Saturday, 09 February 2013 11:56

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

 መልክአ ኢትዮጵያ - ፬

ዛሬ ደግሞ ፊኒክስ - አሪዞና ነኝ፡ ኢትዮጵያዊያኑ ከሃይማኖት፣ ከተፈጥሮና ከባህል ካፈነገጡ ድርጊቶች ለመሸሽና ልጆቻቸውን ከአገራቸው ባህል ጋራ ለማስተሳሰር በያሉበት ቦታ ትንሿን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ይሞክራሉ፡፡ አሪዞና - ፊኒክስ በቆየኹበት ወቅት ያስተዋልኹት ይህንኑ ነበር፡፡
ከመቶ ዓመት በፊት የተቆረቆረችው ፊኒክስ እንደ ታላላቆቹ የአሜሪካ ግዛቶች ሕንጻ በሕንጻ ባትኾንም በቅርብ ጊዜ ተመሥርተው ፈጥነው ካደጉ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ሜዳማ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ያላት ‹‹በረሐማዋ ከተማ›› ይሏታል፡፡ እንደ ሬኖ ያለችውን ከተማ ያላዩ ኢትዮጵያውያን ‹‹እዚህ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ ነው›› ይላሉ፡፡

በተጓዝኹባቸው የአሜሪካ ግዛቶች ዘመድ ወዳጆቼን መፈለግና ማግኘት ከቡድኑ አባላት ሁሉ በተለየ የእኔ አንዱ መታወቂያ ነበር፡፡ ፊኒክስ በገባሁ ማግሥት÷ በዕለተ እሑድ ጠዋት÷ ጓደኛዬ ነፂ ደቡባዊ ፊኒክስ ወደሚገኘው ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይዛኝ ለመሄድ ከእኔ ዘንድ ደረሰች፡፡ ነጺን የተመለከቱ፤ የቡድኑ አባላት ‹‹እዚህም ባለዘመድ ነሽ?›› ሲሉ ነበር በመገረም የጠየቁኝ፤ አንዳንዶቹም ‹‹ዘመደ ብዙ በመኾንሽ በእውነት አስቀንተሽናል›› ብለውኛል፡፡ 

ነጺ እንደገለጸችልኝ፣ ዕለቱ ሰንበት ስለሆነ የአሪዞና ጎዳናዎች ጭር ብለዋል፡፡ከጥቂት ተሽከርካሪዎች በስተቀር በመንገዱ የሚታይ መኪና የለም፡፡ በእግሩ የሚዘዋወር ሰው ማየትማ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ጸጥ ረጭ ብሏል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ መድረሳችን ምንም ጠቋሚ ምልክት በሌለበት አንድ ቅጽር መኪናዋን ሰተት አድርጋ አስገባቻት፡፡ ዙሪያውን የቆሙትን በርካታ መኪኖች በማየት ብቻ ቦታው የቤተ ክርስቲያኒቱ የመኪና ማቆሚያ መኾኑን ጠረጠርኹ፡፡ ከመኪናው ወርደን ትሙክ ትሙክ የሚለውን የግቢውን አቧራ እየረገጥን ከቅጽሩ የሚያወጣንን ጎዳና ተያያዝነው፡፡
ለመኪና ማቆሚያነት የሚያገለግለው ባዶ ቦታና ቤተ ክርስቲያኑ ያለበት ግቢ ከእነ ቤቱ በ180 ሺሕ ዶላር መገዛቱንና ክፍያው ምእመናኑ ባሰባሰቡት አስተዋፅኦ በሁለት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተከፍሎ መጠናቀቁን አጫወተችኝ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ከረዳን ደግሞ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ለመገንባት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎች እየተሠራ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናችንን እንገነባለን›› አለችኝ በሚያስተዛዝን ድምፅ፡፡

ወደ ዋናው የቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ስንጠጋ በግቢው ውስጥ ሰፊ ድንኳን ተጥሏል፡፡ በ29 ዓመቷ በድንገት ያረፈች ወጣት የ80 ቀን መታሰቢያ ተዝካር እንደ ኾነ ተነገረኝ፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ከትምህርቷ ጎን ለጎን ቤተሰቦቿንና ቤተ ክርስቲያኑን በመርዳት ትታወቅ እንደነበር የተነገረላት፣ ውልደቷም ዕድገቷም እዚያው አሜሪካ የነበረው ወጣት ሜሪ አርኣያ፣ የአምስት ዓመት ልጇን የት/ቤት ምረቃ ለማክበር ቤተሰቦቿን አሳፍራ ልጇ ት/ቤት በር ላይ ስትደርስ ነበር ካቆመችው መኪና መውረድ አቅቷት እዛው ሸርተት ብላ ሕይወቷ ያለፈው፡፡ 
ዕለቱ የ80 ቀን መታሰቢያ ቢኾንም ቤተሰቦቿ ሐዘናቸው ገና እንዳልወጣላቸው ያስታውቅ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የሟች ሜሪ አባት ከወራት በፊት ከወንድሙ ጋራ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያለፈው የዶቼ ቬሌ ጋዜጠኛ ታደሰ እንግዳው አጎት ናቸው፡፡ የሁለቱን ወንድማማቾች ሐዘን ሳይረሱ የልጃቸው ተጨመረባቸው፡፡ በሰው አገር ሐዘን ቢደራረብባቸውም ከቤተ ክርስቲያን ወዳጆቻቸው ጋራ እየተወጡት እንደኾነ ያስታውቃል፡፡ ታሪኩን ከሰማሁ በኋላ እኔም ጠጋ ብዬ ‹‹እግዜር ያጽናችኹ›› ስል መጽናናትን ተመኘኁላቸው፡፡ ጋዜጠኛ ታደሰም ወዳጄ እንደነበር ነግሬ እንደገና ሐዘናቸውን ቀሰቀስኹ፡፡ በአነጋገሬ ብጸጸትም ከማዘን ያለፈ ላደርግ የቻልኩት ነገር አልነበረም፡፡
ከድንኳኑ ወጥቼ ያወለቅኹትን ጫማ መግቢያ በሩ ላይ ከተደረደሩት ጋራ ቀላቅዬ መጠነኛ የቪላ ቅርጽ ወዳለው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ዘለቅኹ፡፡ በ13 እና 14 ዓመት ዕድሜ የሚገመቱ አዳጊ ዲያቆናት ዝማሬ እያቀረቡ ነበር፡፡ ከሕፃን እስከ አዛውንት በዐይን ግምት ወደ 250 የሚጠጉ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተገኝተዋል፡፡ በየሰንበቱ እሑድ የማይታጎለው መንፈሳዊ መርሐ ግብር የሚጀመረው ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ ነው፡፡
ዕድሜያቸው ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት የሚገመቱ ሕፃናት በቤተ መቅደሱ በተደረደሩት መቀመጫዎች የኋለኛ ክፍል ተቀምጠው በወላጆቻቸው ስልክ ጌም ይጫወታሉ፡፡ አንዷን ልጅ ለአራት ከበው ቪዲዮ መሰል ነገር የሚያዩም ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በጆሯቸው ማዳመጫ ሰክተው ያዳምጣሉ፡፡ በወላጆቻቸው እቅፍ ያሉ ጨቅላ ሕፃናትም ነበሩ፡፡ ሁሉም በሰልፍ ገብተው ልጆቻቸውን ሲያስቆርቡ ተመልክቻለኹ፡፡ ምእመናኑ ከአገራቸው ምን ያህል ቢርቁ እምነታቸውን ለማጽናት ባሉበት እየተሰበሰቡ ሥርዐቱ በሚያዘው መሠረት የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ነጠላቸውን ተከናንበው ዝማሬ የሚያቀርቡት ዲያቆናት እዚያው አሜሪካ የተወለዱና ያደጉ ቢኾኑም ግእዝና አማርኛ ጠንቅቀው እንዲያውቁ በቤተሰቦቻቸው ጥብቅ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው ተረድቻለኹ፡፡
ጸሎተ ቅዳሴው፣ ትምህርተ ወንጌሉና ዝማሬው እንዳበቃ ምእመናኑ ለመልእክት እና ማሳሰቢያ ዐረፍ ብለው እንዲቆዩ ከመድረኩ ተነገረ፡፡ እኔም አብሬ ቁጭ አልኹ፡፡ መልእክቱ ተጀመረ፤ ‹‹እገሌ የተባለ ሰው ስለ ታመመ ቤቱ እንዲህ ያለ ቦታ ነውና ጠይቁት››፤ ‹‹እገሌ የተባለ ሰው ልጁን በዚህ ቀን ክርስትና ስለሚያሥነሳ እባካችኁ ቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ አቋቁሙኝ ብሏችኋል››፤ ‹‹እገሌ ወንድሙን ስለተረዳ ከቻላችኹ ዛሬ ሄዳችኹ ልቅሶ እንድትደርሱ›› የሚሉና የመሳሰሉ የማኅበራዊ ኑሮ ግዴታዎችን ለመወጣት የሚያተጉ መልእክቶችና ማሳሰቢያዎች ነበሩ፡፡
በመጨረሻ መልእክቱን ያስተላለፉት የደብሩ አስተዳዳሪ አባ አብርሃም ድጋፌ ቃለ ምዕዳን የሚባለውን ማሳሰቢያና ምክር አዘል ቃል ሰጡ፡፡ ‹‹እባካችኁ ልጆቻችኹን ከሕፃንነታቸው ጀምራችሁ ቤተ ክርስቲያን እያመጣችኹ ሥርዐቱን አስተምሯቸው፤ እርስ በእርስም ከአሁኑ እያስተዋወቃችኹ አሳድጓቸው፤›› ሲሉ አበክረው ተናገሩ፡፡
የአባ አብርሃም ቃለ ምዕዳን ቀጥሏል፡- ‹‹ልጆቻችኹ ኋላ ከዚህ ውጭ ኾነው ያድጉና አልባሌ ነገር ይለምዱባችኋል፤ ከአሁኑ ተዋውቀው ካላደጉ የትዳር አጋርም ያጣሉ፤ አሁን የምናያቸው፣ የምንሰማቸው ችግሮችም ይደርስባቸዋል፤ እንዲህ ባለ ከአገር ርቀው በሚኖሩበት ቦታ ቤተ ክርስቲያን ከጸሎት ቦታነቷ በተጨማሪ ማኅበራዊ ችግሮቻችኹን እርስ በርስ ትፈቱበታላችኹ፤ ሐሳብም ትለዋወጡበታላችኹ፤ ስለዚህ እስከ አሁን ያልመጡ ወደዚህ እንዲመጡ፣ የመጣችሁም አጠንክራችኹ እንድትይዙት፣ ልጆቻችሁም እርስ በርስ እንዲተዋወቁ አድርጉና አሳድጉ፡፡››
አባ አብርሃም በዕለቱ የተዘጋጀው ጠበል ጸዲቅ በመደበኛ ጊዜ የሚደረገው ተዝካረ ሰንበት ሳይሆን ቀደም ሲል በተላለፈው ጥሪ መሠረት የሟች መታሰቢያ (ነፍስ ይማር) መኾኑን ገለጹ፡፡ ሟችን በደግ አስታውሰውና በጎ ምግባሯንም ዘርዝረው ምእመኑን ለጠበል ጸዲቁ በመጋበዝ ቃለ ቡራኬያቸውን አስተላልፈው አበቁ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የኾኑ ምእመናን ተሰባስበው ያየኋቸው በፊኒክስ ብቻ አልነበረም፡፡ ቨርጂኒያን በምትጎራበተው አርሊንግተን ከተማ በሚገኘው ፍኖተ ጽድቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ወደ 150 የሚጠጉ ምእመናን ከእነልጆቻቸው ተገናኝተው ሲያስቀድሱ ተመልክቻለኹ፡፡ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ይዞኝ የሄደው ዘመዴ፣ ‹‹ልጅ ሆኜ አገር ቤት ቤተ ክርስቲያን መሄድ አልወድም ነበር፤ በማይገባኝ ቋንቋ ለሰዓታት ጸሎተ ቅዳሴ ሲደረግ መቆም ይከብደኝ ስለነበር፡፡ በቤተሰቦቼ ጉትጎታ እንኳን ብሄድ እግሬንና ወገቤን ስለሚደክመኝ ሰበብ ፈልጌ እቀር ነበር፡፡ እያደግኹ ስመጣማ እኔና ቤተ ክርስቲያን ተለያየን›› አለኝ የልጅነትና የአዳጊነት ዘመኑን በማስታወስ፡፡
ከአገር ከራቀና ቤተሰብ ከመሠረተ በኋላ ግን ለልጆቹ ሲል ቤተ ክርስቲያን ማዘውተር መጀመሩን ነገረኝ፡፡ ይህ ዘመዴ ልጆቹ ወደፊት ከሚጠብቃቸው ከባድ ፈተና ለመከላከል ብቸኛው መፍትሔ ልጆችን በእምነት ጥላ ሥር ማሳደግና ባደጉም ጊዜ ለእምነታቸው ሥርዐት ያላቸው ተገዥነት እንዲቀጥል ማድረግ ኾኖ አግኝቶታል፡፡
ልጆችን በመንፈሳዊ ሥርዐት እየኮተኮቱ ማሳደጉ ወላጆች ከሚሰጉላቸው ነገር መቶ በመቶ ያስጥላቸዋል ማለት ባይቻልም ቢያንስ መጥፎ የተባሉ ነገሮችን ከእምነቱ ትምህርትና ሥርዐት አንጻር እያያያዙ ለመምከር አመቺነቱ እንደታመነበት አጫወተኝ፡፡ ‹‹አለበለዚያ ትምህርታቸውን አቋርጠው ጫትና ሺሻ ቤት ሊያዘወትሩ፣ ሲከፋም በሐሺሽ ሱስ ተጠምደው በወንጀልና በዕዳ ተዘፍቀው፣ ከተመሳሳይ ፆታ ጋራ ግንኙነት ጀምረው ልታገኛቸው ትችያለሽ፤ ያን ጊዜ በምክር ላስጥል ብለሽ ብትነሺ በቀላሉ የሚሳካ አይኾንም›› አለኝና ጥቂት አሰብ አድርጎ፣ ‹‹ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በራሳቸው መንገድ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ሰዎች ልጅ አይዋጣላቸውም ማለቴ ሳይኾን ለእኔ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በበጎ የሚታነፅበት ተመራጩ ማእከል ኾኖ አግኝቸዋለሁ፤›› አለኝ፡፡
በልጅነቱ አገር ቤት ሳለ አልገባ ብሎ የሚያስቸግረው ጸሎተ ቅዳሴም አሁን ገብቶታል፡፡ አርሊንግተን በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያሉ ካህናት የሚቀድሱት ያው በግእዝ ቢኾንም ከፍ ብሎ በተሰቀለው ፕሮጀክተር በግእዝ፣ በአማርኛና በእንግሊዘኛ የሚጻፈው ትርጉም የቅዳሴውን ይዘት እንዲረዳ አግዞታል፡፡
በተለያዩ ግዛቶች ካገኘኋቸው ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ በዕለተ ሰንበት እሑድ ከማይሰርዙት ፕሮግራማቸው አንዱ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድን ነው፡፡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችም እንዲሁ የራሳቸው የአምልኮ ስፍራ አላቸው፡፡ ምንም ዐይነት የኢትዮጵያውያን ቤተ ክርስቲያን በሌለበት ሬኖ ከተማ ‹‹የኔቫዳ ስቴት ዩኒቨርስቲ›› ቅጽር ውስጥ በሚገኘው የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን አንድ ቤተሰብና አንድ ወንደላጤ ኢትዮጵያውያን ላለፉት ዐሥር ዓመታት ከፈረንጆቹ ጋራ አብረው እያመለኩ እንደኾነ አጫውተውኛል፡፡
አቴንስ በተባለች ትንሽ ከተማ ትምህርቱን ከሚከታተለው ዳዊት የተባለ ጋዜጠኛ ጓደኛዬ ጋራ ዋሽንግተን ዲሲ ተገናኝተን ስለዚሁ ጉዳይ አንሥተን ስንጫወት፣ ዘወትር እሑድ ከባለቤቱ ጋራ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሄዱ ነገረኝ፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ሕይወቱ አልፎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለቀብር በሄደ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ስም ያላቸው በርካታ የሟቾች መታሰቢያ ሐውልት ተመልክቶ መደንገጡንና ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው ሲያልፍ የሁሉም አስከሬን ወደ አገር ቤት ይላካል የሚለው ግምቱ የተሳሳተ እንደነበር መረዳቱን ገልጾልኛል፡፡ ከአገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በመካከላቸው ያለውን የብሔርና የፖለቲካ ልዩነት አጥብበው ባሉበት መሰባሰብ እንዳለባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ማሰብ የጀመረው አሜሪካ እንደኾነ ነግሮኛል፡፡
የፊኒክስ ደብረ ምጥማቅ ቅድስተ ማርያም ፕሮግራም ተጠናቆ ከአዳራሹ ስንወጣ፣ ሁሉም ሰው እርስ በርስ ሰላምታ እየተለዋወጠ የ80 ቀን ተዝካሩ ወደተዘጋጀበት ክፍል ያመራል፡፡ ነጺ ካገኘችው ሰው ጋራ ሁሉ ታስተዋውቀኝ ገባች፡፡ የደብሩን አስተዳዳሪ አባ አብርሃምን ተዋወቅኋቸው፡፡ እንግዳ መኾኔን ብትነግራቸውም እርሳቸው አስቀድመው ያወቁ ይመስላሉ፡፡ ‹‹አንድ ሰው ጨመርሽልና›› አሏት ከትውውቃችን አስቀድሞ አብረው እንዳዩን፡፡ ‹‹ኧረ ተመላሽ ናት አባ፤ ለሥራ ነው የመጣችው›› አለቻቸው፡፡ ‹‹ትዳር መሥርተሻል?›› ጠየቁኝ፡፡ ‹‹አዎን አባ ቆይቻለኹ›› አልኋቸው፡፡ ሣቅ አሉና ‹‹እኔ ደግሞ ገና ከሩቁ ሳይሽ ልድርሽ እያሰብኹ ነበር፤” አሉኝ ሐሳባቸው ያለመሳካቱ የፈጠረባቸውን ስሜት በፈገግታቸው እየሸፈኑ፡፡
‹‹ታዲያ እዚሁ ቀርተሽ ባለቤትሽን ብታመጪው አይሻልም?›› ሲሉኝ ወደ አገሬ መመለሱን እንደምመርጥ ነገርኋቸው፡፡ የትዳር አጋር ማግኘት አንዱ ማኅበራዊ ችግራቸው መኾኑን ተረዳኹ፡፡ ለነገሩ ተረዳድተው ካልተጓዙት ኑሮው ከቋጥኝ የከበደ ይመስለኛል፡፡ የአኗኗሩ ክብደት ሠርቶ ችግርን መወጣቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ብቸኝነቱንም ይጨምራል፡፡ ፈገግታ ከፊቷ የማይለያት ነጺ፣ ‹‹አባ ለማን እንዳሰቡሽ ባወቅኹ›› አለችኝ፡፡ አባ አብርሃም ቤተ ክርስቲያኑን ከማስተዳደር ባሻገር የሰዎች ኑሮ መሠረት እንዲይዝና እንዲጸና በተቻላቸው መጠን እንደሚጣጣሩ ነገረችኝ፡፡
ተዝካሩ ወደተዘጋጀበት ቤት ገባን፡፡ በአገር ቤት ከማውቀው የተዝካር ዝግጅት የሚለይ ነገር አላገኘኁበትም፡፡ ነጠላቸውን አዘቅዝቀው ፀጉራቸውን በጥቁር ሻሽ የሸፈኑ ሴቶች ቀይና አልጫ ፍትፍት የያዙ የወጥ ‹ሰታቴያቸው›ን ከፊታቸው ደርድረው ሰልፈኞቹ በሳሕን በያዙት እንጀራ ላይ ወጥ ይጨልፋሉ፤ በሰልፉ ተራ ደርሶት ድርሻውን ያገኘ ምእመን በአዳራሹ አግዳሚ ወንበሮች ላይ በትይዩ ተቀምጦ በለዘብታ እየተጨዋወተ ይመገባል፡፡ ድንኳን ውስጥ መቀመጥ የፈለገ ደግሞ ሳሕኑን እየያዘ ይወጣል፡፡ ዕለቱ የ80 ቀን መታሰቢያ በመኾኑ መስተንግዶው በድንኳን ጭምር ኾነ እንጂ ሰንበቴ ቤቱን በየሳምንቱ እንደሚገለገሉበት ነገሩኝ፡፡በአራት ወር አንድ ጊዜ በሚደርሳቸው ተራ መሠረት አራት አራት ምእመናን አንድ ላይ እየኾኑ በየሳምንቱ እሑድ በሰንበቴ ቤቱ ያበላሉ፡፡ እንደ አገር ቤቱ ጠጅ ባይጥሉም ጠላ ባይጠምቁም የታሸገ ውኃ፣ ለስላሳና ትኵስ መጠጦችንም ያቀርባሉ፡፡ መብል መጠጡ ማኅበራዊ ኑሯቸውን ይበልጥ ስለሚያስተሳስርላቸው እነሱም አጠናክረው ይዘውታል፡፡

በሰንበቴ ቤቱ ተቀምጠን መሐራውን እየተቃመስን ከመግባባታችን የተነሳ ባለቤቷንና ልጇን ካስተዋወቀችኝ መልከ ግቡ ወይዘሮ ጋራ ጨዎታ ይዘናል፡፡ በቅርብ ስለደረሰባት ከባድ ሐዘን አጫወተችኝ፡፡ እርሷና ወላጅ እናቷ ስደት ከወጡ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ እናቷ በሕይወት እያሉ አብራቸው አገር ቤት መጥታ ዘመዶቻቸውን አልተዋወቀችም፡፡ ከእርሷ ውጪ ልጅ ስላልነበራቸው ደግሞ ፊታቸውን ወደ አገር ቤት መመለስ እንዳለባቸው ለደቂቃም አላሰበችም፡፡ ከእርሷው ጋራ ኖረው፣ እርሷኑ ኩለውና ድረው፣ ስትወለድ አርሰው ልጆቿን አብረው አሳድገው ቀሪ ዘመናቸውን ብቻቸውን ለመኖር ፈለጉ፡፡ ፈቃዷን ከመስጠት በቀር ምንም ማድረግ ስላልቻለች ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ እናቷ ደስተኛ ኾነው ብቻቸውን ሲኖሩ ቆዩ፡፡

እናቷ ምን ቢፈጠር በሰንበት እሑድ ከዚች ቤተ ክርስቲያን ቀርተው አያውቁም፡፡ አንድ ዕለት ግን ዐይኗ በር በሩን ቢያይ ሊመጡ አልቻሉም፡፡ ማለዳ ተደዋውለው ደግሞ እንደሚመጡ ነግረዋታል፡፡ ጥርጣሬ ስለገባት ሰው ትልክባቸዋለች፡፡ የፈራችው ነገር አሟቸው ሊኾን ይችላል የሚል ቢኾንም እናቷን ያልገመተችው አጋጥሟቸዋል፡፡ከመታጠቢያ ቤት እንደ ወጡ ወድቀው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ 
የአሟሟታቸው ሐዘንና ጸጸት ተደማምረው ልቧን ሠበሩት፤ መጽናናትም አልኾነላትም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ የእናቷን ዘመዶች አፈላልጋ ሐዘኗን ከእነርሱ ጋራ ለመካፈል ትወስንና ብድግ ብላ ትመጣለች፡፡ ያሰበችው አልተሳካም፡፡ እርሷ ኢትዮጵያ በደረሰችበት ጊዜ ገጠር የሚገኙት የእናቷ ዘመዶች ለጾም ሱባኤ ገብተዋል፡፡ ‹‹አዲስ አበባ እንደደረስኹ የማውቀው ዘመድ ስላልነበረኝ ያረፍኹት የባለቤቶቼ ዘመዶች ዘንድ ነበር፡፡ ከእናቴ ዘመዶች እንዲያገናኘኝ አደራ ያልኹት ሰው በሱባኤ ምክንያት ሊያገናኘኝ እንደማይችል ስለነገረኝ ዝም ብሎ ከመጠበቅ ውጭ አማራጭ አልነበረኝም›› አለችኝ፤ ወቅቱን በማስታወሷ ልቧ በሐዘን ተሠብሯል፡፡
‹‹አንዳንድ ቀን ከቤት እወጣና መሐል መንገድ ላይ ቆሜ አለቅሳለኹ፡፡ በደኅና ጊዜ እናቴን ይዤ ብመጣ ኖሮ እንዲህ ያለ ባይተዋርነት እንደማይሰማኝ አስባለኹ፡፡ የእናቴን አሟሟት ሳስበው ደግሞ የባሰ ሆድ ያስብሰኛል፡፡ ዘመዶቿን ሰብስቤ አብሬያቸው እሪሪ ብሎ ማልቀስ ያምረኛል፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ኾኖ ርቄ ስለከረምኹ ባይተዋርነት ይሰማኛል፡፡ ሳለቅስ ውዬ ሳለቅስ ይነጋል፡፡›› ሐዘኗን ስትነግረኝ እንባዬ እየተናነቀኝ በጆሩዬ ብቻ ሳይኾን በልቤ መስማቴን ቀጠልኹ፡፡
ከሥራ ቦታዋ ያገኘችው ፈቃድ ወደ መጠናቀቁ ሲቃረብ የእናቷ ዘመዶች ከሱባኤ እንደ ወጡ ተነገራትና ወደዛው አመራች፡፡ የነበራት ጊዜ አጭር ቢኾንም ዘመዶቿን ተዋውቃ እርሟን ከእነርሱጋ አውጥታ ሐዘኗ በጥቂቱ ቀሎላት ጥሩ ጊዜ አሳልፋ ተመለሰች፡፡ ወዲያውም ለራሷ ቃል ገባች - ‹‹በቅርብ ጊዜ ውስጥ ልጆቼን ይዤ ተመልሼ እመጣለኹ፡፡ ልጆቼ ሲያድጉ እንደኔ ባይተዋር እንዳይሆኑ በተቻለኝ መጠን እየወሰድኹ ከዘመድ እቀላቅላቸዋለኁ›› ስትል፡፡ ለእኔ ደግሞ ዕለት በዕለት የምሰማው የማየው ነገር ሁሉ ተደማምሮ ከአገር የመራቅ አበሳው ይገዝፍብኝ ጀመር፡፡
በዚች ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሰንበቴ ቤት›› አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጬም በየከተማው ከገጠመኝ÷ ‹‹አገር ቤት እንዴት ነው? የኑሮ ውድነቱን እንዴት ነው የምትቋቋሙት? ፖለቲካውስ? ለምን መጣሽ? ትመለሻለሽ? እዚህ ለምን አትቀሪም? አገር ቤት ጥሩ ሥራና ጥሩ ኑሮ ካለሽ ግን እዚህ ቅሪ ብዬ አልመክርሽም›› ከሚለው ተመሳሳይ ጥያቄ አላመለጥኹም ነበር፡፡ መልስ ላገኘኁለት ስመልስ፣ ምላሽ ላጣኹለት ደግሞ በዝምታ ሳልፍ ሰንብቼ ተመልሻለኹ፡፡
እስቲ ግን እኔ ስጠየቅ ከከረምኋቸው ጥያቄዎች አንዱን ልጠይቃችኹ÷ ‹‹የኑሮ ውድነቱን እንዴት ነው የምትቋቋሙት?›› (ይቀጥላል)

 

 

Read 5249 times Last modified on Friday, 15 March 2013 07:36