Print this page
Saturday, 16 February 2013 11:48

ለፓትርያሪክነት የተጠቆሙት ዕጩዎች ዛሬ ይለያሉ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ፤ ካህናትና ምእመናን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ሊኾን ይገባል የሚሉትን ዕጩ እንዲጠቁሙ ያወጣው የስምንት ቀን መርሐ ግብር ትላንት፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ለፓትርያሪክነት የተጠቆሙት ዕጩዎች ዛሬ ይለያሉ፡ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ እንዲሰጥ፣ የወደደውንና የፈቀደውን በመንበረ ፕትርክናው እንዲያስቀምጥ ካህናትና ምእመናን አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ የታዘዘው የአንድ ሳምንት የጸሎት ሱባኤ እስከ ምርጫው ፍፃሜ የካቲት 21 ቀን 2005 ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት ተላልፏል፡፡ ዐዋጅም መፈጸሙ ተነግሯል፡፡ በምርጫው መሪ ዕቅድ መሠረት፣ በዛሬው ዕለት ካህናትና ምእመናን የዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማ የሰጡበትን ቅጽ የያዘው የታሸገ ሣጥን ተከፍቶ ተጠቋሚዎቹን የመለየት ሥራ እንደሚሠራ የአስመራጭ ኮሚቴው ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

በዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማው ካህናት፣ ምእመናንና ገዳማውያን ሳይቀሩ በንቃት መሳተፋቸውን የተናገሩት ሓላፊው አቶ ባያብል ሙላቴ፤ ጥቆማውን ኮሚቴው በዕጩነት ለሚለያቸው አምስት አባቶች ዋነኛ ግብአት አድርጎ እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል፡፡ ኮሚቴው በዛሬው ዕለት ለጥቆማው አቀባበል በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ካህናትና ምእመናን የጠቆሟቸው አባቶች ለፓትርያሪክነት ለሚመረጡ ዕጩዎች የተቀመጡትን መመዘኛዎች ማሟላት አለማሟላታቸውን ከግል መረጃዎቻቸው ጋር እያነጻጸሩ የመለየትና የማጣራት ሥራዎች እንደሚሠራ አቶ ባያብል አስረድተዋል፡፡

ሓላፊው አያይዘውም በፓትርያሪክነት መመዘኛው መሠረት ተጠቋሚዎቹን የመለየትና ተጨማሪ የማወዳደር ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ፣ ኮሚቴው የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚቀርቡትን አምስት ዕጩዎች ለይቶ የካቲት 14 ያስታውቃል ብለዋል፡፡ 
‹‹በአንድ ሰውም ይኹን በአንድ ሺሕ ሰው የተጠቆሙ የተለያዩ አባቶች ቢኖሩ ኮሚቴው የሚወስደው ለዕጩነት መጠቆማቸውን ነው፤›› የሚሉት አቶ ባያብል፣ ተጠቋሚው በዕጩነት ሊያዝ የሚችለው፣ በምርጫ ሕገ ደንቡ የፓትርያሪክነት መመዘኛውን አሟልቶ ሲገኝ እንጂ በብዙ ሰው ስለተጠቆመ ብቻ ባለመኾኑ የዕጩ ጥቆማውን ጥያቄ ከመምረጥ ወይም ምርጫ ሂደት ጋር ማሳሳት ተገቢ አለመኾኑን ገልፀዋል፡፡
ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ላይ የተጠየቁትን የድጋፍ ደብዳቤዎች አሟልተው የቀረቡ ዕጩ ጠቋሚዎች የተስተናገዱት በግላቸው እንደነበር የጠቆሙት አቶ ባያብል፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች እገሌን ለዕጩነት ጠቁመናል ወይም እገሌን መርጠናል በሚል በቡድን የቀረቡ ማመልከቻዎችን ሳይቀበሉ መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን በዕጩ ፓትርያሪክነት በመጠቆም እንዳቀረቡት የተገለጸው ደብዳቤ ተቀባይነት የሚኖረው፣ ደቀ መዛሙርቱ በነፍስ ወከፍ የኮሌጅ ተማሪነታቸውን ከኮሌጁ አስተዳደር በተጻፈ ደብዳቤ አስደግፈው ለጥቆማ ሲቀርቡ እንደኾነ ሓላፊው አስረድተዋል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት መግለጫው፣ የካቲት 21 ቀን በሚካሄደው የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሚሳተፉት የመራጮች ብዛት 800 እንደኾኑ ካስታወቀ በኋላ በሂደት እየተለዩና ዕውቅና እየተሰጣቸው የተጨመሩ መራጮች መኖራቸው ተመልክቷል፡


በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቷ በሀገር ውስጥ ካሏት 53 አህጉረ ስብከት መካከል 790 መራጮች ይሳተፋሉ፤ ከሀገር ውጭ ባሏት ስምንት አህጉረ ስብከት ከእያንዳንዳቸው አራት (ከሥራ አስኪያጁ ጋር ካህናትን፣ ምእመናንን፣ ሰንበት ት/ቤቶችን የሚወክሉ አንድ አንድ) መራጮች፣ ከግብጽ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ጋር ባለው የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት አራት መራጭ ተወካዮች በአጠቃላይ ማስተካከያው እስከተነገረበት ጊዜ ድረስ 826 መራጮች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

 

Read 4547 times
Administrator

Latest from Administrator