Saturday, 02 February 2013 16:14

‹‹መርዳት እየቻልኩ እንቅፋት ሲገጥመኝ ሆድ ብሶኝ ነው ያለቀስኩት›› አዳነ ግርማ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ጐል በማስቆጠር ታሪክ ሠርተሃል፡፡
በዚህ ጨዋታ ብቸኛው ባለታሪክ እኔ ሳልሆን ብሔራዊ ቡድኑ ነው፡፡ቡድኑ ኢትዮጵያን ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ እንድትሳተፍ አብቅቷል፡፡ስለዚህም ለማንኛውም ስኬት የቡድኑ አስተዋጽኦ ቀዳሚ ነው፡፡ያስቆጠርኩት ጐልም ቢሆን የቡድን ሥራ ነው፡፡ጐሉን እኔ ባገባውም ከዛምቢያ ጋር አቻ የወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንጂ ‹‹አዳነ›› አይደለም፡፡በአጠቃላይ ጥሩ ተፎካካሪ ነበርን፡፡በዚህ ብቃታችን ከመጀመሪያው ዙር መውጣት አልነበረብንም የሚል እምነት አለኝ፡፡የተመኘነው ባለመሆኑ ያስቆጫል፡፡ቡድኑ ከአፍሪካ ዋንጫ ለ31 ዓመታት የራቀ ቡድን አይመስልም ነበር፡፡
በቡርኪናፋሶው ጨዋታ ተጐድተህ ስትወጣ በእልህ እያለቀስክ ነበር፡፡
ማንም አፍሪካዊ ወጣት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታን እያየ ነው ያደገው፡፡ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያንንም ያካትታል፡፡እዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ያለኝ ከፍተኛ ጉጉት በደረሰብኝ ጉዳት በመስተጓጐሉ፣ቡድኔን መርዳት እየቻልኩ በጉዳት እንቅፋት ሲገጥመኝ ሆድ ብሶኝ ነው ያለቀስኩት፡፡ስሜቴም ተደበላልቆብኝ በጉዳቴም ንዴት ተሰምቶኝ ነበር፡፡
አንተ መሰለፍ ያልቻልክባቸውና በሽንፈት የተጠናቀቁትን ሁለቱን ጨዋታዎች እንዴት ትገመግማቸዋለህ፡፡
ከቡርኪናፋሶ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ለመጣው ውጤት በማንም ላይ አልፈርድም፡፡ በጨዋታው እኔና ሌላው ለቡድኑ ወሳኝ ሚና ሲጫወት የነበረው አስራት መገርሳ በጉዳት ሜዳውን ለቀን ለመውጣት ስንገደድ እና፣በሌሎቹ ተጫዋቾች እኛን ለመቀየር ሲወሰን ገና በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ብዙውን ጊዜ ተጨዋች የሚቀየረው ከሁለተኛው አጋማሽ በኋላ ነበር፡፡ የቡድኑ ደካማ ጐን ከተገመገመ በኋላ ነው ተጫዋች የሚቀየረው፡፡አሰልጣኙ የቡድኑን ድክመት በደንብ አገናዝቦ እንዳይቀይር የእኛ በድንገት በጉዳት ከሜዳ መውጣት አሰናክሎበታል፡፡ትልቁ ችግር ይህ ነበር፡፡በናይጀሪያው ጨዋታ ግን ሁላችንም እንዳየነው ቡድናችን ጥሩ ተጫውቷል፡፡በርካታ የጎል ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ከናይጀሪያ የተሻለ ጨዋታም አሳይቷል፡፡በዚሁ ጨዋታ የናይጀሪያ ቡድን ያገባብን ሁለት ጎሎች በሁለት ስህተቶች በተገኙ የፍፁም ቅጣት ምት የተገኙ ዕድሎች ናቸው፡፡
እስካሁን ለዝውውር የጠየቁህ የውጭ ክለቦች አሉ ?
በርካታ ክለቦች እየጠየቁኝ ነው፡፡አብዛኞቹ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ናቸው፡፡እኛ አገር የተጨዋች ወኪል ባለመኖሩ የቀረቡ ጥያቄዎችን በትክክል ማስተናገድ አልቻልኩም፡፡ በደቡብ አፍሪካ የኦርላንዶ ፓይሬትስ እና የሱፐር ስፖርት ደጋፊዎች እኛ ጋር ግባ እያሉኝ በተደጋጋሚ ይጠይቁኛል፡፡

Read 5447 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 16:31