Saturday, 09 February 2013 12:24

የውበት ተራራ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

ምንድነው ከልቤ ሸንጐ የተቀመጠው
ልቤን እንደጡጦ - የሚመጠምጠው
ደመናው ድፍርሱ - አበባ እየረጨ
የጨለመው ሰማይ - ውበት እየነጨ
የተቀነጠሰው አመልማሎ - ፈክቶ
የደረቀው ምንጬ - በውሃ ተሞልቶ
ውስጤን የቆፈረው - ሳቅ የሚያመነጨው
ነፍሴን - በፈገግታ - ሀሴት ያስጐነጨው
ምንድነው - ነገሩ?
የፀሐይ ከንፈሯ - ከንፈሬን ሳይነካ
የጨረቃ ውበት - ተስፋዬን ሳይለካ
ምንድነው እንዲህ - የሚያረሰርሰኝ
ሰማይ ሳይጫወት - አድማሱ ሳይጠቅሰኝ
ልቤን - ቬሎ አልብሶ - ያረገው ሙሽራ
ይህ የውበት ድምቀት - የሰላም አዝመራ
አንቺ ብቅ ስትይ - ነው ወይ የተዘራ…
ይህ የፍቅር ሀውልት - ይህ ሕያው ተራራ!
ይህ የውበት ጮራ!
(8-5-2005 ዓ.ም)

Read 4746 times