Saturday, 09 February 2013 11:17

ትግሉ የሥልጣን ብቻ ሳይሆን የርዕዮት ዓለምም ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተባበሩ”
ካርል ማርክስ “የዓለም ሠራተኞች ተባበሩ፤ ከሰንሰለቱ በስተቀር የሚቀርባችሁ ነገር የለም ብሎ ነበር”፤ እኔም እላለሁ፤ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተባበሩ፣ ከእስራት ሰንሰለቱ በስተቀር የሚቀርባችሁ ምንም ነገር የለም፡፡ (All Ethiopian oppositions Unite! You have nothing to lose but your chains) ማርክስን መጥቀሴ ማርክስሲት ሆኜ አይደለም፤ አባባሉ እውነትነት ያለው ሆኖ ስለአገኘሁት እንጂ! ለነገሩ ማርክስን በደንብ ሳያውቁ ማርክሲስትም ሆነ ፀረ-ማርክስሲት መሆን አይቻልም።
28 የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ፣ ምርጫው ፍትሐዊና ገለልተኛ እንዲሆን ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በአግባቡ ሳይመለሱ ወደ ምርጫው እንደማይገቡ በሙሉ ድምፅ ወስነዋል። ይህ ትብብር ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ በእውነቱ በጣም ታሪካዊ ሊባል የሚችል ነው። የዛሬው ጽሑፌ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ሆኖ በቀጣይ ቢደረጉ መልካም ነው ብዬ በማስባቸው ነገሮች ላይ የራሴን ሐሳብ ለመሰንዘር ነው።
ኻያ ስምንት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ምንም ውጤት በሌለው ምርጫ አንሳተፍም፣ የአገር ሀብትም በማባከኑ ወንጀል ላይ ተሳታፊ አንሆንም” ብለው ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው።

በእኔ እይታ ከዚህ ረብ የለሽ የምርጫ ሂደት ራስን ማግለል ከሰላማዊ ዐመፅ - አልቦ ትግል አማራጮች አንዱ ነው - ከዐምባገነን መንግሥት ጋር አለመተባበር! ይህ በራሱ ግን በቀጣይ እርምጃዎች እስካልተደገፈ ድረስ ውጤቱ “ምንም” የውሳኔ አማራጭ ሊሆን ይችላል። ማርክስ “የፕሮግራም ጋጋታ ብቻውን ለውጥ አያመጣም” ብሏል።

ይህ ሐቅ አሁንም ይሠራል። ወደ ውጤት የማይቀየር ዘጠና ዐይነት ፕሮግራም መኖሩ ምንም አይፈይድም። ትግሉን ለማካሄድ መሠረታዊ በሆኑ ተጨባጭ አጀንዳዎች ላይ ብቻ ተመርኩዞ፣ ባለው ላይ እየተደመረ የሚሄድ የተመረጠ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መኖር አለበት። ወደ ምርጫ መግባት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ተመራጭ የትግል ስልት አይደለም። ከዚህ አንጻር አሁን ወደ ምርጫ አለመግባቱ ቀዳሚው ተመራጭ ስልት ሆኖ ተገኝቷል ማለት ነው። ከዚህ በኋላስ ምን እናድርግ የሚል ጥያቄ መምጣቱ የሚጠበቅ ነው። በተስፋ መቁረጥ፣ አንገት ደፍቶ መቀመጥ “ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ተሰልፈናል” ከሚሉ ኅይሎች የሚጠበቅ ነገር አይደለም። በዚህ ጊዜ ትክክለኛው አማራጭ የሚሆነው ሰላማዊ፣ ዐመፅ አልቦ ትግል ለማካሄድ መነሣት ነው።
ይህ ሰላማዊ፣ ዐመፅ አልቦ ትግል ጄን ሻርፕ “ከዐምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ” በሚለው መጽሐፉ ላይ እንዳስቀመጠው 198 ደረጃዎች አሉት። ሰሞኑን በጋራ በተደረሰበት ውሳኔ አንዱን ብቻ ነው በተወሰነ መልኩ የተጠቀምነው፤ ገና 197 ደረጃዎች ይቀራሉ ማለት ነው። እንግዲህ ተግቶ ደረጃ በደረጃ አንድ በአንድ መተግበር ያስፈልጋል።
ይህ ትግል ጥብቅ ዲሲፒሊን የሚጠይቅ፣ ነገሮች ባልታሰበ ኹኔታ ወደ ዐመፅና ብጥብጥ እንዳያመሩ መጠንቀቅን የግድ የሚል፣ ሐላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ብቻ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ነው። እንደ ማኅተመ ጋንዲ ያለ የሞራል ልዕልና ያለው መሪ፣ እንደ ሕንዶች ያለ ሥርዐት ያለውና በአንድ ላይ ያለልዩነት የሚሰለፍ ሕዝብ መፈጠር ይኖርበታል። ይህ እንዲኾን ከተፈለገ በመጀመሪያ እንደ ሕዝብ ያሉብንን ልዩነቶች ለማጥበብና ለማመቻመች ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል።
ቀጥሎ መሠራት ያለበት ስለሰላማዊ ዐመፅ አልቦ ትግል በስፋትና በጥልቀት ማስተማር፣ ለዚህ መርሕ በተግባር መገዛት እንዲቻል ማለማመድ ያስፈልጋል። በዚህ ዙሪያ ሙስሊም ወንድሞቻችን እስካሁን እያሳዩት ያለው ሰላማዊ ተቃውሞ የሚደነቅ ነው። አገር በቀል የሰላማዊ ትግል ስልት በመሆኑ ለእኛ ጥሩ ትምህርትና ሞዴል ሊሆን የሚችል ነው። ይህ በራሱ የሚያሳየው ነገር አለ፤ ሕዝባችን በአግባቡ የሚመራውና አምኖ ሊከተለው የሚችል መሪ ድርጅት ካገኘ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ አያዳግተውም።
እዚህ ላይ መሠመር ያለበት አንድ ዋና ነጥብ ግን አለ፤ ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ ትግል እርስ በርስ ለስድብና ለዱላ የሚገባበዙ የፖለቲካ መሪዎች የሚመሩት ሊሆን አይችልም። በትምህርት ብዛት ወይም በፖለቲካው ብዙ ዘመን በማስቆጠርም አይደለም። “እገሌ ወደ ፓርላማ የገባው ኢሕአዴግ ስለደገፈው ነው፤ እገሌ ደግሞ የኢሕአዴግ ተለጣፊና ተቀላቢ ነው” እያሉ በማውራትና በማስወራትም የሚሳካ አይደለም። ተጨባጭ አጀንዳዎችና የፖለቲካ ስትራቴጂዎች ላይ የተመሠረተ፤ ሊታይ የሚችል ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማድረግ ግድ የሚል ነው።
ትርጉም የሌለው ስብሰባ በየጊዜው በማካሄድም አይደለም። ስብሰባ በራሱ ቁም ነገር አስገኝቶ አያውቅም። ፖለቲካዊ ትግል ማካሄድ ማለት በየጊዜው ስብሰባ ማካሄድ ማለት አይደለምና። የፖለቲካ አመራሮቹ፣ ፖለቲካውን በተገቢው ሁኔታ ለመምራት ወገባቸውን ጠበቅ፣ ምራቃቸውን ዋጥ አድርገው መነሣት ይኖርባቸዋል።
ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር በሚደረገው ትግል ሐላፊነት ወስደው ለመምራት፣ መታሰርም ካለ ለመታሰር ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። “እኔ ሜዳ ሜዳውን ነው መታገል የምፈልገው እንጂ መታሰር እፈራለሁ” የሚል የፖለቲካ መሪ ካለ አቋሙን መመርመር፣ ካልኾነም ራሱን ከአሁኑ ከፖለቲካው ማግለል አለበት። ከዚህ በኋላ በፖለቲካው የሚኖሩና ለፖለቲካው የሚኖሩ ሰዎች መንገዳቸው አንድ ላይ መሆን የለበትም። ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ መንግሥት ባለበት አገር፣ ሕገ መንግሥቱን ለማስከበር መነሣት በራሱ ወንጀል ሆኖ እስር ቤት ሊያስወርድ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።
ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉት ፓርቲዎች ቀጣይ ርምጃ መሆን ያለበት፣ ሕዝቡን ሰብስቦ ማነጋገር ነው። በምርጫው ላይ ለመሳተፍ “የምርጫው ሜዳ ይስተካከል፣ ምርጫ ቦርድም ገለልተኛ ይሁን” ብለን የጠየቅነው ጥያቄ፣ የኢሕአዴግ መንግሥትና ምርጫ ቦርድ የዝሆን ጆሮ ሰጥተውታል። ይህ ጥያቄአችን ተቀባይነት አግኝቶ ተፈጻሚ እስኪኾን ድረስ ሕዝቡ ሰላማዊ ትግል እንዲያካሂድ መጥራትና መምራት ያስፈልጋል። ፓርቲዎቹ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ይዘው ሰልፍ መውጣት፣ አመራሮቹም ለተቃውሞ መንገድ ላይ ተኝቶ ማደርና መቀመጥ መጀመር ይኖርባቸዋል። ሕዝቡ የፓርቲዎቹን ቁርጠኝነት ሲገነዘብ በልበ ሙሉነት ለመደገፍ ይነሣል፤ መብቱን ለማስከበርም በጽናት መቆም ይጀምራል።
የፓርቲዎቹ አመራሮች እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ ሊታሰሩ ስለሚችሉ ሌላ ተጠባበቂ አመራር ማዘጋጀት፣ እንደገና ያ አመራር ሲታሰር ደግሞ እንደዚሁ ሌላ እየተተካ ጥያቄው እስኪመለስ ድረስ መቀጠል ያስፈልጋል። አንድ እውነት አለ፤ ሁላችንም ለመታሰርና ለመሞት እስከተዘጋጀን ድረስ፣ ኢሕአዴግ ሁሉንም ማሰር፣ ሁሉንም መግደል ፈጽሞ አይችልም። እነ አንዷለም እና እነ በቀለ ገርባ የታሰሩት ሌሎቻችን ዝም በማለታችን ነው። ይህ ሥርዐት የመለወጡ ቁርጠኝነት በሁላችን ዘንድ እስከሌለ ድረስ በተወሰኑ ሰዎች ትግል ብቻ ለውጥ ይመጣል ማለት የዋህነት ነው።
ኢሕአዴግ ሁኔታዎች አስገድደውት ካልሆነ በስተቀር በእኩልነት ሜዳ፣ በገለልተኛ ዳኛ ሥር ሆኖ በምርጫ አይወዳደርም። በማያጠራጥር ሁኔታ ቢሸነፍም ሥልጣኑን በሰላም አያስረክብም። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ማለትም እኩል የመወዳደሪያ ሜዳና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ በትክክል እስኪኖር ድረስ በምርጫ የመሳተፉ ጉዳይ መታሰብ የለበትም። በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲዎቹ ቁርጠኛ አቋም ከያዙ ገዥው ፓርቲ በምርጫ ቦርድ በኩል “በምርጫ ስላልተሳተፋችሁ” ብሎ የፓርቲዎቹን ሕጋዊ ሰርተፊኬት ወደ መቀማቱ እንደሚገባ ምንም ጥርጥር የለውም።
በዚህ ጊዜም ቢሆን ትግሉ ወደ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲሸጋገር ተግቶ መሥራት እንጂ መደናገጥ አያስፈልግም። የግብጽ ሙስሊም ወንድማማች ፓርቲ ሕጋዊ ዕውቅናውን በሙባረክ መንግሥት በኩል ቢያጣም እውነተኛውን ህልውናውን ግን አላጣም ነበር። ሌላው ቀርቶ አባላቱ በግል እየተወዳደሩ የፓርላማውን አሥራ አምስት በመቶ መቀመጫ እስከመያዝ የደረሱበት ጊዜ ሁሉ ነበር።
ከዚህ የምንረዳው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የምስክር ወረቀቱ ሲቀማ የሚጠፋ ከሆነ ሲጀመር የፖለቲካ ፓርቲ አልነበረም ማለት ነው። የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ህልውና በጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ላይ እንጂ በሰርተፊኬት ላይ መቆም የለበትም። ስለዚህ ህልውናውን አላግባብ በሚያጣበት ወቅትም ቢሆን ትግሉ ባለው ሕዝባዊ መሠረት መቀጠል የሚችል፣ ከሰርተፊኬት በላይ የሆነ አቅም ያለው ኅይል መሆን መቻል ይኖርበታል። አንድ ፖለቲካዊ ፓርቲ ጽኑ ሕዝባዊ መሠረት፣ ጠንካራ አደረጃጀትና አመራር ከሌለው በስለላ፣ በጦር፣ በኢኮኖሚና በመዋቅር በደንብ የተደራጀን መንግሥት ማሸነፍና ሥርዐት መለወጥ አይችልም።
ከሁሉም በላይ በእኛ አገር ያለውን ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ በደንብ ማጤን ያስፈልጋል። የአገራችን ችግር የሥልጣን ጥያቄ ብቻ አይደለም። ትግሉ የርእዮተ ዓለም ትግል መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል። ሁለት አብረው ሊሄዱና ሊታረቁ የማይችሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲና የሊበራል ዴሞክራሲ ትግል ነው እየተካሄደ ያለው።
ኢሕአዴግ መሠረቱ ማርክስሲት ድርጅት ስለሆነ ይህን ቅራኔ በሚገባ ይረዳዋል። ዋናው ነጥብ ኢህአዴግ በትክክል በሁሉም ነገር እስካልተሸነፈ ድረስ በምርጫ ስለተሸነፈ ብቻ ሥልጣኑን ያስረክባል ማለት እንዳልሆነ በደንብ መታወቅ አለበት። ኢሕአዴግ ሁልጊዜ በምርጫ የሚወዳደረው እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ሆኖ ነው። እንደሚሸነፍ ቢያውቅ፣ ማወቅ ሳይሆን ቢጠረጥር እንኳ ወደ ምርጫ ውድድር አይገባም።
ስለዚህ ከገዢው ፓርቲ ጋር በምርጫ ለመወዳደር የሚቻለው በመጀመሪያ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም እኩል የውድድር ሜዳ ሲፈጠር ብቻ ነው። ኢህአዴግ ይህን አምኖ እስኪቀበል ድረስ ግን ሰላማዊ ትግሉን ብቻ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ኢሕአዴግን ወደዚህ ደረጃ ሳያመጡ ከእርሱ ጋር በምርጫ መወዳደር እርሱን ከማጀብ፣ የእርሱን ድል ከማድመቅ ውጪ ትርጉም አይኖረውም። በማጀቡ ሂደት ከአሁን በፊት እንደታየው የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮችን ወደ ፓርላማ ማስገባት ይቻል ይሆናል። የሥርዐት ለውጥ ግን በዚህ መንገድ አይመጣም ፤ እስከአሁን የተጓዝንበት ልምድ የሚያሳየውም ይሄንኑ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Read 4233 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 16:02