Saturday, 02 February 2013 12:16

ኀይል የተቀላቀለበት የኤርትራውያኑ ተቃውሞ ቀጥሏል

Written by  ጽዮን ግርማ
Rate this item
(13 votes)

ዓሊ አብዱ ከሥርዐቱ መኮብለላቸውን ዐወጁ .

በአዲስ አበባም የተቃውሞ ሰልፍ ወጡ 
ሳላህ ዩኑስ ከኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር ዓሊ አብዱ ወንድሞች አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ወንድሜ በከፍተኛ በድንጋጤ ውስጥ ይገኛል፤›› ይላሉ ወንድማቸው ስላሉበት ሠቆቃ ‹‹ኤክስፕረሰን›› ለተሰኘው ዕለታዊ የስዊድን ጋዜጣ ሲያስረዱ፡፡
‹‹ኤክስፕረሰን›› እንዳስነበበው፣ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገቡት ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡ አንዱ፥ የሚኒስትሩ አባት፣ ወንድማቸው እና የ15 ዓመት ሴት ልጃቸው የእርሳቸውን መኰብለል ተከትሎ በኤርትራ መንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ቁጥጥር ሥር መውደቃቸውና ጭካኔውን በውል በሚያውቁት ሥርዐት የሚደርስባቸውን ሥቃ ሲያስቡት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ባለፉት ዓመታት በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ሥርዐት ኊልቍ መሳፍርት የሌላቸው ኤርትራውያን ለከፋ ጥፋት የተዳረጉበትን ኹኔታ በማስታወስ ነው፡፡
እ.አ.አ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ለሥራ በተጓዙበት ጀርመን አገር እንደኮበለሉ የሚነገረው የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፥ ድምፃቸውን ለሦስት ወራት አጥፍተው ከቆዩበት ያልታወቀ ስፍራ ኾነው በወንድማቸው አማካይነት ከ‹‹ኤክስፕረሰኑ›› ጋዜጠኛ ካሲም ሃማዴ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ለምን እንደኮበለሉ፣ የትና በምን ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኙ መናገር አይሹም፡፡ ከጋዜጠኞች ጋራ በስልክ እንኳ ቃለ ምልልሱ ለማካሄድ ያልፈቀዱት ሚኒስትሩ፥ ለ‹‹ኤክስፕረሰን›› ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አሜሪካ በሚኖሩት ወንድማቸው ሳላህ ዩኑስ አማካይነት ነው፡፡
የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ቀራቤ መንግሥት ከኾኑት ሹማምንት አንዱ የነበሩት የ47 ዓመት ጎልማሳው ዓሊ አብዱ ሥርዐቱን ትተው መሰደዳቸውን ባረጋገጡበት የ‹‹ኤክስፕረሰኑ›› ቃለ ምልልሳቸው፥ የሥርዐቱ ምስጢራዊነት/ድብቅነት ከውጭው ዓለምና ከሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለፕሬዝዳንቱ ቅርበት ካላቸው ቁልፍ ባለሥልጣናት ጭምር እንደኾነ ሲነገር የቆየውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፋኝ ሥርዐት በአሠቃቂ ኹኔታ ታስረው ስለሚሠቃዩት ቡድን-15 ስለሚባሉት የመንግሥቱ የቀድሞው ባለሥልጣናት፣ሌሎች ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች አንዳችም እንደማያውቁ ነው የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ዓሊ አብዱ የተናገሩት፡፡
በትውልድ ኤርትራዊ በዜግነት ስዊድናዊ የኾነውና እ.አ.አ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አገዛዝ ያለፍርድ በእስር እየማቀቀ ያለውን ጋዜጠኛ ዳዊት ይሥሓቅ በሚገባ እንደሚያውቁት የገለጹት አቶ ዓሊ አብዱ፣ ስለ ጋዜጠኛው ኹኔታ እርሳቸውም ይኹኑ ሌሎች ሚኒስትሮች ለመጠየቅ እንደማይደፍሩ አልሸሸጉም፡፡ በሠላሳ ዓመቱ የጎሬላ ትግል የዳበረው የታዘዙትን ነገር እንደታዘዙት ተቀብሎ ሳይጠይቁ የመፈጸም ባህል ቋሚ የመንግሥቱ ሥርዐት መኾኑን የሚናገሩት አቶ ዓሊ፥ በኤርትራ ማንኛውም ባለሥልጣን ወይም ሓላፊ ከሥራው ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌለው ነገር ጠይቆ ለመረዳት መሞከር አደጋ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡
ትውልደ ኤርትራዊው ዳዊት ይሥሓቅ እ.አ.አ በ1987 በስዊድን የፖሊቲካ ጥገኝነት ጥያቄ አቅርቦ፣ በ1992 ስዊድናዊ ዜግነት አግኝቷል፡፡ ለእስር የተዳረገው ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ ኤርትራ ተመልሶ ‹‹ሰቲት›› ለተሰኘው ሳምንታዊ የግል ጋዜጣ ሲሠራ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አገዛዝ ስዊድናዊውን ዳዊት ይሥሓቅ ለእስር በመዳረግ ደብዛውን ካጠፋበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በሥርዐቱ እና በስዊድን መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እክል እንደገጠመው ቆይቷል፡፡
እንደ አቶ ዓሊ ገለጻ፣ ስለ ዳዊት ይሥሓቅ ዕጣ ፈንታ ስንኳን ሌሎች ሲቭል ባለሥልጣናት የፖሊስ ኀይሉ አዛዥ እንኳን መረጃው የላቸውም፡፡ ጋዜጠኛው የትና በምን ኹኔታ ላይ እንዳለ የሚያውቁት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ እና ከፕሬዝዳንቱ ጋራ እጅና ጓንት ኾነው የሚሠሩት የደኅንነት ሓላፊው ብቻ ናቸው፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የአገሪቱ የተቃውሞ ኀይሎች በኤርትራ የከፋ የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ረገጣ መኖሩን አሰምተው የሚናገሩ ሲሆን ‹‹ኤክስፕረሰን›› ጨምሮ ሌሎችም የስዊድን ብዙኀን መገናኛዎች ጋዜጠኛ ዳዊት ይሥሓቅ ከእስር እንዲለቀቅ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ ይኹንና አሁን ከመንግሥቱ የኮበለሉት የሥርዐቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሰጡት ምላሽ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት ይሥሓቅ ከእስር ሊለቀቅ ቀርቶ በሕይወት ስለመኖሩ እንኳ ለቤተሰቦቹና ለሰብአዊ መብቶቹ ተሟጋቾቹ በጭላጭል የቀረበላቸውን ያለውን ተስፋ ያጨለመ መርዶ እንደኾነባቸው ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት ወቅት፣ ለጋዜጠኞች ይሰጧቸው በነበሩ ከሐቅ የራቁና የተጋነኑ የዐውደ ውጊያ ውሎ መግለጫዎች በቀድሞው የኢራቅ መንግሥት ባለሥልጣን ተመሳስሎ ‹‹ኮሚካል ዓሊ›› የሚል የኩሸት ስም የተሰጣቸው ኮብላዩ የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር ስለ ዛሬዋ ኤርትራ የሚያጋንኑት ይኹን የሚያዛቡት መግለጫ የላቸውም፡፡ ራሳቸውን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው አገዛዙ በዜጎቹ ላይ የሚያወርደው ግፍ ኹነኛ ምስክሮች ናቸው፡፡ ኹኔታው ያንገፈገፋቸው ወገኖች በአገር ውስጥም በውጭም ወደ ዐደባባይ በመውጣትና የኀይል ርምጃም በመውሰድ ተቃውሟቸውን አንድ ርምጃ ወደፊት ወስደውታል፡፡
አሥመራ የሚገኘውን የማስታወቂያ ሚኒስቴር በኀይል በመቆጣጠር የተጀመረው ተቃውሞ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያንም በየኤምባሲዎቹ ቀጥለውበታል፡፡ ከዚህ ቀደም ኤርትራውያን ከአገራቸው ውጭ ሆነው በአገዛዙ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ ገጽታቸውን ከእይታ ሸፍነው የነበረ ሲሆን አሁን ግን አገዛዙን ፊት ለፊት ለመቃወም የወሰኑ ይመስላሉ፡፡ ምንም እንኳን ተቃውሞው በተጠናከረ መልኩ አይቀጥል እንጂ ከ15 ቀናት በፊት ሎንደን በሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ የተጀመረው በሌሎች አገሮች በሚገኙ ኤምባሲዎችም ላይ ቀጥሏል፡፡
በሎንደን ኤርትራውያን ወጣቶች እና አዛውንቶች ኤምባሲውን ሰብረው ከገቡ በኋላ የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን ፎቶ ግራፍ ከተሰቀለበት አውርደው መሬት እየጣሉና ወደታች እየዘቀዘቁ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ የሚያሳይ ምስል በድረ ገጾች ተሠራጭቷል፡፡
ረቡዕ ዕለትም በግብጽ ካይሮ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ በኤርትራውያን ተቃዋሚዎች ተከቦ ውሏል፡፡ “ሜይ 24 ዩዝ ሙቭመንት” በሚል መጠሪያ ተደራጅተው አገዛዙን ለመቃወም የወጡት እነዚህ ወጣቶች፣ በዐረብኛ እና በእንግሊዝኛ የተጻፉ መፈክሮችን አንግበው ታይተዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ኢሳይያስን ፎቶግራፍ ከጋዳፊ ምስል ጋር አጣምረው በመያዝ፣ በጋዳፊ ላይ የ “X” ምልክት አኑረው በአቶ ኢሳይያስ ላይ እንዲያነጣጠር በማድረግ “ተረኛው አንተነህ” የሚል መልእክት አዘል መፈክር ይዘው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
በተመሳሳይ ቀን ጣሊያን ሮም የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ በኤርትራውያን ተቃዋሚዎች ተከቦ የዋለ ሲሆን የኢሳይያስ መንግሥት ጭቆና እና አፈና እንዲያበቃ ጠይቀዋል፡፡ ተቃውሞው በበርሊንም የቀጠለ ሲሆን ሱዳን ካርቱም በሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ተቃውሞአቸውን ለማሰማት የተሰባሰቡ ወጣቶች በፖሊስ ርምጃ መበተናቸው ታውቋል፡፡ ተቃውሞው ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ በሎንደን ቀጥሎ እንደሚውል እየተሰማ ነው፡፡
ቁጥራቸው ወደ 400 የሚጠጉ የኤርትራ ስደተኞች እና ተማሪዎች አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት የቀድሞው መግቢያ በር ላይ ጥር 23 ቀን 2005 ዓ.ም ተገኝተው፤ በኢሳይያስ አገዛዝ ዜጎች ለሞት እና ለማያባራ ስደት መጋለጣቸውን በመግለጽ በኤርትራ መንግሥት በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ኢሰብአዊ ድርጊት እንዲያበቃለት፣ የአፍሪካ መንግሥታት ተመሳሳይ አቋም እንዲወስዱ ጠይቀዋል፡፡ ሰልፉን ያካሄዱት ወጣቶች ከመፈክሮቻቸው በተጨማሪ በፊርማ የተደገፈ አቤቱታቸውን ለኅብረቱ ጽ/ቤት ለማቅረብ ተዘጋጅተው የነበረ ቢኾንም የተቀበላቸው አካል ግን አልነበረም፡፡

Read 6183 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 17:05