Saturday, 16 February 2013 12:00

እውነቱን ወዴትም ልንሸሸው አንችልም!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ ጊዜ አንድ መንገደኛ ቡድሀ ላይ ያለ የሌለውን የስድብ መዓት ያወርድበታል፡፡ ቡድሀ ዝም ብሎ በእርጋታ ሲያዳምጥ ይቆይና ለመንገደኛው ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡ “ስጦታ የተበረከተለት ሰው ስጦታውን አልቀበልም ካለ ስጦታው የማን ይሆናል?” ሰውየውም፤ የሰጪው በማለት መለሰ፡፡ ቡድሃም፤ “ስጦታህን አልቀበለም፤ እነሆ ተረከበኝ” ብሎት ጥሎት ይሄዳል፡፡ አቶ ቶማስ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከታሪክ ጋር ተመሳሳይ ስለሆኑ የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ሊነግሩን ወይም ሊሰብኩን ከፈተኛ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡

በእርግጥ ከክፋት ሳይሆን ከበጐነት በመነጨ ነው ይሄን ያደረጉት፡፡ እንዴት ቢሉ እኛ የሀገራቸው ልጆች አለም የደረሰበትን ሚስጥር እንድናቅላቸው በመጓጓት ነው ታሪኮቹን የነገሩን፡፡ የአቶ ቶማስ ሀሳብ ምንም እንኳን ተራና በጣም ካለማወቅ የመጣ እንደሆነ ቢገባኝም እንደ ቡድሀ ፊቴን አዙሬ መሄድ ግን አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም ይሄ ለከት ያጣ ሃሳባቸው አንዳንድ ሰዎችን ሲያሳስት አስተውያለሁና ፀሃፊው ምን ያህል እንደተሳሳቱ እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡እንግዲህ ለወደፊቱም አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃልና በዚህች የእግዚአብሔር ቅኔ በሆነች ሀገር ላይ አንዳች ፍልስፍናዊ ወይም ሳይንሳዊ አልያም በአለማዊ ምልከታ የተሞላ ተጠራጣሪና ተቺያዊ አስተያየት ከማቅረቡ በፊት በደንብ በነገሩ እንዲያስብበት እመክራለሁ፡፡

የሚስጥራዊ ነገሮች አነፍናፊ የሆነው ግርሀም ሀንኩክ በመጨረሻ አክሱም ላይ መስገዱን መዘንጋት አይገባም፡፡ ሰውየው የሰገደው ለፅላቱ መኖር ከመሰለን አሁንም ሰውየውን አተኩረን አላየነውም ማለት ነው፡፡ (በቅዱስ መፅሀፍ የሚያምን ቢሆን እንኳን እሱ ያለው አለማዊ እውቀት ይሄ ዘመን ለታቦቱ የመስገጃ ጊዜ እንዳልሆነ እንዲያስብ የሚገደድ ሰው ነው) ሀንኩክ የሰገደው ላጠቃላዩ የአምላክ ቅኔ ነው፡፡ የአምላክ መንገድ ቀላል ነው፤ ቅኔውንም መፍታት ቢሆን፡፡ ግን በቅንነት መፈለግ ይገባል፡፡ አንድ ሰው ይህንን መንገድ ሲፈልግም በመጀመሪያ ማድረግ ያለበት በአለማዊ እውቀቶች የተቃኘውን አይምሮ ለጊዜው ገለል አድርጐ አዲስ በሆነ አጀማመር ቅዱስ ቃሉን ማየት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሀሳቦች የሚጋጩት (በእግዚአብሔር ቃሎች ውስጥ) በብዙ የአለም እውቀቶች ተወጥሮ በዛ መነፅር መፅሐፍ ቅዱስን ከማንበብ እንዲሁም ራሱን መፅሐፍ ቅዱስን ትኩር ብሎ ካለማየት ነው፡፡

ይህን ደግሞ በዚህ ሀሳብ ዙሪያ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ አስተያየታቸውን ከሰጡና በሁለት አፅናፍ ባሉ ሰዎች በተካሄደው እሰጥ አገባ በትክክል መረዳት ይቻላል፡፡ አንዱ (አቶ ቶማስ) በቂ ባልሆነ አለማዊ እውቀት ተዓብዮ፣ ሌላው (ዶ/ር ፈቃደ) ሃይማኖቱ ሊነካ አይገባም በሚል መነፅር እየተመለከቱ ነው ሀሳባቸውን የሰነዘሩት፡፡ በሁለቱም ሰዎች ሀሳብ ውስጥ ግን በተለይ በአቶ ቶማስ ፅሁፍ ትክክለኛዎቹ መልሶች ቁልጭ ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ሆኖም ያጠለቋቸው መነፅሮች እነዛን መልሶች ሊያሳዩአቸው አልቻሉም፡፡ አሁን እንግዲህ የእነዚህን ሰዎች መነፅር እናውልቅና መልሶቹን ከፅሁፎቹ ውስጥ እየነቀስን እናውጣቸው፡፡ በእርግጥ አቶ ቶማስ በጣም ቅንና ስሜታዊ መሆናቸውን መገንዘብ አልተሳነኝም፡፡ ልክ መሆናቸውን ለማሳየት ማናቸውንም መስዋእትነት ከመክፈል ወደኋላ አይሉም፡፡ ይሄን ወድጄላቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን ያሳስታሉና እፈራቸዋለሁ፡፡

አሁን ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባ፤ እንግዲህ አቶ ቶማስ በሦስት ሳምንት ከፃፏቸው ሀሳቦች ውስጥ ሁለት ነገሮችን መምዘዝ ይቻላል፡፡ 1ኛው፡- በመፅሀፍ ቅዱስ ወስጥ የተፃፉ የተወሰኑ ታሪኮች ከዛ በፊት በነበሩ ዘመናት በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈፅመዋል፤ ስለዚህም በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ታሪኮች ካለፉ ታሪኮች የተኮረጁ ናቸው የሚል አንደምታ ያለው ነው፡፡ 2ኛው፡- ሀሳብ ደሞ እራሱ መፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ የተጋጩና የማይመስሉ ታሪኮች አሉ የሚል ሲሆን እነዛንም ሀሳቦች ከመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ እያወጡ ሊያስረዱን ሞክረዋል፡፡ እኔም እሳቸው እየለቀሙ ያወጧቸውን ታሪኮች ዋና ዋናዎቹን ከሳቸው ፅሁፍ ውስጥ ለቅሜ አውጥቼ ምን ያህል እንደሳቱ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ ፀሃፊው ሀሳባቸውን ለማስረዳት ከተጠቀሟቸው ማስረጃዎች የተወሰኑትንና ዋና ዋናዎቹን ከራሳቸው ፅሁፍ እጠቅሳለሁ፤ ከዛም ይህንን በስህተት የተሞላ ትንታኔያቸውን ለማስተካከል እሞክራለሁ፡፡ 1ኛ/ “…ከአራት ሺህ አመት በላይ እድሜ ባስቆጠረው ጥንታዊ የግብፅ ሃይማኖታዊ ፅሁፍ ውስጥ የሰፈረውን ዝርዝር አንብቡ፡፡

3ሺህ አመት እድሜ እንዳለው ከሚነገርለት የሙሴ አስርቱ ትእዛዛት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ታገኙታላችሁ” 2ኛ/ “…ለምሳሌ የኦሪት መፅሐፍትንና የጥንት ግብፃውያንን የሃይማኖት ፅሁፎች በማስተያየት ስለ አማልክት ታሪክ ተመሳሳይነት መገንዘብ ይቻላል፡፡ ቃል በቃል አንድ አይነት የሆኑ የሃይማኖት ህግጋትና ትእዛዛት እንደሏቸው በማመሳከር እናያለን፡፡” 3ኛ/ “…እንግዲህ የአምላክ ልጅነት፣ ንግስና፣ ውልደትና የሰላሳ አመት ጥምቀት፤ የሞትና ትንሳኤ በጥንታውያኑ የግብፅ ሃይማኖት ውስጥ ምን ያህል ቦታ እንዳለው የሆረስ ታሪክ ከኢየሱስ፣ ከሚትራ፣ ከክሪሽናና ከዲየስየስ ይመሳሰላል የሚባልበት አንዱ ምክንያት ከእንደዚህ አይነት ትረካዎች የተነሳ ነው፡፡” ሌላው ደሞ ይህንን መኮራረጅ እንደ አቶ ቶማስ ሀሳብ፣ በክርስቲያኑ አለም ያሉ ሰዎችም (ጳጳስ ቤኔዴክት የመሰሉ) ተቀብለውታል በሚል ምን እንዳሉ ሳይገባቸው ለሀሳባቸው ማረጋገጫነት ተጠቅመውበታል፡፡ ለሳቸው ቅኔ የሆነባቸው የጳጳሱ ትክክለኛ ሀሳብ ምን ያህል ከእሳቸው ምልከታ ጋር እንደሚለያይ በስተመጨረሻ ላይ አሳያለሁ፡፡

አቶ ቶማስ ለሦስት ሳምንት ያህል ብዙ ቢዳክሩም ዋናው ሀሳባቸው ከዚህ በላይ እየለቀምኩ ባወጣኋቸው ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው መጀመሪያ በዓምላክ ቃል ላይ ነው የተገዳደሩትና ከሱ ስም እንጀምር፡፡ እሳቸው የዓምላክ ስሞች ብለው የጠቀሷቸው ያህዌ፤ ኤሎሄ፣ አብና ወልድን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስን በወፍ በረር አንብበው ሊተቹ መሞከራቸውን ያረጋግጣል፡፡ ከጠቀሷቸው አራት የተከበሩ ቃላቶች ውስጥ የአምላክ ስም (ምንም እንኳን በትክክል እየጠራነው እንደሆነ እርግጠኞች ባንሆንም) አንዱ ብቻ ነው፡፡ ይሄውም ያህዌ የሚባለው ነው፡፡ በተረፈ ኤሎሄ ማለት “አምላኬ” ማለት እንጂ ስም አይደለም፤ የመለኮት መገለጫ ነው፡፡ አብና ወልድ ደሞ አባትና ልጅ ማለት ሲሆን የአምላክን ሦስትነትና በምድር መገኘት የምናውጅበት ምሳሌ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ፀሃፊው ግራ ተጋብተው ግራ ሊያጋቡን ወደሞከሩበት የኦሪት ዘፍጥረት ትንታኔያቸው እንሂድ፡፡ እሳቸው እንዲህ ነው የፃፉት፤ 2ኛ/ “…አንደኛው ትረካ በፍጥረት ምዕ.1 ላይ መጀመሪያ ቀንና ሌሊት፣ በሁለተኛው ቀን ሰማይን፣ በሦስተኛው ቀን ምድርን፣ ባህርን እንዲሁም እፅዋትን፣ በአራተኛው ቀን ፀሐይ፣ ጨረቃን ኮከቦችን ፈጠረ” አቤት ጉድ! በአምላክ ጥበብ በጣም በጣም ተሰብስቦና አጥሮ (ምን ሊባል እንደተፈለገ ሳይዘነጋ) የተሰጠንን አቶ ቶማስ የበለጠ አሳጥረው ሲነግሩን፣ በዚህ የማሳጠር ጥበባቸው ውስጥ ምን ያህል እንደሳቱና ምን ያህል የተሰጡንን መልእክቶች እንደገደፉ ቢገነዘቡ ኖሮ እንዴት ክው ብለው እንደሚደነግጡ እገምታለሁ፡፡

እስቲ የመጀመሪያዋን የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል (ዘፍ.1.1-5) እንጥቀስና ትልቁን ስህተታቸውን እንመልከት፡- መፅሀፍ ቅዱስ በኦሪት ዘፍጥረት 1፡1-5 እንዲህ ነው የሚለው፡- “በመጀመሪያ እግዚአብሄር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፡፡ 2/ምድርም ባዶ ነበረች፤ አንዳችም አልነበረበባት፤ ጨለማማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሄርም መንፈስ በውሃ ላይ ሰፍኖ ነበር፡፡ 3/እግዚአብሄርም ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ 4/እግዚአብሄርም ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ እግዚአብሄርም ብርሃንና ጨለማን ለየ 5/እግዚአብሄርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፣ ጨለማውንም ሌሊት አለው፡፡ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፣ አንድ ቀን…” እንግዲህ እዚህች ጋ የተሰራች ግድፈት እንዴት መላውን ሃሳባቸውን እንዳበላሸ እናያለን፡፡ የዘፍጥረት ታሪክ እንደሚነግረን እና መላውን መፅሀፍ ቅዱስ ስናነብ እንደሚገለፅልን በምዕራፍ 1 ቁ 1-2 እና ከቁጥር 3-5 ባለው ክፍተት ውስጥ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሰማይና ምድር በመጀመሪያው ቀን ሳይሆን የተፈጠሩት ቀደም ባለው ሌላ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ አምላክ ሰውንና በምድር ላይ ነዋሪዎችን ለመፍጠር ሲነሳ ምድርን ከፈጠራት ቆይቶ ነበር፤ በመጀመሪያው ቀን እግዚአብሔር የፈጠረው ነገር ብርሃንና ጨለማን መለየት ነው፡፡ ይህንንም በትክክል አተኩሮ ያነበበው ሰው ይረዳዋል፡፡

ለርስዎ አላዋቂነት ስንል ግን አንዳንድ መረጃዎች እንስጥዎት፡፡ አዳምና ሄዋንን አሳሳተ ብለው የጠቀሱት እባብ ወይም ሰይጣን (ከየት መጣ አለማለትዎ ገርሞኛል) የአጥቢያ ኮከብ ይለዋል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ የተፈጠረው እንደመልአክት ነበር፤ ትልቅ ስልጣን ነበረውም፡፡ በትምክህቱና መመለክንም ስለፈለገ ከሰማይ ወደ ምድር ተጥሏል፤ ስለዚህም መባረሩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይነግሩናል፡፡ እናም ሰይጣን ወደ ምድር የተጣለው በዚህ ክፍተት መሀል ባሉት ዘመናት ነው፤ ከዛም ምድር ጨለማ ሆና ለዘመናት ቆይታለች፡፡ ከዛ ነው እንግዲህ እግዚአብሔር ጨለማ የነበረችውን ምድር ከብዙ ዘመናት በኋላ ብርሃን ትሁን ብሎ ፈጠራውን የጀመረው፡፡ ሌላው እርስዎ በጥበብዎ አሳጥረው “በሶስተኛው ቀን ምድርን ባህርን እንዲሁም እጽዋትን ፈጠረ” ያሉትን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስንገለብጠው እንዲህ ይላል፡- ምዕ 1-11 “እግዚአብሔርም ምድርን ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን፣ በምድርም ላይ እንደወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ” እንዲሁም ሆነ፡፡

ሌላው አስደንጋጭ ግድፈትዎት ደግሞ ይሄ ነው፡፡ እግዚአብሔር በሶስተኛው ቀን እጽዋትን አልፈጠረም፤ እንዲበቅሉ አዘዘ እንጂ፡፡ ይህ ፈጠራ ሳይሆን ትእዛዝ የተሰጠበት ምክንያት የእጽዋት ዘር በምድር መሀፀን ውስጥ ስለነበሩ ነው፡፡ አዎ ቀደም ብሎ ብርሃን ይሁን ከማለቱ ብዙ ዘመን በፊት ምድርን ሲፈጥር እጽዋትን ፈጥሮ ነበር (አንዳንድ ብርሃነ ልቦና የሆኑ የእግዚአብሔር ሰዎች እንደሚያስቡትም ከሰው ውጭ ሌሎች ፍጥረታት ከብዙ ዘመናት በፊት ተፈጥረው ነበር) በመሃል ሰይጣን በማመፁ እግዚአብሔር እቅዱን እንዳዘገየ ይታመናል፤ ያም ሆነ ይህ እግዚአብሔር የነገረን እጽዋትን በዛ ጊዜ እንዳልፈጠረ ነው፤ እንዲበቅሉ አዘዘ እንጂ፡፡ ስለዚህ ጌታው አቶ ቶማስ የማያውቁትን ታላቅ ሚስጥራዊ መጽሐፍ ለመተንተን መነሳትዎ ትልቅ ስህተት ነው ባይ ነኝ፡፡ ሌላው “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ይለዋል፤ ይሄ ታዲያ የእግዚአብሔር አምሳል ነው” እና “…በእርግጥ እባቡ እንዳለው ፍሬውን ሲበሉ አልሞቱም፤ አይኖቻቸው ተከፈቱ…” የሚለው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ምን ይላል መሰልዎት? “ለናንተ ወተት ወተቱ ነው መሰጠት ያለበት፤ ለጠንካራ ትምህርት ገና ናችሁና” ቅዱስ ጳውሎስ ይሄንን ያለው አማኞች ለሆኑት ግን በመንገዳቸው ገና ላልጠነከሩት ነው፡፡ ለእርስዎ ምን እንደሚሰጥዎ ግራ መጋባቱ አይቀርም፡፡ አምላክ ይህን ህግ ባፈረሳችሁ ግዜ ወይም ከዚህች ተክል በበላችሁ ግዜ ትሞታላችሁ ሲላቸው፣ ስለመንፈሳዊ ሞት እየነገራቸው ነው - ስጋ መንፈሳዊ ክብርን ተሸካሚ ነው፡፡

እኛ መንፈሳዊ አካላትነታችን የበዛ ፍጥሮች ነን፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ የተናገረውም ስለመንፈሳዊ ሞት ነው፡፡ ከዛ መንፈስ የተገነጠለ ሰው ጐስቋላ ነው፡፡ ሁሉንም የሚተች ደግሞ ሁሉን የሚጠላ ነው፡፡ ለዚህም ነው አይናቸው የተከፈተው አዳምና ሄዋን በአካላቸው እራቁትነት አፍረው ከአምላክ ለመሸሸግ የሞከሩት፡፡ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የምድር ፍጥረታት ስም ማውጣት የቻለውና የዳበረ አይምሮ ባለቤት የነበረው አዳም፤ በገነት ዛፎች ውስጥ ከአምላክ ለመሸሸግ ሞከረ፡፡ አዎ ብዙዎቻችን እስካሁንም እየሸሸን ነው፡፡ ከምን እንደምንሸሽ ባናውቅም፡፡ ወደ ታሪካዊ መኮራረጁ ከመሄዳችን በፊት የአቶ ቶማስ ታላቅ ስህተት የሆነው የኖህ ታሪክ እንመልከት፡፡ አንዱ ጥያቄያቸው ወይም ለመተቸት የሞከሩት እንዲህ ብለው ነው፡- “ኖህ ከአዳም አስረኛ ትውልድ ነው፤ እንዴት በ10 ትውልድ አለም በሰው ልጆች ቆሻሻ ተሞላች” ሲሉ የጠየቁት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ወይስ መደመርም አይችሉም ልበል? ኖህ እኮ የነበረው አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ 2ሺህ 1 መቶ 56 አመት (2156) በኋላ ነው፡፡ ምናልባት ከመቶ አመት በኋላ መስሎዎት ይሆን እንዴ? በኖህ ጊዜ ህዝቦች በምድር ላይ ለ2156 አመታት ያህል ኖረዋል፡፡

ሌላው አንድ ሚሊዮን እንኳን አይደርሱም ነው ያሉት (እንዴ? ትንሽ ያስቡ እንጂ!) አንድ ሚሊዮን ሊሞሉ እንደማይችሉ ለማስረዳት የተጠቀሙት ደሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለዎትን እውቀት የሚያስገምት ነው፡፡ አዳም ስድስት ልጅ ነው የወለደው ነው ያሉት፡፡ እስቲ ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን እንይ፡- ዘፍጥ ም5፡ 4 እንዲህ ይላል “አዳም ሴትን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ አዳም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ሰላሳ አመት ሆነ” አዪ ምን ያህል ቅዱሱን መጽሐፍ እንዳላነበቡ!! ዓምላክ ለእብራውያን በሰጠው ቅዱስ ቃሉ ላይ በስም የገለፃቸው አባቶች የመሲሁን (የክርስቶስን) ግንድ የያዙትን ብቻ ነው፡፡ በኖህ ሰዓት ስለነበሩት ህዝቦች ብዛት ግን ትንሽ ሂሳብ ቢሰሩ ተቀራራቢ ግምት ይኖርዎት ነበር፤ ነገር ግን አዳም የ500 አመት ሰው በነበረበት አካባቢ እስከ 10.000 ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል፤ ይህም በትክክለኛ ሂሳብ የተቀመጠ ነው፡፡ ያንን ሂሳብ ለእርስዎ ለማሳየት ብሞክር ግን የጋዜጣውን ቦታ መሻማት ይሆናል፡፡ ነገር ግን በኖህ ዘመን ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡

(አስፈላጊ ከሆነ ሂሳቡ እንዴት እንደሚሰራ በግልዎ ልልክልዎት እችላለሁ፡፡) ሌላው ስለኖህ መርከብ ጉዳይ ነው፡፡ እንዴት አንድ ኳስ ሜዳ የሚያህል መርከብ ያን ሁሉ ፍጥረታት ቻለ፡፡ አይ የኢንተርኔት ዘመን - ችግሩ ይሄ ነው ጥራዝ ነጠቅ ያደርጋል! የአለም የኳስ ሜዳዎች ምን ያህል ህዝብ እንደሚይዙ አያውቁም ልበል፡፡ ከ5000 አመት በፊት አምላክ መርከቡን እንዲህ አድረገህ ስራ ነው ያለው ዘፍጥ 7፡16 ላይ “…የመርከቢቱን በር በጐንዋ አድርግ፤ ታችኛውንም ሁለተኛውንም ሦስተኛውንም ዓርብ ታደርግለታለህ” ከዓርቡም በተጨማሪ በጣራው ወጋግራ ላይ ብዙ ፍጥረታት ሊቀመጡ እንደሚችሉ ሊያስቡ ይገባል፡፡ ሌላው ደሞ ስለ ፍጥረቶቹ ብዛት የገለፁት የተሳሳተና ከ5000 ዓመታት በላይ የጊዜ ልዩነትን ያላገናዘበ ነው፡፡ ለምሳሌ የድመት ዘሮች የሚባሉትን ካወቁ ከዚህ በታች ያለው ለኖህ የተነገረው የእግዜአብሔር ቃል ይገባዎት ይሆናል፡፡ ቁጥር 20 ላይ “ከወፍ እንደ ወገኑ ከእንስሳም እንደወገኑ ከምድር ተንቀሳቃሽ ሁሉ እንደወገኑ በህይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ” በተጨማሪም የአለማት ፈጣሪ ፀጋ በመሃላቸው እንዳለ አይዘንጉ፡፡ ወደ ሁለተኛው የመኮራረጅ ነገር ስንሄድ አቶ ቶማስ እንደማስረጃ የተጠቀሙበት የጳጳስ ቤኔዴክት አባባል እሳቸው እንዳሰቡት እንደማይል ከራሳቸው ትርጉም ተነስቼ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በነገራችን ላይ አቶ ቶማስ ስለፃፉት የግብፆችም ሆነ የባቢሎን ሙሴ የኦሪት መጽሐፍት ከመፃፉ በፊት ስላሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚመሳሰሉ ታሪኮች በህዝቦች ታሪክ ላይ ስለመፃፉ አንዳችም ተቃውሞ የለኝም፡፡ እንደውም እነዛ ታሪኮች ባይኖሩ ነበር አስገራሚ የሚሆነው፡፡ አሁን ወደ ጳጳሱ አባባል ልመለስ፡፡ እንዲህ ነው ያሉት፣- “የሰው ልጅ ነፍስ በአንዳች መንገድ እጁን ወደ አዳኝ አምላኩ እንደዘረጋ ነው” ይህ ምን ለማለት ነው? ይህን ለማብራራት ወደ ዘፍጥረት ታሪክ መመለስ ይኖርብናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን በሰራው ሀጥያት ከገነት ሲያስወጣው ያደረገው ነገር ቢኖር ለአዳምና ለሄዋን ቆዳ ማልበስ ነው፡፡ አዎ ቆዳው ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አንድ እንስሳን በመሰዋት ለአዳም ያለ መስዋዕት እንደማይድን ሲያመላክተው ነው፡፡ በመጨረሻው ዘመንም ልጁን ልኮ በልጁ መስዋዕትነት እንደሚያድነው ሲነገርው ነው፡፡ አቶ ቶማስ እንደመሰላቸው በሙሴ የተፃፉት ህጐች ከ3000 አመታት በፊት የታወቁ ሳይሆን አዳም ገና ከገነት ሲወጣ ከዛሬ 7500 አመታት በፊት ይታወቁ ነበር፡፡ ለሙሴ የተሰጡ ህጐች ስለመሲሁ የተሰጡ ተስፋዎች፣ ከአዳም ስህተት በኋላ ለው ልጅ መዳኛ የተዘጋጁ እቅዶች ናቸው፡፡ አዳም ከገነት ሲወጣ ይህንን ተስፋ ተሸክሞ ነው፡፡ አምላክ ያጠፋ ፍጥሩን ዝም ብሎ ሜዳ ላይ አለቀቀውም፡፡ ህጉንና ተስፋውን ሰጥቶት እንጂ፡፡ ስለዚህም ነው እሱ የነገራቸው አቤልና ቃየል መስዋዕትን የፈፀሙት፡፡ በሀዲስ ኪዳን ዘመን ጳውሎስ እንዳለው፤ “በእግዚአብሔርና በሰው ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ አሰራሩ አንድ ስለሆነ፣ ለእግዚአብሔር ያለውን ወስዶ በመንፈሱ አማካኝነት ለሰዎች ይነግራቸዋል” ስለዚህም ከአዳም በኋላ ያሉ ህዝቦች የአምላክን ተስፋ፣ የአዳኛቸውን የእግዚአብሔር ልጅ በምድር ላይ የሚያደርገውን ድርጊት በሙሉ ያውቁ ነበር፡፡ ምርጦቹ ያንን ተስፋ በሩቅ እያዩ ሩጫቸውን አስተካክለው ይጓዙ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው ህጉን ስላላከበሩ፣ የሰጠውን ተስፋውን ስለናቁ በኖህ ጊዜ ሰዎች በጥፋት ውሃ የተቀጡት፡፡ ኖህ መንገዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ ይህንን ህግና ተስፋ ለልጆቹ ነግሮአቸዋል፡፡ ልጆቹም ለልጅ ልጆቻቸው፡፡ እንግዲህ ከኖህ በኋላ ያሉ ከዛሬ (550) አመት በፊት መሆኑ ነው፡፡

አንዳንዶች መንገዱን ሲከተሉ (እንደ ኢዮብና አብርሃም ያሉት) ሌሎቹ ደሞ በራሳቸው መንገድ ተርጉመው ተጠቀሙበት፡፡ አንዳንዶቹም “እኔ ነኝ ያ ነብይ” ብለው ታሪክ ፃፉ፤ ታሪክ አስፃፉ፡፡ ንጉሱ በሀውልቱ ላይ የፃፈውን ከድንግል ነው የተወለድኩት፣ በሰላሳ አመቴ ተጠመቅሁ ወይም በትክክል የእግዚአብሔር ልጅ (እውነተኛው) የሚያደርገውን የሰው ልጆችን ተስፋ ጽፎ ወይም አስጽፎ፡፡ ከኖህ የተላለፈውን የእግዚአብሔርን ህግም የኛ ነው ብሎ አስፍሮ ቢገኝ ምን አስገራሚ ይሆናል፡፡ እንግዲህ ሙሴ ከ3000 አመት በፊት የፃፈው ከአዳም ጀምሮ የሚታወቅ ህግና ተስፋን ነው፡፡ ሙሴ የክርስቶስን መንገድ የሚያመቻቹ ህዝቦች አሰልጣኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር በሰይጣን የተታለለው ህዝብ በትክክል እንደምኞቱ ሊሆንለት ስላልቻለ፣ ከመረጠው ሰው (ከአብርሃም) ከሀጥያት የራቀ ህዝብ ለማሰልጠን ጀመረ እናም ያንን ለዘመናት በልቡ የነበረውን ለአዳም የሰጠውን ህግና ተስፋ ሰጣቸው፡፡ ስለዚህም ጳጳሱ ሊሉ የሞከሩት “በዘመናት ሁላ የሰው ልጆች በትክክልም ይሁን በተሳሳተ መንገድ እጃቸውን ወደ አምላካቸው እንደዘረጉ ነበር” ነው፡፡ በኖህና በሙሴ መካከል ባለው ዘመን የኖሩ የዓለም ህዝቦች በሙሉ አምላክ ለአዳምና ለነብያቱ የነገራቸውን ህግና ተስፋ በተለያየ መንገድ (በተለያየ አረዳድ ሰምተው ነበር፡፡) ስለዚህም አቶ ቶማስ፤ ግብፆች ይሁኑ ባቢሎናውያን ከማርስ ወይም ከጁፒተር እስካልመጡ ድረስ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ አካል ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ነገስታቶቻቸውና ካህናቶቻቸው ቢያምታቷቸውና ተስፋዎቹን ቢበሩዙባቸውም ወይም ታላቁን ተስፋ ከሌሎች አማልክት ቢሰጡባቸውም ስለ ሁሉም ነገር ያውቁ ነበር፡፡ (በተጣመመ መንገድ ቢሆንም) አሁን እንግዲህ እዚህ ጋ የሚመጣው ጥያቄ፤ ከነዚህ ሁሉ በዘመናት ካለፉ የእውነተኛውን የአምላክ ልጅ ታሪክ የኛ ነው ካሉ የአዳም ልጆች መሀል ትክክለኛው የእግዚአብሔር ልጅ አዳኙ ማነው የሚል ነው፡፡ ለዚህ መንገድ ማሳያ ከሐዋሪያት ስራ አንድ ሃሳብ እጠቅሳለሁ፡፡ እነ ጴጥሮስን ስለ ክርስቶስ በመስበካቸው ሊያስሯቸው ፈልገው ለያዟቸው ፈሪሳውያን አንድ ገማልያል የተባለ ፈሪሳዊ ሊቅ እንዲህ አላቸው፤ “ከዚህ ዘመን በፊት አንዱ እንዲሁ ተነሳ፤ ብዙዎችን አስከተለ፤ ከእግዚአብሔር ስላልሆነ ጠፋ፡፡ እነዚህም ከእግዚአብሔር ካልሆኑ ይጠፋሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ከሆኑ ግን ምንም ልታደርጓቸው አትችሉም፡፡ ይልቁንስ ከእግዚአብሔር ስትጣሉ እንዳትገኙ” እንግዲህ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነው የክርስቶስ ወንጌል በሚያስገርም ፍጥነት በመላው አለም ተሰብኳል፡፡ ተስፋፍቷልም፡፡ ለእውነትነቱ ምስክርም ህያውነቱ ነው፡፡ ለዛሬ ይሄን ያህል ካልኩ ይበቃኛል፡፡ ከአቶ ቶማስ ጋርም የተግባባን ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ ባንግባባም ችግር የለውም፤ እውነቱ ግን ይሄው ብቻ ነው!!

Read 8998 times