Saturday, 02 February 2013 13:00

“ውሃ ሄዳለች” - የካፌዎች ፋሽን!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ከወዳጅዎ ጋር ቡና እንደወረደ ጠጥተው (ለነገሩ አሁን አሁን ቡና እንደወረደ ሳይሆን ገብስ እንደወረደ እየተባለ ነው) ሲጨርሱ ውሃ መጠጣት ይፈልጉና “አስተናጋጅ እባክሽ ውሃ ታመጭልኝ” ይላሉ በትህትና፡፡ ቀልጣፋዋና ስልጡኗ አስተናጋጅ ከአፍዎ ቀበል አድርጋ “ሀይላንድ ወይስ የስ? አኳ ሴፍ ይሁን አኳ አዲስ?” እያለች የማዕድን ውሃ አይነት ትደረድራለች፡፡ እርስዎም “ኧረ የእግዜር ውሃ ነው ያልኩት” ይላሉ በግርምት፡፡ ቀልደኛ ቢጤም ከሆኑ እሷ አኳ ሴፍ ስትል “ኧረ ቧንቧ ሴፍ” ብለው ሊቀልዱ ይችላሉ፡፡ እሷ እቴ! ወይ ፍንክች “ውሃ ሄዳለች” የሚል ሌላ ቀልድ ትቀልዳለች፡፡እርሶ ምናልባት ቡና ካዘዙ በኋላ ወደ መፀዳጃ ቤት (አሁን እንኳን “ማረፊያ ቤት የሚል ዘመናዊ ስም ወጥቶለታል) ጐራ ካሉ በቧንቧ ውሃ እጅዎን ተለቃልቀው ይሆናል፡፡ እናም “እንዴ አሁን እኮ ቧንቧ ላይ እጄን ታጠብኩ… ከመቼው ውሃ ጠፋች?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ አጅሪት መች መልስ ታጣለች፡፡ “እንዴ እሱማ የታንከር ውሃ እኮ ነው” ትልዎታለች፡፡

በዚህን ጊዜ ትዕግስት ከሌለዎት መናደድና እልህ መጋባት ይጀምሩ ይሆናል፡፡ “ይሁን የታንከሩ ይምጣ” ካሉ እሺ ብላ ሄዳ ከነመፈጠርዎት ትረሳዎታለች፡፡ ይህን የሚያደርጉት ሁሉም የመዲናዋ ካፌዎች እንዳልሆኑ ሁሉ አንዳንድ ትልልቅ ሆቴሎችም “ውሃ ሄዳለች” የሚለው ፋሽን ተከታይ እየሆኑ እንደመጡ ሰምቻለሁ፡፡ እርሶ ድንገት ከእጮኛዎ አሊያም ገና ውሃ አጣጭ ትሆነኛለች ብለው ካሰቧት ሴት ጋር፣ አሊያም ከማይፈልጉት ሰው ጋር ሊሆን ይችላል እዚያ ካፌ ውስጥ የተቀመጡት፡፡ ታዲያ በዚህን ጊዜ “ሼም ነገር” ቆንጠጥ ያደርግዎትና “በቃ ሁለት የስ ውሃ አምጭልን” ይላሉ፡፡ አንጀትዎ እያረረ በጀትዎ እየበረሩ መቼስ እርሶ ጠጥተው አብሮ ያለው የክብር እንግዳ አይቀር አብሮ ያለውም ቢሆን እኔ ውሃ አላሰኘኝም የሚል ላይሆን ይችላል፡፡ ለማንኛውም በዛን ሰዓት ለቡና የበጀቱን ገንዘብ ከቡና አልፎ ላልታሰበ ነገር ይውልና በተለይ ደሞዝተኛ ከሆኑ እንደ ዩሮ ዞን አገራት የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ገብተው እርፍ! ፋሽኑ ከየት መጣ? በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ በውሃ እጥረት እየተናጠች ትገኛለች፡፡ ያነጋገርናቸው የካፊቴሪያና የሆቴል አስተናጋጆችና ባለቤቶችም እንደምክንያት የሚያቀርቡት የውሃ እጥረቱን ነው፡፡

“መቼም አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖር ሰው ውሃ በስንት ቀን ቧንቧውን እንደሚጐበኘው ያጣዋል ብዬ አላስብም” ይላሉ ፒያሣ የሚገኝ የአንድ ትልቅ ካፊቴሪያ ሃላፊ፡፡ የውሃ እጥረቱ የሚታወቅ መሆኑን የሚገልፁ አንድ ካፍቴሪያ የሚያዘወተሩ ጐልማሳ በበኩላቸው፤ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ውሃ በሚኖርበት ጊዜ ለመጠጥ አገልግሎት የሚውል ውሃ በዕቃ አጠራቅመው ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ አለባቸው ባይ ናቸው፡፡ እንደ ጐልማሳው ገለፃ፤ አንዳንድ ካፌና ሬስቶራንቶች የውሃውን መጥፋት ሰበብ አድርገው ለስላሳና የማዕድን ውሃቸውን ለማጣራት ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ ወጣት ኢብራሂም ፒያሣ አካባቢ የሞባይል መሸጫ ሱቅ አለው፡፡ በምሣ ሰዓትም ሆነ በሻይ ሰዓት የሚያዘወትራቸው የአካባቢው ካፌና ሬስቶራንቶች ምግብ አቅርበው ውሃ አብረው ለማቅረብ እንደሚቸገሩ ይናገራል፡፡

“ውሃ የለችም ሌላ የሚጠጣ ምን ላምጣልህ? ለማለት በጣም ፈጣን ናቸው፤ ለመሆኑ አንድ ምግብ ቤት ውሃ ከሌለው ለምን ምግብ ያቀርባል” ሲል ይጠይቃል ኢብራሂም፡፡ ወጣት እስጢፋኖስና ጓደኞቹ ጉዳዩን አስመልክተው ሲናገሩ፤ የውሃ እጥረት እንኳን ካፌና ሬስቶራንት ውስጥ ዘንድሮ ለፀበል የሚሆን እንኳን ጠፍቶ በጥምቀት ፀበል አለመረጨታቸውን ይናገራሉ፡፡ “የቧንቧ ውሃ እያለ ውሃ ሄዷል ማለት በአብዛኛዎቹ ካፌና ሬስቶራንቶች እየተለመደ ነው፡፡ በተለይ ትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ የቧንቧ ውሃ ለመጠጥ መጠየቅ እንደነውር እየተቆጠረ ነው” ይላል ወጣት እስጢፋኖስ የእስጢፋኖስ ጓደኛ አንድነት በበኩሉ “የውሃ ነገር ያሳሰበኝ በጥምቀት ዕለት ባየሁት እጥረት ነው፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ ለሚካሄድ የእምነት ሥነ ሥርዓት ለፀበል የሚሆን ውሃ ካጣን፣ ካፌና ሬስቶራንት ውስጥ ብናጣ ሊገርመን አይገባም” ሲል ስጋቱን ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ አስተያየት ሰጪዎቹ በየሁለትና ሶስት ቀኑ ውሃ ሲመጣ የመጠጥ ውሃ ገዝቶ በውሃ ማከሚያዎች ማከምና ማዘጋጀት እንጂ ወሩንና ዓመቱን ሙሉ “ውሃ ሄዳለች” በሚል ሰበብ የተጠቃሚን ኪስ መበዝበዝና ማራቆት አይገባም ባይ ናቸው፡፡ በዚህም አለ በዚያ ህብረተሰቡ በተለያዩ ምክንያቶች ብዝበዛ እየተከናወነበት ነውና የሚመለከተው አካል በካፍቴሪያዎችና ሬስቶራንቶች ላይ ተገቢውን ክትትል ቢያደርግ መልካም መሆኑን ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚገልፁት፡፡

Read 2476 times