Print this page
Saturday, 26 January 2013 14:46

የታገል ሰይፉ ግጥሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(31 votes)

ሰለሃገራችን ግጥም ስናነሳ ታገል ሰይፉ ፈጽሞ የማይረሳ ተዋናይ ነው፡፡እንደ ታገል በአስራስድስት አመቱ ብዕር ጨብጦ ግጥም የጻፈና በዚያ እድሜው ሰዎችን ያስደመመ ሌላ ማንም ታዳጊ አልነበረም፡፡ በተለይ “ፍቅር” በሚል ርዕስ የጻፈው መጽሃፉ፣ በዚያ እድሜ እንደዚያ ይታሰባል ለማለት የሚቸግር ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ “ቀፎውን አትንኩት” በሚል ጥራዙ ጥሩ-ጥሩ ሃሳቦችን አንስቷል፤ሌላውና የተለየ ስራው “ኢህአዴግ ውስጥ የገባ አውሬ” (መካከለኛ ልብወለድ) ነው፡፡ ካሁኑ አዲስ መጽሃፍ ሌላ “የሰዶም ፍጻሜ”፣“የሃምሳ አለቃ ገብሩ” እና “የእድሜ ጅረት” የተሰኙ መጻህፍትን፣ እንዲሁም ምስል የለበሱ ሁለት የሲዲ ግጥሞችን አሳትሞ ለህዝብ አድርባል፡፡ ይሁንና ታገል በቴሌቪዥን በሚያቀርባቸው ምስል-ለበስ ግጥሞቹ ቢወደድም፣የግጥም ውበት፣ ጥልቀትና ግርማውን ተነጥቆ ነበር፡፡በዚህም እውነተኛ የግጥም ወዳጆቹን ቅር ያሰኘ ይመስለኛል፤እኔም የወዳጅነቴን “ወድቀሃል” ብዬ ነግሬው ነበር፡፡

ደግነቱ ታገል በፈጠራ ስራዎቹ ላይ የሚሰጠውን አስተያየት ለመስማት ከብዙዎቻችን የተሻለ ልብ አለው፡፡ይህ ደስ የሚል ልምምዱ ነው፡፡ታገል ወርዶ ያልቀረውና መልሶ መሰላሉን የጨበጠው ለዚህ ይመስለኛል፡፡አንድ ጊዜ በግጥም ምክንያት “ተበላሽተሃል” ብዬው የመረረ ንግግር ተነጋገርን፣ባንድ ታክሲ መምጣታችንን አስታውሳለሁ፡፡ያለመኮራረፋችን የታገልን ከኔ የተሻለ ታጋሽነትና ሂስ ተቀባይነት ያሳየኝ ይመስለኛል፡፡ የታገልን አዲስና ዛሬ የምቃኘውን መጽሃፍ እንዳነብበው ታገል ቀደም ብሎ ቢነግረኝም ጊዜ በማጣት ሳላነብበው ለገበያ በመቅረቡ አዝኛለሁ፤ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ግጥማችንን ወይም ጽሁፋችንን የሚያይልን ሰው ከአልተፈለጉ ስህተቶች ሊያድነን ይችላል፤እኔ በዚህ አምናለሁ፤መጽሃፍት መግቢያ ላይ እንደዋዛ ስማቸውን የምንጽፋቸው ሰዎች ከስንት ጉድ ያዳኑን እንደሆኑ ልባችን ያውቀዋል፡፡እኔም ያዳኑኝን አልረሳም፡፡የሚያሳስቱም እንዳሉ-ሁሉ ማለቴ ነው፡፡የታገል አዲስ መጽሐፍ ርዕሱ “በሚመጣው ሰንበት” የሚል ነው፡፡

እውነት ለመናገር ይህ መጽሃፍ በታገል የግጥም ሥራዎች ታሪክ ውስጥ በውበትና በሃሳብ ልቀት ከፍ ያለ ነው፡፡ጭብጦቹ ወደ ትውልድ ያነጣጠሩ፣የሃገር ድምጽና መልክ የጠቀለሉ፤ናቸው፡፡ከዚህ ቀደምም በአብዛኛው የማይታማበት የቃላት አጠቃቀምም የተሻለ ሆኖ ቀርቧል፡፤ዜማና ምት ላይ ታገል ሁሌም አሪፍ ነው፡፡ ለምሳሌ “ልጄን ላንተ ካራ” የሚለው ግጥሙ የዘመናችን በሽታ ማሳያ ነው፡፡ትንሽ እንይ፡- “የተማረ ይግደለኝ”- የተባለ ለታ የተጣባው ደዌ -የገባው በሽታ አጎነቆለና-በኔ ላይ ግርሻቱ ልጄን ትገድሉት ዘንድ-ፈቀድኩ እኔ አባቱ …………….

ከዕውቀት የጎደለ-ከጥበብ የሌለ ህይወት አልባ ቃላት እያንበለበለ ላይበስል ያፈራ-ላያድግ የበቀለ የምናቡን ድርቀት-የቋንቋውን ኦና ያንበለብልና-ያንበለብልና…. ፍሬ የለሽ ክምር-ውሃ አልባ ደመና ላይበላ እንደራበው-ላይጠጣ እንደጠማው ማሲንቆን ሳያውቀው-በገናን ሳይሰማው በሞዛርት ፒያኖ-በነቾፐን ፍሉት ግድ የለም ግደሉት-ግድ የለም ግደሉት “መለያየት ሞት ነው!” ይባል የነበረ ፍቺው በዚህ ዘመን -እየተቀየረ ሰው ለንደን በኖረ-ሰው ዲሲ በኖረ መለያየት ህይወት መሆን ከጀመረ ግደሉልኝ ኧረ የምን ተባ ፈራ ፈቅጄ በሰጠሁ- ልጄን ላንተ ካራ ማነው የሚቆጣ-ማነው ሚነደው የተስፋውን ግልገል ሳይሰባ ብታርደው አሁን የለምና! ተደፈርን የሚል-ኢትዮጵያዊ ጀግና…. እያለ ይቀጥላል፡፡ ስለማንነት ውድቀት መረር ያለ ሂስ ነው፡፡ራሳችንን ትተን ሌሎችን የመሆን አባዜ ተጠናውቶን ከርታታ ሆነናል፤የባህር ላይ ኩበት ነው የሚል!! ያ ብቻ አይደለም፣ በዚህ ሁሉ ስካር ውስጥ መንገድ ተሳስተሃል የሚል መሪም የለም፡፡ማንነቱን እየጣለ ነው የሚል ሽሙጥና ግልጽ ቁጭት፣ሽንቆጣም ነው፡፡ልምጩ ልቤን ነክቶታል፤ገርፎታልም፡፡…ገጣሚ መሪ ነው፤አስተማሪ ሳይሆን ጎልጉሎ የሚያሳይ ባለ ንስር ዓይን፡፡

ታገል የሚብከነከነው ቋንቋችን ሲንኳሰስ ነው፡፡በተጨማሪም ፈረንጅ ሃገር መሄድ ብርቅ መሆኑን ያሽሟጥጣል፡፡ዶክተር በድሉ ደግሞ ፈረንጅ ሃገር ሆኖ የሃገር ሰቀቀንን እንዲህ ገልፆታል- ”አንተንስ እኔን አያርግህ” በሚለው ግጥሙ፡- እኔም አውሮፓ ላይ ፣ በሲጋራ ጢስ ውስጥ ፣በማኪያቶ አረፋ መሽቶ የማይነጋ ቀን፣ዕድሜዬን ስገፋ፣ በሰለጠነ ዓለም”፣እትልቅ ከተማ በሰው ተከብቤ፡- ብቸኝነት ሰብሮኝ፣ፍቅርን ተርቤ፣ አንተን ባረገኝ እላለሁ፤ የታገል ግጥሞች ከወትሮው የተለየ ውበትና ጥንካሬ አይቼባቸዋለሁ፡፡ከአዳዲስ ግጥሞቹ “አመሰግናለሁ”ን እናንብብ፡- እንደ አቦል በረካው-እንደቡናው ስባት መፋጀትሽ መሃል-ላየሁት ደም ግባት አመሰግናለሁ! እንደግዚሃር ባርኮት-እንዳምላክ ስጦታ በማስጨነቅሽ ውስጥ -ለቀመስኩት ደስታ አመሰግናለሁ! እንደ ጨረቃዋ ድምቀታዊ ጉልበት በጨለማሽ መሐል -ለተቸርኩት ውበት አመሰግናለሁ እንደ መተሬ ጣም እንደ ኮሶ ቃና መራርነትሽ ውስጥ ላገኘሁት ጤና አመሰግናለሁ! ስለፍቅር የሚያወራ የሚመስለው ግጥም ከመራራ መድሃኒት ውስጥ የሚገኘውን ፈውስ ያሳያል፡፡

ደምግባት፣ደስታ፣ውበት፣ጤና ተቃራኒ ከሚመስሉ ተግዳሮቶች ውስጥ መወለዳቸውንና አንጻራዊነትን ያጎላል-ታገል፡፡ ህይወት የምትበርባቸው ክንፎች ሚዛንም ነው - ይሄ!! “ኮተታም ገጣሚ” አንዱ የታገልን አቅም የሚያሳይ ትልቅ ግጥም ነው፡፡እንደ እሳተ ገሞራ እሳት የሚተፉ ሃይለኛ ቃላት ተጠቅሞ፣ያሽሟጥጣል፡፡ግጥሙን ከባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን “እከካም ተማሪ”የቀጠለ እና የተቃረነ የዘመን ፍተሻ ብሎታል-ገጣሚው፡፡ የተወሰኑ ስንኞች ልቀንጭብ፡- …ፉጨት የተራቡ-ጭብጨባ የተጠሙ “ብራቮ” እንደ ዘኬ የሚለቃቅሙ ሲባል እንደሰሙ-“ኪነት የህዝብ ናት!” እንዳዘን ቤት ንፍሮ ማንም የሚዘግናት ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንደማህበር ፅዋ -እንደ ፀበል ፀዲቅ ሁሉ ሲዳረሳት -ሁሉ ሲቃመሳት ካልተጣደበት ድስት -ካልተያያዘ እሳት እየገነፈለ እንከን አየሁ አለ ቅኔውን ሲያሰማኝ -እዬዬውን ሲኛኝ ያ!አባቱን ኮናኝ -አምላኩን አራሚ ቀኑን አጨላሚ እሱ ኖሯል ለካ -ባንተ ቀን ለምላሚ ባንተ መድረክ ቋሚ ያ!ጭንጋፍ ገጣሚ -ኮተታም ገጣሚ… እያለ ይቀጥላል፡፡…ይሁንና የግጥሙ ርዕስና ሃሳቡ ተጋጭቷል፡፡”ኮተታም ገጣሚ” ብሎ ሃያሲውንም አስገብቷል፡፡…ግጥሙ ገጣሚውን ብቻ ሳይሆን ሃያሲውንም ይተቻል!! የታገል መድበል ሸጋ ሸጋ ግጥሞችን ይዟል ብንልም የቀለደባቸውም እንዳሉ ሳይዘነጋ ነው፡፡ “ፋሲካን ለማርታ” በሚለው ግጥሙ ከላይ እስከ ታች በሳድስ፣ሳድስም ሆኖ በአንድ “ሽ” ጀምሮ ጨርሶታል፡፡ ሌሎችም ችግሮች አሉት፡፡ ”ፍቅር ለኔና አንቺ” የሚለውን ግጥሙን በከፊል ጋብዤ ለዛሬ ቅኝቴን ልቋጭ፡፡ …ካለስዋ አይበራም ስል -የዘመኔ ፅልመት የቀኔ ጨለማው፣ አውቃለሁ ውሸት ነው -ፍሬ ቢስ ገለባ ለሰማኝ በሩቁ፣ እስከዛሬ ድረስ -የሷ አይነት አበባ በቅሎ አለማወቁ፣ ግና ይሄ ውሸት -ይህ ውዳሴ ከንቱ አገር ያቀለለው፣ በኔ እና እሷ መሐል -ዕውነት መሆኑ ነው ፍቅር የሚባለው፡፡ …አይመችም?…ፍቅር በሁለት ሰዎች መካከል የሚታይ ተዐምር ነው፡፡ባገር ሰላም ለብቻ ማበድ መሰለኝ!! ለሌላው ሰው ቀልድ፣ለተዋናዮቹ እልም ያለ ውበት፡፡…ፍቅር ለማረጋገጫ የማንንም ፊርማ አይጠይቅም፤አይፈልግም እያለ ነው፣የሁለት ሰዎች ቋንቋ ነው-ለሌሎች አይገባም፡፡ፍቅር ስንል ግን ውሲባዊ ቅብጠትን አይደለም፤የነፍስን ዜማና-ዝማሬ ነው፡፡…

Read 10534 times