Saturday, 09 February 2013 12:25

የአቶ አልአዛር የቤተእስራኤሎች ጹሑፍ ተጋንኗል!

Written by  ዳዊት ከኢየሩሳሌም
Rate this item
(3 votes)

ለእዚህ መጣጥፌ ምክንያት የሆነኝ ባለፈው ሳምንት በእስራኤል የሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን በተመለከተ “ የእስራኤል “ኩሽሞች” (ባሪያዎች) ” በሚል ርዕስ አልአዛር ኬ የተባሉ ሰው የጻፉት ፅሁፍ ነው ። ፈላሻ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን የሰው ልጅ ደግሞ ሀገሩን ለቆ የሚፈልሰው ወይም የሚሰደደው ወዶ ሳይሆን በሀገሩ ጦርነት ሲነሳ፣ የኑሮ ሁናቴ አልስተካከል ሲል ወይም በሌሎች ችግሮች ነው። ታዲያ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ሀገራችን ገቡ የሚባሉት ቀዳማዊ ምኒሊክ አባቱ ንጉሥ ሰሎሞን ዘንድ ቆይቶ ሲመለስ ብዛት ያላቸው ቤተ-እሥራኤላውያን ተከትለውት ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ “ክብረ ነገስት” የሚባለው ጥንታዊ መጽሐፍ ይገልፃል። ራሳቸው ቤተእስራኤላውያንም በአፈታሪክ የሰሙትን ሲናገሩ ይደመጣሉ። ከዛም በኋላ በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ወደ ግብጽ ከተሰደዱት እስራኤላውያን ከፍለው ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ቤተ-እስራኤላውያን በኢትዮጵያ ይኖሩ ነበር ።
ኢትዮጵያዊያንም እነዚህን ማኅበረሰብ ከሀገራቸውን ርቀው ተሰደው የሚኖሩ ለማለት “ፈላሻ ፤ ፈላሾች” ይሏቸዋል። ልክ እስራኤላውያን በሀገራቸው ተሰደው የሚኖሩትን ሰዎች “ዖቭደይ ዛሪም” እንደሚሏቸው ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ግን “ፈላሻ” የሚለውን ቃል እንደ ስድብ ሲጠቀሙበት ይሰማል።(የተጠቀምኩበት ዘመን በጠቅላላ እ.ኤ.አ ነው)
እንደሚታወቀው ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ይሁዳዊያን ወደ እምነት ሀገራቸው እስራኤል በየጊዜው ይጓዛሉ። ባለፉት ሶስት ዓመታት እንኳን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የተጓዙትን ቤተ-እስራኤላዊያን ብዛት ብንመለከት፣ በ2010 ዓ.ም 1,652፣ በ2011 ዓ.ም 2,666 እና በ2012 ዓ.ም 2,355 ቤተእስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድራቸው ተጉዘዋል ። በአሁኑ ጊዜ የሀገሪቱ የህዝብ ብዛት ከ7.9 ሚልዮን በላይ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 124 ሺ ያህሉ ቤተ-እስራኤላውያን ናቸው።ለመጀመሪያ ጊዜ ብዛት ያላቸው ቤተ-እስራኤላዊያን ከ1981 ዓ.ም እስከ 1984 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከጎንደርና ከትግራይ አካባቢዎች ተነስተው ወደ ሱዳን ተጓዙ፤ ታዲያ እነዚህ ሰዎች እስራኤል እስኪደርሱ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ የተወለዱበትና የአደጉበትን ቀዬ ትተው፣ ወልደውና ከብደው ከኖሩበት መንደራቸው ተነጥለው፣ ለስንቅና ለችግር ብለው የያዙትን ጥሪት በዘራፊዎች ተነጥቀው፣ በደዌና በረሃብ ልጆቻቸውንና ወላጆቻቸውን ያጡትን ቤቱ ይቁጠረው።

(አራት ሺህ የሚጠጉ ቤተ-እስራኤላውያን በሱዳን ምድር በረሃብና በበሽታ እንዳለቁ ቤተ-እስራኤላውያን ይናገራሉ)
ታዲያ ያንን ሁሉ አልፈው እስራኤል ሲደርሱ ቋንቋው፣ ባህሉ፣ የሀገሪቱ ሕግ፣ የልጅ አስተዳደጉ፣ ለዛውም የሚያውቁትና ያደጉበት የቶራ ህግ (የኦሪት ህግ) እንኳን ሳይቀር የ”ግማራ” እና የ”ሚሽናህ” ትምህርት ተጨማምሮበት ብዙው ነገር ለእነርሱ አዲስ ነበር ። ቢሆንም ግን ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ ትሄዳለች እንደሚባለው ከነጭ አይሁዳዊያን ጋር ተዛንቀው መኖር ጀመሩ። ይህን ስል ግን አብዛኛው እድሜው ገፍቶ ከኢትዮጵያ የሄደው ሰው እስካሁን ድረስ የሀገሪቱን ቋንቋና ባህል መልመድ እንደተሳነው እሙን ነው።(ይህ ችግር አሁን በቅርቡ የሄዱትንም ያጠቃልላል)። ይህም ቢሆን የእስራኤል መንግስትም ሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህዝቡን ከመርዳትና ከማስተማር አልቦዘኑም። ምንም እንኳን የተለያዩ ችግሮች በእስራኤል ቢኖርባቸውም አቶ አልአዛ ያዩበት መነጽር እኔ በቅርበት ከማየው ጋር አልተስማማልኝም።

በመጀመሪያ አቶ አልአዛር ቤተእስራኤላዊያንን ከድሩዚም ጋር አመሳስለው ነው ያቀረቡት። ሁለቱን ህዝቦች ያመሳሰሉት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ታማኝ በመሆናቸው ነው። ይህ ደግሞ ነውሩነቱ ምን ላይ ነው? በመንግስት ላይ በአመጽ አለመነሳታቸው ወይስ ወደ ኢትዮጵያ መልሱን ባለማለታቸው ይሆን? ደግሞስ ይሄን ያህል የሚያማርር ነገር ምን ተገኝቶ ነው? አንድ ኅብረተሰብ በሀገሩ ጉዳይም ሆነ በራሱ ጉዳይ ያልመሰለውና የማይዋጥለት ነገር ሲኖር ሃሳቡን በጽሁፍም ሆነ በሰላማዊ ሰልፍ መግለጽ ንጹህ የዲሞክራሲ ባህል ነው። ይህን ደግሞ እርሶም ያውቁታል ብዬ አምናለሁ። እስራኤል ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ይሁዳዊያን የሚኖሩባት የይሁዳዊያን ሀገር ናት (ዐረብ እስራኤላውያን ጨምሮ) ታዲያ በዚች ሀገር በየጊዜው የተለያዩ ኅብረተሰቦች የመንግስትን ፖሊሲ በመደገፍና በመቃወም እንዲሁም ሃሳባቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ አደባባይ ይወጣሉ። ቤተ እስራኤላውያንም የኅብረተሰቡ አንድ ክፍል እንደመሆናቸው በተለያየ ጉዳይ አደባባይ ወጥተዋል። እርሶ እንዳሉት ጠቅላላ ቤተ-እስራኤላውያንን ያነሳሳ ከ1996 ዓ.ም ለሜጌን ዳቪድ(የእስራኤል ቀይ መስቀል) የለገሱት ደም በመደፋቱ ካደረጉት ተቃውሞ ውጪ ያን ያህል የተጋነነ ነገር አልታየም። እስቲ በጽሑፍዎት ላይ ያነሷቸውን የቤተእስራኤላውያን ችግሮች በዝርዝር እንመልከት ፥
የቤት ግዢ
በአሁን ሰዓት በእስራኤል የቤት ዋጋ ጣራ ነክቷል፤ ለምሳሌ አንድ መለስተኛ ባለ ሶስት ክፍል ቤት (ሁለት መኝታ ቤትና አንድ ሳሎን ያለው) ለመግዛት ከሚልዮን እስከ 1.5 ሚልዮን ሼቄል(የእስራኤል መገበያያ ገንዘብ) ሲያስፈልግ፤ ይህንኑ ቤት ለመከራየት ደግሞ ከ2800 እስከ 4000 ሼቄል በወር ያስከፍላል። በዚህም ምክንያት አብዛኛው በመካከለኛ ኑሮ የሚገኝ እስራኤላዊ ቤት መግዛት ተስኖታል። ኢትዮጵያዊያን አዲስ ገቢዎች ደግሞ አመትና ሁለት አመት በ”መርካዝ ክሊታ”(ጊዜያዊ መጠለያ) ቆይተው ቤት ይገዛሉ። ለቤት መግዣ የሚቀበሉት ገንዘብ በስጦታና የተወሰነው በብድር ሲሆን፤መጠኑም የሚወሰነው እንደ ቤተሰባቸው ብዛት ነው። የሚገዙት ቤት እንደ ቤተሰባቸው ቁጥር ማብሰያ፣ መታጠብያና መጸዳጃ ክፍሎችን ሳይጨምር ሶስትና ከሶስት ክፍል በላይ ነው።እውነት ለመናገር አብዛኛው ኢትዮጵያውያን አዲስ ገቢዎች (ቤተእስራኤላውያን) ቤት ለገዙበት ብድር በወር ለባንክ የሚከፍሉት ሶስትና አራት ቀን ሰርተው ያገኙታል። ይህን ቤት ግን እንከራይ ቢሉ በወር የወር ደሞዛቸውን 75% ይከፍሉ ነበር ።


ሌላው “ቤት ሲገዙ አንድ ቦታ እንዲገዙ ይገደዳሉ” ብለው አቶ አላዛር ያነሱት ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ሲሆን እራሳቸው ቤተ-እስራኤላውያን ግን ቤት ሲገዙ ለለቅሶም፣ ለድግሱም፣ ቡና ለመጠጣጣትም ጭምር ሲሉ ተፈላልገው አንድ አካባቢ ይመርጣሉ። ይህን ጉዳይ የእስራኤል የአዲስ ገቢዎች መስሪያ ቤት በጥብቅ እንደሚቃወመው የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህም ሆኖ የከተማው አዲስ ገቢ ኢትዮጵያዊያንን የመቀበል ኮታው እስኪሞላ ድረስ እነርሱ ራሳቸው የፈለጉት ቦታ መርጠው ይገዛሉ። በዚህም ምክንያት ነው ቤተ-እስራኤላውያን በአንድ ቦታና ከተማ በብዛት ተሰባስበው የሚኖሩት።
በ1985 የአይሁዳዊያን አዲስ ገቢዎች መስሪያ ቤት ወደ እስራኤል የሚገቡ ቤተእስራኤላውያን በ25 የተለያዩ ስፍራዎች ቤት ገዝተውም ይሁን የአሚዳር ቤት (የመንግስት የኪራይ ቤቶች) ተቀብለው እንዲኖሩ ሲያደርጋቸው ከእያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪዎች ብዛት አንጻር የቤተእስራኤላውያን ቁጥር ከ2% እና 4% በላይ እንዳይሆን ወስኖ ነበር፤ በ2010 ዓ.ም በወጣው መረጃ መሰረት ግን ቤተ-እስራኤላውያን በክርያት-መልሂ ፣ በአፉላና በያቭኔ ከተሞች ነዋሪዎች መካከል ከሰባት እስከ አስራ አምስት ከመቶ የሚሆን ቁጥር ነበራቸው። ይህ ማለት ግን በከተማው ከሚኖረው ከሌላው የእስራኤል ማኅበረሰብ አንጻር እንጂ ቤተ-እስራኤላውያን በብዛት የሚኖሩባቸው ከተሞች ናታንያ፣ አሽዶድ፣ ሪሾን ለጽዮን፣ ሮሆቮት፣ ኢየሩሳሌምና የመሳሰሉ ናቸው።
አብዛኞቹ ላጤ ቤተእስራኤላውያን የማሽካንታ ተቋዳሽ አይደሉም። እንደማንኛውም እስራኤላዊ እንዲገዙ በመንግስት ተወስኖ ከሰሩና መግዛት ለሚፈልጉት ቤት 30% የቤት መግዣ ገንዘብ ካላቸው የተቀረውን ከባንክ መበደር ይችላሉ። ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ግን እንደወገኖቻቸው እነርሱም ገንዘብ ተሰጥቷቸው ይገዙ ነበር።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አቶ አልአዛር፣ ቤተእስራኤላውያን የሚገዙት ቤት ሁለት ክፍል ብቻ እንደሆነና አንድ አካባቢ እንዲገዙ እንደሚገደዱ ከመግለፃቸውም ባሻገር “ሁሉም በብድር ያገኙትን ገንዘብ ይዘው ያመሩት ርካሽ የመኖሪያ ቤቶች ወደሚሸጡባቸው፣ ምንም አይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ባልተዘረጉባቸው ኋላቀርና ጭራሹኑ ወደተዘነጉት አካባቢዎች ነበር፡፡” ብለዋል።
እንዲህ ማለታቸው የሚያሳፍር ነው። ለመሆኑ አቶ አላዛር የሚሏቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? አፉላን፣ ክርያት መላኺን፣ ክርያት ጋትን፣ ዖር ይሁዳን የመሳሰሉትን ከተሞች ማለታቸው ይሆን? አቶ አልአዛር የመሰረተ ልማት አገልግሎት ያልተዘረጋባቸው ሲሉ ስልክ፣ ጋዝ፣ ውሃ፣ መብራት ያልገባላቸው ቤቶች የተገነቡባቸው ማለታቸው ነው ወይስ መንገድና የህዝብ ማጓጓዣ የሌለባቸው ከተሞች ለማለት ነው፤ አሊያስ ለልጆች መጫወቻ ስፍራና ትምህርት ቤት የሌለባቸው መንደሮች ማለታቸው ነው? ለማንኛውም ስለከተሞቹ የማያውቁ ከሆነ ጎግልን ይጠይቁ። በዛውም ስለነዋሪዋቻቸውም ይመልከቱ።
ኩሺም ተብለው መጠራታቸው
ሌላው ቤተእስራኤላውያን ኩሽ ወይም ኩሺም ተብለው ስለመጠራታቸው (ስለመሰደባቸው) አንስተዋል ። በዕብራይስጥ ቋንቋ ኩሽ ማለት ባርያ ማለት ሲሆን ኩሺም ደግሞ ባርያዎች ማለት ነው። ሌላው ኩሽ ስንል የኖህ የልጅ ልጆች ምድርን ሲከፋፈሉ ከምጽራይም (ከግብጽ) በታች በስተደቡብ ባለው ስፍራ የኩሽ ልጆች እንደሰፈሩና ምድሪቱም የኩሽ ምድር ተብላ ትጠራ እንደነበር መጻህፍት ይናገራሉ። በዚህም መሰረት እኛ አበሾች የኩሽ ልጆች ነን።
ሌላው በዕብራይስጡ ቶራ (ኦሪት) ላይ እንደተጻፈው የታላቁ ነብይ ሙሼ (ሙሴ) ሚስት ኩሺ እንደነበረች ይናገራል። ኩሺ መባልዋ በኩሽ ምድር የተወለደች ኩሺት ስለሆነች ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ እስራኤላዊ ራብ (የኦሪት ምምህር) ባንድ ወቅት ያለኝን ላነሳ እወዳለሁ “የሙሼ ራቤኑ ሚስቱ እንዳንተ ኩሺ ነበረች “ ብሎኛል። ይህን ማለቱ እኔ እንደሚገባኝ እንዳንተ ጥቁር ነበረች ለማለት ነው። ይህ ራብ የሙሴ እህት ሜርያም (ማርያም) ሙሴ ኩሺት ኢትዮጵያዊት በማግባቱ ብትቃወም የደረሰባትን ስለሚያውቅ በዚህ ጉዳይ እኔ ላይ እንደማይቀልድ አውቃለሁ። ዛሬ በአማርኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል በእናት ቋንቋው በዕብራይስጥ ላይ ብንመለከት “ኩሽ፣ የኩሽ ምድር” እያለ ነው የሚያስቀምጠው።
ታዲያ ዛሬ ነጭ እስራኤላውያን ቤተ እስራኤላውያንን “ኩሺ” ብለው መጥራታቸው ጥቁሮች ወይም ኢትዮጵያዊ ለማለት ነው። እኛም እኮ ነጭ ስናይ “ፈረንጅ”፤ ጥቁር አፍሪካዊያንን ደግሞ ስናይ “ኔግሮ” እንደምንለው ነው። ለአብዛኞቹ እስራኤላውያን ኩሺ ማለት ጥቁር ማለት ነው።
የሞያና የክህሎት ስልጠና
እስራኤል ውስጥ ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ዩንቨርስቲዎችና 49 ኮሌጆች ይገኛሉ። አብዛኞቹ እስራኤላውያን የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፤ ይህ ግን ለአብዛኛው ኅብረተሰብ ሥራ ለመያዝ፣ ተፎካካሪ ለመሆንና ቤተሰብ ለማስተዳደር ብቁ አያደርጋቸውም። የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁናቴ እንዲህ በሆነበትም፣ በጣት የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያን ለመጀመርያም ሆነ ለሁለተኛ ዲግሪ በዩንቨርስቲዎችም ሆነ በኮሌጆች ገብተው ይማራሉ። በ2011 ዓ.ም በክነሴት (በእስራኤል ፓርላማ) በቀረበ አንድ ሪፖርት፤ ከእስራኤላውያን የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች መካከል የቤተእስራኤላዊያን ተማሪዎች ብዛት 8% ብቻ ነበር። በ2009 ዓ.ም የቤተእስራኤላውያን ከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች ብዛት 1921 የነበረ ሲሆን ፤ ይህ ከጠቅላላው ካገሪቱ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች 0.9% ነበር። የ2005 እና የ2009 ሲነጻጸር የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ከ155 ወደ 298 ጨምረዋል።


ያለፈው አመትን ሳይጨምር በጠቅላላው 2060 ቤተእስራኤላውያን የከፍተኛ ተቋማት ተመራቂዎች ሲኖሩ፤ ከነሱም 88% የመጀመሪያ ዲግሪ ሲሆን የተቀሩት ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ናቸው። በሳይንስ፣በህክምና፣በእርሻ፣በቋንቋና በመሳሰሉት የትምህርት ዘርፎች ላይ ብዙ ቤተእስራኤላውያን ሲሳተፉ አይታዩም። ይህም የሆነው የመግቢያ መስፈርቱን ብዙዎች ስለማያሟሉ ነው ።
ሌላው የአጭርና የረዥም ጊዜ የሞያ ስልጠና እየወሰዱ የተወሰኑት በሰለጠኑበት ሞያ ተሰማርተው ይገኛሉ። አቶ አልአዛር ኬ እንዳሉት የነርሲንግ፣ የልብስ ስፌት፣ የብረታብረትና የእንጨት ሥራ በመሳሰሉት እንዲሰለጥኑ ይደረጋሉ። በዚህም በሰለጠኑበት የተወሰኑት በስራ ላይ ቢሰማሩም፤ ይህ በቂ ነው ማለት አይደለም። ቢሆንም ግን ከሌላ ሀገር ከሚመጡ አዲስ ገቢ ይሁዳዊያንና አረብ እስራኤላውያን ጋር ተወዳድረው ስለሆነ መፍረድ አይቻልም። ለዛውም ሌሎቹ ከመጡበት ሀገር የስራ ልምድ ይኖራቸዋል።
መቼም መንግስት ቤተእስራኤላውያን ብቻ ሰልጥነው የሚሰሩበት የስራ ዘርፍ ይፍጠር አልያም ሌሎቹን ወደጎን አድርጎ የእነርሱን ብቻ ይመልከት ማለት አይቻልም። በዚህም ላይ አብዛኞቹ ከመማር ይልቅ ኬሴፍ (ገንዘብ) ወደሚያገኙበት ሥራ መሰማራት ይቀላቸዋል። እኔ እንደማስበውና በገሃድም እንደሚታየው የቤተእስራኤላውያን ችግር ምንጮች ነጭ ይሁዳውያን ሳይሆኑ(የተወሰኑ ዘረኞች ቢኖሩም እንኳን) ራሳቸው ቤተእስራኤላውያን ናቸው። ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ወገናቸው የችግር ምንጮች ራሳቸው ቤተእስራኤላውያን ናቸው። ወደፊት እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በዝርዝር ለማንሳት እሞክራለሁኝ። እስከዛው የተዛባ መረጃ ከማስተላለፍ እንቆጠብ እያልኩኝ እሰናበታለሁኝ። ቸር ቆዩኝ።

Read 10947 times