Saturday, 02 February 2013 15:46

የሁለት እብዶች ታሪክ

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

ቀን አልቦ፡- የተከበርኩ ሰው ነኝ፡፡ ብዙ ጉራ ላለመንዛት ብዙ ሰው ያከብረኛል፡፡ ከመስሪያ ቤት ልጀምር፡፡ የመምሪያ ኃላፊ ነኝ፡፡ አለቆቼ ይወዱኛል፡፡ ምንዝሮቼ ይፈሩኛል፡፡ እኩዮቼ ያከብሩኛል፡፡ የምኖርበት ሰፈር ውስጥም እንዲሁ፡፡ ለምን እንደሆን አላውቅም፡፡ ዝም ስለምል ይሆናል፡፡ የምጠላውም የምወደውም ሰው ስለሌለ ይሆናል፡፡ ሁሌ ደስተኛ ስለሆንኩ (መስዬ ስለምታያቸው) ይሆናል፡፡ ተቸግሬ የማውቅ አይመስላቸውም፡፡ ለምንም ነገር (ለሴት፣ ለስልጣን፣ ለዝና፣ ለገንዘብ) ስስገበገብ አይተውኝ አያውቁም፡፡ ብዙ እንደማውቅ ያስባሉ፡፡… ላጤ ነኝ፡፡ ለቁጥር የማላስታውሳቸው ባልና ሚስቶች እንድሸመግል ተለምኜ አድርጌዋለሁ። ልጅ የለኝም፡፡ ወላጆች (አንድም፣ አምስትም፣ አስራአንድም… የወለዱ) አመለጥፉ ልጆቻቸውን እንድመክር ሁሌ በሬን ያንኳኳሉ፡፡ የተማርኩት አካውንቲንግ ነው፡፡ ከሳሾችም ተከሳሾችም ግን እንዴት አንዳቸው ሌላቸውን ልክ እንደሚያስገቡ ያማክሩኛል፡፡ ብቻ እንዴት ዝም ማለት እንደሚቻል፣ በገቢ ልክ የመኖርን ሚስጥር፣ ብዙ ጓደኛ የማፍራትን ጥበብ፣ መነበብ ያለበትን መፅሀፍ፣ መታየት ያለበትን ትያትር እና ፊልም፣ መጠላት ያለበት ሰው የቱ እንደሆነ… ይጠይቁኛለ፡፡ ከዛ፡- “እሱያለው ያለው መሬት ጠብ አትልም” ይላሉ፡፡ እሱያለው ስሜ ነው፡፡ ቀን አሀዱ፡- ሥራ አርፍጄ ገባሁ፡፡ መግባትም አልፈልግም ነበር፡፡ ሥራ ላይ መቆየት አልቻልኩም፡፡ ወደ ቤት ተመለስኩ፡፡ ቀን ክልኤቱ፡- ከሥራ ቀርቼ አላውቅም ነበር፣ ስራ ከጀመርኩበት ቀን ጀምሮ፡፡ ከስራ ቀረሁ፡፡ ተኝቼ ዋልኩ፡፡ ምግብ አልበላሁም፡፡ ምን እንደሆንኩ ሳስብ፣ ሳስብ ሳስብ… ቀን ሰልስቱ፡- ተኝቻለሁ፡፡ ሥራ አልገባሁም፡፡

ምን እንደሆንኩ ዛሬ ታወቀኝ፡፡ ሀይለኛ የድብርት ስሜት ይዞኛል፡፡ ድብርት ወይም ድባቴ በሽታ ነው፤ ታምሜያለሁ፡፡ አሥር ሰዓት ነው ከቀኑ፡፡ ደክሞኛል፡፡ ምግብ አልበላሁም፡፡ ለሶስት ቀናት ሙሉ፡፡ የቤቴን ስልክ ነቅያለሁ፡፡ የኪሴን አጥፍቼዋለሁ፡፡ በሽታ አያጠቃኝም፡፡ በተለይ እንዲህ አይነቱ በሽታ አያጠቃኝም፡፡ በአካል በጣም ጠንካራ ነኝ፤ በመንፈስም እንዲሁ፡፡ ይህ በሽታ በምን እንደያዘኝ አላወኩም፤ ግራ ገብቶኛል፡፡ እኔ? እኔ የከፍተኛ ድብርት ህመም ሰለባ? እንዴት? ለማሰብ ሞከርኩ። አልቻልኩም፡፡ የህመሙ አንዱ ምልክት ይህ ነው፡- ማሰብ አለመቻል፡፡ ወይም በትክክል ማሰብ አለመቻል፡፡ አንድ ሃሳብን ተከትሎ እስከ ጥግ ድረስ ማሰብ አለመቻል፡፡ አቤት እንዴት ቀፋፊ ህመም ነው?! የቤቴ በር ተንኳኳ፡፡

ንድድ፣ እርር፣ ቅጥል፣ ድብን አልኩ፡፡ በእነዚህ ሶስት ቀናት ህማሜን ካባባሱብኝ መሃል ዋነኛዋ ሠራተኛዬ ናት፡፡ ጠዋት ታንኳኳለች፡፡ “ጋሼ ቤት አይፀዳም ዛሬ? “አዎ፤ አይፀዳም ዛሬ” ከሰአት ታንኳኳለች፡፡ “ጋሼ ምሳ አይበሉም?” “አዎ፤ አልበላም” ማታ ታንኳኳለች፡፡ “አይፈልጉኝም?” “አዎ፤ አልፈልግሽም” በሩን ፊቷ ላይ ድርግም፡፡ አሁንም በር እየተንኳኳ ነው፡፡ የአሁኑንስ ኳኳታ መቋቋም አልቻልኩም፡፡ ለምንድን ነው ግን አንድ ነገር ኳአ! ባለ ቁጥር ብርግግ የምለው? እያንዳንዷ ኳኳታ ታስበረግገኛለች፡፡ ከተሰቀለው ኮቴ ውስጥ ሶስት መቶ ብር አውጥቼ በሩን በረገድኩት! “ይኸውልሽ - ይሄን - ያዢ - ከዛሬ - ወዲህ---“ ሰራተኛዬ አይደለችም፡፡ ጓደኛዬ ነው፤ አሳየኸኝ፡፡ “በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ” ፊቴ ቆሞ ያማትባል አሳየኸኝ፡፡ “እህ? አንተ ነህ አሳየኸኝ?” “በስመአብ!!” “ምን ሆነሃል?” “አንተ ምን ሆነሃል?” “ምን ሆንኩ?” “ሰው አትመስልም” “ምን እመስላለሁ?” “ሠይጣን” “በል ግባ” ገባ፡፡ አሳየኸኝ ሳየው የሆነ ነገር ታወቀኝ፡፡ ሰው እፈልግ እንደነበረ ታወቀኝ፡፡ ቅልል አለኝ፡፡ አሁን ረሃቤም ጤነኛ ሆነ፤ ምግብ አሰኘኝ፡፡ ልብሴን ለብሼ እራት ልንበላ ወጣን፡፡ እራት በልተን እንደጨረስን አሳየኸኝ ወሬ ጀመረ፡፡ “ምን ሆነሃል?” “አሞኛል” “ምንህን?” “የአይምሮ ህመም ነው” “ምን?!” “ምነው ደነገጥክ?” “የአይምሮ ህመም?! አንተን?!” “አዎ፤ ብዙ አይደለም ድብርት ነው መሰለኝ የሚባለው፡፡ Depression የሚሉት ሠዎቹ፡፡

በአማርኛ ድባቴ ልንለው እንችላለን” ከት ብሎ ሳቀ፡፡ “አያስቅም፤ ድብርት ማለቴ ድባቴ ህመም ነው” “ድብርት ማለት ድባቴ አሞህ ነው ሶስት ቀን ከስራ የቀረኸው?” “አዎ” ሌላ ሳቅ፡፡ “ሳቁን ተወውና ለምን ቤት እንደመጣህ ንገረኝ። ለምንድን ነው የፈለከኝ? ለምንድን ነው የፈለከኝ?” ብንን አለ፡፡ የኔ ሁኔታ የመጣበትን ጉዳይ አስረስቶት ነበር፡፡ መልስ አልሰጠኝም፡፡ “ከሚስትህ ጋር ተጣላችሁ?” “ኧረ እንደውም፡፡ ባለፈው ካስታረቅኸን በኋላ ፍቅር በፍቅር ሆነናል” “ከአለቃህስ ጋር ሰላም ናችሁ?” “ኡህ! እንዴት ተገላገልኩ መሰለህ፡፡ ለስልጠና ብሎ ወደ ውጭ ሄዷል፤ ለ-ሶ-ስ-ት ወ-ራ-ት” “ብር አልቸገረህም አይደል?” “ደሞዝ ከወሰድን እኮ ገና አንድ ሳምንታችን ነው። በጣም አባካኝ አድርገህ ነው አይደል የምታስበኝ?” “ቆጣቢ እንዳልሆንክ ነው የማውቀው፡፡ ጤናህንስ እንዴት ነህ?” “ያው ጨጓራዬ ነው የሚያስቸግረኝ፡፡ አሁን ደህና ነኝ፡፡ መጠጥ፣ ቡና፣ ንዴት፣ ቀንሻለሁ፤ ምግብ መምረጥ ጀምሬአለሁ” “ለምን እንደፈለከኝ አንተው ንገረኛ እንግዲህ” “ዛሬ እንኳን የመጣሁት ለራሴ ጉዳይ አይደለም፤ ለሌላ ነው” “ለምን?” “የባለቤቴን ወንድም ታውቀዋለህ አይደል? ያ ዩንቨርስቲ የሚማረው?” “ተመሰገን” “አዎ፤ አዎ፡፡ ሰው አትረሳም፡፡ አንዴ ነው ያገኘኸው እኮ” “ሁለቴ” “እንዴት አይነት ጂኒየስ ነበር መሰለህ፡፡ ከትምህርቱ ውጪ ምንም አያውቅም፡፡ አራት አመት ኢንጅነሪንግ፣ ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ነው መሰለኝ ከተማረ በኋላ ጠላሁት ብሎ ወደ ቋንቋ ለወጠ። ከዛ በኋላ ፀባዩ መለወጥ ጀመረ፡፡ ለፈተና ካልሆነ ትምህርት ቤት ሄዶ አያውቅም፡፡ አሁን ጭራሹን ተወው፡፡ ሁሉን ነገር ትቶታል፡፡ አብዷል” “ኖ! ኖ!” ጮህኩ፡፡ “ምነው?” ደንግጧል፡፡

“አብዷል ነው ያልከው?” “ታድያ ይሄ ምን ይባላል?” “ጓደኞቹም የሚያስቡት እንዳበደ ነው?” “አዎ” “ቤተሰቦቹም?” “በትክክል፡፡ ሁሉም ሰው እንደ አበደ ነው የሚያስበው” “አየህ ልጁን እያሳበዳችሁት ያላችሁት እናንተ ናችሁ፤ አብዷል ብላችሁ ደምድማችሁ የምታዩት፣ የምትቀርቡት፣ የምታናግሩት በዚህ እሳቤ ነው፡፡ ይህ ደሞ ጤኛውን ሰው እንኳን በሁለት ሌሊት እብድ ያደርጋል፡፡ ለምን ብቻውን አትተውትም?!” “እሱም የሚለው ይሄንኑ ነው፡፡ ብቻዬን ተውኝ” “እውነቱን ነው! ብቻውን ተውት” “እስከመቼ?” “ማለት?” “ይህ ልጅ እንዲህ መሆን ከጀመረ አመት ሆነው እኮ፤ ማለት አመት ሊሆነው ነው” “እስኪ አንተ አበደ የሚስብሉህን ነገሮች ንገረኝ?” “ነገረ ስራው ሁሉ የእብድ ነው፡፡ አራት አመት ሙሉ የለፋበትን ትምህርት ትቶ ሌላ መቀየር ምን ይባላል?! ያውም ከኢንጅነሪንግ ወደ ቋንቋ” “እሱን ተወው፡፡ ያ ውሳኔው የፍላጐት ጉዳይ ነው፡፡ ፍላጐታቸውን አውቀው እንዲህ አይነት ውሳኔ የሚወስኑ ጤነኞች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው፡፡ ሌላ ምክንያት አለህ?” “እርሱንም ትቶታል እኮ ነው የምልህ!” “ጭርሱኑ?” “እሱን አይደል የምነግርህ?” “ሌላ ምክንያት?” “ሰው አያናግርም” “ሌላስ?” “ሌላ ምን ልበልህ?! ለማበዱ ከዚህ ውጪ ምን ማስረጃ ትፈልጋለህ?!” “እስኪ በየቀኑ የሚሰራውን ንገረኝ?” “ምንም አይሰራም” “አይደለም! በየቀኑ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ ማለቴ ነው” “አምሽቶ ይተኛል፤ አርፍዶ ይነሳል፤ ገላውን ይታጠባል፤ ምሳውን ይበላል፤ ቅጠሉን እየበላ ክፍሉ ውስጥ ሲያነብ ይውላል፡፡ ሲመሽ ደሞ ገላውን ታጥቦ ሊጠጣ ይወጣል፡፡ በውድቅት ሌሊት ይመጣል። ገላውን ታጥቦ ይተኛል፡፡ በቃ ይህንኑ ነው ሁሌ የሚያደርገው፤ ሁሌ” ሁለታችንም ዝም አልን፡፡ የዘረዘርካቸው ነገሮች በሙሉ አበደ አያስብሉም። ለማንኛውም ግን ለምን ባለሙያ እንዲያማክር አትነግሩትም? ሀኪም እንዲያይ” “እንዲያ ስንለው ነዋ የሚብስበት፡፡ ሀኪም ቤት እንሂድ ሲባል አበደ ብላችሁ ነው አይደል! ቆይ እብደት እንዴት እንደሆነ ላሳያችሁ ይልና ሲጮህ፣ ሲጓጉር፣ የቤት ዕቃ ሲሰብር፣ የቤቱን ሰው ሲደበድብ ይውላል፡፡ የሰይጣን ቁራጭ ይሆናል፡፡

በኋላ ገለል ሲልለት አያችሁ እብደት እንደዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ሰላማችሁን ከፈለጋችሁ ተውኝ ይላል” እውነቱን ነው፤ ብቻውን ተውት” “እሱያለው በናትህ ይሄን ቃል ተወው፡፡ ቆይ አንተ ልጁ ጤነኛ ነው፣ ነው የምትለው?” ግራ ገባኝ፡፡ “አሁን እኔን ለምንድን ነው የፈለከኝ?” “ይሄማ ግልፅ ነው፤ ልጁን እንድትረዳው፤ እንድታናግረው፤ በቃ የሆነ ነገር እንድታደርግ ነው የፈለኩህ፡፡ ጨርቁን ጥሎ ሳያብድ፣ ያንን ደግሞ በቅርቡ ያደርገዋል፤ ድረስለት፤ እባክህ” “እሺ እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” ሳቀ፡፡ ይህን ልጅ የሚያስቁት ነገሮች ይገርሙኛል። ከልቡ ሳቀ፡፡ “እንዴ እሱያለው እሱንማ ካንተ ውጭ ማን ያውቃል? እንዴት ሰዎች ተሸክመው ከሚኖሩት ጭንቀት ነፃ እንደምታወጣቸው፣ የጨለሙ አይኖች አንዴት ብርሃን እንዲያዩ እንደምታደርግ፣ የተሰበሩ ልቦችን እንዴት መጠገን እንደምትችል ካንተ ሌላ ማን ያውቃል? ያንን ለማወቅ ያለኝን ሁሉ እሰጣለሁ” ድምፁ ውስጥ የሌለ ነገር የለም፡፡ አድናቆት አለ። ቅናት ይሰማል፡፡ የበታችነት ስሜት በስሱ ከጀርባ ሆኖ ይደመጣል፡፡ ቀጠለ፡፡ “ዛሬ ለምን ክፉ እንደሆንክ ገርሞኛል፡፡ ደሞኮ አንተንም ፍፁም ደስታ የሚሰጥህ ነገር ነው” ገረመኝ፤ የመጨረሻውን አረፍተ ነገር በእርግጠኛነት ነው የተናገረው፡፡ “እኔን ፍፁም የሚያስደስተኝ ምንድን ነው?” “የተቸገረን ሰው መረዳት” ዝም አልኩ፡፡ “ምነው ጠየከኝ?” ብሎ ጠየቀኝ ደንገጥ ብሏል፡፡ “ምን?” “የተናገርኩት ነገር ያስከፋህ ትመስላለህ” “አልተከፋሁም፡፡ ልጁን እንዴት ነው አግኝቼ የማናግረው?” ሰዓቱን አየ፡፡ “ሶስት ሰአት ሊሆን ነው፡፡ ይሄኔ እየጠጣ ነው። የት እንደሚጠጣ ታውቃለህ? ያቺ እኔና አንተ የምንሄድባት ከኔ ቤት በላይ ያለችው ቤት ነው የሚጠጣው፡፡ ለምን እዛ ሄደን አናገኘውም አሁን?” መታመሜን እረስቶታል፡፡ “አሁን?” “አዎ አሁን” ሄድን፡፡ ግሮሠሪዋ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች የምናውቃቸው ናቸው፡፡ ሁሉንም ሰው በየተራ ሰላም አልን፡፡ ተመስገን ጥግ ተቀምጧል፡፡ በሚገርም ሁኔታ ያልተያዙት ወንበሮች እሱ የተቀመጠበት ጠረጴዛ ላይ ያሉት ብቻ ናቸው፡፡ መጀመሪያ ዘመዳሞቹ ሰላም ተባባሉ ከዚያ እኔና ተመስገን፡፡ አሳየኸኝ ምን እንደሚያደርግ ግራ ገብቶታል፡፡ “ተቀመጡ” አለን ተመስገን በእርጋታ፡፡ እርጋታው ይገርማል፡፡ ያስቀናል፡፡ ተቀመጥን፡፡ ቢራ አዘዝን፡፡ ከብዶኛል፡፡ ምንም ደስ አላለኝም፡፡ የተመስገን አስተያየት ያስጠላል፡፡ በተለይ እኔን ነው የሚያየኝ፤ የሚያፈጥብኝ ማለቴ፡፡ ወሬ የለም፡፡ አንደኛውን ቢራ ጨርሰን ሌላ አዘዝን፡፡ አሁንም ወሬ የለም፡፡ “አቶ እሱያለው!” ብንን አልኩ፤ ተመስገን ነው፡፡ “እህ! አቤት?” “ለምን እንደመጣችሁ አውቃለሁ፡፡

ለቢራ አይደለም፡፡ አሳየኸኝን ተወው፡፡ እሱ ምንም ቢያስብ አልቀየመውም፡፡ የዋህ ነው፤ ሞኝ ነው፤ ምስኪን ነው። እኔን እንድታናግረኝ ማለት እንድትረዳኝ ነው ይዞህ የመጣው፡፡ ችግር እንዳለብኝና ጤነኛ እንዳልሆንኩ አሳምኖህ ነው አይደል?” “ኖ! ኖ! እኔ ያንን አላመንኩም” “ብራቮ! እሱን ካላመንክ ሸጋ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ተቀምጠህ ምንም አትሰራም፡፡ ቢራውን የምትጠጣው በግድ ነው፡፡ ፊትህ ልክ አይደለም፤ የደከመህ-ያመመህ ትመስላለህ፡፡ ለምን ወደ ቤትህ ሄደህ አትተኛም? ፊትህ የእውነት ልክ አይደለም” በእርጋታ ነው የተናገረው፡፡ ለምን እንደሆነ እንጃ ወሬውን እንዲቀጥል ፈልጌያለሁ፡፡ በዛ ድምፀት በዛ በማያወላውል እርጋታ ሲያወራ መስማት አጓጉቶኛል። ፍፁም ጤነኛ ነው ድምፁ፡፡ የእኔን ህመም ከፊቴ ላይ ማንበቡ ደንቆኛል፡፡ ጥሩ ቀዳዳ አገኘሁ፡፡ ወሬውን ከራሴ ጀምሬ ከዛ ወደ እሱ መውሰድ ይቻለኛል፡፡ “ልክ ነህ! እኔንም ትንሽ አሞኛል፤ ድብርት ቢጤ …” “አቶ እሱያለሁ ስላንተ ህመም መስማት አልፈልግም፡፡ እዚህ የመጣኸውም ስለ ህመምህ ልታወራኝ አይደለም፡፡ የመጣኸው አሳየኸኝ በነገረህ መሰረት እኔን ልትረዳኝ ነው፡፡ ቆይ ቆይ አብዷል ብለህ ታስባለህ?” “እ?” “አብዷል ብለህ ታስባለህ ወይ?” “አላስብም” “ስለዚህ ጤነኛ እንደሆንኩ ታምናለህ?” “አምናለሁ” “በቃ በዚህ ከተስማማን ሌላ የምናወራበት ምንም ጉዳይ የለም፡፡ እህ ስለሌላ ጉዳይ እናውራ ልትል ነው፡፡ ፊትህ ላይ ይታያል፡፡ ክፋቱ ግን እኔ ስለምንም ነገር ማውራት፣ ሲወራ መስማት ፈፅሞ፣ ፈፅሞ አልፈልግም” “ይሄውልህ ተመስገን…” “ኦ-ኦ ተናገርኩ እኮ፡፡ አንድ ስለ መጣህበት ጉዳይ መናገር የምትችለው እብድ እንደሆንኩ ካመንክ ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛ ከዛ ውጪ ምንም ነገር ማውራት ነፃነቴን መጋፋት ነው፤ አልፈልግም ብያለሁና…” ተናደድኩ፡፡ “ይሄን ያህል የሚያስቆጣ ምንም ነገር አልተፈጠረም፡፡ ለምንድነው የምትጮኸው?! አዎ ልክ ነህ የመጣሁት አንተን ለማግኘት ነው፤ እያመመኝ፡፡ ይሄ ታዲያ ሀጢያት ነው? ጥፋት ነው? ለዚህ ነው የምትቆጣው? የምትጮኸው?” “ይቅርታ፤ መቆጣቴ አልታወቀኝም፡፡ ተቆጥቼ ከነበረ ይቅርታ” ለአፍታ ዝም ተባባልን፡፡ የተፀፀተ ይመስላል፡፡ ትክክለኛው ሠዓት መድረሱ ታወቀኝ፡፡ የተፀፀተ ልብ ደግሞ ክፍት ነው፡፡ ይሄኔ ነው መግባት፡፡ (ይቀጥላል)

Read 7506 times