Saturday, 02 February 2013 14:01

“አዲስ ታይምስ” መጽሔት ታገደ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በድጋሚ ተቀጠረ

በዓዲ ኀትመትና ማስታወቂያ ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም እየታተመ የሚወጣው “አዲስ ታይምስ” መጽሔት፤ ከብሮድካስት ባለሥልጣን የሞያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እድሳት በመከልከሉ ከኅትመት ውጪ ሆነ፡፡ አሳታሚው ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጸው፤ የአገሪቱ የፕሬስ ሕግ በሚያዘው መሠረት የመጽሔቱን ዓመታዊ ፈቃድ ለማሳደስ ከድርጅቱ የሚጠበቁትን መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ቢያሟላም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ጥር 2 ቀን 2005 በላከው ደብዳቤ ለመጽሔቱ የሞያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እድሳት እንደማያደርግ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን እድሳቱን እንደማያደርግ ለአሣታሚው በላከው ደብዳቤ ያመለከተው ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶችን በመጥቀስ ነው። እነዚህም የአክስዮን ባለቤቶችና የአድራሻ ለውጥ ሲደረግ በ15 ቀን ውስጥ ለባለሥልጣኑ ማሳወቅ አለመቻል፣ ለኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት መወዘክር የዐሥራ አምስት ቀን እትም አለማስገባት እንዲሁም መፅሔቱ “በሕጋዊ ባለቤቶቹ ሳይሆን ምንጩ በማይታወቅ ገንዘብ ነው የሚተዳደረው የሚሉት ናቸው፡፡ የ“አዲስ ታይምስ” መፅሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን በበኩላቸው፤ የአክስዮን ባለቤትነት እና የአድራሻ ለውጥ ሲያደርጉ በጊዜው በደብዳቤ ማሳወቃቸውን፣ በየዐሥራ አምስት ቀኑ ለኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሁለት ሁለት ኮፒ ያስገቡበትን ደረሰኝ ለባለሥልጣኑ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ማንነቱ በማይታወቅ የገንዘብ ምንጭ ነው የሚንቀሳቀሰው›› የሚለውን የባለሥልጣኑን ምክንያት ደግሞ “በጥንቆላ ላይ የተመሠረተ መረጃ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ “ጉዳዩን ይዘን ወደ ፍርድ ቤት እናመራለን” ያሉት አቶ ተመስገን፤ የመጽሔቱ መታገድ ‹‹የአቶ ኀይለማርያም መንግሥት የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን ሲል የነበረውን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ያመለክታል” ብለዋል፡፡ የአራት ወራት ዕድሜ ያስቆጠረው “አዲስ ታይምስ” መጽሔት ከ35 ሺሕ ኮፒ በላይ እየታተመ በየሁለት ሳምንቱ ይሠራጭ እንደነበር፣ ይህም በአገሪቱ ካሉ መጽሔቶች በኅትመት፣ ብዛትና በተደራሽነት ቀዳሚ እንደሚያደርገው አቶ ተመስገን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ተጠባባቂ ሓላፊ የሆኑት አቶ ወርቅነህ ጣፋ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ የእድሳት ክልከላውን ከማድረጉ በፊት ከባለአክሲዮኖቹ ጋር የአድራሻ ቅየራ እና የአክሲዮን ድርሻ ለውጥ ሲደረግ አለማወቃቸው እንዲሁም በቤተ መጻሕፍት ወመዘክር የመጽሔቱ ቅጂዎች እየደረሱ እንዳልሆኑ ተወያይተንባቸው ችግሩ እንዳለ አምነው ተቀብለው ነበር ብለዋል፡፡ የመጽሔቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ደሳለኝ፤ የአክስዮኑ 93 በመቶ ድርሻ ባለቤት አገር ውስጥ እንዳልሆኑና ሰባት በመቶ ድርሻ ያላቸው ግለሰብ ብቻ አገር ውስጥ መኖራቸውን በመግለፅ አገር ውስጥ ያሉትን ብቻ አነጋግሮ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ የፋይናንስ ምንጩን በተመለከተ ሲናገሩ፤ ‹‹አሁን በግልፅ ይፋ ባናደርግም መረጃው አለን” ብለዋል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የሕዝብን ሐሳብ ማናወጥ፣ ሕዝቡን በሕገ - መንግሥቱ ላይ ማነሣሣትና የመንግሥትን ስም ማጥፋት የሚሉ ሦስት ክሦች የተመሰረተባቸውና ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለስድስት ቀናት ከታሰረ በኋላ ክሱ ተቋርጦ በነጻ የተለቀቁት የቀድሞው የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ተመስገን ደሳለኝ፤ ከሦስት ወር በኋላ ክሱ በዐቃቤ ሕግ ተንቀሳቅሶ በ50ሺሕ ብር ዋስ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ትእዛዝ ታኅሣሥ 27 ቀን 2005 ዓ.ም ቀርበው ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጣቸው የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማስተዋል ብርሃኑ እና የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አቶ ተመስገን ደሳለኝ ትላንት ጥር 23 ቀን 2005 ዓ.ም ቢቀርቡም “መዝገቡን አልመረመርነውም” በሚል ብይኑ ሳይሰማ የቀረ ሲሆን ችሎቱ ለየካቲት 1 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 5458 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 16:50