Print this page
Saturday, 02 February 2013 13:43

ኢህአዴግ “የተቃዋሚዎች አለመሳተፍ ጥቅምም ጉዳት የለውም” ማለቱን 29 ፓርቲዎች ተቃወሙ

Written by  አበባየሁ ገበያው እና ሠላም ገረመው
Rate this item
(4 votes)

መድረክ አዲስ የትግል አቅጣጫ ማንፌስቶ ያፀድቃል ከአዲስ አበባና የአካባቢ ማሟያ ምርጫ ጋር በተያያዘ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት የሰጡትን መግለጫ 29ኙ ፓርቲዎች ተቃወሙ፡፡ አቶ ሬድዋን፤ የተቃዋሚዎች አለመሳተፍ ትርፍም ኪሳራም የለውም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ የመግለጫው አጠቃላይ ይዘት ኢህአዴግ ከእብሪት ስሜት አለመላቀቁንና በአገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች እኔ ብቻ ነኝ መፍትሔ ሰጪ በሚል ስሜት እየተነዳ መሆኑን ይጠቁማል ብለዋል - ፓርቲዎቹ ባወጡት መግለጫ፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ እንደማይጠቅምና ብዙ ርቀትም እንደማያስኬድ የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤ በህዝብ ትግል ሊገታ እንደሚገባውም አስታውቀዋል፡፡ ኢህአዴግ ተነሳሽነት ወስዶ የፓርቲዎችን የጋራ ም/ቤት እስከ ቀበሌ አዋቅራለሁ ማለቱን ያወሳው የፓርቲዎቹ መግለጫ፤ በምርጫ ህጉ መሠረት የጋራ ም/ቤት የሚቋቋመውና የሚሰበሰበው በምርጫ ቦርድ እንደሆነ፤ ኢህአዴግ አደርገዋለሁ የሚለውም ህገወጥ ድርጊት መሆኑንና በወንጀልም እንደሚያስጠይቅ ጠቁሟል፡፡

በህጋዊነት ከተመዘገቡት ፓርቲዎች 28ቱ ብቻ ተሳትፈው የተቀሩት አለመኖር የምርጫ ሂደቱን እንደማያጐድለው የኢህአዴግ ሃላፊው መናገራቸውን ያወሱት ፓርቲዎቹ፤ ይሄም የጥቄያችንን ትክክለኛነትና የኢህአዴግን አግላይ ባህርይ ያሳያል ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ለራሱ ፖለቲካዊ ጥቅም የሚበጀው ሲሆን፤ 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን እንደሚገልጽ፤ በሌላ በኩል ፓርቲዎች በጋራ ሲነሱበት ደግሞ የምርጫ ቦርድን ስልጣን በመውሰድ ፓርቲዎች ውስጣቸው በተገቢው መንገድ ይፈተሽ እያለ እራሱን የፓርቲዎች ደረጃ መዳቢ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ይሄም ምርጫ ቦርድ “የኢህአዴግ ጉዳይ ፈፃሚ ነው” በማለት የደረስንበትን መደምደሚያ ያጠናክርልናል ብለዋል፡፡ ፓርቲዎች አክለውም፤ የመገናኛ ብዙሀን ፍትሃዊ አጠቃቀም እንዲኖር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት እንዲረጋገጥ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከገዢው ፓርቲ ተጽእኖ ተላቆ ገለልተኛ እንዲሆን፣ በገዢው ፓርቲ ተጽእኖ የወጡና ለአፈና የዋሉ ህጐች እንዲከለሱ ወይም እንዲሻሩ፤ በአጠቃላይ የዜጐች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ እና የምርጫ ውድድር ሜዳው እንዲስተካከል በመግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡ ኢህአዴግ ፀሐይዋ እያዘቀዘቀችበት ቢሆንም ጨርሶ አልመሸበትምና አቋሙን እንደገና መርምሮ ራሱን ለውይይት እንዲያዘጋጅ እንመክራለን ያሉት ፓርቲዎቹ፤ መላው ህዝብ የዚህ ምርጫ አካል በመሆን ኢ-ህገመንግስታዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ይሁንታ ከመስጠት እንዲቆጠብ እና ጥያቄያቸውም ምላሽ እንዲያገኝ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት ጠቅላላ ጉባኤውን በፅ/ቤቱ እንደሚያካሂድ የጠቆመው መድረክ ፓርቲ፤ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመመርመርና ሊያሰሩ በሚችሉ ሁኔታዎች ላይ በመምከር አዲስ የትግል አቅጣጫ ማኒፌፍስቶ እንደሚያፀድቅ አስታወቀ

፡፡ ፓርቲው በዚህ ጉባኤው በተጓደሉ አባላት ምትክ አዳዲስ አባላትን እንደሚመርጥና የስድስት ወር የስራ ሪፖርት እንደሚያደምጥ የመድረክ ምክትል ኃላፊና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና ገልፀዋል፡፡ በዛሬው ጉባኤ፤ በሞትና በሌሎች ምክንያቶች የተጓደሉ የአመራር አባላት እንደሚተኩ የገለፁት ዶ/ር መረራ፤ የአመራር አባላት የስልጣን ዘመን ከአንድ ዓመት በላይ እንዲሆን የሚያስችል አጀንዳም ለውይይት ይቀርባል ብለዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በሚያዝያ ወር የሚደረገውን የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ በተመለከተ ሲናገሩ፤ መንግስት ከምርጫው አስገድዶ እያስወጣን ቢሆንም የስራ አስፈፃሚው ከምርጫው ጋር ተያይዞ የወሰዳቸውን እርምጃዎች እንደሚገመግሙና የሚያሰሩ ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች እንደሚመረምሩም ገልፀዋል።

Read 3381 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 16:50