Saturday, 26 January 2013 15:29

የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ ክስተቱ ታሪካዊ መስሏል፡፡ ገና በጅምሩ የብሔራዊ ቡድኑ ተሳታፊነት በአስደናቂ ሁኔታዎች እና ድባቦች የታጀበ ሆኗል፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ በተለይ በጆሃንስበርግና የምድብ 3 ጨዋታዎች በሚደረጉባት ሬልስፕሪት አረንጔዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን በመልበስ፣ ፀጉራቸውንና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን በመቀባት፣ የብሔራዊ ቡድኑን ዋልያዎችና የአገሪቱን ባንዲራ ያጀቡ አልባሳትን በተለያዩ ዲዛይኖች ሠርተው ለገበያ በማቅረብና በመልበስ ከፍተኛ ድምቀት ፈጥረዋል፡፡
ውድድሩ ከሳምንት በፊት ጆሃንስበርግ በሚገኘው የሶከር ሲቲ ስታድዬም በአዘጋጇ ደቡብ አፍሪካና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችው ኬፕቨርዴ መካከል ሲጀመር ስታድዬም በገቡ ኢትዮጵያውያን ውድድሩ ድምቀት ተላብሷል፡፡
በሶከር ሊቲ ስታድዬም የተለያዩ ክፍሎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ማልያ የለበሱና ያነገቡ ኢትዮጵያውያን ብዛት ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡
ከኢትዮጵያና ከዛምቢያ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችና አምበሎች እዚያው ቦምቤላ ስታድዬም መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የነበረው አጠቃላይ ድባብ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ1 እኩል ውጤት ቢደመደምም ዛምቢያ እንዳሸነፈች ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች ነበር የተቆጠረው፡፡ ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ለአምበሉ አዳነ ግርማ ከተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን የዛምቢያና የናይጀሪያ ጋዜጠኞችም ይገኙበታል፡፡ ከ10 በላይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በታደሙበት መግለጫ ላይ አንድ ሁለት ጋዜጠኞች የኢትዮጵያ አሰልጣኝ እና አምበሉ ተሰናብተው የተቃራኒ ቡድን አሰልጣኞች መግለጫ ሲሰጡ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ልክ እንደ ጆሴ ሞውሪንሆ ከጋዜጠኞቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አስገራሚና አጭር አረፍተነገሮች በመጠቀም ምላሽ መስጠት ችለዋል፡፡
አሰልጣኙ ስለቀጣዩ ተጋጣሚዎች ምን እንደሚያስቡ ለአሰልጣኙ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ለተቃራኒ ቡድን ጠንካራ ግምት ይዘው እንደሚገቡ ገልፀዋል፡፡ በስታድዬሙ የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ቩቩዜላ እና የውሃ መጠጫ ላስቲኮች ለምን ወረወሩ ሲባልም ደጋፊዎቹ እኛን በመቃወም ያን ተግባር አልፈፀሙም ብለዋል፡፡
በመግለጫው የኢትዮጵያ አሰልጣኝና አምበል ማብራሪያ ሲያበቃ እዚያ ለነበርን የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ሁለት ነገር ገርሞን ነበር፡፡ የመጀመሪያው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል አዳነ ግርማ የአማርኛ ማብራሪያ በእንግሊዝኛ ትርጉም የሰጡት የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ብቃት ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፕሬስ አታሼ የሆኑት የፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በመግለጫው አብረው መድረኩ ላይ ቢገኙም የአዳነ ግርማን የአማርኛ ማብራሪያ አለመተርጐማቸው ነበር፡፡ ይባስ ብሎ የኢትዮጵያ አሰልጣኝና አምበል መግለጫቸውን ጨርሰው ሲሄዱ እኝህ የፕሬስ አታሼ ቀጣዩን የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እና አምበል መግለጫ እንደመከታተል እሳቸውም አብረው ውልቅ አሉ፡፡ የሚያናድደው እኝህ የፕሬስ አታሼ የዛምቢያው አሰልጣኝ ሄሮሼ ሬናልድ፡፡

“ብሔራዊ ቡድኑ ሩብ ፍፃሜ ይገባል”
ስለሺ ይማም
ደቡብ አፍሪካ ከገባሁ ስምንት ዓመት ሆኖኛል፡፡ የተወለድኩት በአዲስ አበባ አሮጌ ቄራ አካባቢ ነው፡፡ ትምህርቴን እስከ 9ኛ ክፍል ተምርያለሁ፡፡ ሙያ አልነበረኝም፤ አዘውትሬ ኳስ እጫወት ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ በንግድ ስራ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ ጐን ለጐን በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ የእግር ኳስ እንቅስቃሴዎች ብዙ እንሳተፋለን፡፡
በተለይ ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የኦሎምፒክ ማጣርያ እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ጋር በተገናኘ በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብና በማስተባበር ብዙ ስራዎችን አከናውነናል፡፡
ዋና አላማችን ብሔራዊ ቡድኖቻችን ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ጨዋታዎቻቸው ተመልካች እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ከ29ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ጋር በተያያዘ ከራሳችን ወጭ አድርገን እንዲሁም ከህዝብም አሰባስበን በጆሃንስበርግና በየክፍለሀገሩ ፖስተሮችን በመለጠፍ፣ በራሪ ወረቀቶቼን በመበተንና ተንቀሳቅሰናል፡፡ ገንዘብ የሌላቸውንም እየደገፍን ኳሱን እንዲከታተሉ አስችለናል፡፡
ማንኛውም ተግባራችን ከፖለቲካ ጋር አይገናኝም፣ አይያያዝም፡፡ የምንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች በደቡብ አፍሪካ ብለን ነው፡፡ በምድብ 3 ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ጋር በኔልስፕሪት ላደረገችው ጨዋታ እያንዳንዳቸው ከ60 በላይ ተመልካቾች የሚይዙ 11 አውቶብሶችን በማስተባበር 400 ኪ.ሜ ተጉዘን ብሔራዊ ቡድኑን ደግፈናል፡፡
ከ7ሺ በላይ ትኬቶችን ሸጠናል፡፡ በኔልስፕሪት በሚገኘው የሞምቤላ ስታድዬም የኢትዮጵያን ጨዋታ ለመከታተል ስታድዬም የገባው ህዝብ ብዛት በጣም ይገርማል፡፡ የኢትዮጵያ ጊዜ መምጣቱን እያስመሰከሩ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ቡድናችን ማንንም መፎካከር የሚችል ሆኗል፡፡ በደጋፊዎች፣ በተጨዋቾች ብቃትም አስተማማኝ ሆኗል፡፡ በእርግኛነት ሩብ ፍፃሜ እንገባለን፡፡
በእርግጠኛነት ስምንት ውስጥ እንገባለን፡፡
ምንተስኖት ደስታ (አቡሽ)
የትውልድ ስፍራዬ የጌድዮ ዞን ዋና ከተማ ዲላ ናት፡፡ የብሔራዊ ቡድናችን አጥቂ ጌታነህ ከበደ የዲላ ልጅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመጣሁ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፡፡
ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርቴን በማጠናቀቅ ዲፕሎማዬን አግኝቻለሁ፡፡
ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጣሁበት ምክንያት በዚህ ከሚኖሩ ቤተሰቦቼ ጋር ለመስራት ነው፡፡ ቤተሰቦቼ በደቡብ አፍሪካ ከ11 ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡ አሁን በቤተሰቦቼ የንግድ ሱቅ እየሠራሁ ነኝ፡፡ ቤተሰቤ ባለ 5 ፎቅ ህንፃ አለው፡፡ ህንፃውንም አስተዳድራለሁ፡፡
በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ ከገመትኩት በላይ ሆኖብኛል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ቡድኑ ሲጫወት በሜዳው የሚወዳደር ይመስላል፡፡ ይህ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ ያው እንግዲህ ኢትዮጵያኖች በጣም እግር ኳስ እንወዳለን፡፡
በብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነት ሁላችንም ሰርፕራይዝ ሆነናል፡፡ በእርግጠኝነት ሩብ ፍፃሜ እንገባለን፡፡ እኛ የምንሰራበት አካባቢ “ታውን” ይባላል፡፡ በዚያ የሚሠሩ የደቡብ አፍሪካ፣ የናይጀሪያ፣ የማሊ ዜጐች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እጅግ ተደንቀዋል፡፡ ስለአፍሪካ ዋንጫው ስናወራ በሩጫ ብቻ የሚያውቋት ኢትዮጵያ በእግር ኳስም ምርጥ መሆኗን መገንዘባቸው አስገርሟቸዋል፡፡
አብረውን ከሚሠሩት የናይጀሪያ ዜጐች ጋር ስናወራ ለኢትዮጵያ የናይጀሪያ ቡድን ከባድ እንደሚሆንበት ነግረውናል፡፡ ሩብ ፍጻሜ እንደምንገባም ራሳቸው ነግረውናል፡፡ዳዊት ሰለሞን (ግራኝ)
የትውልዴ ስፍራ ኮልፌ ቀበሌ 11 ነው፡፡ በተለምዶ ጅማ ሰፈር የሚባለው አካባቢ ኳስ ተጨዋች ነበርኩ፡፡ የጀመርኩት በባንክ “ቢ” አንድ ዓመት፤ መብራት ኃይል አንድ “ቢ” አንድ ዓመት ፣ በኦሜድላ ዋና ቡድን እና በሊያ፣ (አንዋር ያሲን በነበሩበት ጊዜ) ገብቼ ለአንድ ዓመት ተጫውቻለሁ፡፡ ከባንክ “ቢ” የወጣሁት በበጀት ምክንያት ክለቡ ሲፈርስ ነበር፡፡
ከዚያ መብራት ኃይል ሄጄ በመጨረሻም ኦሜድላ ገባሁ፡፡
ባንኮች በኦሜድላ አንድ ዓመት እንደተጫወትኩ ባንኮች እኛ ያሳደግነው ልጅ ነው ብለው ወደ ክለቡ መለሱኝ፡፡ ያኔ የባንክ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ አሸናፊ በቀለ ነበር፡፡ በባንኮች ክለብ ለአምስት ዓመት ተጫወትኩ፡፡
ሁለገብ ተጨዋች ነበርኩ፡፡ በተለይ ግን ግራ ተመላላሽ እና አማካይ ስፍራ ላይ እሰለፍ ነበር፡፡ ከባንኮች በኋላ አየር መንገድ ለአንድ ዓመት፣ ከዚያ በኋላ በጉና እና በትራንስ ክለቦች እያንዳንዳቸው ለሁለት ዓመት ተጫወትኩ፡፡ ከዚያ ኳሴን አቆምኩ እና የአሰልጣኝነት ኮርስ ወሰድኩ፡፡ በትምህርቱም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የክብር ተመራቂ ሆንኩ፡፡ “ሮሃ ራይዚንግ” የተባለ እና የጐዳና ተዳዳሪ ልጆችን በእግር ኳስ የሚያሳትፍ ፕሮጀክት አቋቁሜ በአሰልጣኝ ታምሬ ተፈራ (ፑፒ) አማካኝነት ከአንድ ዓመት በላይ ሠራን፡፡ እግር ኳስ መጫወት ያቆምኩት በዕድሜ ምክንያት አልነበረም፡፡ ከክለብ ተገቢውን መልቀቂያ ላገኝ ባለመቻሌ ነው፡፡
የፕሮጀክቱን ስራ በድንገት አቆምኩት፡፡ ምክንያቱም ወደ ደቡብ አፍሪካ መጥቼ ከዚያም ወደ አሜሪካ ለመሄድ ነበር፡፡ እዚህ በነበረኝ ቆይታ ኑሮን ለማሸነፍ መስራት ስለነበረብኝ ወደ ንግድ ስራ ገባሁ፡፡
ላለፉት ሰባት ዓመታት የንግድ ስራውን ሳከናውን ቆይቻለሁ፡፡ እግር ኳሱን ደግሞ በትርፍ ሰዓት ኤደን ቪል የሚባል የሶከር አካዳሚ ባለቤት የሆነ ብራዚላዊ ጋር እያሰለጠንኩ ሰራሁ፡፡ እድሜያቸው ከ10-12 የሆኑ የብዙ አገር ዜጐች ህፃናትን ለአንድ ዓመት አሰልጥኛለሁ፡፡
ደቡብ አፍሪካ ገብቼ ሦስት ዓመት ከኖርኩ በኋላ የልጅነት ጓደኛዬ (ሃና ቀፀላ ትባላለች) ወደአለሁበት እንድትመጣ አደረግሁ፡፡
ከዚያ ትዳር መሰረትን፣ ቤተሰብ ጀመርን፡፡ አንድ ልጅ አፈራን፡፡ ቅዱስ ይባላል፡፡ የተወለደው ደግሞ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የዓለም ዋንጫን ባዘጋጀችበት ዓመት የመክፈቻው ዕለት ነበር፡፡
በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጠበቅሁት በላይ ብቃት አሳይቷል፡፡ የብቃታቸው ምስክርና ቁልፍ የተጨዋቾቹ በስነልቦና ከፍተኛ ጥንካሬ ማሳየታቸው ነው፡፡ እኔ ባሳለፍኩት የእግር ኳስ ህይወት ውስጥ የነበረው ብሔራዊ ቡድን ሙሉ ቢሆንም ግብ የማስቆጠር ብቃቱ ላይ ደካማ ነበር፡፡ ውጭ ወጥቶ ተሸንፎ ነው የሚመጣው፡፡
ጐል አያገባም፣ ሀገር ውስጥ ሲጫወት ያሸንፋል ግን 1ለ0 ነው፡፡ ይህ አጥቂዎቹ ከተቃራኒ ቡድኖች ጋር ተጋፍጦና ጐል አስቆጥሮ የመጫወት ብቃት እንደሌላቸው የሚያመለክት ነበር፡፡
አሁን ያሉት ልጆች ግን ሀገር ውስጥ ከ2 እና ከ3 በላይ ጐል ያገባሉ፡፡ ከአገር ውጭም ውጤት የሚቀይር ጐል አግብተው ይመላለሳሉ፡፡ ይህ እጅግ ከፍተኛ ለውጥ ነው፡፡
በእኔ ግምት የአሁኑ ብሔራዊ ቡድን ሩብ ፍፃሜ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ለዚህ ደረጃ መብቃትና በአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ኢትዮጵያ መታየቷ፣ ለመጭው ትውልድ አፍሪካ ዋንጫ መግባትን ሳይሆን ዋንጫ መብላትን እንዲያልሙ ያደርጋቸዋል፡፡

Read 6085 times Last modified on Saturday, 26 January 2013 17:00