Print this page
Saturday, 09 February 2013 11:32

የብሮድካስት ባለስልጣኑ ውሳኔ እና የሕገ መንግስቱ ዋስትና ምንና ምን!?

Written by  ገዛኸኝ ፀ.
Rate this item
(0 votes)

“አዲስ ታይምስ” ወደ ፍርድ ቤት ለማምራት የመወሰኑ አንደምታ
ለሐሳብ ነፃነት ከመሠለፍ ለ”ዳቦ” መሠለፍ፣ የዜጐች የምርጫ ጉዳይ ከሆነ…

ባለፈው ሣምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ፣ “አዲስ ታይምስ” መጽሔት ከህትመት መታገዱን አንብበናል፡፡ የብሮድካስት ባለሥልጣኑ መስሪያ ቤት መጽሔቱን ለማገድ ሦስት ምክንያቶች እንዳስገደዱትም ተገልጿል፡፡ እነሱም፣ አንደኛ የአክሲዮን ባለንብረቶች ሲቀያየሩና የአድራሻ ለውጦች ሲደረጉ ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባለማሣወቅ፣ ሁለተኛ ለብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመፃሕፍት ኤጀንሲ የመጽሔቱን ኮፒዎችን ባለመስጠትና ሦስተኛ ምንጩ በማይታወቅ ገንዘብ በመጠቀም የሚሉ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ 

የብሮድካስት ባለስልጣኑ፣ መጽሔቱ ግዴታዎቹን ባለመውጣቱ አገድኩት ቢልም፣ የመጽሔቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስጌን ደሳለኝ “የአክሲዮን ባለቤትነትና የአድራሻ ለውጥ ሲያደርጉ በጊዜው በደብዳቤ ማሳወቃቸውን፣ለኢትዮጵያ ቤተመፃሕፍት ወመዘክር ሁለት ሁለት ኮፒ ያስገቡበትን ደረሰኝ ለባለሥልጣኑ ማቅረባቸውን›› ይናገራል፡፡
ባለሥልጣኑ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ስለመጠቀማቸው አለኝ ያለውን መረጃም ከእውነት የራቀ እንደሆነ፣ ያስረዳል፡፡
እዚህ ላይ የባለሥልጣኑን የእግድ ውሳኔና ለውሳኔ ያበቁትን ሦስት ምክንያቶች ተገቢነት፣ ተጠያቂያዊነትና ህገመንግስታዊ የህግ መሠረት ከወቅቱ ሀገራዊ አውድ ጋር እያናበቡ መሄስ የዚህ ጽሑፍ ተቀዳሚ ዓላማ ነው፡፡ በርግጥ፣ የ”አዲስ ታይምስ” እግድ የዚህ ጽሑፍ መነሻ እንጂ መድረሻ አይደለም፡፡ ሃሳብ በመግለጽ ነፃነት ዙሪያ ብዙ የገነገኑ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉንና፡፡ በቅርብ ጊዜ በአምባገነን ሥርአት የተፈጠሩ የሚመስሉን ግን፣ በጊዜ እርሾ የራሳቸውን መልክ እየያዙ ለነፃነት ያለንን ግምት የሚወስኑብን የአስተሳሰብና የአሠራር ዘልማዶች በተለያዩ ማሳያዎች ለማመልከት መሞከርም አማራጭ ብቻ አይመስለኝም፤ እንደውም ዋናው ጉዳይ ነው፤ (በሌላ ጊዜም እመለስበታለሁ፡፡) እዚህ ላይ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደማመጥ ባህላችንን አለመጠየቅ ከባድ ይመስለኛል፡፡
ነገሬን ከብሮድካስት ባለሥልጣኑ ሃላፊነትና ወሰን እንጀምር፡፡ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ 531/1999 ዓ.ም በግልጽ እንደደነገገው፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስርጭት አገልግሎት ብቻ እንደሚመለከት ተገልጿል፡፡ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን መቆጣጠር የሚያስችለውን ሥልጣን በአዋጅ ተሠፍሮና ተደንግጐ እንዳልተሰጠው የብሮድካስት አገልግሎት አዋጁን በማንበብ በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፤ ይህ ማለት ግን ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በጓሮ በርም ቢሆን ይህን ተጨማሪ ሥልጣን ሊጐናፀፍ አይችልም አያስብልም፡፡
የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ያልተፈቀደለትን ሃላፊነት እንዴት ይሠራል ብለን መሟገት (ከሕሊናችን ጋር ማለቴ ነው) ባንችልና “ባይገባም” እንኳ፣ በየትኛውም መንገድ ያገኘውን ሥልጣን ሲጠቀም፣ ህገመንግስታዊ መሠረት ሊኖረው ይገባል ማለትም ግድ ይላል፡፡ በተለይ በምንም መልኩ የህግ አውጪነትንና የህግ ተርጓሚነትን ሚና ሊጫወት እንደማይችል ቢያንስ በመርህ ደረጃ ይታወቃል፡፡
የ “አዲስ ታይምስ” መጽሔትን ለማገድ ካቀረባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ፣ “ምንጩ የማይታወቅ ገንዘብ መጠቀም” የሚል ነው፡፡ ከቀረቡት ሦስት ምክንያቶች መጽሔቱ በቀላሉ ማስረጃ አጣቅሶ የማይሞግትበት ምክንያትም ይኸው የገንዘብ ጉዳይ ነው፡፡ የባለሥልጣን መስሪያቤቱም ይበልጥ አጽንኦት የሰጠው ይኼንኑ ምክንያት ነው፤ “አሁን በግልጽ ይፋ ባናደርግም መረጃው አለኝ” በማለት፡፡ በፀረ ሽብር አዋጁ ለመወንጀልም ይኸው ምክንያት የበለጠ ቅርብ ነው፡፡
መጽሔቱ ተግባራዊ አላደረጋቸውም የተባሉት እክሎች በራሳቸው፣ መንግሥትና ህዝብን ይኼን ያህል ይጐዳሉ ተብሎ አይታሰብም፤ ለምሣሌ ለመወዘከር ሁለት ኮፒ አለማስገባት በራሱ ወንጀል አይደለም ማለቴ ነው፡፡ ግን ፣ መጽሔቱ ይዞት የሚወጣው ይዘት (መረጃ) ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና በሀገር ላይ ሽብር የማይፈጥር መሆኑን ለመቆጣጠር የተባሉት ምክንያቶች በወጉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ሽመልስ ከማል “አዲስ ታይምስ” የታገደው ባቀረበው ይዘት ሳይሆን በአስተዳደር ጉዳይ ነው ያሉትን ልብ ይሏል፡፡
መጽሔቱ በሚያቀርበውም ይዘት ሊጠየቅ ቢችልም፣ ከመጠየቅ ይልቅ ያለመጠየቅ እድሉ በጣም ሰፊ እንደሆነ በመርህ ደረጃ መገመት አይከብድም፤ በህገመንግሥቱ ላይ በመፃፋቸው ሳይሆን እንዴት “ሾልከው” ሊፃፉ እንደቻሉ የሚገርሙን አንቀጾች አሉ፤ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት፣ አንፃራዊ ገደብ ያለው እስከማይመስለን ድረስ በወጉ ሰፍረዋል፤ በህገመንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡ ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም አይነት መረጃና ሃሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል” ይላል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 3 ላይ በተለይ “የፕሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙሃን…ነፃነት ተረጋግጧል” በማለት ያስረግጣል፤ “የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን” (ያሰመርኩበት እኔ ነኝ) በማያሻማ መንገድ ደንግጓል፡፡
የህመት ሚዲያዎች እንዲፈፅሟቸው የሚያስገድዱ መለኪያዎች እና/ወይም ህጐች የሚያስፈልጉት በዋናነት በሚያነሱት ይዘት የሌሎች በሰላም የመኖር መብቶችን ደፍጥጠው የችግር ምንጭ እንዳይሆኑ በሚል እንደሆነ ይነገራል፡፡ ህገመንግሥቱ ደግሞ፣ ይዘታቸውም ቢሆን “በማንኛውም መልክ” በቅድሚያ ሊመረመር እንደማይችል ዋስትና ይሰጣል፡፡
የብሮድካስት ባለሥልጣኑ ግን የመጽሔቱን ዋነኛ ጉዳይ ማለትም የሚያቀርበውን ይዘት (ሃሳብ) ሳይሆን፣ የይዘቱን “ትክክለኝነት” ለመቆጣጠር ያስችላሉ በተባሉ ደንቦቹ ሳቢያ፣ መጽሔቱን እንዳይታተም ማገዱ ምን ይባላል?
የብሮድካስት ባለሥልጣኑ በዋናነት “ያሳሰበው” ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ጉዳይም፣ መጽሔቱን እንዳይታገድ የማድረግ አቅም የለውም ማለት ይቻላል፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እንደሠጋው ገንዘቡ ከህገወጥ ቡድኖች የተገኘ ቢሆን እንኳን፣ መጽሔቱ የቡድኖቹን አጀንዳ ለማራገብ፣ የገንዘብ ምንጮቹን “ህገወጥ” አቋም ለማራመድ መሞከሩ እስኪረጋገጥ ድረስ፣ የገንዘብ ምንጭ አለመታወቁ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ መጽሔት እንዳይታተም እስከማድረግ አያደርስም፡፡ የብሮድካስት ባለሥልጣኑ፣ የዚህን ያህል የሚያሰጋው ጉዳይ ከሆነ የመጽሔቱን ባለቤቶችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረግ አይችልም? በመሠረቱ ግን ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብን መጠቀም ወንጀል ነው? ከሆነስ ተጠርጣሪው መጽሔት ወንጀለኛ መሆኑን የሚፈርደው ፍርድ ቤት መሆኑ ቀርቷል? እዚህ ላይ የብሮድካስት ባለሥልጣኑ፣ የህግ አውጪንም የህግ ተርጓሚንም “ሥልጣኖች” መወሰዱ ግልጽ ነው፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ የወንጀል ጉዳይ ነው፡፡ ወንጀለኛን ቀጥተው የሚያስተምሩ የወንጀለኛ መቅጫ ህግና ህግ የመተርጐም ሥልጣን የተሰጣቸው ፍርድ ቤቶች አሉ፡፡
የሙያ ማረጋገጫ ፍቃድ እድሳት ለመከልከል የሚያስችል ወንጀል ካለ የፍርድ ቤቶች ህልውና ሳይጣስ፣ ፍርድ ቤቶች የወንጀለኝነት ውሳኔ እስኪሰጡ መጠበቅ፣ የአንድን መጽሔት ህልውና ከመወሰን ያለፈ የሀገር የህግ መሠረት የሚያፀና ጉዳይ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እራሱ ህግ አውጥቶ፣ እራሱ ከስሶ እራሱ ፈራጅ የሆነበት አጋጣሚ፣ የህግን መሠረት የሚንድ ጉዳይ አድርጐ አለማየት ይከብዳል፡፡ ካልሆነ “ወንጀለኛ ልትሆን ስለምትችል” ብሎ በአጠራጣሪ ጉዳይ ላይ የወንጀለኝነት ውሣኔ መስጠት ያስመስላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ “ሁሉንም ሰው ጠቅሎ ካሠሩ በኋላ፣ ጉዳዩን እያጣሩ መፍታት ይቻላል” የሚል የአንደምታ ትርጉም ይሰጣል፡፡
የ“አዲስ ታይምስ” መጽሔት ባለድርሻ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ “ጉዳዩን ይዘን ወደ ፍርድ ቤት እናመራለን” ያለበት ውሣኔ የህግ የበላይነትን ከመቀበል ያለፈ መሪር እውነት የሚናገር ይመስላል፡፡ ከመጽሔቱ የህትመት እገዳ ጀርባ “ሌላ ሥጋት” ይነበባልና…አሊያ ኪሊማንጀሮ ኢንተርናሽናል የተባለ ተቋም ከሥነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር በተደረገ ጥናት፣ የህብረተሰቡን አመኔታ ካጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መካከል ፍርድ ቤቶች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ የሚለውን የጥናት ውጤት “አውቆ መርሣትም” ብልህነት ነው ያለ ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ እንዲባል እፈልጋለሁ፡፡
ለእኔብሮድካስት ባለሥልጣኑም ሆነ “አዲስ ታይምስ” መጽሔት በሀገራችን ማህበረ ፖለቲካዊና ባህላዊ መስተጋብሮች ውስጥ የተለያዩ አውዳዊ ትዕምርቶች (Symbols) ናቸው፡፡
ሁለቱም ከሀገራዊ ሰላማችን ጋር አይወዳደሩም፤ ለሀገራዊ ደህንነታችንም ሆነ ለአንድ ዜጋችን ጦስ ከሆኑ አያስፈልጉም ማለት ይቻላል፤ ስለዚህ ለማህበረ ፖለቲካዊና ባህላዊ መዋቅሮቻችን ተምሣሌት ስለሆኑ፣ ለማሳያነት አነሳናቸው እንጂ እነርሱ እራሳቸው ብቻ መተኮሪያ ጉዳይ አይደሉም፡፡ ትዕምርት ወይም ተምሣሌት የመሆናቸው ውክልና እውን ከሆነ፣ ከእነሱ የፊትለፊት መስተጋብራዊ ሕይወት ጀርባ ያለው “ሀገራዊ እውነት” ነው ዋናው ጉዳያችን፡፡
“የአዲስ ታይምስ” ከህትመት መታገድ ወይም የብሮድካስት ባሥልጣን የአንድ አጋጣሚ የህገመንግሥት ጥሰት ላያሳስበን ይችላል፡፡ የተቃርኖ ሚናቸው ወይም የተግባራቸው መስፈሪያ አልባ ተምሣሌትነት፣ ሀገራዊ መልክ የመያዙን ጫፍ ስናስብ ግን “የሀገርን ስልጣኔ መከሸፍ” እያብሰለሰሉ ከመቆዘም ያለፈ ያምማል፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጫፍ ላይ ሆነን፣ ሉዓላዊ ሀገር እያለን፣ ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን የአያቶቻችንን ያህል እንኳ ሳንኖረው ቀርተናል፤ ነፃነትን የማወቅና የመጠቀም ብቃት፣ ህፃናት ከማይደርሱበት ቦታ የተቀመጠ ፈንጂ ያህል የሚያስፈራና የማይጨበጥ የመምሰሉ ተምሣሌትነት የምር ለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ፈተና ነው፡፡
ለሃሳብ ነፃነት ከመሠለፍ፣ ለዳቦ መሠለፍ የኑሮው መርህ ያደረገ ልፍስፍስ ግን ደግሞ፣ ብልጣ ብልጥ የሆነ ትውልድ እንዲደረጅ ማድረግ፣ ሀገራዊ ጦሱ ብዙ ይመስላል፡፡ የሀገር ህልውናን አሳልፎ መስጠት፣ የገዛ ነፃነትን በሆድ የመደለል ያህል ቀልሎ ሊታይ ይችላል፡፡ “ባለራዕዩ መሪ” አቶ መለስ፣ ቢበጅም ባይበጅም ያመኑበትን ሃሳብ በድፍረት የሚገልፁትን መንፈሰ ጠንካራ ሰዎች እንደሚያከብሩ መናገራቸውን አለመርሳት ብልህነት ነው…

Read 3507 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 15:15