Saturday, 09 February 2013 12:15

ራሳችሁ ላይ አነጣጥሩ!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ብዙዎቹ መከፋቶችና መጥፎ ስሜቶች የሚመነጩት ከፉክክር ወይም ራስን ከሌሎች ጋር በማነፃፀር ነው፡፡ ሌሎች ከኛ የተሻለ ሥራ ሰርተው ስናይ ስለራሳችን መጥፎ ስሜት ይሰማናል፡፡
ትኩረታችንን ድክመቶቻችን ላይ ባደረግን ቁጥር ስለራሳችን ፈፅሞ ጥሩ ስሜት ሊሰማን አይችልም፡፡ ሌሎች ከኛ የበለጠ መልከመልካምና ቆንጆዎች በመሆናቸው ብቻ እንከፋለን፡፡ ሌሎች ከእኛ የበለጠ ገንዘብ፣ አውቶሞቢሎችና መኖርያ ቤቶች ስላላቸው በመጥፎ ስሜት እንዋጣለን፡፡
የሥራ ባልደረቦቻችን እድገት አግኝተው እኛ በማጣታችን ሆድ ይብሰናል፡፡ ሌሎች ከኛ የበለጠ ደስተኞች በመሆናቸው ብቻ ከጥሩ ስሜት እንፋታለን፡፡
አያችሁ - ራሳችሁን ከሌሎች ጋር ማነፃፀር ካልተዋችሁ በቀር ሁልጊዜም ከእናንተ የተሻለ ሰው ማግኘታችሁ አይቀርም፡፡
እናም መቼም ቢሆን ጥሩ ስሜት አይሰማችሁም ማለት ነው፡፡ ማብቂያ በሌለው የፉክክር ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅ ይልቅ ራሳችንን ነፃ በማውጣት ህይወትን ለምን በመረጥነው መንገድ አንመራም? ሌሎች ከእኛ የሚሻሉባቸው ጉዳዮች ላይ ከማተኮርና ስለራሳችን መጥፎ ስሜት እንዲሰማን ከማድረግ ይልቅ ለምን ከሌሎች መማርና ክህሎታችንን ማሻሻል ላይ አናተኩርም?
የህይወት ቀዳሚ ግብ ማደግ እንጂ መፎካከር አለመሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡
አትኩሮታችሁን ምንጊዜም ራስን በማሳደግና ምርጡን በማለም ላይ ልታውሉት ይገባል፡፡ ይሄ ከተሳካላችሁ የማታ ማታ ትልቁን ሽልማት መቀዳጀታችሁ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2004 የአቴንስ ኦሎምፒክ ላይ በወንዶች የ110 ሜትር የመሰናክል ውድድር፤ ለቻይና የመጀመርያውን ወርቅ ያስገኘላት ቻይናዊው አትሌት ሊዩ ዚያንግ ነበር፡፡ ይሄ አትሌት በኦሎምፒክ ለቻይና አዲስ ታሪክ አስመዘገበ፡፡ የአራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮንና በውድድሩ ተፎካካሪው የነበረው አለን ጆንሰን ከውድድሩ ቢወጣ ኖሮ ውጤትህን ይለውጠው ነበር ወይ ተብሎ የተጠየቀው ዚያንግ፤ “በፍፁም! እኔ የራሴን እቅድ ብቻ ነው የምከተለው፤እናም የላቀ ውጤት ማስመዝገቤ አይቀርም ነበር“ በማለት ነው የመለሰው፡፡ አያችሁ ይሄ አትሌት ከማን ጋር ነው የምሮጠው ብሎ እንኳ አይጨነቅም፡፡ ምርጥ ውጤት ለማምጣት ብቻ በትኩረት ይተጋል እንጂ!
ምንጭ- (The Lost Secrets of Manifestation)

Read 2868 times