ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ እንዴት ነው በየፊልሙ ላይ መሪ ሴት ገጸ ባህሪያት በሙሉ መልከ ቀና የሚባሉት ብቻ የሚሆኑት! ለዚህም ይመስለኛል ብዙ ሴት ገጸ ባህሪያት ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ነገር የሚሆኑብን፡፡ በነገራችን ላይ ሴት ገጸ ባህሪያት አመራረጥ ላይ ስላሉ ‘ያልተጻፉ መስፈርቶች’ የምንሰማቸው ነገሮች ሁሉ እውነት ከሆኑ የምር አስቸጋሪ ነው ማለት ነው፡፡
ሴት ዳይሬክተሮችና ፕሮዲዩሰሮችን ያብዛልንማ! ያኔ ምናልባት ሰልካካም፣ ጎራዳም እኩል ሚዛን ላይ ይቀመጣሉ፡፡)
እናላችሁ…እዚህ አገር ለራስ የሚሰጥ ከልክ በላይ የሆነ ግምት ብዙ ነገሮች እንዳንግባባ እያደረገን ነው፡፡
እሱና እሷ ትንሽ ጊዜ አብረው ቆይተው ይጣላሉ፡፡
እሱ ነው እንግዲህ “ብዙም መልክ ስሌለሽ አልፈልግሽም…” ያላት፡፡ እናላችሁ… እሷዬዋ “እግርህ እስኪነቃ ብትሄድ እኔን የመሰለች አታገኝም፣” ትለዋለች፡፡ እሱዬው ምን አላት መሰላችሁ… “አንቺን ካልፈለግሁኝ፣ የአንቺ አይነት ምን ታደርግልኛለች!” (እንትናዬዎች…ለራስ ከፍተኛ ግምት ሰጥቶ ከመፎከር በፊት የሚሰጠውን መልስ አስቡማ!)እናላችሁ…ትወና ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት በከፍታው ዳሸን ተራራን ሊስተካከል ምንም አይቀረው፡፡ አንድ ተዋናይ ከአንድ የመድረክ ላይ ትርኢት በኋላ ለጓደኛው ምን ይለዋል… “የምሞትበትን ሲን ስሠራ ሰዉን ሁሉ በዕንባ አራጨሁት አይደል!” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝዬው ምን ቢለው ጥሩ ነው…“ቀላል አራጨኸው እንዴ! ግን ሰዉ በዕንባ የተራጨው ፊልሙ ላይ በመሞትህ ሳይሆን የእውነት ባለመሞትህ ነው፡፡”ይሄ ለራስ ከልክ በላይ የሆነ ግምት መስጠት በተለይ በስነ ጥበብ፣ በስነ ጽሁፍ አካባቢ በብዛት ይታያል፡፡

በአንዲት የግጥም መጽሐፍ “ደግሞ፣ እዚህ አገር ምን ገጣሚ አለና ነው!” የምንል፡ አንዲት ፊልም ላይ ብቅ ባልን ቁጥር “አሁን እዚህ አገር ተዋናይ አለ!” የምንል፣ የሆነች ጋዜጣ ላይ አንድ፣ ሁለት መጣጥፍ ጽፈን፣ ወይም በኤፍ ኤም ላይ የክሪስቲና አጉሊዬራን ወለምታ ‘ሰበር ዜና’ ምናምን አይነት ወሬ ስላወራን፣ “ምን ጋዜጠኛ አለና ነው” የምንል…ብቻ ምን አለፋችሁ በየመስኩ “ምን…አለና ነው!” የምንል ሰዎች መአት ነን፡፡አንዳንዴ ደግነቱ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…አንባቢው፣ ተመልካቹ ወይም አድማጩ የሚያውቀው እሱ ዘንድ ሥራችንን ብቻ ስለሆነና እነኚህን “ዘውድ ጫኑልኝ…” አይነት የምንላቸውን ነገሮች ስለማያውቅ ‘የበሰበሰ ቲማቲም’ የሚወረውርብን የለም፡፡
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስለ ትወና ምናምን ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሮሚዮና ጁሊየት እየታየ ነው፡፡ ሁለቱም ተዋንያን ቀሽም ያሉ ስለነበሩ የሚያዩት በድብርት ነበር፡፡ ጁሊየት፡— ሳመኝ ሮሚዮ፣ ሳመኝና እቤቴ እሄዳለሁ፡፡
ሮሚዮ፡— ልስምሽ አልችልም፡፡
ጁሊየት፡— እባክህ ሮሚዮ ሳመኝና እቤቴ እሄዳለሁ
ሮሚዮ፡— አዝናለሁ፣ ግን ልስምሽ አልችልም፡፡
ጁሊየት፡— ሮሚዮ እባክህ፣ እባክህ ልለምንህ ሳመኝና እቤቴ ልሂድ፡፡ ይሄን ጊዜ ከተመልካቹ መሀል አንዱ ምን ብሎ ጮኸ መሰላችሁ… “አቦ፣ ሳማትና ሁላችንም ቤታችን እንሂድ!”
እንዲህም አይነት መሰላቸት አለላችሁ እላችኋለሁ፡፡
ደግሞላችሁ… በ‘ፕሮፌሽናሎች’ አካባቢም ይሄ ለራስ ከፍተኛ ግምት የመስጠት ነገር በሽ ነው፡፡ ለምሳሌ በሆነ የጤና መታወክ አንድ ክሊኒክ ትሄዱና ትታከማላችሁ፡፡ በሌላ ጊዜ ሌላ ክሊኒክ ለድጋሚ ምርምራ ስትሄዱ “በዛ ሰሞን እንዲህ የሚባል ክሊኒክ እከሌ የሚባል ዶክተር እንዲህ፣ እንዲሀ ብሎኝ ነበር…” ስትሉ አብዛኛውን ጊዜ የሚገጥማችሁ ምላሽ “እነሱ ናቸው እኮ የህክምና ሙያን የሚያሰድቡ… አይነት ነገር ነው፡፡ “አዎ፣ እሱ ዶክተር እኮ አገራችን አሉን ከምንላቸው አንዱ ነው…” ምናምን የሚባል ነገር መስማት…አለ አይደል…ሙሉ ለሙሉ አይቻልም ባይባልም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
በብዙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ አስተማሪዎች “እሱ ምን ያውቅና ነው፡ ጠቅላላ ገልብጦ አይደል እንዴ ፔፐሩን የሠራው…” አይነት ‘በተዘዋዋሪ’ ለራስ የሚሰጥ ከፍተኛ ግምት በብዛት የሚታይ ነው፡፡ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን የሆነ ቦታ ያገኘኋትን ነገር እዩዋትማ! እግዜሐር በቅሎን ፈጠረ፡፡ “በቅሎ ትባያለሽ፣ ከባድ ሸክሞች በጀርባሽ ትሸከሚያለሽ፡፡ ሳር ትመገቢያለሽ፣ የማሰብ ችሎታ አይኖርሽም፡፡ ለ50 ዓመትም ትኖሪያለሽ” ይላታል፡፡ በቅሎይቱም፣ “በዚህ አይነት ሁኔታ ለ50 ዓመት መኖር ይበዛብኛል፡፡ እባክህ ከ20 ዓመት በላይ አትስጠኝ፣” ትላለች፡፡ እንዳለችውም ይደረግላታል፡፡
እግዜሐር ውሻን ፈጠረ፡፡ “ውሻ ትባላለህ፡፡ የሰው ልጅን መኖሪያዎች ትጠብቃለህ፣ ዋናው አጋሩም ትሆናለህ፡፡ ትርፍራፊ ትመገባለህ፣ ለ25 ዓመትም ትኖራለህ ይለዋል፡፡ ውሻ ሆዬም “በዚህ አይነት ለ25 ዓመት መኖር ይበዛበኛል፡፡ እባክህ ከ10 ዓመት በላይ አትስጠኝ” ይላል፡፡

እንዳለውም ይደረግለታል፡፡እግዜሐር ጦጢትን ይፈጥራል፡፡ “ጦጣ ትባያለሽ፡፡ ከዛፍ ዛፍ እየዘለልሽ ነገረ ሥራሽ ሁሉ የደደብ ይሆናል፡፡ አስቂኝ ትሆኛለሽ፣ ለ20 ዓመትም ትኖሪያለሽ” ይላታል፡፡ ጦጢትም፣ “ፈጣሪ ሆይ ደደብ ሆኖ ይህን ያህል መኖር ይበዛብኛል፡፡ እባክህ ከ10 ዓመት አታስበልጥብኝ፡፡” እንዳለችውም ይደረግላታል፡፡
በመጨረሻ እግዜሐር የሰው ልጅን ፈጠረ፡፡ “ሰው ትባላለህ፣ ብቸኛው በምድር ላይ የሚኖር ምክንያታዊ ፍጡር ትሆናለህ፡፡ በምድር ላይ የበላይ ትሆናለህ፣ ለ20 ዓመትም ትኖራለህ፡፡” የሰው ልጅም፣ “ፈጣሪ ሆይ 20 ዓመት በጣም ትንሽ ነው፡፡ እባክህ አምላኬ በቅሎዋ አልፈልግም ያለችውን 20 ዓመት፣ ውሻ አልፈልግም ያለውን 15 ዓመት፣ ጦጢት አልፈልግም ያለችውን 10 ዓመት ጨምርልኝ፣” ሲል ይለምናል፡፡ ይህም ተፈጸመ፡፡
እግዜሐር የሰው ልጅ 20 ዓመት እንዲኖር፣ ከዛም እንዲያገባና በጀርባው ከባድ ሸክም እየተሸከመ 20 ዓመት እንደ በቅሎ እንዲኖር አደረገው፡፡ ከዛም ልጆች ይወልድና 15 ዓመት እንደ ውሻ ቤቱን እየጠበቀ ከልጆቹና ከቤተሰብ የተራረፈውን እየተመገበ ኖሮ በመጨረሻም በእርጅና ዘመኑ የልጅ ልጆቹን ለማስደሰት እንደ ጦጢት የደደብ እንቅስቃሴዎች እያደረገ 10 ዓመት እንዲኖር አደረገው ይባላል፡፡እናላችሁ…ይሄ ለራስ ከልክ በላይ የሆነ ግምት መስጠት የሆነ ነገር ካላበጀንለት በስተቀር የምር ለመራመድ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
የዚህ አገር ‘ቦተሊካ’ አንዱ ትልቁ ችግር የሚመስለኝ በየሰፈሩ ያሉት ‘ቦተሊከኞች’ ብዙዎቹ ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ይመስለኛል፡፡ ይህን ለማወቅ የግድ ‘ጠጠር መበተን’ ምናምን አያስፈልግም፡፡ በየንግግሮቻቸው፣ በየመግለጫዎቻቸው፣ በየቃለ መጠይቆቻቸው የምናየው ነው፡፡
ደግሞላችሁ…እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ‘ስብስብም’ እዚህ አገር በጥቅል የሚሰጥ ቡድናዊ የተጋነነ ግምት ጆሯችንን ሊበጥስ ምንም አይቀረው፡፡
እግረ መንገዴን… ይሄ የኳሳችን ነገር፣ አለ አይደል ያው ለልጆቹ ላደረጉት በተለያዩ ሚዲያዎች ጥረት ምስጋና ተሰጥቷል፡፡ ግን አልፎ አልፎ እነኚህን ምስጋናዎች ከልክ በላይ የመለጠጥ ነገሮች እየሰማን ነው ልበል! ጫፌን ትነኩና አይነት ነገር አሪፍ አይመስለኝም፡፡
ለራሳችን ተገቢውን ቦታ የምንሰጥበትና ለሌሎችም ተገቢውን ስፍራ የምንሰጥበትን ዘመን ያምጣልንማ! መሻሻል ናፈቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4133 times Last modified on Saturday, 16 February 2013 15:42