Saturday, 26 January 2013 15:13

“እንደ አቅሜ አኑረኝ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ከጥቂት ወራት በፊት የሆነ ሠርግ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ…እንዲህ ለአብዛኛው ሰው ውሉ እየጠፋ ባለበት ዘመን ሰዎቹ ድንኳን ጥለው ከአቅማቸው በላይ ተጋባዥ ጠርተዋል፡፡ ሁለቱም የመንግሥት ደሞዝተኞች ናቸው፡፡ ታዲያላችሁ…ከዘመድም፣ ከቁጠባ ማህበርም በመከራ በተሰበሰበች ገንዘብ የተዘጋጀችው ምግብ ለግማሹ ሰው እንኳን ሳትዳረስ ማለቅ! እዛ ላይ ነገሩ ቢያልቅ ጥሩ ነበር፡ ግፋ ቢል “ምግብ አለ ብዬ ባዶ ሆዴን ሄጄ ጦሜን የሰደዱኝ እግዜሐር ይይላቸው…” ምናምን አይነት ነገር ቢኖር ነው፡፡ (እኔ የምለው…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…ለምንድነው ሠርግ ምናምን በመሳሰለው ግብዣ በቂ ምግብ ያላገኘነውም፣ እምብርታችን እንትን እስኪል ‘የዋጥነውም’ እኩል “በእነሱ ቤት ጋብዝው ሞተዋል!” እያለ መሄዱ…በቃ ‘ኮምፐልሰሪ’ ሆነ ማለት ነው! እናላችሁ…በቆልቲ ጋብዛችሁ ወይም አሮስቶ ዲቢቴሎ… “ድንቄም ተጋበዘ!” መባል እንደማይቀርላችሁ እወቁማ!) እናላችሁ…ምግቡ ተሟጦ ሰዉ ፍጥጥ ሲል የወንድና የሴት ቤተሰብ ግርግር ፈጥረው ድንኳኑን ቀወጡት አሉ፡፡ ሙሽሮች በዓቨናቸው ዕንባ ግጥም ብሎ ነበር ተብሏል፡፡

እኔ የምለው መጀመሪያ ነገር…እዚሀ አገር በቃ አቅሚቲን የማወቅ ነገር ተረሳ ማለት ነው! ብዙ ነገሮች ላይ ከአገር ጀምሮ እስከ እኛ ተራዎቹ ድረስ…ሁላችንም አቅማችንን እየረሳን ነገርዬው ሁሉ እኮ ግራ የሚያጋባ እየሆነ ነው! ስሙኝማ…መአት መሥሪያ ቤቶች ዕቅዳቸውን ሲያሳውቁ ትሰሙልኛላችሁ አይደል… በዓመቱ መጀመሪያ ላይ… “በዚህ ዓመት ምርታችንን በመቶ ምናምን ፐርሰንት ለማሳደግ በጥናት የተደገፈ ዕቅድ ተይዟል…” ምናምን ይባላል፡፡ ድንገት የአንድ እርከን ዕድገት ወይም ቦነስ አገኛለሁ ብሎ የቋመጠ ሠራተኛ አዳራሹን በጭብጨባ ያናጋላችኋል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ላይ እኛው መቶ ምናምን ፐርሰንት ያሉት ሰውዬ ተመልስው መድረክ ላይ ይወጣሉ፡፡ “በተለያዩ ምክንያቶች የዘንድሮው ዕድገት ቀደም ብሎ በዕቅድ ከተያዘው ሃያ ስምንት ፐርሰንት ሆኗል…” ምናምን ይሉላችኋል፡፡ እናላችሁ…የመጀመሪያው የመቶ መናምን ፐርሰንት ፉከራ ለዜና አመቺ ሆነና…“ይህን ያህል የምታሳደጉት በየትኛው አቅማችሁ ነው?” ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ ስሙኝማ…እዚህ አገር ምን የተለመደና ‘የማያስጠይቅ’ ነገርም አለ መሰላችሁ…ማጋነን! በሁሉ ነገር በዓለም ምናምነኛ የተለመደው እኮ ማንም ሰው “በምን ላይ ተመስርተህ ነው እንዲህ ልትል የቻልከው?” “የትኛው ተቋም ነው አጥንቶ እዚህ ላይ የደረሰው?” ምናምን ብሎ የሚጠይቅ ስሌለ አቅሚቲን ባይኖርም የተፈለገውን ነገር አደርጋለሁ ምናምን ማለት ይቻላል፡፡

በተለይ አንዲት ጫፏ የምትያዝ ነገር ከተገኝችማ…ምን አለፋችሁ… “ዓለም ሳይቀር ያደነቀው…” የምንላት ‘ስታንድ አፕ’ ኮሜዲ ከፊት ወይም ከኋላ ትገባለች፡፡ “ዓለም ሳይቀር ማድነቁን በምን አረጋገጥክ?” ተብሎ የመጠየቅ ስጋት ስሌለ የሌለንን አቅም “አለን” ማለት እንደ ሺሻ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሱስ እየሆነብን ነው፡፡ እናማ…ነገራችን ሁሉ “የእከሊት ልጅ ድል ባለ ሠርግ አግብታ የእኔ ልጅ ያለሠርግ የምትገባው ምን በወጣት!” እየተባለ ሦስተኛ ዲቪዥን ሆኖ “እንደ ፕሬሚየር ሊግ ካልሆንኩ ከምላሴ ጸጉር…” አይነት ነገሮች የብዙዎችን ጎጆ ወጪዎች ኑሮ እያናጉ ነው፡፡ ፍቺዎች በዙ ምናምን የሚባለው ነገር…አለ አይደል… ብዙ ጊዜ ችግሩ የጀመረው ገና የሠርጉ ጊዜ ይሆናል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሆሊዉድ ነው አሉ…እናላችሁ ሙሽርዬዋ የሆሊዉድ ተዋናይት ነች፡፡ እናማ…ሙሽራው ሆዬ ወደ እሷ እየሄደ ባለበት ጊዜ መንገዱ በመኪና ተጨናንቆ እንደልቡ መንቀሳቀስ ስላልቻለ አርፍዷል፡፡ ታዲያላችሁ…ሞባይል ደውሎ ምን አላት መሰላችሁ…ወዳንቺ እየመጣሁ መንገዱ በትራፊክ ተጨናንቆ ነው በሰዓቱ ያልደረስኩት፡፡ ብቻ አደራሽን… እስከደርስ ድረስ ሌላ ሰው አግብተሽ እንዳትጠበቂኝ…” ሆሊዉድ እንዲህ ነዋ! (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሙሽራው ባረፈደ ቁጥር ሙሽርዬዎቹ ሌላ ‘ቤንች ላይ’ የተቀመጠ ‘የሚያገቡ’ ቢሆን ኖሮ የአገራችን ‘እጩ ሙሽራ’ ሁሉ አጨብጭቦ ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር፡፡) አቅምን ያለማወቅ ነገር በዝቷላ! እናማ በአቅም መኖር እያቃተን ብዙ ነገራችን ውሉ እየጠፋ ነው፡፡ በየቡና ቤቱ እየተጋፋን መጠጥ ስንገለብጥ የምናመሸው አብዛኞቻችን…አለ አይደል… አቅሙ ኖሮን ሳይሆን ነገርዬው “ከማን አንሼ…” አይነት ነገር ነው፡፡

የምር… ከማን አንሼ ያፈረሰው ቤት ሩቡን ያህል እንኳን ‘ለልማት’ ተብሎ አልፈረሰም፡፡ እናማ…ያለ አቅም ‘የሚሞከሩ’ ሠርጎች አብዛኞቹ የዚሁ የ“ከማን አንሼ” ነገር ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሰውዬው ጓደኛውን ምን ይለዋል መሰላችሁ… “አንድ አምስት ሺህ ብር አንተ ጋ ታስቀምጥልኛለህ?” ይለዋል፡፡ ጓደኝዬውም “ለምን?” ይለዋል፡፡ ምን ብሎ ይመልስላችኋል…“ገና ትናንት ነው ያገባሁት፡፡” ይሄኔ ጓደኝዬው… “ታዲያ ገንዘብህን ቤትህ ለምን አታስቀምጠውም?” ሲለው ጓደኝዬው ምን ቢል ጥሩ ነው…“የማላውቃት ሴት እቤቴ ገብታማ አምኜ ገንዘቤን እቤቴ አላስቀምጥም!” ሠርጉ ላይ ተጠርቶ የመጣው ሰው ሁሉ በውሀ ጥም ጉሮሮው ደርቆ…አለ አይደል… “ለክርስትና እንመጣለን ገና…” የሚለው አሽሙር ስለሚመስል ይቅርልንማ፡፡ ልክ ነዋ… ሙሸሮቹ እንዴት እንደ ሠረጉ ብናውቅ ኖሮ እኮ ዘፈንዬው ተለውጦ “ለማጽናናት እንመጣለን ገና…” ምናምን የሚል አዲስ ሪሚክስ ይሆን ነበር፡፡ እናማ…በሠርጋቸው ማግስት ወደ እናቶቻቸው ሮጠው ስለሄዱ ሙሽሮች ሰምተናል፡፡ (እኔ የምለው… አንዳንድ ሙሽሮች ‘ትዋይላይት’ ላይ እንደምናያቸው ሰዎች ያደርጋቸዋል እንዴ! አሀ…“ለዘላለም ገባች” የተባለች፣ ሙሽርዬው “የጠቅላይ ተሰካልኝ” ያለላት እንትናዬ በማግስቱ እግሬ አውጪኝ ስትል ግራ ይገባናላ!) እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሰውየው ለሚስቱ ብዙም ፍቅር የለውም አሉ፡፡

እናላችሁ… አንድ ቀን ለጓደኛው “ሚስቴ እኮ ጥላኝ ጠፋች…” ይለዋል፡፡ ጓደኝየው ምን ብሎ መለሰለት መሰላችሁ… “እስቲ ትንሽ ቀን ጠብቃትና በዛው ከቀረች ብርችንችን ብለን እናከብረዋለን፡፡” ሌላው ሰውዬ ደግሞ ምን አለ… “ሚስቴ ጥዬህ እሄዳለሁ እያለች እየፎከረችብኝ ነው…” ብሎ ለጓደኝዬው ሲነግረው ጓደኝዬው ምን አለ መሰላችሁ…“ፉከራ አይደለም ጥዬህ እሄዳለሁ ብለሽ ቃል ግቢልኝ በላት…” ሰውዬው የእሱ ቤት ጭቅጭቅ ሰፍኖ የጓደኛው ቤት ሰላም መሆኑ ግርም ስለሚለው ይጠይቀዋል፡፡ “እንዴት ነው እኔ መከራዬን እያየሁ አንተ ቤት ሰላም የሆነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየውም ምን ብሎ ይመልሳል መሰላችሁ…“ሚስቴ የገንዘብ ሚኒስትር ነች፣ እናቷ የጦር ሚኒስትር ነች፣ ምግብ አብሳይ ደግሞ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ነች…” ጓደኝየው በማብራሪያው ግራ ይገባውና “ታዲያ በዚህ መሀል አንተ ምንድነህ?” ሲል ይጠይቀዋል። ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“እኔ ግብር ከፋዩ ሰፊው ህዝብ ነኝ፡፡” ዓለም ላይ የለየለት አምባገነን ማን እንደሆነ ታውቃለህ ሲባል ምን አለ መሰላችሁ… “አንተ እንዴት አወቅህ… እኔ አይደለሁ እንዴ ያገባኋት!” አለና ቁጭ አለላችሁ፡፡ አስተማሪው ተማሪውን “አባትህ ሦስት መቶ ብር ቢኖረውና ግማሹን ለእናትህ ቢሰጣት እናትህ ምን ይሰማታል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ልጁ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“በድንጋጤ ልቧ ቀጥ ይላል፡፡” በድንጋጤ ልባችን ቀጥ ከማለት ያድነንማ! “እንደ አቅሜ አኑረኝ” ማለት ይልመድብንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3026 times