Saturday, 09 February 2013 12:36

የሁለት እብዶች ታሪክ

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

“ተመስገን፤ አለም በችግሮች የተሞላች ናት፡፡ ሁላችንም የየራሳችን ችግሮች አሉብን፡፡ ችግሮቻችን ጉልበት አግኝተው ሊያሸንፉን የሚችሉት አጋነን ስናያቸው ነው፡፡ ምን እንደሚባል ታውቃለህ? የእያንዳንዱ ሰው ችግር ለጨረታ ቢቀርብ …”
“እያንዳንዳችን የየራሳችንን ችግር መልሰን እንገዛለን” ተመስገን ነው አረፍተ ነገሩን የጨረሰው፡፡ ይህንኑ ነው እኔም ልል የነበረው፡፡
“አዎ፤ አዎ፡፡ ያንኑ ነበር ልል የነበረው፡፡ እና ደግሞ ችግሮች የሚገዝፉት በሶስት መንገድ ነው ይላል አንድ አሜሪካዊ ፀሐፊ፡፡ አንደኛ ሁሉን አቀፍ አድርገን ስናያቸው፡፡ ሁለተኛ…”
ተመስገን ከአፌ ነጠቀኝ …
“ሁለተኛ ቋሚ ወይም ለረጅም ጊዜ የማይፈቱ አድርገን ስናስባቸው፡፡ ሶስተኛ ግለሰባዊ ወይም እኛ ላይ ብቻ የደረሱ ሲመስለን ነው፡፡ በአጭሩ ልትጠቅሰው የሞከርከው ፀሐፊ በሀገሩ ቋንቋ እንዳለው ችግሮች Pervasive, Permanent, and Personal አድርገን ስናያቸው ነው በጣም የሚከብዱን” ልቀጥል የነበረውን ነው የጨረሰልኝ፤ ቃል በቃል እንዳሰብኩት አድርጎ፡፡ የምለው ግራ ገባኝ፡፡ ሁለተኛውን ወሬ ከአፌ ተቀብሎ ያወራው በሹፈት ነው፤ እያላገጠ፡፡
“ልክ ነህ ተመስገን፡ አሪፍ ጭንቅላት እንዳለህ አውቃለሁ፡፡ አሳየኸኝ ነግሮኛል፡፡ እና ችግሮች …”
ለሶስተኛ ጊዜ አቋረጠኝ፡፡
“አሁንም ልትቀጥል ነው አቶ እሱያለው? አይኑ ውስጥ ቁጣ እና ንቀት ፍንትው ብለው ይታያሉ፣ ቅድም ስናገር አልተቆጣሁም፡፡ አሁን ግን ቁጣ እየበላኝ ነው፡፡ ትዕግስቴ አልቋል” ወደ አሳየኸኝ ዞሮ፡፡ አሁን ገና ነው ወደሱ የዞረው፤ “ይኼውልህ አሳየኸኝ፤ ጓደኛህ አፉን እንዲዘጋልኝ ብለምነው እንቢ ብሏል፡፡ መጥፎ ነገር ከመከሰቱ በፊት እንዳመጣኸው ይዘኸው ሂድ፡፡ እንቶ ፈንቶውን ሄዶ የለመደበት ያውራ”
ዝም አለ፡፡
በህይወቴ እንዲህ አይነት ውርደት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ ደሜ በረዶ፣ አጥንቴ ብረት፣ ትንፋሼ ውርጭ ሆነ፡፡
“አንተ እኔ ላይ ነው አፍህን የከፈትከው?”
“ባክህ አንተ ነህ አፍህን እንድትዘጋ ብትለመን እምቢ ያልከው”
“ዝም በል አንተ፤ ክፍት አፍ፤ እብድ”
“ምንድን ነው ያልከው?”
“እብድ ነው ያልኩት፡፡ እብድ ነህ”
“የምትለውን እየሰማኸው ነውን?”
“አዎ፤ ምን ትሆናለህ?! እብድ ነህ”
“ተናደሃል፤ እራስህን መቆጣጠር እስኪሳንህ ተናደሃል፡፡ ለዚህ ነው አስሬ እብድ ነህ የምትለኝ፤ ልታናድደኝ፤ አልተሳካም፡፡ አሁንም የመጨረሻ ዕድል ልስጥህ፡፡ አንድም ስላመመህ በጊዜ ቤትህ ሄደህ እረፍት አድርግ፡፡ ሌላም አፍህን ዝጋ፡፡ አለበለዚያ …”
“አለበለዚያ ምን?! አንተ…”
“አለበለዚያማ አሳይሃለሁ! I will make you pay for it.”
ከወንበሩ ተነሳ፡፡ ባለበት ቆሞ አጨበጨበ፡፡ ቤቱ እስኪያስተጋባ ደጋግሞ አጨበጨበ፡፡ መጀመሪያ በቅርብ ወንበሮች ላይ የተቀመጡት ሰዎች ዝም አሉ፡፡ ጭብጨባው ቀጠለ፤ ቤቱ በሙሉ ዝም እስኪል ድረስ፡፡ ቤቱን የሚሰማ ዝምታ ዋጠው፡፡
“ጨዋታችሁን በማቋረጤ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ከልቤ፡፡ ግን ሁላችሁም መስማት የምትፈልጉት ነገር እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እዚህ አጠገቤ የእህቴ ባል አቶ አሳየኸኝ እና ሁላችሁም የምታውቁት ክቡር አቶ እሱያለው አሉ፡፡ ስለ ክቡር አቶ እሱያለው አንድ ሁለት ነገር ልነግራችሁ ነው፡፡ አቶ እሱያለው እዚህ ያለው በእህቴ ባል ጉትጎታ እኔን ሊረዳኝ መጥቶ ነው፡፡ ይህ አያስገርምም፡፡ እንደምታውቁት አዝኖ አቶ እሱያለሁ ያላፅናናው፣ ተቸግሮ ያልደገፈው፣ ግራ ገብቶት ከአቶ እሱያለው ምክር ያልጠየቀ ሠው እዚህ ውስጥ ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ ነው የአቶ እሱያለው ህይወት፡፡ የተከበረ ሰው ነው፡፡ እዚህ ቤት ከሠዐት በፊት ሲገባ ያሳያችሁት ክብር ስለ አቶ እሱያለው ማንነት ልክ እንደሆንኩ ምስክር ነው፡፡ እኔ አብጃለሁ፡፡

በዚህም ሁላችሁም እንደምትስማሙ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለዚህም ነው አቶ እሱያለው እዚህ የተገኘው፤ እኔን ለመርዳት ብሎ፡፡ ችግሩ እኔ እርዳታውን አልፈለግሁም፡፡ ይህንን የሱን ክብር በሚመጥን ትህትና ነግሬዋለሁ፡፡ ሊሰማኝ አልፈቀደም፡፡ ከልብ የተጠየቀን እና የምር የሚያስፈልግን ዕርዳታ መንፈግ ግፍ እንደሆነ ሁሉ ያልተጠየቁትንም እርዳታ፣ አልፈልግም እየተባለ መቸርም ንቀት ነው፡፡ ምንም ባብድ ይህ ሀቅ አልጠፋኝም፡፡ እናንተም እንደምታውቁት እኔም እየመሰከርኩ እንዳለሁት እብድ ነኝ፡፡ ለምን ታዲያ የአቶ እሱያለውን እርዳታ ትጋፋለህ ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም፡፡ የንግግሬ ዋና አላማም ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ነው፡፡
“አቶ እሱያለው አርባ ሁለት አመቱ ነው፡፡ የሴት ጓደኛ የለውም፡፡ ትዳር አልመሰረተም፡፡ ልጅ አልወለደም፡፡ ለምን ብላችሁ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? ለምን የሴት ጓደኛ የለውም? አፍቅሮ በመልሱ መፈቀርን መሻትና ያንን ማግኘት ወይም ማጣት ጨለማን ተገን አድርጎ ከሸርሙጣ ጋር ዋጋ የመደራደርን ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ወይም ትኩሳት በተሰማን ቁጥር ሰራተኛችንን ወደ አልጋ እንደመጎተት አልተሳካም፡፡ ትዳር የለውም ብያለሁ፡፡

ለምን የለውም? የሴት ጓደኛ ስለሌለው አይደለም መልሱ፡፡ አትሳቁ፤ አያስቅም፡፡ ባያፈቅርም ኖሮ ትዳር መመስረት አያቅተውም ነበር፡፡ ያለ ፍቅር የቆሙ ብዙ ትዳሮች አሉ፡፡ ይሄን ከኔ በላይ አቶ እሱያለው ያውቃል፡፡ የብዙዎችን ትዳር ሲጠግን ነው የኖረው፡፡ አያችሁ መልሱ ያለው እዚህ ጋ ነው፡፡

ትዳር ጥቂት ተፋቃሪዎች ብዙ ደፋሮች የሚገቡበት ዓለም ነው፡፡ ትዳር መመስረት የተጣሉ ባልና ሚስትን የማስታረቅ ያህል ቀላል የትርፍ ጊዜ ስራ አይደለም፡፡ ልጅ የለውም፡፡ ለምን? ሚስት ስለሌለው አይደለም መልሱ፡፡ አሁንም አትሳቁ፤ አያስቅም፡፡ ምክንያቱ ይህ ነው፡- ልጅ ወልዶ ማሳደግ የጎረቤት ልጅን የመምከር አይነት ሽበት ያለው ሁሉ የሚሞክረው የደቂቃ የጉንጭ ማልፋት አይደለም፡፡ ሠውን የመስራት ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ ትልቅ አዕምሮ፣ ጠንካራ ጫንቃ ይፈልጋል፡፡
“ምንም ጥርጥር የለውም አቶ እሱያለው አስተዋይ ሰው ነው፡፡ በዚህ ሁላችሁም ትስማማላችሁ፡፡ አትስማሙም? አዎ ልክ ነኝ፡፡ ትስማማላችሁ፡፡ እድሜ ዘላለሙን ግን አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመረቀ፡፡ እዚህ መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጠረ፡፡ ይኸው እስከዛሬ እዚያው ነው ያለው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ የደረሰበት የሀላፊነት ጣራ የክፍል ሀላፊ መሆን ነው፡፡ ይህ ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ የሱን ያህል አስተዋይ ያልሆኑ የራሱ ጓደኞቹ፣ እኩዮቹ፣ ታናናሾቹ፣ የታናናሾቹ ታናናሾች የት እንደደረሱ እሱኑ ጠይቁት፡፡ እነሱ መክሊታቸውን ተጠቅመዋል፡፡ እሱ መክሊቱን ቀብሮታል፡፡ በመክሊታቸው ነግደው የሚያተርፉ ደፋሮች ብቻ ናቸው፡፡
“አሁንም ሁላችሁም የምትስማሙበትን ነገር ልናገር፡፡ እየጨረስኩ ነው፡፡ እንዴት ላስቀምጠው? አዎ ይሄ የእህቴ ባል የተጠቀመውን ንግግር ልጠቀም፡፡ አንዴ ከእኔ ጋር እያወራን የአቶ እሱያለውን አይነት ፍፁም ሠው ይኖር ይሆን? ብሎ ጠይቆኛል፡፡ በህይወቴ እንዲህ አይነት ጅል ጥያቄ ሰምቼ አላውቅም፡፡ አሳየኸኝ የዋህ ነው፤ ሞኝ ነው፤ ምስኪን ነው፡፡ ከአንጀቱ ነው የጠየቀኝ፡፡ የሚገርመው ደሞ መልስ ከእኔ ይጠብቅ ነበር፡፡ በእርግጥ አቶ እሱያለው ፍጹም ነው ብሎ ያምን እንደሆነ ጠየኩት፡፡ ያንን በሙሉ ልቡ እንደሚያምን ነገረኝ፡፡ ‘ፍፁም’ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስጠይቀው ግን ችግር ተፈጠረ፡፡ አምጦ የወለደው መልስ ፍፁም ማለት ስህተት የማይሰራ ማለት ነው የሚል ሆነ፡፡ እሺ በዚህ ልስማማ፡፡

አሁን እናንተ ተጠየቁ፡፡ ልጠይቃችሁ፡፡ ስህተት የማይሰሩ እነማን ናቸው? እኔ ልመልሰው፡፡ በመሉ አፌ በሙሉ ልቤ ነው የምመልሰው፡፡ ስህተት የማይሰሩ ሠዎች የማይኖሩ ሠዎች ናቸው፡፡ ለሌላ ጉዳይ የተባለ ነገር እዚህ ጋር ልንገራችሁ፡፡ ለኔ ወሬ እንዲመች አድርጌ ነው ታዲያ፡፡ ላለመሳሳት ከፈለክ ምንም ነገር አትበል፤ ምንም አታድርግ፤ ምንም አትስራ፡፡ ባጭሩ ላለመሳሳት ከፈለክ መኖር አቁም ማለት ነው፡፡ ህይወት ማለት፤ መኖር ማለት አለመሳሳት ማለት አይደለም፡፡ አንድን ስህተት ሁለቴ አለመስራት ነው ህይወት፡፡
“ስለዚህ የእህቴ ባል ጥያቄ እንዲህ ቢሆን እወድ ነበር፡፡ ትክክለኛ መልስ ይኖረኛል ያኔ፡፡ መነሳት ያለበት ጥያቄ እውን የአቶ እሱያለውን አይነት ፍፁም ሰው ይኖር ይሆን? አይደለም፡፡ እውን የአቶ እሱያለውን አይነት ሰው ይኖር ይሆን? ነው ትክክለኛው ጥያቄ፡፡ እኔ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ እሱም አቶ እሱያለው ነው፡፡ አልገባችሁም አይደል? እኔም አልረካሁም፡፡ ቆይ መልሼ ላስተካክለው ጥያቄውን፡፡ እውን የአቶ እሱያለውን አይነት ሰው ያልሆነ ሰው ይኖር ይሆን? መልሴ ያው ነው፡፡ ከአርባ ሁለት አመታት ውስጥ አንዲቷን ቀን ሣይኖር የኖረ የማውቀው ብቸኛው ሠው አቶ እሱያለው ነው፡፡


“አሁን ሁለት ነገር ተናግሬ ላጠቃልል፡፡ ንግግሬ ካሰብኩት በላይ ረዝሟል፡፡ ሁለት ነገር ተናግሬ ይብቃኝ፡፡ የመጀመሪያው ለናንተ ነው - ለአድማጮቼ፡፡ ነገርን ሁሉ ለሚገባው ሥጡ፡፡ እሬሳ የሚገባው ክብር ለህያው ከምንሰጠው የተለየ ነው፡፡ ታውቃላችሁ፡፡ ህያዋን ከሙታን ወይም ደግሞ ህይወት ከሞት እልፍ አእላፍ ግዜ እንደሚገዝፍ ታውቃላችሁ፡፡
“ማነው ክብር የሚገባው? እናንተ ወይስ አቶ እሱያለው? በገቢያችሁ መኖር አቅቷችሁ የሰው ፊት ታዩ፣ ብድር ትጠይቁ ይሆናል፡፡ ኑሮአችሁ በልጆቻችሁም ሆነ በሌላ ነገር ታምሶ ግራ ገብቷችሁ፣ ማጣፊያው አጥሯችሁ ይሆናል፡፡ ከምንም ነገር በላይ የምትሳሱለት ህይወታችሁ በተደጋጋሚ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ይሆናል … ግን እየኖራችሁ ነው፡፡ ህይወት እንዲህ ናት፡፡
“እብድ ነኝ ብያችኋለሁ፡፡ አሁን ግን እብድ የምትሰሙ አትመስሉም፡፡ ለማንኛውም …እ…አላበድኩም፡፡ እንደፈለጋችሁ፡፡ … አበደም ካላችሁ …፡፡ በእብደት እንድጠረጠር ያደረገኝን ምክንያት አሁን ልንገራችሁ፡፡ ህይወት ከማፈቅራት ልጅ ውጪ ምንም ቢሆን ግድ የለኝም እኔ፡፡ ትምህርቴን ከአራተኛ ዓመት ኢንጅነሪንግ ወደ አንደኛ ዓመት ቋንቋ ትምህርት የቀየርኩት አንዲት የቋንቋ ተማሪ ውብ ልጅ አፍቅሬ ነው፡፡ …እ! ጨርሻለሁ፡፡”
ወደ በሩ ተራመደ፡፡ ቤቱ ውስጥ የሚሰማው የሱ ጫማ ኮቴ ብቻ ነው፡፡ በር ላይ ከደረሠ በኋላ፡-
“አቶ እሱያለው አትፅናና፡፡ እብድ ነው መባሌ እስካሁን ያልኩትን ሀሰት አያደርገውም፡፡ ማበድም ህይወት ነው፡፡ አንተ እሱንም አታገኝም፡፡ እብደት እብድ አይደለም፤ እንደ አንተ አይነቱን አይዝም፤ ብቻ አሁንም አልረፈደም፤ ጊዜ አለህ፤ መኖር ጀምር፡፡ ለምን ከአሁኗ ደቂቃ አትጀምርም?”
ወጥቶ ሄደ፡፡ ከሴኮንዶች በኋላ ተመለሰ፡፡
አሁንም ቤቱ ዝም እንዳለ ነው፡፡
“ሥላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ” አለ ከልቡ እየሳቀ፡፡
ወጥቶ ሄደ፡፡
ዝምታው ቀጠለ፡፡
ተነስቼ ወጣሁ፡፡ አሳየኸኝ አልተከተለኝም፡፡
ከትንሽ እርምጃ በኋላ … ባለሁበት ቆምኩ፡፡ እንዲህ አይነት ውርደት ተቀብዬማ ሹልክ ብሎ መውጣት …
ተመለስኩ፡፡
በር ላይ ስደርስ አሁንም ቤቱ ዝም እንዳለ ነው፡፡ አስፈሩኝ፡፡ ሁሉም አፈጠጡብኝ፡፡ ፊታቸውን ደስታ አብለጭልጮታል፡፡ አይናቸው ውስጥ ብርሃን ይንቦገቦጋል፡፡ አፋቸው በአግራሞት ገርበብ ብሎ ተከፍቷል፡፡
ለምን እንደተመለስኩ፣ ምን ማለት እንዳለብኝ፣ ምን ማድረግ እንደሚሻል? እያሰብኩ እያለ የራሴን ድምፅ ሠማሁት፡፡
“ምን ታፈጡብኛላችሁ? እብዶች”
ዝም፡፡
ሄድኩ፡፡
ከአንድ አምስት እርምጃ በኋላ ግሮሰሪዋ ውስጥ አንድ ነገር ፈነዳ፡፡ ሳቅ፡፡
አቤት!? እንዴት እንደደረስኩ አላስታውስም፡፡
ቀን አርባእቱ፡-
አዕምሮዬ ውስጥ ሺ ሚሊዮን ነገር ይተራመሳል፡፡
ሳቅ-ዲስኩር፣ረዥም-ዲስኩር-የመስማት ጉጉት-ጓደኛ-ትዳር-ልጅ-ስህተት-ደስተኛ ፊት-ሳቅ-ህይወት-አርባ ሁለት-እብደት-ህይወት-ክፍል ሃላፊ-ሳቅ-ጓደኛ-መክሊት-አርባ ሁለት-ልጅ ደፋር-ስህተት-ሳቅ-ዝምታ-ፍቅር-ሰራተኛ-ሸርሙጣ-ፍፁም-ዋጋ-ቀላል-ደፋር-ሳቅ-ዝምታ-እብደት፤ እብደት፤ እብደት፤ እብድት፤ እብደት…፡፡
የግርጌ ማስታወሻ፡-
አንባቢዎች እንደምትገምቱት ይህን ፅሑፍ የፃፍኩት ከህመሜ ከዳንኩኝ በኋላ ነው፡፡

Read 4703 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 15:25