Saturday, 02 February 2013 12:36

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(7 votes)

    መልክአ ኢትዮጵያ - ፫

ከአትላንታ ወጥቼ ሬኖ-ኔቫዳ ገብቻለሁ፡፡ይህች ከተማ እንደ ላስቬጋስ ታላቅ አትሁን እንጂ እንዳቅሟ የደራች የቆማሪዎች ሀገር ናት፡፡በመሀል ከተማዋ ከ12 በላይ ታላላቅ ቁማር ቤቶች አሏት፡፡ቆማሪዎቿ ከካሊፎርኒያ ጭምር እንደሚተሙባት በየቁማር ቤቶቹ መኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ የተደረደሩት የመኪና ሰሌዳ ቁጥሮች ይናገራሉ፡፡የከተማዋ እብደት የሚያበቃው ደግሞ መሀል ከተማዋ (Down town) ላይ ነው፡፡ከዚያ ውጭ ያለው ዙሪያዋ በተራራ የተከበበ፣ጸጥታ የሰፈነባት የመኖሪያ ከተማ ናት ይሏታል፡፡ ሬኖ ለኢትዮጵያውያን ተመራጭ ከተማ አልመሰለችኝም፡፡ ዋሽንግተን ተቀምጬ የናፈቀችኝን አሜሪካ እዚህ አግኝቻታለሁ፡፡ በከተማዋ የምትገኘው አንዲት የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤት አልፎ አልፎ ካልሆነ በሀገሯ ልጆች አትጎበኝም፡፡ ደንበኞቿም የውጭ አገር ዜጎች ናቸው፡፡በሬኖ የሀገርን ልጅ መንገድ ላይ ፈልጎ ማግኘት የማይቻል ስለሆነ ከተማዋ ትጨንቃለች፡፡

‹‹ከየት ነው የመጣሽው?›› የሚለው የአሜሪካኖቹ ተደጋጋሚ ጥያቄ በርከት ብሎ የቀረበልኝ በዚህች ከተማ በቆየሁበት ወቅት ነበር፡፡ ግብረ ሰዶማዊነት በአሜሪካ መባባሱ እና ቀስ በቀስ በተለያዩ ግዛቶች ለጋብቻ ሕይወትም እየተፈቀደ መሄዱ የኢትዮጵያውያን ራስምታት ጭምር መሆኑን ባለፈው ጠቆም አድርጌያችኀለሁ፤አንዲት እናት ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድ ልጇ ‹‹ማሚ ጓደኛዬን አስተዋውቅሻለሁ› ሲል በሰጣት ቀጠሮ ስላጋጠማት ጭንቀት ያወጋችኝን ልነግራችሁ ጀምሬ ነበር፡፡ ከአትላንታ ወጥቼ በአንድ ጊዜ ሬኖ የገባሁትም ለዚሁ ነው፡፡እንዳልኹት ሬኖ ለጥቂት ጠንካሮች ካልሆነ ብቸኝነቱ ሆድ ያስብሳል፡፡በዚህች ከተማ መኖር ከአገር ርቆ መኖርን የበለጠ የሚያከብደው ይመስለኛል፡፡የአገር ልጅ ያጡ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከዲያስፖራ ፊልፒንሶች ጋር ወዳጅነት መመስረታቸውን ተመልክቻለሁ፡፡ እኔና ወ/ሮ ሐረገ ወይን የተገናኘነው ጥቂት ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት በዚህች ከተማ ‹‹ሆስፒታል›› ውስጥ ነው፡፡

‹‹ሆስፒታል›› ስላችሁ ደግሞ ፈጠን ብላችሁ ‹‹ጥቁር አንበሳን›› ወይም ሌላ የምታውቁትን ሆስፒታል ታስቡ ይሆናል፡፡ሆስፒታሉ በሀገረ አሜሪካ ያየኋቸውን ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች ያስንቃል፡፡እርስ በርሳቸው ውስጥ ለውስጥ የሚገናኙ አምስት ሕንጻዎች አሉት፤ከአንደኛው ሕንጻ ወደ ሌላኛው ለመግባት ምቹ በሆኑ ሶፋዎች ላይ ዐረፍ ብሎ የመግቢያ ፈቃድ መጠበቅ የግድ ይላል፡፡ ይህን ሆስፒታል ልታስጎበኘኝ የወሰደችኝ ወ/ሮ ሐረገ ወይን የሆስፒታሉ ሠራተኛ ስትሆን የዘመዴ ጓደኛ ናት፡፡ሥራዋም በተመደበችበት ቦታ ላይ እየተዟዟረች በባለሞያዎቹ በሚሰጣት ጥቆማ መሠረት ያልተሟሉ ነገሮች እንዲሟሉ በሬዲዮ ጥሪ ማድረግ ነው፡፡ቀለል ያለ ሥራ ይመስላል፡፡ እኔና አስጎብኚዬ ከሶፋው ላይ ዐረፍ ብለን እየተጨዋወትን የሕፃናት ሕክምና የሚሰጥበትን ቦታ ለመጎብኘት ፈቃድ እስኪሰጥ እንጠብቃለን፡፡ቦታው ጸጥታ የሰፈነበት በመሆኑ የሹክሹክታ ያህል ቀስ እያልን ነበር የምናወጋው፡፡

በዚህ መካከል የተከፈተው የአሳንሰር ድምፅ ሁለታችንንም ወጋችንን አቋርጦ ትኩረታችንን ሳበው፡፡ ፀጉሯን በፋሽን የተቆረጠች፣ ቀጭን ዝንጥ ያለች ልጅ ቦርሳዋን በአንድ እጇ አስገብታ በአንድ እጇ የስታር ባክስ ቡናዋን እንደያዘች ከአሳንሳሩ ወጣች፡፤የፋሽን ትርኢት በምታሳይ ሞዴል አረማመድ በሽቶዋ አውዳን፣ማስቲካዋን እያላመጠች በአጠገባችን እልፍ አለች፡፡ ከሴቶች ማጌጫ የቀራት ነገር አለ ማለት አይቻልም፡፡ እኔ ‹‹ልጅቷ›› አልኳት እንጂ እሷ እንኳን ‹‹ልጁ›› ነበረች፡፡በጣም ተገርሜ ‹‹ወንድ ነው አይደል?›› ስል ወ/ሮ ሐረገወይንን ጠየቅኋት፡፡ ‹‹አዎ፤ ወንድ ነው፣ ግን ደግሞ ሚስት ነው›› አለችኝ፡፡ መጸየፏ ከፊቷ ያስታውቃል፡፡ እንዲህ ያለን ከተፈጥሮ ያፈነገጠ(?) ነገር ከሦስተኛ ወገን እየሰሙና እያወቁ አብሮ መዋል እንዴት ፈተና እንደሚሆን አሰብኩ፡፡ ‹‹እኔ እኮ በጣም ነው የሚገርሙኝ፤ወንዶቹ ሴት አንፈልግም ይሉና እንደ ሴት ይሆናሉ፤ ሴቶቹ ደግሞ ወንድ አንወድም ይሉና ወንድ ይመስላሉ፤ ተፈጥሮን አምሰው ገና ብዙ ጉድ ያመጡብናል›› አለችኝ አስጎብኝዬ፡፡ ከሃይማኖት፣ ከተፈጥሮና ከባህል ያፈነገጠ ነገር በሚካሄድበት አካባቢ ልጅ ወልዶ ማሳደግ ከባድ መሆኑንም አጫወተችኝ፡፡

በተለይ እንደ ሬኖ ባሉ ኢትዮጵያውያን በብዛት በማይገኙበት አካባቢ የእምነት ተቋማትና የማኅበረሰብ መሰባሰቢያዎች ስለሌሉ ልጆቹ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማይኖረው ድርጊት ክፉኛ ይጋለጣሉ፡፡ እዚያው የሚወለዱ እና የሚያድጉ ልጆች ቤተሰቦቻቸው የመጡበትን ሀገር ባህል በቃል እየነገሩ ብቻ እንዲቀበሉት እና እንዲጠብቁት አድርጎ ማሳደግ ቀላል አይደለም፡፡ በአብዛኛው ውሏቸውን የመምሰል ዝንባሌያቸው ጽኑ በመሆኑ ቤተሰብ በማይፈልገው መንገድ የመጓዛቸው ዕድል ሰፊ እንደሚሆንም አወጋችኝ፡፡ ወ/ሮ ሐረገወይን የሰባት ዓመት ልጇን ይዛ አሜሪካ የገባችው ከ16 ዓመታት በፊት ዲቪ ደርሷት ነው፡፡ መጀመሪያ የሄደችው ስፖንሰር የኾነቻት የሩቅ ጓደኛዋ ወደምትኖርበት ላስቬጋስ ነበር፡፡በተለያዩ ምክንያቶች ቬጋስ ምቾት አልሰጣትም፡፡ ልጇን እንደያዘች ከቬጋስ ኔቫዳ ወደ ሬኖ ኔቫዳ በዘመድ ትውውቅ ከተዘዋወረች በኋላ አገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቿን እየረዳች ኑሮዋን እየመራች ትገኛለች፡፡ ወ/ሮ ሐረገወይን ወዳጫወተችኝ ነገር ልመልሳችሁ፡፡ የወንድ ልጇ ውሎ ከነጭ ጓደኞቹ ጋር ነው፡፡ አሜሪካ እንደገቡ እርሱ በአብዛኛው ከአማርኛው ንግግር እየራቀ ለእንግሊዘኛው እየቀረበ ሲመጣ፤ እርሷ ደግሞ ካለችበት ብዙም ፈቀቅ አላለችምና እናትና ልጁ የሆድ የሆዳቸውን ለመጫወት ብዙም አላስቻላቸውም፡፡ ንግግራቸው ውስን ነው፡፡ ጠርከር ያለ የቤተሰብ ውይይት ለማድረግ ቋንቋ እንቅፋት ሆኗል፡፡ እርሱ ደግሞ ቅርበቱ የበለጠ ከፈረንጅ ልጆች ጋር እየሆነ ወደ ጓደኞቹ ቤተሰቦች እያደላ ትምህርት ቤት ሲዘጋም የእረፍት ጊዜውን ከእነርሱ ጋር ከከተማ ወጣ እያለ ማሳለፍ ጀመረ፡፡ እርሷ ኑሮዋን ለማሸነፍ ከምታደርገው ሩጫ በተጨማሪ የልጇ ውሎም ያስጨንቃት ገባ፡፡ ‹‹የሚገርምሽ ነገር ልጄ ላይ ያየሁት የተለየ ነገር የለም፤ ግን ጓደኞቹ ሁሉ ወንዶች ናቸው፡፡ እኔም ቤት ሲመጡ ኮምፒዩተር ላይ ተተክለው አያቸዋለሁ፡፡

እዚህ ደግሞ ምንድን ነው የምትሠሩት ብሎ ጥልቅ ማለት ያስቸግራል፡፡ በኢንተርኔት ምን ሲያዩ እንደሚውሉ ማወቅ አልችልም፡፡ እንደ እናት እና ልጅ ቁጭ ብለን በደንብ እንዳንወያይ ደግሞ የቋንቋ ችግር ነበረብን፡፡ ብቻ ምን አለፋሽ የሚሆነውንም የማይሆነውንም እያሰብኹ ሁልጊዜ እጨነቃለሁ›› አለችኝ፡፡ መፍትሔ ቢኾናት በማለት ብታደርገው ይሻላል ያልኹትን ነገር እጠቁማት ጀመር፡፡ እርሷ ግን ለሁሉም መልስ አላጣችለትም፡፡ ‹‹ገና ከልጅነቱ ቋንቋውን እንዳይረሳ አታደርጊም ነበር›› አልኋት፤ ‹‹እንዴት አድርጌ፤ እንደመጣን አካባቢ አንድ ሥራ እየሠራኹ፤ ለሥራ የሚጠቅመኝን ኮርስ ደግሞ እወስዳለሁ፤ እሱ ደግሞ ትምህርት ቤት ይሄዳል፤ እኔ እስክመጣ ሞግዚት ጋር ይቀመጣል፤ ቀኑን ሙሉ አማርኛ የማውራት አጋጣሚ አይኖረውም፤ እኔም ከመጣሁ በኋላ ራቱን በልቶ ስለሚደክመው ይተኛል፡፡ የት እንገናኛለን፡፡ የእኔ እንግሊዝኛ ደግሞ ቀለል ያሉትን መግባቢያዎች እንጂ ሌላውን ከየት ላምጣው፤ እንዲህ በመዋል በማደር ርቀታችን ሰፋ›› አለችኝ፡፡ ‹‹ቶሎ ቶሎ ወደ ኢትዮጵያ አትወስጅውም ነበር›› ሁለተኛ ያልኹት አማራጭ ነበር፡፡ ሣቀችብኝ፡፡ ‹‹በዚያ ሰዓት የእኔና የልጄን ወጪዎች ሸፍኜ ኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦቼን ለመርዳት ቀን ከሌሊት ሁለት ሥራ እየሠራኹ መልፋት እንጂ እርሱን እንዴት አድርጌ አስበዋለኹ›› አለችኝ፡፡ በመጨረሻ እርሷና ልጇ አንዴ ሲራራቁ አንዴ ደግሞ ሲቀራረቡ እርሱ አማርኛውን ሲረሳው፣ እርሷ ደግሞ እንግሊዝኛዋን በመቆየት ስታሻሽል ልጇ ዩኒቨርስቲ ገባላት፡፡፡ ልጇ ለአካለ መጠን የደረሰ ቢኾንም አንድም ቀን የሴት ጓደኛውን አስተዋውቋት አያውቅም፡፡ ‹‹ያለሁት ሀገሬ ቢሆን’ኮ በዚህ ዕድሜው የሴት ጓደኛ ያዘ መባሉን ብሰማ እንኳን ምን ሲደረግ ብዬ ረብሻ አነሣ ነበር፤ ግን እኔ ያለሁት አሜሪካ ነው፡፡ እሷ ደግሞ የጉድ አገር ናት፡፡ የነጻነት አገር ናት እየተባለ ለአእምሯችን የሚከብድ ነገር ይከናወንባታል፡፡ አንዳንዶቹ ጓደኞቹ ደግሞ እንደሴት ስለሚያደርጋቸው እፈራቸዋለሁ፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ላዋየው አስብና ይህን ዓይነት ነገር ማንሣቱ በራሱ ያስፈራኛል፡፡ አንዳንዴ ቴሌቭዥን ላይ እንደዛ ዓይነት ሲወራ አብረን ከሰማን የጎንዮሽ አነሣበትና አስጸያፊ እንደኾነ ሳወራው፡- ‹‹ማሚ መብታቸው እኮ ነው››ይለኛል፤ የባሰ እደነግጣለሁ፡፡ እናት እንዲሁ ግራ እንደተጋባች ልጁ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ሲጨርስ ወደ ኢትዮጵያ ይዛው ለመሄድ ወስና የሐሳብ ዝግጅት ጀምራለች፡፡ በዚህ መሃል አንድ ቀን እርሱ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ ‹‹ማሚ ጓደኛዬን አስተዋውቅሻለሁ›› አላት፡፡ ልጇ ጓደኛዬን እንጂ የሴት ጓደኛዬን አላላትምና ደነገጠች፡፡

‹‹ጉዳዩን አብራርቶ እንዲነግረኝ መጠየቁ አስጨነቀኝ፤ ምን ዓይነት ጓደኛ ብለው እንዴት በመጥፎ ነገር ጠረጠርሽኝ ብሎ ሊጣላኝ ይችላል፡፡ የወንድ ጓደኛ ቢለኝ ደግሞ የመሞቻዬ ሰዓት ያኔውኑ ነው፡፡ እንዲሁ በድንጋጤ ዝም እንዳልኹት ሌላ ሐሳብ ሳይመጣልኝ እሺ ብዬ የቀጠሮ ቀን ተቀበልኹት፡፡›› ወ/ሮ ሐረገወይን እንዳጫወተችኝ ከልጇ እንደተለየች ወዲያውኑ ለአንዲት ፊሊፒንስ ጓደኛዋ ትደውልና ጭንቀቷን ታዋያታለች፡፡ ጓደኛዋ ነገሩን ቀለል አድርጋ ‹‹ጓደኛህ የኛ አገር ልጅ ናት ወይስ ፈረንጅ ናት?›› ብላ እንድትጠይቀው ትመክራታለች፡ ‹‹ኢትዮጵያዊ ከየት አመጣለሁ ብለሽ ነው፤ ቢለኝስ ወይም ደግሞ የፈራሁትን ቢነግረኝ?›› ትላትና ሐሳቧን ሳትቀበል ሁሉንም የዕለቱ ዕለት ለማየት ትወስናለች፡ ጭንቀቷን የተረዳችው ፊልፒናዊት እና ከሬኖ ወጣ ብላ በምትገኘው ሳክራሜንቶ የምትኖር ዘመዷ በቀጠሮው ቀን መጥተው አብረዋት ሆኑ፡፡ ወ/ሮ ሐረገወይን ስታወራ የፊልም ታሪክ የምትተርክ ትመስላለች፡፡ ጨዋታ ደግሞ ታውቅበታለች፡፡ እኔ ልቤ ከመሰቀሉ የተነሣ የመጨረሻውን አስቀድማ እንድትነግረኝ ሁሉ ወትውቻት ነበር፡፡ ‹‹ቆይ ልነግርሽ አይደል?›› እያለች መጨረሻውን እየቆጠበች ካቆመችበት ትቀጥላለች፡፡ ዕለተ ቅዳሜ ትውውቁ በምሳ ፕሮግራም ነው፡፡

እርሷ የመሥራት አቅም አጥታለች፤ ጓደኞቿ ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡ ‹‹እኔ ምንም አልሠራም እነሱ ሲሠሩ ሥር ሥራቸው እየሄድሁ ማውራት ብቻ ነው፡፡ ውስጤ ጭንቅላቴ የሚያስበውን አልተቀበለውም፤ ልጄን ባልዋለበት እያዋልኹት እንደሆነ ይታወቀኛል፤ ግን ደግሞ እንደ ጓደኛ ሆነን ምስጢር እየተጋራን ስላላሳደግኹት ከየትኛው ምድብ እንደዋለ ለመገመት ተቸገርኹ፤ ቀኑም ዓመት ሆነብኝ፡፡›› አይደርስ የለምና ሰዓቱ ደረሰ፤ እናትና ልጅ የሚኖሩበት አፓርትመንት የመኖሪያ በር መጥሪያ ተደወለ፡፡ ‹‹ደውሉን ስሰማ መደበቅ አምሮኝ ነበር፤ ግን ደግሞ በሩን መክፈት ያለብኝ እኔ ነኝ፤ እንደምንም ብዬ በሩን ከፈትኹ፡ ዐይኔ ማመን አቃተኝ፤ የልጄ ጓደኛ ሴት ነች ያውም ቆንጅዬ ኢትዮጵያዊት፡፡ ደስታና ድንጋጤ ተፈራረቀብኝ፡፡ የፈራሁትን ይዞ ቢመጣ እንኳን እንደዚያ የምደነግጥ አይመስለኝም”፡፡ እርሷ የምታውቃቸው በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ከተማ ልጇ ከምን ውስጥ እንዳመጣት ግራ አጋብቷታል፤ ድንጋጤውም ከዚህ ግራ መጋባት የመነጨ ነው፡፡ ‹‹በጣም ከመደሰቴ የተነሳ ወርቄን አውጥቼ ስጦታ ሰጠኋት፡፡ ልጅቷን ከኢትዮጵያ በማደጎ ያመጧት አሜሪካውያን አሳዳጊዎቿ ናቸው፡፡ አሳዳጊዎቿ ከሚኖሩበት ሀገር ልጄ ወደሚማርበት ዩነቨርስቲ ልከዋት እዚያ አብረው ሲማሩ ነው የተገናኙት፡፡ “እግዜር ይስጣቸው ከጭንቀት ገላገሉኝ አልኹ፡፡ በአንድ ጊዜ ቤተሰብ ሆንን›› አለችኝ፡፡ ስለ ልጆቹ ዕድገትና ስለታዘበችው ማንነትን ፍለጋ በመገረም አጫውታኛለች፡፡ ‹‹የገረመኝ ደግሞ ልጄ ሲመጣ እንደነገርኩሽ ሰባት ዓመቱ ነበር፡፡ እርሷ ደግሞ በጣም ሕጻን ሆና እንደመጣች ነግራኛለች፡፡ ሁለቱም ኢትዮጵያ ስለምትባል ሀገር ምንም ትዝታ የላቸውም፡፡ አሜሪካውያን ናቸው፤ያደጉትም ከአሜሪካውያን ጋር ነው፤ ግን እንዲህ ተፈላልገው መገናኘታው አይገርምም?›› ስትል መልሳ እኔኑ ጠየቀችች፡፡ ‹‹አሁን ሲያልፍ እንዲህ እየቀለድኹ ላውራው እንጂ በወቅቱ በጣም አስጨንቆኝ ነበር፡፡እኔ መጀመሪያ እዚህ ስመጣ ቁማር ቤቶች ውስጥ ጽዳት ነበር የምሠራው፡፡ ቁማር ቤቶቹ ውስጥ ደግሞ መዝናኛ ቤትም ጭምር ነበር፡፡

በቤቶቹ ውስጥ ዐየው የነበረውን ጉድ መልሶ ለማሰብ እንኳን ይከብደኛል፡፡ ወጣቶች ይመጡ ስለነበር ልጄን የማየው በእነሱ ዐይን ነው፡፡ ሁለተኛው ሥራዬ ደግሞ የትምህርት ቤት ውስጥ ጽዳት ነበር፡፡ በት/ቤቱ ጥሩ ተማሪዎች እንዳሉ ሁሉ ያልሆነ ሥራ የሚሠሩ በርካታ ተማሪዎችም አያለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ ጭንቀት ውስጥ ወደቅኹ፡፡ ሌላ ከተማ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተፈላልገው አንድ አካባቢ ይሠራሉ፤ አንድ አካባቢ ይኖራሉ፤ ቤተ ክርስቲያን አንድ ላይ ይሄዳሉ ሲባል እሰማለሁ፡፡ በጣም ትክክል ናቸው ወደው አይደለም እንዲህ የሚያደርጉት፡፡ የኛ ባህል የተለየ ስለሆነ የሚመጣውን ነገር በጸጋ መቀበል አንችልም፡፡ ስለዚህ ባለንት እርስ በእርሳችን መወዳጀት ይሻለናል›› በማለት ትመክራለች፡፡ አሁን የወ/ሮ ሐረገወይን ጭንቀት ተወግዷል፡፡ ልጇ ከሴት ያውም ከኢትዮጵያዊት ጓደኛው ጋር አስተዋውቋታል፡፡የነበራትን ስጋት ግን ለእኔ እስካጫወተችኝ ድረስ ለልጇ አልነገረችውም፡፡ የነገረችኝን እንደምጽፈው ስነግራት ‹‹ምኑን?›› አለችኝ፤ ያጫወትሽኝን ነዋ፤ይህ እኮ ለብዙ ወላጆች ማስተማሪያ ይሆናል አልኋት፡፡››ትንሽ አሰብ አደረገችና ‹‹ጻፊዋ ልጄ እንደሆነ አማርኛ አያነብ፤››አለችኝ፡፡ ወ/ሮ ሐረገ ወይን ስለአሳለፈችው ጊዜ ስታስብ ምናልባት በርካታ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ቦታ ብትኖር ኖሮ እንዲህ ያለው ጭንቀት እንደማይጎበኛት ትናገራለች፡፡ ይህ አስተሳሰብ ግን የእርሷ ብቻ ነው፡፡ እኔ ያገኘኋቸው አንዳንድ ወላጆች የትም ይኑሩ የት ይህን ከማሰብ አላገዳቸውም፡፡ አንዲት በቦስተን የምትገኝ የዘጠኝ ዓመት ሴት ልጅ ያላት ዘመዴ ስለዚህ ጉዳይ አንሥተን ስንጨዋወት ‹‹ስላላወቀች ነው እንጂ እነሱኮ ጓደዬን ላስተዋውቅሽ ሳይሆን “ፓርትነሬን” ነው የሚሉት›› አለችኝ፡፡ ስለራሷም ልጅ አንሥታ ‹‹የእኔ ልጅ ግን ከአሁኑ ለይታልኛለች፤ ተገላግዬአለሁ›› አለችኝ፡፡ ‹‹ገና በዘጠኝ ዓመቷ?›› ደንግጬ ያቀረብሁት ጥያቄ ነበር፡፡ ድንጋጤዬን የጨመረው ደግሞ የእናት እየሣቁ ማውራት ነበር፡፡

ልጇ በዘጠኝ ዓመቷም ቢሆን አንድ የክፍሏን ተማሪ እንደ ወደደችው ስለነገረቻት ደስ ብሏታል፡፡ ያስደሰታት ልጁን መውደዷ ሳይሆን ፍላጎቷ ከወዲሁ ወደ ተቃራኒው ፆታ ማመዘኑን በማረጋገጧ፡፡‹‹ሌላው ነገር ከዕድሜ ጋር የማይሄድ መሆኑን መክሮ መመለስ ቀላል ነው፡፡ እኔም አባቷም መክረን መልሰናታል” ትላለች፡፡ የዚህች ልጅ እናት እና አባት የሚሠሩት ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነው፡፡ ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ስላጋጠማት ነገር አውግታኛለች፡፡ በምትሠራበት ዲፓርትመንት ውስጥ አንዲት በጣም ጎበዝና ቆንጆ ወጣት ኢትዮጵያዊት አለች፡፡ ልጅቷ በሰው ዘንድ ተወዳጅና በሥራዋ ደግሞ ምስጉን ነች፡፡ ምንም እንኳን የዕድሜ አቻዋ ባትሆንም ስለምወዳት ታቀርባታለች፡፡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋርም ትተዋወቃለች፡፡ ‹‹እኔ እዚህ በመጣኹበት ጊዜ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት አፍቃሪዎች ራሳቸውን መግለጽ ይፈሩ ነበር፡፡ በአንዳንድ ግዛቶች የጋብቻው ሕጋዊነት ከተረጋገጠም በኋላ ቢሆን የእነርሱ ወደሆኑ ቦታዎች ካልተሄደ እና ግምታዊ ፍረጃ ካልተሰጠ በስተቀር “እኔ እንዲህ ነኝ” ብሎ የሚናገር ሰው አላጋጠመኝም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ራሳችንን መደበቅ የለብንም፤ ማንነታችንን መግለጽ አለብን፤ የሚል ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ ታዲያ ልጅቷ ይህን መነሻ አድርጋ አንድ ቀን ምሳ ስጋብዛት “ፓርትነሬን ይዤ መምጣት እችላለሁ?” አለችኝ “የት? እኔ ቤት? ይቅርታ ላስተናግድልሽ አልችልም” ስል መለስኩላት፡፡

ከዚያ ቀን ጀምሮ ደግሞ የልጅቷን ማንነት አወቅኹ›› በጣም ደነገጥሁም ተናደድኹም፡፡ የደነገጥኹት የልጅቷ ጉብዝና እና ሥነ ሥርዓት እንድወዳት አድርጎኝ ነበርና በዚህ አላሰብኋትም፡፡ የተናደድኹት ደግሞ ኢትዮጵያዊት በመኾኗ ነበር፡፡ ግንኙነቴን በፊት ከነበረው ብቀንስም የእርሷ ጥሩ ጠባይ ግን አልተቀየረም ነበር፡፡ አንድ ቀን ኢትዮጵያ ደርሳ ተመልሳ ምሳ ስንበላ ሀገር እንዴት እንደሰነበተ ጠየቅኋትና ስትመልስልኝ ቆየች፡፡ስለወላጆቿ ጤንነት ስጠይቃት “ለቤተቦቼ ነገርኳቸው እኮ” አለችኝ በድንገት፤ ‹‹ምኑን?›› ስላት ልጅ እንዳይጠብቁ፤ መሀል አናቴን በአንዳች ብረት እንደተመታ ሰው ተሰማኝ፡፡ ለእናት ለአባቷ አንድ እንደሆነች አውቃለሁ፡፡ እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን ምን ሊሰማኝ እንደሚችል አሰብኹ፡፡ እርሷ ቤተሰቦቼ ሲሰሙ ‹‹ጥቂት ከመደንገጥ በስተቀር ምንም አላሉም” ትበል እንጂ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ አባት እና እናት ምን ሊሆን እንደሚችል ስለምገምት አሳዘኑኝ፤” አለችኝ፡፡ ግብረ ሰዶማዊነትን የሚቃወም የአሜሪካ ሕዝብ አንዳለ ሁሉ በሐሳብም በተግባርም የሚደግፈው ሰው ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡ አሁን አሁን እንዲያውም የደጋፊው ቁጥር ከተቃዋሚው እየበለጠ ድርጊቱ የመብት ጉዳይ መሆኑና ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ ራስምታት ሆኗል፡፡እንዲህ ያለ ወደ ተመሳሳይ ፆታ የሚያተኩሩ ሰዎች ለሌሎች ሰዎች በጣም መሆንን እንደ አንድ መለያ ባሕሪ አድርጎ መንቀሳቀስ ሳይወዱ በግድ ለመቀራረብ ምክንያት እየሆናቸው መምጣቱን ኢትዮጵያውኑ አጫውተውኛል፡፡ ግብረሰዶማውያኑ በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ሠርገው ከመግባታቸው በተጨማሪ ቤተክርስቲያ ሳትቀር ድጋፍ ስትሰጥ ተስተውላለች፡፡

አንድ ቄስም በቴሌቭዥን ውይይት በሚደረግበት ጊዜ ራሳቸው ግብረሰዶም መሆናቸውን እና ስለጥሩ ባሕሪያቸው ማብራሪያ ሲሰጡ ተመልክቻለሁ፡፡እንዲህ ያሉ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ደግሞ በየቀኑ በበርካታ የቴሌቭዥን ቻናሎች ላይ ስለሚተላለፉ ኢትዮጵያዊያን የማየት ዕድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በመጀመሪያ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ከክርስቲያን ቤተሰብ የተገኙ በመሆናቸው የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን (ግብረ ሰዶማዊነትን) እንደማይደግፉ ሲናገሩ ብዙዎች ግብረሰዶማዊነት የሕግ ዕውቅና እንደማያገኝ ተስፋ እንደነበራቸው ነግረውኛል፡፡ አሁን ደግሞ በማይታወቅ ምክንያት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ደጋፊ ሆነዋል፡፡  ከዚህም ባሻገር በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ጋብቻውን ሕጋዊ ያደረጉ ግዛቶች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ አህጉር የፓርቲ ፖለቲካ ሥልጣን መወሰኛና የመንግሥታቱን ፖለቲካዊ ድጋፍ ያገኘው የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ፤ ድንበር ተሻግሮ የልማት ርዳታ መስፈርትና የአገሮቹን ግንኙነት የሚወስን ከፋፋይ አጀንዳ ለመኾን የደረሰ መስሏል፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4801 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 12:51