Saturday, 09 February 2013 12:12

“የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ አንደኛ መጽሐፍ” - ታሪክ ነው ተረት?

Written by  ኦርዮን ወልደዳዊት
Rate this item
(4 votes)

“የዚህ መጽሐፍ ዓላማ የኢትዮጵያ አዲሱ ትውልድ ማንነቱን በቅድሚያ እንዲያውቅ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ የራሱን ታሪክ በቅድሚያ ባለማወቁ ለጥራዝ ነጠቆች መሣሪያነት እንደዋለ አይተናል” ይላል - የመጽሐፉ መግቢያ የመጀመሪያ አንቀጽ፡፡ 

መጽሐፉ ከታሪክ ዘገባ ሊፈረጅ ይችላል፡፡ ሆኖም አንድ የታሪክ ጸሐፊ ከምንም አይነት የሃሳብ መዋለል ፀድቶ በተቻለ መጠን በጠንካራ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ የነበረውን “እውነት” እንዳለ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ በእውነት ላይ ተመስርቶ ከወገናዊነት ልክፍት ፀድቶ የሚጽፈው ታሪክ እውነትም ትውልድን ሊያስተምር ይችላል፡፡ በተረፈ ግን ገና ከመነሻው ወደ አንድ ጐን ያዘነበለ ሃሳብ እና እምነት ይዞ ታሪክ ለመጻፍ መነሳት በደልም ወንጀልም ነው፡፡
ታሪክ ልብወለድ አይደለም፤ተረትም ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ጸሐፊው እውነቱን ከነግሳንግሱ ይዘግባል እንጂ እንደ ልብወለድ ማጣፈጫ፣ ግነት፣ ልብ ሰቀላ ወይም ሴራ መፍጠር ወዘተ አያስፈልግም፡፡ ህጻናትን ለማማለል ሲባል እንደ ተረትም አንደበተ መልካም መሆን አያሻም፡፡ ታሪክ የሆነ፣ የተፈፀመ ድርጊት ነው፡፡ በቃ፤ ሌላ ባዕድ ቅጽል አያሻውም፡፡
ብዙውን ጊዜ ታሪክ የሚጻፈው ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ በመሆኑ የሚዘለሉ፣ ወይም ተዛብተው የሚቀርቡ ብዙ ቁምነገሮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ አንዳንዴ ባለታሪኩ እያለ ታሪክ ሊጻፍ ይችላል፡፡ ይህም ሌላ ችግር አለው፡፡
አንደኛ፤ ታሪክ ጸሐፊው የባለታሪኩ የቅርብ አሽከር ወይም ባለሟል ይሆንና የተሻለ ቁራሽ ለማግኘት ሲል ጥቂቱን መልካም ነገር እጅግ እያጋነነ፤ ምንአልባትም ቅዱስና እንከን አልባ አድርጐ ስለሚጽፈው ከታሪኩ ይልቅ የተስፈኛው ጸሐፊ ከንቱ ውዳሴ ይሞላውና እውነቱን ይሸፍነዋል፡፡ አብዛኛውን የሀገራችንን መሪዎች ታሪክ ስንመለከት ይህን እውነት እናገኛለን፡፡ የዜና መዋዕል ጸሐፊዎች ምንም እንኳ “ስራቸው ሁሉ ዋጋ ቢስ ነው” ማለት ባያስደፍርም ንጉሡ፣ ራሱ፣ ጳጳሱ፣ ወይም ሌላው ባለስልጣን ስለፈፀመው እጅግ የተጋነነ “ቅዱስ” ነገር እንጂ በህዝብና በሀገር ላይ ስላደረሰው አሰቃቂ በደል አይዘግቡም፡፡ ከዚህ የተነሳ የባለታሪኮቹ ስራ ገድል ይመስላል፡፡ ባለታሪኮቹ ግን ምን አልባትም የሳጥናኤል ቁራጮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ “የ20ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያ አንደኛ መጽሐፍ”ን ስንመለከተው በአመዛኙ የዚህ ዓይነት ስህተትና ስብከት ይታይበታል፡፡
የመጽሐፉ ርዕስ “የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” የሚል ቢሆንም የሚጀምረው ግን በ “3987 ዓመተ ዓለም ነግሣ ነበር” ከሚላት ከንግሥተ ሳባ ነው፡፡ የሚጠናቀቀው ደግሞ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ሞት፡፡ ታዲያ የት ላይ ነው የ20ኛው ክ/ዘመንዋ ኢትዮጵያ ያለችው?
ከሁሉም በላይ መጽሐፉ ግዙፍ የዘመን ስህተት ይታይበታል፡፡ ለምሳሌ ገጽ አንድ ላይ “ንግሥተ ሳባ በ3987 ዓመተ ዓለም ነገሰች” ካለን በኋላ፣ለ31 ዓመታት በስልጣን ላይ ቆይታ በ3518 ዓመተ ምሕረት ሥልጣኗን ለልጇ ለእብነ እልኪም ማውረሷን ይተርካል፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ታላላቅ የታሪክ ዝንፈቶች ይታያሉ፡፡
አንደኛው ዓመተ ዓለምንና ዓመተ ምሕረትን መቀላቀል ሲሆን ሁለተኛውና ዋናው ስህተት ደግሞ “ስልጣን ያዘች” የተባለበት ዘመንና “ስልጣኗን ለልጇ አስረከበች” የተባለበት ዘመን ርቀት ነው፡፡ ታሪኩ ሊነግረን የፈለገው ንግሥተ ሳባ ለ31 ዓመታት ስልጣን ላይ መቆየቷን ነው፡፡ ግን እኮ በ3987 ዓ.ዓለምና በ3518 ዓ.ምሕረት መሃል ያለው ልዩነት 469 ዓመት ነው፡፡ በዚያ ላይ 3518 ዓ.ምሕረትን እንኳን ንግሥተ ሳባ ታሪክ ጸሐፊውም ሆኑ አንባቢያን ገና አልደረስንበትም፡፡
“በ12ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መግሥት በዛጉየ ሥርዎ መንግሥት ጊዜ ንጉሥ አርማህ በሚገዛበት ወቅት ኢትዮጵያ በየጊዜው ከግብጽ ሊቀ ጳጳስ ማስመጣቷን ስላልወደደ ከእኛ ውስጥ ሰው ሹሙልን ብሎ ግብጾችን አጥብቆ ጠይቋቸው ነበር” (ገፅ 3)፡፡
ይህም ሌላው የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ ምክንያቱም ንጉሥ አርማህ የነበረበት ዘመንና የዛግዌ ሥርወ መንግሥት በስልጣን ላይ የቆየበት ጊዜ እጅግ የተራራቀ መሆኑ ነው፡፡ “የጳጳስ ከኢትዮጵያ ሹሙልን” ጥያቄም የንጉሥ አርማህ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ኢትዮጵያውያን ነገስታት ፍላጐትና ውትወታ ነበር፡፡
በዚህና በመሳሰሉት ህጸጾች እየተሞላ አብዛኛውን የታሪክ ወቅትም እንደማይፈለግ ወረቀት እየጨመደደ ይመጣና ገጽ ስምንት ላይ ስለዳግማዊ ምኒሊክ መተረክ ይጀምራል፡፡ እዚህ ላይም ሌላ የታሪክ ድፍረት ወይም ስህተት እናገኛለን እንዲህ የሚል፡፡
“አጼ ቴዎድሮስ፣ አፄ ተክለ ጊዮርጊስና አፄ ዮሐንስ በተወላጅነት ሳይሆን በጦር ኃይላቸው ለመንገሥ ችለዋል፡፡ መጨረሻ ላይ ዳግማዊ ምኒሊክ በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የልጅ ልጅነት ወይም በቀዳማዊ ምኒሊክ ሥርወ መንግሥት ተወላጅነት ነገሱ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያሻው ከላይ የተጠቀሱትን ነገሥታት ጉልበተኛና ያለዘራቸው የነገሱ መሆናቸውን ሲገልጽ ዳግማዊ ምኒሊክ ግን ከሰሎሞን ባላቸው መለከታዊ ደም ምክንያት ለዘውድ መብቃታቸውን ሊሰብከን መሞከሩ ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ጸሐፊው ከተሥፈኛ ዜና መዋዕል ጸሐፊዎች በምንም መልኩ አለመሻላቸውን እንገነዘባለን፡፡ ማንኛውም ፖለቲከኛ ሥልጣን ላይ የሚወጣው አንድም በህዝብ ምርጫ ነው፤ እንደ እኛና እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ደግሞ ጭካኔ በተሞላበት መንገድና በጉልበት ብቻ ነው፡፡
ዳግማዊ ምኒሊክ ለዘውድ የበቁትም “የተባረከው ‹‹የቀዳማዊ ምኒሊክ ዘር›› በመሆናቸው አይደለም፡፡ ሌላው ይቅርና የንጉሠ ነገሥቱ የሸዋ እንደራሴ የነበሩትን ደጃዝማች በዛብህን በአሰቃቂ ሞት ቀጥተው ነው ለዘውድ የበቁት፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ለሟቹ ደጃዝማች:-
“አንተም ጨካኝ ነበርህ፤ ጨካኝ አዘዘብህ፤ እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብህ” ሲባል በወቅቱ የተገጠመው፡፡ በወቅቱ ደጃዝማች በዛብህ ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ተከታዮቻቸውም በምኒሊክ ሰራዊት በሞት ተቀጥተዋል፤ እጅና እግራቸውም በጭካኔ እንዲቆረጥ ተደርጓል፡፡
ስለዚህ ወዳጄ ሆይ! መቸምና የትም ቢሆን አታላዮችና ጨካኞች እንጂ የዋሆች ሥልጣን አልያዙም፤ ሊይዙም አይችሉም፡፡ “ጻድቅ፣ ብጹእ ወዘተ” እየተባሉ የሚሞካሹትም ቢሆኑ በግብራቸው ሳይሆን በተስፈኛ ዜና መዋዕል ጸሐፊዎች የከንቱ ውዳሴ ብዕር ነው፡፡
መጽሐፉ ስብከቱን በማጠናከር “ከመለኮት” ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የሰሎሞንን ዘር በሰፊው ይዘረዝርልናል፡፡ በመሠረቱ ይህ ታላቅ ስህተት ነው፡፡ የአጼ ምኒልክ እናት እኮ የቤት ሰራተኛ (በወቅቱ አጠራር ገረድ) ነበሩ፡፡ ምኒሊክም የጠጅ ቤት አሳላፊያቸውን ደፍረው ወ/ሮ ሸዋረጋን ወልደዋል፤ ሸዋረጋም የሰለሞን ዘር ከሌለባቸው ራስ ሚካኤል ኢያሱን ወልደዋል፡፡ የት ላይ ነው ታዲያ የጠራ የበራው ደም ብቻውን ለዘውድ የበቃው?
ለነገሩማ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም የአባታቸውን ዘር እስከ ፍጻሜው ሲደረድሩ የእናታቸውን ስም ግን አሟልተው መጥራት አይፈልጉም ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ “አንድም ብቁ ክርስቲያን” መሆናቸውን ለማሳየት፣ ወይም ህዝቡን ለመደለል የተጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡ ወይም በእናታቸው ያፍሩ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ መቸም እናትን ታህል ታላቅ ዘመድ “የሺአመቤት ዓሊ” ብሎ መጥራት አይቸግራቸውም፡፡ ከዚህ ሌላ ጸሐፊው ሌላ የታሪክ ስህተትም ፈጽመዋል፡፡ እሱም ንግሥተ ሳባ ከእሷ በኋላ ወንድ እንጂ ሴት እንዳይነግሥ ደንግጋ ነበር ካሉን በኋላ ይህ ሥርዓት ከዳግማዊ ምኒሊክ ሞት በኋላ በንንገሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘውድ መጫን ምክንያት ለ2919 ዓመታት ፀንቶ የቆየው ሥርዓት መዛባቱን ይነግሩናል (ገፅ አንድና ስምንት)፡፡ ገጽ አስራ ስምንት ላይ ደግሞ ከንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በፊት 12 ሴቶች ለዘውድ በቅተው እንደነበር ያወጉናል፡፡ በዚህ የተነሳ ጸሐፊው ሃሳባቸውን እርስ በርሱ በጥፊ ያደራግሙታል፡፡

 

Read 4275 times