Saturday, 02 February 2013 13:03

“ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮዽያዊም…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

     እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ…ቁጥሮች አንዳንድ ጊዜ ሙሉውን ታሪክ ላይገልጹ ይችላል፡፡ ብሔራዊ ቡድናችን አንድ አግብቶ ሰባት ቢገባበትም ከቁጥሮች ይልቅ ትክክለኛ ስዕሉን የሚያሳየው ሜዳ ላይ የነበረው ሁኔታ ነው፡፡ ሜዳ ላይ ደግሞ ባየናቸው ሁኔታዎች ልጆቻችን ያለባቸውን የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች የልምድ ማነስ፣ የነበረባቸውንና እኛ ልንገምት እንኳን የማንችላቸውን ጫናዎች፣ ለማሸነፍ የነበራቸውን ዕልህና ፍላጎት እንዲሁም በዚህ መሀል የተፈጠሩ ነገሮችን በማየት…በእርግጥም ልጆቹ ብዙዎቻችን ከጠበቅነው በላይ ሠርተዋል፡፡ እናማ…ይመቻቸውማ! ለህዝቡና ለዚች አገር ያደረጓቸው ነገሮች እነሱም እኛም ልናስበው ከምንችለው በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእኛ የዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ የኳስና የተሳትፎ ነገር ብቻ አልነበረም፡፡ አሁንም ይመቻችሁ! ስሙኝማ…እግረ መንገዳችንን ግን የሆኑ ነገሮች መነጋገር ያለብን ጊዜም አይመስላችሁም! በተለይ ደግሞ የስፖርት ጋዜጠኝነቱ በተመለከተ…አለ አይደል…ትንሽም ቢሆን “በላ፣ ልበልሃ!” ብንባባል ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም በተጋነነ እምነትና ከተጨባጩ እውነታ ይልቅ በስሜት ላይ በተመሠረቱ አስተያየቶች የሰዎች ስሜት ተጎድቷልና! የምር ግን….አለ አይደል….የስፖርት ጋዜጠኞች የበሰሉና ሙያን መሠረት ያደረጉ ሀሳቦች በማቅረብና፣ ስሜታቸውን በመቆጣጠሩ ረገድ ከእኛ ከተራዎቹ ተመልካቾች የተወሰኑ እርምጃዎች ርቀው መሄድ አለባቸው፡፡ እንዴት መሰላችሁ…በማይሆን በስሜት ብቻ በሚመራ ፍላጎት ‘ሰማይን ለመጨበጥ’ ስንሞክር ጋዜጠኞቹ “ምኞታችሁ ጥሩ ነው፣፡፡ ግን በዚህ በዚህ ምክንያት ሰማይን ለመጨበጥ አስቸጋሪ የሚያደርጉብን ነገሮች አሉ…” ብለው ‘መሬት ላይ እንድንቆይ’ ሊያደርጉን ይገባል፡፡ ሰሞኑን ግን ሁሉም ባይሆኑም ብዙዎቹ ጋዜጠኞች አብረውን ሰማይን ለመጨበጥ ሲሞክሩ ነበር፡፡ እናማ…በተለይ ከቡርኪናፋሶ ጨዋታ የታየው የብዙዎች ድንጋጤና የስሜት መጎዳት ‘ሰማይን ለመጨበጥ’ ስንሞክር “እርጋታና ሰከን ማለት ያስፈልጋል…” የሚሉ ድምጾች በማነሳቸው ነው፡፡ እናማ… ውጤቶች ምንም ይሁኑ ምንም ጋዜጠኞቹ ከስሜታዊነት የጸዱና ቅጽሎች ያልታጨቁባቸው አስተያየቶች ሊሰጡን ይገባል፡፡ በእርግጥ…ጋዜጠኞቹ ሁሉንም አስተያየት የሚሰጡት ከቅንነትና የኢትዮዽያ እግር ኳስ እንዲያድግ ባላቸው ቁጭት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ግን በዚህ ጉዞ ላይ ብዙ የሚያዳልጡ ተዳፋቶች ስላሉ በሰሞኑ ውድድር አንዳንድ ጋዜጠኞቻችን በእነዚሀ ተዳፋቶች ላይ ከእኛ ጋር አብረው ሲንሸራተቱ ማየቱ አሪፍ አይደለም። “ሁለቴ አይተህ አንዴ እርገጥ…” ሊሉን ሲገባ እዚሀ ስህተት ላይ የሚወድቁ ጋዜጦቻችን የግል ስሜቶቻቸው ዘገባዎቻቸውን እንዳያበላሹባቸው መጠንቀቅ ያለባቸው ይመስለናል፡፡ እናማ…ልጆቻችን ከእነጉድለቶቻቸውም ቢሆን፣ ከማጣሪያ ውድድሮች ጀምሮ እሰከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ላደረጉት ሁሉ “ለልቦቻችን ብርሀን ስለፈነጠቃችሁልን አንድዬ የእናንተም ልቦች በብርሀን ያጥለቅልቅላችሁ!” ልንላቸው ይገባል፡፡ በነገራችን ላይ…ፌዴሬሽኑም ቢሆን ‘ከሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ጋር ዘምኖ’ ያንን ያህል ጋዜጠኞችን ይዞ በመሄዱ ምስጋና የሚገባው ይመስለኛል፡፡ የሄዱት ጋዜጠኞች ሁሉ የሚጠበቅባቸውን አድርገዋል፣ አላደረጉም ሌላ ጉዳይ ነው፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን በሚቀጥለው ጊዜ ፌዴሬሽኑ “ያለፈው ጊዜ ወስደናችሁ ምን የረባ ነገር ሠራችሁ…” ቢል ሊያምርበት ይችላል፡፡ (በነገራችን ላይ…አንድ ሰሞን እንደ ‘ማርያም ጠላት’ ሁሉም ሲወርድበት የነበረው ፌዴሬሽን ላይ ይሰሙ የነበሩት ትችቶች በውድድሩ ዋዜማ ሰሞን ‘ሁሉም ጭጭ፣ ሁለም ምጭጭ’ አይነት የመሰለው ነገርዬው ከ‘ኦሮብላን’ ትኬቷ ምናምን ጋር የሚያያዝው ነገር አለ እንዴ! አይ… ውስጤ ከሚቀር ልተንፍሰው ብዬ ነው…ቂ…ቂ…ቂ…) በነገራችን ላይ ስም መጥራት አስፈላጊ አይደለም እንጂ ጥሩ ሲሠሩ የነበሩና በስፍራው ያለውን ሁኔታ እየተከታተሉ ሲያሳውቁን የነበሩ ጋዜጠኞች እንደነበሩ መጥቀሱ አስፈላጊ ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ስለ ስፖርት አዘጋገቡ ካወራን ይሄ ጨዋታዎችን በቀጥታ ስለማስተላለፉ ጠቀስ ማድረግ አሪፍ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ቡድናችን ከሆነ አገር ቡድን ጋር ያደርግ የነበረው ጨዋታ በሬድዮ እየተላላፈ ነበር። ታዲያላችሁ…ተከለካዩ አስፋው ባዩ ኳስ ይይዛል። የሚያስተላልፈው ጋዜጠኛም “አስፋው ይዟል! አስፋው ይዟል!…” እያለ ድምጹ እየጨመረ፣ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በመጀመሪያ ነገር አስፋው ይሄን ያህል ገፍቶ ወደተጋጣሚው ክልል መግባቱ በራሱ ‘ብሬኪንግ ኒውስ’ ነበር፡፡ እናማ… አድማጩ ይጠብቅ የነበረው ከአሁን አሁን “ጎ…ል!” የሚለውን ‘የጩኸቶች ሁሉ እናት’ ነበር፡፡ እናማ… “አስፋው ይዟል!” የሚለው ድምጽ ጣራ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚያስተላልፈው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው…“ለበረኛችን አቀበለው…” ለበረኛችን ሊያቀብል እየገፋ ወደ ኋላ የመለሳት ኳስ ምን የሚያስጮህ ነገር አላት! እናማ በዘንድሮ አፍሪካ ዋንጫ “ለበረኛችን አቀበለው…” አይነት ነገር ስንታዘብ ስለነበር አሁንም ስሜቶች ሙያን ባይጫኑ ጥሩ ነው፡፡ ጨዋታን ቀጥታ ማስተላላፍ ገና ብዙ ሊሠራበት ይገባል፡፡ ጋዜጠኞች በተቻለ መጠን ራሳቸውን ከስሜታዊነት ካላረገቡ በስተቀር ኳስ መሀል ሜዳ ባለፈች ቁጥር ድምጽ ሲጨምር አድማጩ ላይ የሚፈጥረው ስሜት የተሳሳተ ይሆናል፡፡ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የስፖርት ጋዜጠኞች ሰብሰብ ብለው ስለ አቀራረባቸው…አለ አይደል…ቢያንስ ቢያንስ በመሠረታዊ ነገሮች ላይ ቢሞክሩ ሸጋ ነው፡፡ ከኳሱ ባለፈ ተጫዋቾቻን ያደረጉት ትልቁ ነገር ምን መሰላችሁ…አንድ አድርገውናል፡፡ ምናልባትም ከብዙ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳንገለማማጥ፣ ደግሞ በሆነ ነገር “ይፈርጁኛል፣” “ዓይናቸውን ይቸክሉብኛል” ምናምን ሳንባባል በጋራ እንድንዘፍን አድርገውናል፡፡ ዘላለሙን “ውሀ ቢወቅጡት…” ምናምን የሆነው ቦተሊካችን ከምላስ በስተቀር ጆሮ የሌለው ሀምሳ ትንንሽ ያደረገንን ሁሉ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን አጥሮቹን አስወግደውልን ጎን፣ ለጎን እንድሆን አድረገውናል፡፡ ምን አለ ለዚህ እንኳን ቢሆን ቆይታችን ትንሽ በረዘመ እንድንል አድርገውናል፡፡ ስሙኝማ…ይሄ “እነ እንትና አደነቁን…” “እነ እንትና አጨበጨቡልን…” የሚባሉ ነገሮች ግርም አይሏችሁም፡፡ ዋናውና ‘ውሀ የሚያነሳው’ ነገር እኛ ለራሳችን ማጨብጨባችን ነው፡፡ ‘የእነሱ’ ማጨብጨብ ብዙ ጊዜ የሆነ ‘የተሸጎጠ’ ነገር አያጣውም፡፡ (እነሱ ራሳቸው ‘ቢትዊን ዘ ላይንስ’ እንደሚሉት ማለት ነው፡፡) እናላችሁ…ብዙ ጊዜ ከሚነገሩት ነገሮች አንዱ “የውጪዎቹ ለእኛ ብዙም ፍቅር የላቸውም” የሚለው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አባባሉን ብንለጥጠውም …የተወሰኑ ነገሮች ስታዩ ይሄ ዝም ብሎ ‘ባዶ ፓትሪዮቲዝም’ ምናምን ነገር አይደለም፡፡ የምርም በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ የላይ ላዩን ትቶ ነገሬ ብሎ ላዳመጠ ‘የተሸጎጠውን’ ስለ እኛ ያሉ ጥሩ ነገሮችን ከመናገር የዛምቢያ መውጣት እንደሚያሳዝንና የናይጄሪያ ማለፍ ‘ሳይታለም የተፈታ’ አይነት ነገር ነው የሚያስመስሉት፡፡ የውጪ ሚዲያዎች ስለቡድናችን ‘አድናቆት ማዝነባቸውን’ ከማውራት በፊት የቃላት አጠቃቀማቸውን ነገሬ ማለት አሪፍ ነው፡፡ የኢትዮዽያ ቡድን ዛምቢያ ላይ አቻነቷን ጎል ሲያገባ ጋዜጠኛው “የማይታመን!” (Unbelievable) ብሎ ሲጮህ ከማድነቅ ብቻ እንዳልሆነ ከአነጋገሩ ቃናና አስከትሎ ከተናገራቸው ነገሮች የሆኑ ምልክቶች ይኖራሉ፡፡ ነገርዬው “እነዚህ ሚጢጢዎች ዛምቢያ የሚያህል ዝሆን ላይ እንዴት ያገባሉ!” አይነት ነገር የሚያስመስሉ ቃናዎቻቸው ያሉት ነው፡፡ የስፖርት ጋዜጦቻችን ማወቅ ያለባቸው አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቃላት በመደበኛ ሁኔታዎች ስንነጋገርባቸው የሚሰጡት ትርጉምና ስፖርት ውስጥ ሲገቡ የሚሰጡት ትርጉም ተመሳሳይ ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነ ነው፡፡ የስፖርት ጋዜጠኛ አሪፍነቱ ቃላትን ጋዜጠኛው በፈለገ መንገድ ሊጠቀምባቸው ማስቻሉ ነው፡፡ አለበለዛ ግን ከየአረፍተ ነገሩ ‘ቅጽሎቹን’ ብቻ እየመዘዙ ‘አየር ላላነሰው ፊኛ አየር መሙላት መሞከር’ አሪፍ አይደለም፡፡ የዛምቢያ ጨዋታ ዕለት በረኛችን ቀይ ሲያይ ተጫዋቾቻችን ከዳኛው ጋር ትንሽ ክርክር ቢጤ ገጥመው ነበር፡፡ ይህ በማንኛውም ጨዋታ ላይ — የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨምሮ — የተለመደ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ጨዋታውን የሚያስተላልፈው ጋዜጠኛ የተጫዋቾቻችንን ክርክር ለመግለጽ የተጠቀመበት ቃል “Silly” የሚለውን ቃል ነበር፡፡ እንደዚህ አይነት ኳስ ዘገባ ላይ የማይዘወተሩ ቃላት መሀል ላይ ሲደነቀሩ ዝም ብለው የገቡ አይደሉም፡፡ ለዚህ ነው “አደነቁን!” “ዱአ አደረጉልን!” ምናምን ከማለት በፊት ‘የተሸጎጡ’ ትርጉሞችን ማየቱ አሪፍ የሚሆነው፡፡ የናይጄሪያ ዕለት የእኛን ቡድን ከጎዱት ነገሮች አንዱ የ“ዲሰፕሊን…” ጉዳይ እንደሆነ ጋዜጠኛው ሲነግረን ነበር፡፡ ብዙዎቻችን እንዳየነው ተጫዋቾቻችን ሲፈጽሟቸው የነበሩ ስህተቶች ያለመረጋጋትና ውጥረት የፈጠራቸው እንጂ ‘የባህሪይ ጉድለት’ እንዳልነበረ ማንኛውም ጋዜጠኛ ሊያየው የሚችል ነው፡፡ ኳስ አቀባዮችን የሚራገጡ ተጫዋቾች በአገራቸው ሞልተው የእኛን የተለመዱና በማንኛውም የእግር ኳስ ግጥሚያ ተደጋግመው የሚታዩ የኳስ ሜዳ ጥፋቶችን ከአጠቃላይ ‘የዲሲፕሊን ጉድለት’ ጋር የሚያስተሳስሩ ዘጋቢዎች የሚሉትን ማስተጋባቱ ቀሺም ይሆናል፡፡ የናይጄሪያ ጨዋታ ዋዜማ ላይ ቢቢሲ ቴሌቪዥን ላይ ስለ ቡድኖቹ የማለፍ ዕድል ሲያወራ የነበረ በስፍራው የነበረ ጋዜጠኛ የእኛን ቡድን እንደሌለ ሁሉ የሚያወራው ስለተቀሩት ሦስት ቡድኖች ነበሩ፡፡ ስለዚህ “አነደቁን” ቅብጥርስዮ ባንባባልና አንድናቆቱ የራሳችን ቢሆን እንመርጣለን፡፡ እናሳ ከተባለ ሌላ ትልቅ ነጥብ አለ…ምናልባትም በብዙ የአፍሪካ ዋንጫዎች ባልታየ መልኩ ከአገር ውጪ የሚጫወት ቡድን ልክ አገሩ ውስጥ የሚጫወት ያህል ያንን ያህል ደጋፊ ማግኘቱ በራሱ ተደጋግሞ ሊነገር የሚገባው ነበር፡፡ ስንቶቹ ‘የሚያደንቁን’ የውጪ ሚዲያዎች ናቸው ባለፍ አገደም ከመጥቀሰ ይልቅ የሚገባውን ትኩረት የሰጡት! ለዚሀ ውድድር ትልቁን ድምቀት የሰጡት በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የደመቁት ኢትዮዽያውያን ናቸው፡፡ ስንቶቹ የውጪ ጋዜጠኞች ናቸው ይህንን እውነታ ‘ህቅ’ ሳይላቸው ሊገልጹ የሞከሩት! “አደነቁን” አትበሉንማ! በነገራችን ላይ…ስፖርት በቀጥታ የማይመለከታቸው ፕሮግራሞች ሁሉ ስለ እግር ኳሱ መዘገባቸው ክፋት አልነበረውም፡፡ የአገር ጉዳይ ስለሆነ ይመለከታቸዋልና! ሆኖም ማበረታቻዎችን ከማስተላለፉ ባለፈ ሙያዊ ትንታኔዎች ውስጥ መግባታቸው ትክክል አይመስለኝም — ልክ የስፖርት ፕሮግራሞቹ ፊልምና ትያትር ሙያዊ ትንታኔ ውስጥ መግባታቸው ‘ፌይር’ እንዳልሆነ ማለት ነው፡፡እናማ…ማድነቁም ማወደሱም በእኛ ነው የሚያምረው፡፡ ልጆቻንን እናደንቃለን፣ እናወድሳለን፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው የፈጠሩት ነገር ከኳስ ያለፈ ነበር፡፡ እናማ…ልንሸልማቸው ይገባል፡፡ ይሄ እንዲህ ካለፋችሁ እንዲህ ታገኛላችሁ ምናምን ሲባል ከነበረው በዘለለ ልንሸልማቸው፣ ልናመሰግናቸው ይገባል፡፡ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ካብ ለካብ እንድንተያይ እያደረጉን ያሉትን የፖለቲካ፣ የዘር፣ የኃይማኖትና የመሳሰሉት አጥሮች ሁሉ ሰባብረው በአንድ ድምጽ እንድንጮህ ስላደረጉን አንድዬ ውለታችሁን ይመልስላችሁ ብለን ልንሸልማቸው ይገባል፡፡ በተለያየ ምክንያት ደቡብ አፍሪካ ሄደው ከከባዱ ኑሮ ጋር ቀን ከሌት የሚታገሉ ወገኖቻችን ለጥቂት ቀናትም ቢሆን በአገራቸው፣ በባንዲራቸው፣ ኢትዮዽያዊ በመሆን ጸጋቸው እንዲኮሩ ስላደረጓቸው አንድዬም ይስጣቸው እኛም ልንሸለማቸው ይገባል፡፡ የአዳነ ዕንባ የአገር ዕንባ ነበር፣ የእልህ እንባ ነበር፡፡ እንደዛ በተመስጦ ሲጸልዩ የነበሩ እህቶቻችን ይጸልዩ የነበሩት የሁላችንንም ጸሎት ነበር፡፡ ዕንባቸውን ያፈሱ የነበሩ የቡድናችን ደጋፊዎች የሁላችንም የእልህ ዕንባ ነበር ሲያነቡ የነበሩት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በመቶዎች እየሆንን በመርከብና በእግር ከአገር መውጣታችን ብቻ የሚታየው ዓለም፣ በየአገሩ ዋና ከተሞች መፈክሮችን ይዘን እርስ በእርሳችን መወጋገዛችን ብቻ የሚታየው ዓለም…አለ አይደል…ምንም መጣ ምንም፣ በእርግጥም “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮዽያዊም ኢትየዽያዊነቱን እንደማይተው…” ወደደም፣ ጠላም እንዲያምን ስላደረጉልን አንድዬም አለሁላችሁ ይበላቸው፤ እኛም ልንሸልማቸው ይገባል፡፡ ሁለት የሚመቹኝ አባባሎች አሉ…የሸገር ኤፍኤም. “ኢትዮዽያ ለዘለዓለም ትኑር!” እና ‘የአዲስ ዜማ’ “ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን!” የሚሉት፡፡ ኢትዮዽያም ለዘላለም ትኖራለች፣ በደቡበ አፍሪካ የታየው የልጆቻችን ጥረት፣ በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የነበረው የኢትዮዽያውያን አርቲፊሻል አጥሮችን ያፈረሰ አንድነት…አለ አይደል… ትልቅ የነበርን መሆናችንና ትልቅም እንደምንሆን በጣም አነስተኛ ከሆኑ አመላካቾች አንዱ ነው፡፡ በእርግጥም “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮዽያዊም ኢትዮዽያዊነቱን… አይተውም፡፡ ልጆቻችንን ልንሸልማቸው ይገባል፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3747 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 13:26