Saturday, 26 January 2013 15:25

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by 
Rate this item
(15 votes)

መልክአ፣ ኢትዮጵያ ፪

አሁንም ከአትላንታ ጆርጅያ አልወጣኹም፡፡ ባለፈው ሣምንት ጽሑፌን ለዛሬ ያቆየኹት በራቁት ዳንስ ቤት (Strip Club) ውስጥ በአግራሞት ስለተመለከትኋት ሐበሻዊ - መልክ - ራቁት - ደናሽ ልተርክላችኹ ቀጠሮ ይዤ ነበርና ከዚያው ልቀጥልላችኹ፡፡ ዓርብ እና ቅዳሜ የአሜሪካኖቹ የመዝናኛ ዕለታት ናቸው፡፡ ማታ ወጥቶ መዝናናት የሚያሰኘው ካለ ዓርብ እስኪመጣ መጠበቅ ግዴታው ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ባሉት ቀናት ወደ ምሽት መዝናኛ ቤቶች ጐራ ማለት የብርዳም (ቁራጭ) ምሽቶች ሰለባ ያደርጋል። መዝናኛ ቤቶቹ ዐይነታቸው ለየቅል ነው። የአትላንታ ምሽት ቤቶችም እንደ ሌሎቹ የአሜሪካ ከተሞች ሁሉ ዓርብን መስለዋል። መኪና ማቆሚያዎች በተሽከርካሪዎች፣ መግቢያ በሮች ደግሞ በሰው ተጨናንቀዋል። በከተማው ይገኛሉ ሲባል ከሰማኋቸው ራቁት ዳንስ ቤቶች ሁሉ እኔ አሁን ያለሁበትን መርጫለኹ፡፡ ሐበሻዊ መልክ ያላት ደናሽ በዚህ ቤት ትገኛለችና፡፡ ቀናት በፈጀ ልመና ቦታውን ሊያስጐበኙኝ ፈቃደኛ ሆነው ያካሄዱኝ ሦስት ወንድ ጓደኞቼ ዓርብ እና ቅዳሜ ተመራጭ ቀናት መሆናቸውን በመጠቆም ይዘውኝ የወጡት በአንዱ ዓርብ ነው፡፡ ከቦታው ደረስን፡፡

ከፊት ለፊታችን በተንጣለለው የመኪና ማቆሚያ ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መኪኖች ተደርድረዋል። ዙሪያ ገባውን በተደረገ ፍለጋ እንደምንም አንድ ማቆሚያ ተገኘ፡፡ መኪናችንን ግራና ቀኙን ጠብቆ ያለምንም ስሕተት ለማቆም የሁሉም ሰው ርዳታ አስፈልጐ ነበር፡፡ ቀድመው ቦታ ይዘው በቆሙት መኪኖች ላይ ጭረት ማሳረፍ በቀላሉ የሚታለፍ ጥፋት አይደለም፡፡ በፊልም እና በማስታወቂያ የማውቃቸው የዓለም ውድ ሞዴል መኪኖች በመኪና ማቆሚያው ከተደረደሩት መካከል ቀላል የማይባለውን ቁጥር ይዘዋል፡፡ የቤቱ መለዮ የኾነው ማስታወቂያ ከሩቅ ይጣራል፡፡ በዐሥራ አምስት ደረጃዎች ከፍታ በተሠራ የቪላ ቤት ቅርጽ ግዙፍ ቤት አናት ላይ “Pink Pony” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎበታል፡፡ በታላላቅ ፊደላት የተቀረጸ ሲሆን ሮዝ መልክ ባለው መብራት ያሸበረቀ ነው፡፡ በሁለቱ ቃላት መካከል ፊቷን ያዞረች ራቁት ደናሽ ሴት ምስል ተጣምሮ ተሰቅሏል። ወደ መግቢያው ስንጠጋ ሁለት ሙሉ ጥቁር የፖሊስ ልብስ የለበሱ ነጭ ጠባቂዎች ዙሪያቸውን መሣሪያ ታጥቀው ወደ ዳንስ ቤቱ የሚገቡት ሰዎች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች አለመሆኑን መታወቂያ እያገላበጡ በማየት የይለፍ ምልክት ይሰጣሉ። ተራችንን ጠብቀን የይለፍ ማኅተሙን እጃችን ላይ ካስመታን በኋላ ተራ በተራ ፍተሻችንን እያጠናቀቅን የመግቢያ ክፍያ ወደሚከፈልበት ቦታ ሄድን፡፡

ለአንድ ሰው መግቢያ 15 ዶላር ይከፈል ነበርና ለአራታችን ለመክፈል ወደ ሒሳብ ተቀባዩዋ ስንጠጋ፣ ወደኋላ ቀርቶ የነበረው ታክሲ አሽከርካሪ ጓደኛችን ለሒሳብ ተቀባዩዋ የሆነ ምልክት አሳያት፤ የገባት አልመሰለኝም፤ ምን እንደሚል ደግማ ጠየቀችው፡፡ ባለታክሲ መሆኑንና ደንበኞችን ይዞ መምጣቱን ጠቆማት፡፡ “ገባኝ” በሚል ስሜት እየተፍለቀለቀች የኛን ወስዳ የሱን መለሰችልን፡፡ ኢትዮጵያውያን ባለታክሲዎች ደንበኛ ይዘው ወደዚህ ቤት ከመጡ መግቢያ ሳይከፍሉ ገብተው ይታደማሉ ወይም ደግሞ ኮሚሽን ይቀበላሉ፡፡ በአሜሪካ ከአምስት ኢትዮጵያውያን ጋር የመገናኘት ዕድል ቢገጥማችሁ አንዱ ባለታክሲ መሆኑ ግድ ነውና እዚህ ቤትም አብረውኝ ከመጡት ጓደኞቼ አንዱ ባለታክሲ ነው፡፡ እንዲህ ላለው የከተማ ወሬ ከእነሱ የቀረበ ስለማይኖር ጥያቄዬን ለሱው መወርወር ጀመርኹ፡፡ “የዳንስ ቤቱ ጠባቂዎች ይህን ሁሉ ሽጉጥ የታጠቁት ለምንድነው?” ስል ጠየቅኹት፡፡ “የትኞቹ? በር ላይ ያለፍናቸው ነው? ፖሊሶች ናቸዋ” አለኝ፡፡ እንደገና ወደኋላ ተመልሼ መታወቂያቸውን መጠየቅ አማረኝ። በራቁት ዳንስ ቤት መግቢያ በር ላይ ፖሊሶች ቆመው በትጋት ይቆጣጠራሉ። “ለዐቅመ አዳምና ሔዋን የደረሳችሁ እንደፍጥራጥራችሁ” በሚል ስሜት ወደ ውስጥ ያሳልፋሉ፡፡ የቆረጥነውን ትኬት ሁለተኛው በር ላይ ላገኘነው ተቆጣጣሪ ሰጥተን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ በሩ ወለል ብሎ ሲከፈት ድፍረቴ ጥሎኝ ጠፋ፡፡ ሰውነቴ በላብ ተዘፈቀ፡፡ ከወደፊት ይልቅ ወደኋላ የመመለስ ፍላጐቴ ጨመረ፡፡ የደም ግፊት እንዳለበት ሰው የጭንቅላቴን የኋለኛ ክፍል ጨምድዶ ያዘኝ። በድንጋጤ ክው ብዬ ቀረኹ፡፡ ወድጄ እና ፈቅጄ የመጣሁ ሳይሆን የሆነ ሰው በሲዖል ደጃፍ አምጥቶ የጣለኝ መሰለኝ፡፡

ዐይኔ ለጊዜው ማስተዋል የቻለው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ እጅግ ሰፊ በሆነው ዳንስ ቤት ውስጥ ርቃናቸውን የሆኑ በርካታ ሴቶች ይርመሰመሳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ውስጥ በጐበኘኋቸው “ስም ያወጡ” ራቁት ዳንስ ቤቶች ውስጥ የተመለከትኋቸው ኢትዮጵያውያን እንስቶች “በስንት ጣዕማቸው?” አሰኘኝ፡፡ ጡታቸውን እና ሃፍረተ -ገላቸውን በእራፊ ጨርቅም ቢሆን ሸፈን ያደርጉታል፡፡ ያኔ ይህን ቢዝነስ ሠለጠኑ ከተባሉት አገሮች ቀድተው አዲስ አበባ ያመጡትን የዳንስ ቤት ባለቤቶች ረግሜያቸው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ለእራፊ ጨርቃቸውም ቢሆን አመሰገንኋቸው፡፡ ያጋነንኹ ካልመሰላችሁ እውነቱን ልንገራችኹ፡፡ ከቆምኹበት ብንቀሳቀስ የምወድቅ ስለመሰለኝ አንገቴን ወደ መሬት ቀብሬ ትንሽ ትንፋሽ ወሰድኹ፡፡ ጐትቼ ያመጣኋቸው ወዳጆቼ ወኔ ሲከዳኝ ሲያዩኝ ተሣሣቁብኝ፡፡ ከፊል እርቃኗን የኾነች አስተናጋጅ ፊቷን እንደ ጸዳል አብርታ በሚያብረቀርቅ ፈገግታ “ቁጥራችሁን ንገሩኝና ቦታ ልስጣችሁ?” ስትል ጠየቀች። ባይሆን ከለል ያለ ቦታ እንዳለ ለማየት እንደምንም ተጣጥሬ ቀና አልኹ፡፡ የቤቱ ስፋት በአንድ ጊዜ ይህን ለመቃኘት አያስችልም፡፡ ቀና ማለቴ ከፈራኋቸው ራቁት ሰውነቶች ጋር መልሶ አገጣጠመኝ፡፡ “የቱ ጋር እንቀመጥ?” በሚል ጠያቂ አስተያየት ሁሉም ወደ እኔ ተመለከቱ “ያስመጣሽን አንቺ ነሽ፤ እንግዲህ ተወጪው ይመስልባቸዋል፡፡ ከለል ያለ ቦታ ካገኘን ብዬ ከእነድንጋጤዬ ጠየቅኋቸው፡፡

ባለታክሲው ወዳጄ “ለዚች ልብሽ ነው እንዴ?” ሲል በድንጋጤዬ ላይ አላገጠብኝ፡፡ በቤተኝነት ስሜትም ከቤቱ መግቢያ በር በስተቀኝ በኩል ካለው የመጠጥ መሸጫ ክብ ባንኮኒ ላይ እንድንቀመጥ ወደዚያው ወሰደን፡፡ በዙሪያ ገባው ምን እየተከናወነ እንደሆነ የማየት አቅም ለጊዜው ስላጣሁ ዐይኔን በክቡ ባንኮኒ ውስጥ ቆመው መጠጥ በሚሸጡት ሴት እና ወንዶች ላይ ተከልኹ፡፡ አማራጭ ማጣት ኾኖብኝ እንጂ እኒህም የሚታዩ ሆነው አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ በውስጥ ሱሪ እና በጡት ማስያዣያ፣ ከፊሎቹ አጭር ቁምጣ በተጣበቀ አላባሽ፣ ከሰውነታቸው ከፊሉን አራቁተው ለማሻሻጫነት የቆሙ ናቸው፡፡ የአዲስ አበቦቹን “ከፊል ራቁት ደናሾች” ከእራፊው ጨርቅ በመለስ ያለውን ገላቸውን አጋልጠው ለሽያጭ በማቅረብ በቀጫጭን ብረቶች ታግዘው፣ ሰውነታቸውን ከወሲብ ቀስቃሽ ሙዚቃ ጋር አዋሕደው እየተገለባበጡ የሽልማት ገንዘብ ሲሰበስቡ ሳይ “አይ ድህነት አያደርገው የለ” ስል ለእንስቶቹ ሆዴ ተላውሶላቸው ነበር፡፡ በርካቶች ሥራ ፍለጋ በሚሰደዱባት የዓለም ቁንጮ በሆነችው ሀገረ አሜሪካ፣ ገላቸውን ለሽያጭ ላቀረቡት ወጣት እንስቶችስ “አይ የእንጀራ ነገር” ስል ደረቴን ልድቃላቸው ይሆን? ጉዳዩ የእንጀራ አይመስልም፤ እናም ደረት የመድቃቱ ነገር አስፈላጊ አልመሰለኝም፡፡ ቀስ እያልኹ የቤቱን መብራት እና ድምፅ ተላመድኹት፡፡ አቀማመጤን አስተካክዬም ሰረቅ እያደረግሁ ቀረብ ካሉት “የገላ ነጋዴዎች” ቅኝቴን ጀመርኹ። የቤቱ አጠቃላይ ስፋት በግምት ሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እጅግ ሰፊ ወጥ አዳራሽ ነው፤ ግን ደግሞ በተለያየ መንገድ ተከፋፍሏል፡፡ አራት መዓዝን ቅርጽ ያላቸው ሰፋፊ የመጠጥ መሸጫ ባንኮኒዎች፣ በርካታ የመደነሻ መድረኮች አሉት፡፡

ነጭ እና ጥቁር ቀለም ያላቸው ሴቶች ተራ በተራ ወደ መድረኩ እየመጡ የዕርቃን ትርኢት ያሳያሉ፤ ጨርሰው ሲወርዱም ግብዣ ያቀረበላቸውን ሰው ይዘው በአንደኛው የቤቱ ኮርነር በርከት ብለው ወደተደረደሩትና የመኝታ ያህል ተለጥጠው የሶፋ መቀመጫዎች ይዘው እየሄዱ ሥራቸውን በግል ይቀጥላሉ። ልዩ ክፍያ የሚከፍል ደግሞ ሴቶቹን ወደውስጠኛው ክፍል ይዞ እንዲገባ ይፈቀድለታል፡፡ “እዚህ ቤት ግን በርግጥ ኢትዮጵያውያን ይመጣሉ?” - ቀደም ሲል የሰማሁትን መረጃ ተጠራጥሬ እንደገና ለማረጋገጥ ለባለታክሲው ያቀረብኹለት ጥያቄ ነው፡፡ በርግጥ ጥያቄው የሞኝ ይመስላል፡፡ በአዲስ አበባዎቹ የምሽት ዳንስ ቤቶች ውስጥ ተገኝተው በአዳጊ እንስቶች የውስጥ ሱሪ ገንዘብ እየጨመሩ የሚዝናኑ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያ ምድር አይቼ እንዲህ በዘመነች አገር የኢትዮጵያ ልጆች ታዳሚ መሆናቸውን መጠየቅ በርግጥ “ሞኝነት” ነው፡፡ ግን ደግሞ የቤቱን አስነዋሪነት ስመለከት በዚህ ቦታ የሀገሬ ልጆች ተሳታፊም ታዳሚም ናቸው መባሉን አምኖ መቀበል ከባድ ኾነብኝ፡፡ መብሰክሰኬ ብዙም ሳይቆይ ከጓደኞቼ የአሻግረሽ ተመልከቺ የቀስታ ጥቆማ ደረሰኝ። በቀላሉ አልታይ አለኝ፡፡ ከተቀመጥኹበት ረጅሙ የባንኮኒ ወንበር ተንጠራርቼ ዐይኔን አሻገርኹ፡፡ ከፍ ካሉት የመደነሻ መድረኮች ዝቅ ብለው ከተደረደሩት መቀመጫዎች ላይ አንዲት ሴት እና ሁለት ወንዶች ተቀምጠው እንቅስቃሴውን ፈዘው ያስተውላሉ፡፡ በመጠጥ ጭምር እየተዝናኑም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ያየኋቸው ከርቀት ቢሆንም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን መለየት አላስቸገረኝም፡፡ ባያውቁኝ ባላውቃቸውም እዚያ ቦታ ቁጭ ብዬ በሌላ የሀገሬ ሰው በመታየቴ ብቻ ሃፍረት ተሰምቶኝ ለመደበቅ ሞከርኹ፡፡ እነርሱ እኔ የተሰማኝ ስሜት የተሰማቸው አልመሰለኝም፡፡ ማንም በዚያ ቦታ ቢኖር ግድ ያላቸው አይመስሉም፡፡ እንደ ውጭ አገር ዜጐቹ ሁሉ እነርሱም ተራ በተራ እየተነሡ ዶላር ይሸልማሉ፡፡

በቃል ያልተመለሰው ጥያቄዬ በተግባር ተመለሰልኝ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በዚያ ቤት ነበሩ፡፡ ባለታክሲው ወዳጄም፤ “የኛ አገር ልጆች በብዛት የዚህ ቤት ደንበኛ አይደሉም። አልፎ አልፎ የእኔ ቢጤ ባለታክሲ ደንበኛ ይዞ ይመጣል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እንዲህ እንዳንቺ እንግዳ እና አዲስ ሰው ከሀገር ቤት ሲመጣ አሳዩኝ ይልና ለማየት ይመጣል፡፡ ግን ከአንድ ቀን በላይ እዚህ ቤት የሚመጣ ኢትዮጵያዊ በጣም ጥቂት ነው፡፡ አንዳንዱ እዚህ በመምጣቱ ብቻ ራሱን እንደረከሰ ሰው ቆጥሮ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ጠበል ይጠመቃል አትላንታ ካለው ኢትዮጵያዊ በጣም ጥቂት ቁጥር የሚይዙ ሰዎች ግን የቤቱ ደንበኞች ናቸው፡፡እንዲህ ያለ ቤት ስለመኖሩ የማያውቁ ደግሞ በርካቶች ናቸው፤” አለኝ። የቤቱን ታዳሚዎች ኹኔታ በግምታዊ አኅዝ ለማስቀመጥ 300 በሚሆኑ እንግዶች መካከል ከ70 በላይ የሚሆኑ እርቃን ሴቶች ይርመሰመሳሉ፡፡ ከእኔ ጥያቄ እና ከባለታክሲው ወዳጄ መልስ ውጪ በመካከላችን ጸጥታ ሰፍኗል፡፡ ሁለቱ አገጫቸውን እጃቸው ላይ አስደግፈው ጸጥ ብለዋል፤ ተፋፍረዋልም፡፡ እውነት ነው፤ እንዲህ ያለውን ነገር አንድ ላይ ኾኖ መመልከት በራሱ ያስተፋፍራል፡፡ በቤቱ እንደምትሠራ የተነገረኝ አበሻዊ መልክ ያላት ደናሽ አለመምጣት ካሰለቸኝ ከአንድ ሰዓት በኋላ “መጣችልሽ፣ መጣችልሽ!” አለኝ ባለታክሲው ወዳጄ፡፡ ክንፍ ያለኝ ይመስል አኮበኮብኹ፤ ልጅቱን ፍለጋ አንገቴን አንቀዠቀዠኹት፡፡ መካከል ላይ ወዳለው መድረክ የምታመራ፣ ያማረ ተክለሰውነት ወዳላት ወጣት አሳየኝ፡፡ ወደ መድረኩ እየሄደች ስለሆነ ፊቷን ማየት አልቻልኹም፡፡ የሚታየኝ ጀርባዋ ነበር፡፡ አዲስ አበባ እንዳየኋቸው ሴቶች ከእራፊ በላይ በሆነ ጨርቅ ሰውነቷን ሸፍናለች፡፡ ጡቶቿን ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍን ጡት ማስያዣ እና ሣሣ ያለም ቢሆን ታፋዋ ድረስ የሚሸፍን ቁምጣ መሰል ነገር ለብሳለች፡፡ ትልቅ ተረከዝ ያለው ቡትስ ጫማም ተጫምታለች፡፡ መድረኩን አስቀድማ ስትደንስበት ከነበረችው ባለነጭ ገላ ሴት ተረክባ የተከፈተላትን የሙዚቃ ምት ተከትላ፣ ቀስ እያለች ወደ መድረኩ ወጣች። ዙሪያውን ከበው የተቀመጡት ታዳሚዎች የቀደመችውን በጭብጨባ ሸኝተው እሷንም በጭብጨባ ተቀበሉ፡፡ የእኔ ዐይን እንዳፈጠጠ ነው፡፡ ጭንቅላቷ በአርተፊሻል፣ ፀጉር ቢሸፈንም መልኳ ሐበሻዊ መሆኑን ለመለየት ነጋሪ አላስፈለገኝም፡፡ በዝግታ የጀመረችውን ዳንስ እያፈጠነችው መጣች፡፡ ሰውነቷ በከፊል የተሸፈነ መሆኑን ስመለከት፣ ምናልባት አንዳች ማኅበረሰባዊ ሞራል በጥቂቱም ቢሆን ተጭኗት ሊሆን ይችላል ስል ጠረጠርኩኹ፤ ግን ደግሞ በቤቱ ውስጥ ከደናሾቹ እንደ አንዷ ኾና መድረክ ላይ ከወጣች በኋላ፣ ሰውነትን በእራፊ ጨርቅ መሸፈኑ ትርጉም አልባ ሆነብኝ፡፡ መጀመሪያውኑ ተወልቆ የተጣለ ነገር ነውና። ልጅቱ እንቅስቃሴዋን ቀጥላለች፡፡

ከመድረኩ ጀምረው ወደላይ የቤቱን አናት እንደምሰሶ ደግፈው የያዙትንና ለዚሁ አገልግሎት ተብለው የተዘጋጁትን ቀጫጭን ብረቶች እየተጠቀመች ስሜትን ለወሲብ በሚቀሰቅስ እንቅስቃሴ ለደቂቃዎች ስትናጥ ቆየች፡፡ ቀጠለችና አንዱን ብረት በአንድ እጇ እንደያዘች የአንድ እግር ጫማዋን አወለቀች፤ አስከትላም ሁለተኛውን ደገመች። በመድረኩ የጽዳት እና የዶላር ሽልማት ሰብሳቢ ሠራተኛ አማካኝነት የወለቀው ጫማ ተነሣ፡፡ ዳንሱ በባዶ እግር ቀጠለ፡፡ ቆየት ብላ የጡት ማስያዣዋን ፈታ ጥላ ከወገቧ በላይ እርቃኗን ሆነች፡፡ “ኦ! አምላኬ! የፈጣሪን ስም ጠራሁ። ሸላሚዎች ተነሡ፡፡ መጠኑ ስንት እንደሆነ መለየት ባልችልም ዶላር ይዘንብላት ገባ፡፡ ቆየት ብዬ እንደተረዳሁት ከቤቱ ደንበኞች ውስጥ ከዐሥር እስከ 100 ዶላር የሚሰጡ ባይጠፉም አብዛኛው ደንበኛ ግን ዘርዝሮ ይዞ አጠገባቸው ይቆምና በተለያየ ስልት እየስደነሰ ዶላሩ አምስት እና ዐሥር ላይ ሲደርስ ቦታው ሄዶ ይቀመጣል፡፡ በቤቱ ውስጥ ራቁት ደናሾቹ በመድረኩ ላይ እያሉ እያዩ ከማስደነስ ውጪ ቀርቦ መንካት የተከለከለ ነው፡፡ ልጅቷ ዳንሷንም እራፊ ጨርቋንም ከሰውነቷ ላይ እያነሣች መጣል ቀጥላለች፡፡ ሥሡን ቁምጣዋን አውልቃ ጥላ በውስጥ ሱሪ ብቻ ቀርታለች፡፡እየተዟዟረች ሽልማቷን ትሰበስባለች፡፡ አዲስ አበባ ላይ ደናሾቹን ባገኘሁ ጊዜ ዳንሱን ሥራ ብለው የያዙት አማራጭ ከማጣት ተነሥተው እንደሆነ አንጀት በሚበላ የችግር ታሪካቸው አዋዝተው ተርከውልኝ ነበር፡፡

በተለይ አንዲት 18 ዓመት በቅጡ የማይሞላት አዳጊ፤ “በትምህርቴ ብዙም ሳልገፋ እናት እና አባቴ ሁለት ታናናሾች ጥለውብኝ ሞተው እነሱን አስተምራለሁ፡፡ የምንኖረው በቀበሌ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ረኀብ እና ጥማት ተራ በተራ እየተፈራረቀ ችግር የቤታችን አባል ቢሆንብኝ አንዷን ጐረቤት ተከትዬ ገላዬን ለመሸጥ ጐዳና ወጣሁ፤ ጓደኛዬ እዚህ የመቀጠር ዕድል ሲቀናት ለእኔ ደግሞ መንገዱን አሳየችኝ፤ ከመራብ ገላን መሸጥ፣ ገላን ከመሸጥ ደግሞ አሳይቶ ገንዘብ ማግኘት አይሻልም?” ስትልም ጠይቃኝ ነበር፡፡ ያን ጊዜ “መራብ ይሻላል” እንዳልላት እሷ ሥራውን የመረጠችው መራብ ባስከተለባት መዘዝ እንደሆነ ነግራኛለች። መራብ የሚያመጣውን መዘዝ ደግሞ ምን እንደሚያስታውሰን አላውቀውምና ዝም አልኋት፡፡ የጀመርሽው መንገድ የተሻለ ነው እንዳልል ደግሞ ድርጊቱ አስነውሮኛል። እናም ያኔ ከንፈሬን በሐዘኔታ መጥጬ በደንብ ዝም አልኳት፡፡ ይቺኛዋን ግን ምን ልበላት፡፡ እኔ እሷን እያየሁ ሐሳቤን ሳነሣ ስጥል፣ እርሷ ልብሷን ጥላ ጨርሳ በመጨረሻም እርቃን ገላዋን፣ መለመላዋን ቀርታለች፡፡ አሁን እኔም ኢትዮጵያዊ እንዳትሆን አጥብቄ ተመኘሁ። ይኼኔ እኮ እንዲህ ሆና የምታገኘውን ዶላር ከምትልክላቸው ቤተሰቦቿ ውስጥ አንዱ ወንድሟ እየፈነጨበት ይሆናል ስል አሰብኹ፡፡ የተቀመጡትም የቆሙትም ወንዶቹ በራቁት ገላዋ አፋቸውን ከፍተዋል፡፡ በዛ ሰዓት የሚደንሰው ራቁት ሰውነት የእርሷ ብቻ አልነበረም፡፡ በርካቶች ሥራ ያሉትን እርቃን ዳንስ ተያይዘውታል፡፡

ምን ያህል ሰዓት መድረክ ላይ እንደቆየች ለማስተዋል ባልችልም ሲበቃት ወረደች፡፡ መጨረሻዋን ለማየት በዓይኔ ተከተልኳት፡፡ እንደ ባልደረቦቿ እሷም የመድረኩን ካበቃች በኋላ የግሏን ጀመረች። ተጠርታ መሰለኝ ከወንዶች ጋር ተቀምጣ ስታያት ወደ ነበረች ወጣት ፈረንጅ ሴት ሄዳ ትደንስላት ጀመረች። የዳንሱ እንቅስቃሴ መተሻሸትንም ይጨምር ነበር፡፡ ሲላት ደግሞ ትቀመጥበታለች። ልጅቷን ከዛ በላይ ተከታትሎ መመልከት ለእኔ ሕመም ሆነብኝ፡፡ እንደምንም ብዬ ላነጋግራት ሞከርኩ፡፡ በጉዳዩ ላይ ከወዳጆቼ ጋር ተወያየሁ፡፡ ለማነጋገር ያለው አንድ አማራጭ ለዳንስ መጋበዝ ብቻ ሆኖ ተገኘ። ማነው የሚጋብዘው? ደፋር ከመካከላችን ጠፋ፡፡ እንደምንም ለትንሽ ደቂቃ ብዬ ባለታክሲውን አግባባሁት፡፡ በአንዷ አስተናጋጅ አማካይነት ጥሪ ተላለፈላት፡፡ ቆየት ብላ በውስጥ ሱሪ እና በጡት ማስያዣ መጣች፡፡ ቁርጥ ሐበሻ። እንደመጣች ባለታክሲውን እየተሻሸች መደነስ ጀመረች፡፡ ከየት እንደመጣች ለማወቅ በአማርኛ ሰላምታ ሰጠኋት። በማውቃቸው ጥቂት ትግርኛ ቋንቋ ሞከርኋት፡፡ አሁንም ዝም አለች፡፡ ባለታክሲው እየቀፈፈው መጣ፤ ሊታገሠኝ አልቻለም፡፡ ለመገፍተር የዳዳው ይመስላል። ሰላምታውን በፈረንጅ ቋንቋ አደረግሁና “የሀገሬ ልጅ መስለሽኝ ነው” አልኋት፡፡ ዳንሷን ሳታቋርጥ “የት ነው ሀገርሽ?” አለች። “ኢትዮጵያ”፣ አንገቷን በማወዛወዝ ምላሽ ሰጠችኝ፡፡ እኔ ከዛ አይደለሁም ማለቷ ነበር፡፡ “ከአሥመራ?” አሁንም አንገቷን አወዛወዘች፡፡ “መልክሽ ግን የኛን አገር ሰው ይመስላል” አልኋት፤ ዝም ብላ መወዛወዟን ቀጠለች፡፡ “ይውለቅልህ” ለባለታክሲው ጥያቄ አቀረበችለት፡፡ ያችኑ እራፊ ጨርቋን ልታወልቅ መሆኑ ነው፡፡ “አልፈልግም፤ አልፈልግም” አለና ተቻኩሎ ከኪሱ ካወጣቸው ዶላሮች መካከል አምስት ዶላር ሰጣት አሜሪካን ሀገር ባለታክሲን ከሌላው ሰው ለየት የሚያርገው በርካታ ዝርዝር ዶላሮች በኪሱ መያዙ ነው፡፡

እንደ ሌላው ሰው በየማሽኑ ላይ ካርድ ሲጭር አይውልም። “ዐሥር ዶላር ነው” ስትል አምስት ዶላር ጭማሪ ጠየቀችው፤ እንዲያቆያት በዐይኔ ብለማመነውም ፈቃደኛ አልሆነም። ዐሥር ዶላር ጨመረላትና እንድትሄድለት “አመሰግናለሁ” አላት፡፡ ምስጋናውን በፈረንጅ ቋንቋ ነበር ያቀረበላት፡፡ እሷም ዶላሩን ተቀብላው “አመሰግናለሁ” አለችው። መልሱ ግን በአማርኛ እንጂ በፈረንጅኛ አልነበረም።ሁለታችንም በድንጋጤ “እንዴ?” የሚል ቃል አወጣን፡፡ እኔማ ከተቀመጥኹበት ተነሥቼ ይዤ ላስቀራት ምንም አልቀረኝም። ፈገግ ብላ “ያቐንየለይ” ስትል ምስጋናውን በትግርኛ ጨምራልን፣ አረማመዷን አፍጥና ግራ አጋብታን ወደመጣችበት ተመለሰች፡፡ ዳንስ ቤቱን ለማየት ከመሄዴ በፊት ስለሐበሻዊ መልኳ ደናሽ የነገሩኝ ኢትዮጵያውያን ልጅቷ ኤርትራዊ ስለመሆኗ ሳይጠራጠሩ ነበር ያወሩኝ፡፡ ኤርትራውያን ባገኘሁ ጊዜም ስለዚችው ልጅ ጠይቄያቸው ኢትዮጵያዊ ስለመሆኗ ነው ያወሩኝ፡፡ አብረውኝ የመጡት ልጆችም ልጅቱ ኤርትራዊ ስለመሆኗ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አልነበራቸውም፡፡ሁለቱም ከኛ ወገን አይደለችም ሲሉ፤ እዚያ እና እዚያ አሽቀንጥረው ሊጥሏት ይሞክራሉ፡፡ ዋናው ምክንያታቸው ደግሞ በድርጊቱ ማፈራቸው ነው፡፡ የልጅቷ ዜግነት የማወዛገቡ ሌላው ምክንያት ራሷ ልጅቷ መሆኗ ገባኝ። በሁለቱም ቋንቋ ትናገራለች፤ መልኳም የሐበሻ ነው፡፡ ለእኔ ግን መምጫዋ አላስጨነቀኝም፡፡ እሷ ከየትኛውም ትምጣ፤ ከሁለቱም ሀገር ቀያቸውን ጥለው የሚሰደዱ ዜጎች፤ ወይ በትምህርት፣ በፖለቲካ ጉዳይ አሊያም ሥራ ፍለጋ ነው፡፡ “እንጀራ ፍለጋ 15 ሺሕ ኪሎሜትር ተጉዞ ገላን በአደባባይ አራቁቶ ለሰፊ ሕዝብ መሸጥን ምን አመጣው?” አላናገረችኝም እንጂ ይህችንም እንደ አዲሳባዎቹ ልጠይቃት ያሰብኹት ጥያቄ ነበር፡፡

ምናልባትም “ከምራብ ብዬ” ነው ትለኝ ይሆናል፡፡ የሷ ግን እንደአዲሳባዎቹ መልስ አልባ አያደርግም፤ “ስንት እንጀራ ለመብላት ነው?” እላት ነበር፡፡ ለእኔ ሰቅጣጭ ከሆነብኝ ከዚህ ቤት ወጥተን ያመራነው ወደ ኢትዮጵያውያን ጭፈራ ቤት ነበር። መቼም “ከሺሻ እና ከዳንስ ቤት አትወጪም ወይ?” እንዳትሉኝ እኔ ያየሁት እንዳይቀርባችሁ ከሚል እሳቤ ነው!! ሌላ ሌላውንም ያየኹትን፣ የታዘብኹትን ያህል ቀስ እያልኹ አወጋችኋለሁ፡፡እናም በዚህ ጭፈራ ቤት በመጠጥ ተሟሙቀው፣ሲያሻቸው እየተሻሹ ሲላቸው እየተሳሳሙ፣ሲላቸው እየቆሙ፣ሲፈልጉ ደግሞ ተቀምጠው ሺሻቸውን እያጨሱ፤በጭሱ ደግሞ ታፍነው ልባቸው እስኪጠፋ በሀገራቸው ዘፈን እየጨፈሩ ያየኋቸው ጥንዶች እጅግ ጨዋ ሆነው ታዩኝ። የአስነዋሪ እና የአኩሪ ተግባር መለኪያው ጠፋብኝ፡፡ በአሜሪካ ቆይታዬ በአገሬ የማውቀውን የአስነዋሪ እና የአኩሪ ታሪክ መለኪያ ካጠፋብኝ ሌላው የጥቂት ኢትዮጵያውያን ተግባር አንዱ ደግሞ የግብረሰዶማውያን ነገር ነው፡፡ለአሜሪካኖቹ ሳይቀር አስጨናቂ በሆነው ግብረሰዶማዊነት ተዘፍቀው ያየኋቸውና ታሪካቸውን የሰማሁት ኢትዮጵያውያን እስካሁን አስጨንቀውኛል። ጎዳና የወጡ ኢትዮጵያውያንን ማየት እነዚህኞቹን እንደማየት አልከበደኝም፡፡ ግብረሰዶማዊነት በአሜሪካ መባባሱ እና ቀስ በቀስ በተለያዩ ግዛቶች ለጋብቻም እየተፈቀደ መሄዱ የኢትዮጵያንም ራስ ምታት ሆኗል። አንዲት እናት ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድ ልጇ “ማሚ ጓደኛዬን ላስተዋውቅሽ” ሲል በሰጣት ቀጠሮ ስላጋጠማት ነገር ያወጋችኝን ደግሞ እስቲ ልንገራችሁ። (ይቀጥላል)

Read 11206 times Last modified on Friday, 15 March 2013 07:55