Saturday, 09 February 2013 10:59

“መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”- ዕውቅ ምሑራንን ሊያወያይ ነው

Written by  ዓለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

በቅርቡ ለንባብ የበቃውና የብዙዎችን ትኩረት በመሳብ አነጋጋሪ የሆነው የፕሮፈሰር መስፍን ወ/ማርያም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘ መጽሐፍ፤ በነገው ዕለት ታዋቂ ምሑራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና ጋዜጠኞች በተገኙበት በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ፤ በተለያዩ ሐሳቦች ዙሪያ ፊት ለፊት ተገናኝተው ውይይት እንደሚያደርጉበት ተገለፀ፡፡


በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነትና ስፖንሰር አድራጊነት በሚከናወነው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ፤ቀደም ሲል በመጽሐፉ ዙሪያ ደግፈውም ተቃውመውም የጻፉ እንዲሁም የተነሳው ጉዳይ ‹‹ይመለከተናል›› ያሉ፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ሰለሞን ተሰማ (የአዲስ ጉዳይ መጽሔት አምደኛ)፣ አስራት አብርሃም (ከመለስ በስተጀርባ መጽሐፍ ደራሲ)፣የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ብርሃኑ ደቦጭ፣ በታሪክና በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፕሮፌሰሩ ጋር በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ሲሟገቱ የቆዩት የሕወሓቱ ስብሃት ነጋ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ፤እንዲሁም ፕ/ር ገብሩ ታረቀ፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም፣ ዶ/ር ሽመልስ ተ/ፃዲቅ እና ፕ/ር እንድርያስ እሸቴ ተገኝተው በመጽሐፉ ዙሪያ ያላቸውን ሐሳብ እንደሚያቀርቡ የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ አርአያ ጌታቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

በመጽሐፉ ዙሪያ ብቻ በሚደረገው በዚህ ውይይት ላይ የሚገኙት የመጽሐፉ ደራሲ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በበኩላቸው፤ ስለ መጽሐፉ የሚቀርቡ ማንኛውም አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን እንደሚያስተናግዱና ምላሽ እንደሚሰጡ፤አስተያየት ለመቀበልም ፈቃደኛ እንደሆኑ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Read 6409 times Last modified on Saturday, 09 February 2013 14:10