Saturday, 26 January 2013 17:14

ጎንደርን ጉብኝት - በበዓለ ጥምቀት ለታሪካዊ ቅርሶች ተገቢው ትኩረት አልተሰጠም

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekle@gmail.com)
Rate this item
(2 votes)

“ቱሪዝም በኢትዮጵያ” በተሰኘ በጥናት የተደገፈ መጽሐፋቸው ጌታቸው ደስታ የጥምቀት እንዲሁም የቃና ዘገሊላ ሚካኤል ክብረ በዓላትን አስመልክተው “በጐንደር በተለይ አፄ ፋሲለደስ መታጠቢያ ተገኝቶ የጥምቀት በዓልን ማክበር እጅግ በጣም ጐብኚዎችን የሚያስደምም ትርዒት ነው” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ በዓለ ጥምቀት መዲና የሆነችው ጐንደር፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶችንም ጭምር ተመልከቱልኝ ትላለች፤ ጥምቀቷን አስታካና ከዚያም ውጪ ባሉ ቀናት፡፡ ጥምቀትን ተንተርሰው በከተማይቱ አስተዳደርና በሀገሬ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ከተዘጋጁት ፌስቲቫሎች አንዱ ባለፈው ሳምንት ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው “ኢትዮጵያን በጐንደር የባህል ፌስቲቫል” ነው፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ከጐበኘሁአቸው ታሪካዊ ቅርሶች መካከል ልክ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ከቋራ ወጥተው የኢትዮጵያን ታሪክ ለመለወጥ የጣሩ አንዲት ትልቅ ሴት ይገኙበታል፡፡ በ18ኛው ክፍለዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ፣የነገሥታት ልጆች ታስረው ከሚጠበቁበት ለንግሥና የበቁት አፄ በካፋ ሁለተኛ ሚስታቸውን ያገቡት እንደተራ ሰው መስለው በሄዱበት ሲታመሙ በወላጆቿ ፍቃድ አንዲት ልጃገረድ አስታማቸዋለች፡፡ ከሕመማቸው ያገገሙት በካፋም ንግሥት አደረጓት፡፡

የንግሥትነት ዘውድ የተቀዳጀችው የያኔዋ ብርሃን ሞገሳ ወይም ወለተ ጊየርጊስ በኢትዮጵያ ታሪክ የምትታወቀው “ቋረኛዋ እቴጌ ምንትዋብ” በሚል ስሟ ነው፡፡ እንደ ንግሥቲቱ ሁሉ ከቋራ የፈለቁት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ አንድነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አምና በጐንደር ከተማ እምብርት ላይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ትተውት ከሄዱት ታሪክ ውጭ በጐንደር እንደቀደምት ነገሥት ቤተመንግሥት ያልተውት አፄ ቴዎድሮስ ያህልም ባይሆን ቋረኛዋ እቴጌ ምንትዋብ በዘመናቸው የነበረችይቱን ኢትዮጵያ በዙፋን እና ከዙፋን ጀርባ መርተዋል፡፡ ምንም እንኳ ከባላቸው አፄ በካፋ የተጀመረ አመራራቸው እስከ ልጅ ልጃቸው ተፍፃሜተ - መንግስት አፄ ኢዮአስ ቢደርስም የንግሥና ዘመናቸው በራስ ስዑል ሚካኤል ቀታሌ ንጉሥ ሲያበቃ የተዳከመች ኢትዮጵያን ጥለው አልፈዋል፡፡ እኒሁ ንግሥት ከተዋቸው መንፈሳዊ ቅርሶች አንዱ ራሳቸው ያሰሩት የቅድስት ቁስቋም ማርያም ቤተክርስትያን ናት፡፡ ቤተክርስትያኗ የንግሥቲቱን፣ የልጃቸውን የቋረኛ አፄ ኢያሱን እና የልጅ ልጃቸውን አፄ ኢዮአስን አጽም ጨምሮ በርካታ ቅርሶችን ይዛለች፡፡ ከነዚህ ቅርሶች መካከል የታላቁ አባይ ወንዝን መነሻ ለማጥናት ብሎ አስቴር የተባለች ኢትዮጵያዊት ያገባው ስኮትላንዳዊው አሳሽ ጀምስ ብሩስ መኖሪያ ቤት ፍርስራሽ አለ፡፡

ከዚሁ ጐን ንግሥቲቱ በአደፍ ወቅት የቤተክርስትያን አገልግሎት የሚሳተፉበት ቤት እና ጳጳሱ ወይም በማዕረግ ከፍተኛ የሆነው ካህን “እግዚአብሔር ይፍታሽ” የሚሉባቸው ከፍታ ቦታም ይገኛል፡፡ ከሱ ባሻገር የሚገኘው ደግሞ እቴጌ ምንትዋብ ካህናቱንና ሌሎች እንግዶች ግብር የሚያገቡበት ወይም በዘመኑ አጠራር ምግብ የሚያበሉበት አዳራሽ ይገኛል፡፡ አዳራሹ የንግሥት እና የካህናት ብልሃት የተወዳደረበት አንድ ታሪክም አለው፡፡ ቋረኛዋ ምንትዋብ መንገዶቻቸው ቢለያዩም እንደ ቋረኛው ካሳ አፄ ቴዎድሮስ ሁሉ ካህናቱን በእጅ ለማስገባት ያደረጉት ጥረት፣ ንግሥታዊ ምንጣፋቸውን የሽንት ጨርቅ አድርጐባቸዋል፡፡ ካህናት ሁሌ ያሸንፉኛል፡፡ ዛሬ ግን እኔ አሸንፋቸዋለሁ ብለው የተነሱት ንግሥት፣ እጅጉን ጨው የበዛበት ምግብ ለካህናቱ በማስቀረብ የወይን ጠጅ በገፍ እንዲንቆረቆር አደረጉ፡፡ የግብር አዳራሾቹ በሮች እንዲዘጉ ጥብቅ ትእዛዝም አስተላለፉ፡፡ በቆይታ ብዛት ፊኛቸውን የቀበተቻቸው ካህናት የሚያደርጉትን አጡ፡፡ የተፈጥሮ ግዴታቸውን ለመወጣት ባለመቻላቸውም ማውጠንጠን ጀመሩ፡፡ አስበው አስበውም አለቃ ኢሳይያስ በተባሉ ቄስ አንድ ሃሳብ አመነጩ፡፡ አለቃም በላቀ ዘዴ ንግሥቲቱን ጠየቁ፡፡ “እቴጌ አምስት መቶና አምስት መቶ ስንት ነው?” “”ሺነዋ!” አሉ እቴጌ ምንትዋብ፡፡

“እቴጌ ካሉስ እሺ!” አሉና አለቃ ኢሳይያስ እጀጠባባቸውን ከፍ ዝቅ በማድረግ ሽንታቸውን ሸኑ፡፡ ሌሎቹም ተከተሏቸው፡፡ የእቴጌ ምንትዋብ ውድ የአበባ ምንጣፎች በሽንት ራሱ፡፡ እቴጌም በአለቃው መላ በመገረማቸው ሸለሟቸው፡፡ አዳራሹም እስካሁንም ድረስ “ሽነዋ አዳራሽ” ይባላል፡፡ ከዚህ አዳራሽ እልፍ ብሎ የእቴጌይቱን ዘመን የሚያስታውስ አነስተኛ ቤተመዘክር ተቋቁሟል፡፡ ቤተመዘክሩ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን አጽሞች ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊና አለማዊ ቅርሶች ይዟል፡፡ ከነዚህም መካከል ነጋሪት፣ መጽሐፈ ግንዘት፣ ስዕለ አድህኖ፣ እቴጌይቱ በአንባቸው ርስራስ አሰሩት የተባለው ስዕለ መርቆሬዎስ፣ ተደራራቢ ጠፍር አልጋ፣ ልብሰሐዋርያት፣ ግብረ ሕማማት፣ የመጾር መስቀል፣ ነገረ ማርያም፣ ማህሌተ ጽጌ፣ ተዐምረ ማርያም፣ ድጓ፣ ግንዘት፣ ስንክሳር፣ ዐርባዕቱ ወንጌል፣ ታሪክ ነገሥት፣ መጽሐፈ ቅዳሴ፣ ተዐምረ ኢየሱስ እና የወርቅ ሚዛን ይገኙበታል፡፡ በእድሜ ጠገብ ጥዶች የተከበበ ይህንን ቤተመዘክር እና ቤተክርስትያኑን ለመጐብኘት ለኢትዮጵያዊ 10 ብር፣ ለውጭ ሀገር ዜጋ 50 ብር፣ ለቪዲዮ ካሜራ 75 ብር መክፈል የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ጐብኚዎች በርካታ ሆነው በመጡበት ጊዜ አንድም አስጐብኚ አልነበረም፡፡ በዚያ ምትክ የግቢው ጥበቃ ናቸው ገለፃ ሲያደርጉ የነበሩት፡፡ አስጐብኚ ተብለው የመጡት መነኩሴም አንዳንድ ማብራሪያዎቻቸው እርግጠኝነት የማይታይባቸውና በ”መሠለኝ” የተሞሉ ነበሩ፡፡

ለቅርሶቹ በቂ ጥገና ባለመደረጉም በተለይ ሕንፃዎቹና ፍርስራሾቹ ለበለጠ ጉዳት እየተጋለጡ ነው፡፡ ግቢው ተቆጣጣሪ ስለሌለውም በጀምስ ብሩስ መኖሪያ ቤት ፍርስራሽ ላይ በቀይ ቀለም “በአቶ አባተ መልኬ ፈረሰ” የሚልና ሌሎች አልባሌ ጽሑፎች የታሪክ መፈራረሱን እያፋጠኑት ይመስላሉ፡፡ በዚህ መልክ እየፈራረሱ ካሉት ቅርሶች መካከል የባልትና መምህርቷ እቴጌ ምንትዋብ ጥልፍ፣ ቅመማ፣ ወዘተ ማስተማርያ አንዱ ነው፡፡ ራሷ ቅድስት ቁስቋም ቤተክርስትያንም ተከታታይ ጥገና ካልተደረገላት ነገ የሚታይም ሆነ የሚነገር ታሪክ አይኖራትም፡፡ የ”ሽነዋ” አዳራሽ ጥገና ተጀምሮ እንደተቋረጠ በዐይን አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እንዲህ የተጀመረ ጥገና መቋረጡና ጭራሽ ትኩረት አለመሰጠቱ አነጋጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ቤተክህነትና የከተማዋ አስተዳደር “የኔ ነው የኔ ነው” በሚል የባለቤትነት ውዝግብ የተነሳ እየተጐዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም የስብከተወንጌል ኃላፊ አባ ጽጌማርያም ጥበቡ፣የቤተክርስትያኑ ጣራ ክረምት ክረምት በማፍሰሱ በውስጡ ያሉ መቀደሻዎችና ሌሎች ቅርሶች ጉዳት እንዳገኛቸውና ያለከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ፈቃድ መጠገን እንደማይቻል እንዲሁም የአዳራሹን ጥገና እያካሄዱ ያሉ ሠራተኞች በቅጡ ባለመስራታቸው የበለጠ የቅርስ ጉዳት መኖሩን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የጐንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረ ስለዚሁ ጠይቀናቸው፣ “ቅርሶቹ በተመሳሳይ ጊዜ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ቅድሚያ ሰጥተን የምንጠግናቸው አሉ፣ ቤተክህነቷም የምትጠግናቸው አሉ፡፡ በቤተክህነትና በአስተዳደራችን መካከል የጥቅም ግጭት የለም፡፡ ቁስቋም ማርያም ድረስ በጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ መንገድና መፋሰሻ እየሰራን ነው፡፡” ብለውናል፡፡

Read 4479 times