Print this page
Saturday, 26 January 2013 12:22

“የገበሬ ልጅ ነኝ፤ ፕሬዚዳንት ለመሆን ማለም አልችልም ነበር” ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከአዲስ አድማስ ጋር- ልዩ ቃለምልልስ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(8 votes)
  • ስለድሮና ስለአሁኑ ፓርላማ ነፃነት እያነፃፀሩ ያስረዳሉ 
  • የሦስቱን መንግስታት ጠንካራና ደካማ ጎኖች ይገልፃሉ 
  • ስለንጉሱና ከንጉሱ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ይናገራሉ 
  • “መደነስ እወድ ነበር፤እነ ራሔል ዮሐንስ ደስ ይሉኛል” ብለዋል

በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን የፓርላማ አባል እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የያኔውንና የአሁኑን ሲያነፃፅሩት፤በአፄ ኃ/ ስላሴ ዘመን የነበረውን የፓርላማ ነፃነት እንዴት ይገልፁታል---- እንደ ዛሬ በፓርላማ ለሚነሱ ጥያቄዎችና በመከራከሪያ ነጥቦች ዙሪያ የሚካሄደው ውይይት ምን ይመስል ነበር?

በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በዛን ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲ አልነበረም፡፡ የገዥ ፖለቲካ፣ የተገዥ ፖለቲካ የሚባል ነገር የለም፡፡ግን በሀሳብ መስማማትና በሀሳብ ያለመቀራረብ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ እኔ የምናገረው ነገር የሚጥማቸውና የሚስማማቸው አሉ ሆን ብለው ደግሞ የሚቃወሙ አሉ የሀሳብ ቡድን እንጂ የፓርቲ ቡድን አልነበረም፡፡ የአሁኑ ልዩነቱ ፓርቲ ነው፤ የፓርቲ ዲሲፕሊን አለ፡፡ ያኛው ለክርክር የበለጠ ነፃ ነው፡፡ ሁሉም እንደፈለገው ነው የሚናገረው፣ የሚመዝንለት አብዛኛው እዛው ያለው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ፓርቲ ስለሆነ ከፓርቲ ዲሲፕሊን ውጪ ምንም መናገር አይቻልም፣ የፓርቲን ዲሲፕሊን መከተል አለበት፣ ስለዚህ ሁኔታው የተለያየ ነው፡፡

በንጉሱ ጊዜ በፓርላማ ሳሉ እንደ ህዝብ አጀንዳነት የሚከራከሩባቸው ነጥቦች ምን ምን ነበሩ? የትኞቹ የህብረተሰብ ጥያቄዎች ጎልተው ይሰማሉ?

የህዝብ ጥያቄ ሲባል መሬት ላራሹ፣ የጉልት ገዥ እንዳይኖር ማድረግ እና ሌሎችም የህዝብ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹም እንዲስተካከሉ ለማድረግ ችለናል፡፡ “ድሮና ዘንድሮ” በሚል በታተመውና የእርስዎን የህይወት ታሪክ በሚያስነብበው መጽሐፍ ላይ እንደተገለፀው፤

በንጉሱ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የፓርላማ ተመራጭ ሆነው ፓርላማ ሲገቡ የተሰጠዎት ቢሮ ምድር ቤትና በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ቢሮዎትን በራስዎት አውቶሞቢል ውስጥ አድርገው ነበር እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ----

ነገሩ እንደዚህ አይደለም፡፡ ቢሮው ጠባብ ነው፤ ትንሽ ነው፤ ምድር ቤት አይደለም፡፡ ከእኔ በፊት የነበረው ሃይለማርያም ከበደ እዚህ ቢሮ ነበር፡፡ ከተሰጠኝ ቢሮ በላይ ያለው ሰፊ ቢሮ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ተብሎ ባዶውን ነው ያለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር የህዝብ እንደራሴ አይደለም፡፡ እታች መውረድ አለበት፡፡ የህዝብ እንደራሴው መሪ የበላይ ነው፤ እላይ መሆን አለበት ነበር ጥያቄው፡፡ አይቻልም ሲሉ እንግዲያውስ እኔም አልገባም ጥሩ መኪና አለችኝ፤ዛፍ ጥላ ስር እቆምና፣ ዶክመንቱን ስታመጡ እዚሁ እፈርማለሁ፤ በኋላም አዳራሽ እገባለሁ እንጂ እዚያ ቢሮ አልገባም አልኩኝ፡፡ ይሄንን የመወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የነበሩት አስራተ ካሳ ሰሙ፡፡ ስለሆነም መወሠኛና መምሪያ ሁለት የተለያዩ ምክር ቤቶች ቢሆኑም ትንሽ የበላይነት አላቸው፤ የንጉሱም ምርጫ በመሆናቸው፡፡ እነኛ በህዝብ ተመርጠው ሳይሆን፣ በንጉሱ ተመርጠው ነው ሴናተርነት የሚሾሙት፡፡ የሴኔቱ ፕሬዚደንት የጋራ ጉባዔ በምናደርግበት ጊዜ እሳቸው ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ይሄን ሲሰሙ ወዲያውኑ ዋና አስተዳዳሪውን አዘዙት፤“እሳቸው እውነታቸውን ነው፤ የህዝብ ምክር ቤቱ እላይ መሆን አለበት፤የህዝብ ምክር ቤት ይበልጣል፤ የጠየቀው ልክ ነው አንሱለት” ተባለ እንደውም በራፌ ላይ የሚቆመው ተላላኪ የቤቴን ቀለም ዓይነት የለበሰ እንዲሆን አድርገው፤በእሳቸውና በእኔ መካከል የዘውድ ማለፊያ የሚባል ነበር፤በዛችው ኮሪደር በነፃ እንድንተላለፍ አዝዘው ከሰዓት በኋላ ወደ ስራ ስገባ፤ ‹‹ወዲህ፣ ወዲህ›› አሉኝ፡፡ ‹‹ወዴት?›› አልኩኝ ‹‹ቢሮ ተከፍትዎሎታል›› ብለው አስገቡኝ፡፡ በጣም ደስ አለኝ፤ አሸነፍኩ ማለት ነው፡፡ የህዝብን የበታችነት ላለመቀበል ነው እንግዲህ አሻፈረኝ ያልኩት፡፡ በኋላ ላመሰግናቸው ቢሮዋቸው ሄጄ ነበር፤ እሳቸው ግን ‹‹ምስጋና አይገባኝም፤ትክክል ነው ጥያቄህ፤የህዝብ ምክር ቤት ነው ዋናው፤እኛ እንኳን ሹማምንቶች ነን፣ የህዝቡ ባለቤቶች እናንተ ናችሁ፣ የሚገባውን ነው የጠየቅኸው›› አሉኝና ቢሮዬ ገባሁ፡፡

ለፓርላማ ለመወዳደር ከወሰኑ በኋላ የመረጡት የምረጡኝ ቅስቀሳ መንገድ---- በመኪና እየዞሩ እና ዊንጌት ትምህርት ቤት ተገኝተው ያደረጉት ህዝባዊ ውይይት ነበር፤ በወቅቱ እንደተፎካካሪ የነበረብዎት ፈተና ምን ነበር?

የነበረው ቻሌንጅ ስለመንግስት በይፋ በአደባባይ አይነገርም ነበር፡፡ መንግስት ሲባል ህዝቡ አንድ የሚመለክ ነገር እንጂ አንድ የአስተዳደር ቡድን መሆኑን አያውቅም፡፡ ህዝቡ ይህን እንዲያውቅና መንግስት ምን እንደሆነ እንዲገነዘብ፤ የሚመርጠው እንደራሴ ምን እንደሚጠበቅበት እንዲያውቅ፣ ጥያቄም ካለው እየጠየቀ እንዲረዳ የምርጫ ካምፔን ነበር ያደረግነው፡፡ በዓይነቱ የመጀመሪያ እና ያልተለመደ ነበር፡፡ አሁን አሜሪካ ሀገር ከሚገኘው ዘውዴ ከተባለ ሰው ጋር ነበር፡፡ አንድ ቦታ ላይ የምርጫ ዘመቻ ስናደርግ በአጋጣሚ ከዊንጌት ተማሪዎች አንዱ፣ ‹‹አንተ አጭበርባሪ መቶ አለቃ እስኪ እኛ ጋ ናና እንደዚህ ተናገር›› አለኝ፡፡ ‹‹እናንተ ምንድን ናችሁ?›› ‹‹የዊንጌት ተማሪዎች›› ‹‹ታዲያ እኔ ዊንጌት ምን ይወስደኛል፤ቀራኒዮና ልደታ ነው የምርጫ ጣቢያዬ፡፡ ጥሩ እንግዲያው እመጣለሁ›› አልኩኝ፡፡ መቼም የዊንጌት ተማሪ ቤት ታውቂው እንደሆነ አዳራሹ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ያሉ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የወጡ ተማሪዎች ሁሉ ተገኙ፡፡ ከአሰብኩት በላይ አዳራሹ ጢም ብሎ ነበር፡፡ ክርክር ተጀመረ፤ ብዙ ተከራከሩኝ በዛው ት/ቤት መምሬ ዘውዴ የተባሉ የሞራል አስተማሪያቸው ምረጡኝ ብለው ቀስቅሰዋል፡፡ እና ብዙዎቹ እድሜያቸው የደረሱ ልጆች እንዲመርጧቸው አስመዝግበዋል፡፡ ለተማሪዎቹ ምን አልኳቸው፤ ‹‹ይሔ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፤የኢትዮጵያን ፖለቲካ መሻሻል የምትፈልጉ እኔን ትመርጡኛላችሁ፤መንግስተ ሰማያት መግባት የምትፈልጉ ቁልፉ መምሬ ዘውዴ እጅ ነው፤እሳቸውን ምረጡ›› አልኳቸው(ሳቅ)፡፡

ለምንድን ነው እንደዚያ ያሉት?

ቄስ ስለሆኑ ነው፡፡ እኔ እዚያ አካባቢ ንክኪ የለኝም፡፡ መንግስተ ሰማያትንና ፖለቲካን ምን አመጣው ብትይ---- እሳቸው የሚመረጡበት ነገር ቢኖር እንዲባርኩ ብቻ ነው የሚሆነው(ሳቅ)፡፡

ይህን በመናገርዎት ምን ተፈጠረ?

መምህሬ ዘውዴ ጠዋት ዊንጌት ትምህርት ቤት ባንዲራ የሚያሰቅሉ እሳቸው ናቸው፡፡ ተማሪዎቹ የትምህርት ቤት በራፍ ላይ ጠበቁዋቸውና ‹‹ጊዜዎንም ገንዘብዎንም አያጥፉ፤ ስለ እኛ መናገር የሚችልና እኛ የገባነው ሰው አግኝተናል፤ የምንመርጠው መቶ አለቃ ግርማን ነው›› ብለው ተስፋ አስቆረጡዋቸው፡፡ እኔ ግን ከዛ አካባቢ 8 በመቶ ድምፅ አገኘሁ በዛች በአንድ ቀን ቻሌንጅ ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያን የዓለም ፓርላማ አባል ለማድረግ ባደረጉት ጥረት ኢትዮጵያን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ አድርገዋታል፤ በዚህ ምን ይሰማዎታል?

በጣም ጥሩ ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ ሁሉ ሰው ፈርቶ ነበር፡፡ የሚገርምሽ የአለም ፓርላማ አባል ጥሪ ግብዣው አስራ ስድስት ዓመቱ ነበር፡፡ ለሴኔቱ ፕሬዚዳንት ልዑል አስራት ካሳ ሄድኩና ‹‹እኔ ይሄን ነገር ማስፈቀድ አለብኝ›› አልኳቸው፡፡ ‹‹እረ በፍጹም እንዳታደርገው፣ይጣሉሃል›› አሉኝ፡፡ ‹‹ለምን ይጣሉኛል፣እኔ የቤቴን አዘጋጅቻለሁ፤አባል ይሆናሉ ያልኳቸውን ሰዎች መርጫለሁ›› አልኳቸውም፡፡ መመዘኛው ቡድን ነበር፡፡ ‹‹ንጉሠ ነገስቱን የውጪ ጉዳይ ስለሆነ አስፈቅዳቸዋለሁ›› አልኳቸውና ንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ሄድኩኝ፡፡ ‹‹እንግዲህ ህዝብዎ የተፃፈ ህገ መንግስት ጥቅም ባላወቀበት ጊዜ የተፃፈ ህገ መንግስት ሰጡት፡፡ አሁን እድገቱ አንድ ቦታ ላይ ደርሶ የዓለም ፓርላማ አባል መሆን አስፈላጊ ሆኗልና ይሄንን እንዲፈቅዱ ነው›› አልኳቸው ታውቂያለሽ ምን እንዳሉ ---- ‹‹እሺ ፈቅደናል›› አይደለም ያሉት፡፡ ‹‹ባጀቱን ጭምር ፈቅደንላችኋል›› ነው ያሉት (ሳቅ)፡፡ ወጪም ቀነሱልን በጣም ደስ የሚል ሁኔታ ነበር፡፡ ንጉሱ ብዙ ግዜ ፖዘቲቭ ናቸው፤ደህና አድርገው ካስረዱዋቸው፡፡ ችግሩ ሳያስረዷቸውና አንዳንድ ሰው ለማስረዳት ስለሚፈራ ነው፡፡ እኔ ግን ማን አይዞህ እንዳለኝ አላውቅም፤ ፍርሃቷን አስወግጃለሁ (ሳቅ)፡፡

ከንጉሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራችሁ ማለት ነው?

በጣም በጣም፡፡ ጥሩ ግንኙነት ነበረን ለማለት እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ እየተከሰስኩ(እየተወቀስኩ) ነበር የምቀርበው፡፡ ስቀርብ ግን አስረድቼ እወጣለሁኝ፡፡ ሳስረዳቸው ያምኑኛል፣ ያመሰግኑኛል፡፡ እንደውም አንዷ አንድ ወቅት የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትሩ አስቸገረን አሉና አቀረቡላቸው፡፡ እሱ ሲመጣ የሚናገረውን አታውቁትምና ተውት አሉ (ሳቅ) እንደውም ይከላከሉልኝ ነበር ማለት ነው፡፡

በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሃገሮችን ስልጣኔና የቋንቋ ውርስነት በማገናዘብና በማየት አንዳንድ ኢትዮጵያውያን “እንደው ጣሊያን አምስት ዓመት ተጨማሪ ገዝታን በሆነ ነበር---” በሚል ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ እርስዎ በዚያን ዘመን በተለያየ የመንግስት ስራ ሃላፊነት ላይ ነበሩ፡፡ ጣሊያኖችን እንዴት ያስታውሷቸዋል፣ የሚጠቅሱት የእነሱ ውለታ አለ?

በጣሊያኖች ጊዜ ሰራተኛ አልነበርኩም፡፡ኩሊ ነበርኩ፣ተሸካሚ የተማርኩትም ከአንድ ቤት አንጣፊ ጋር አሸዋ እየተሸከምኩለት፤ አንድ ቀን እሱ ሌላ ቦታ ሲሄድ እሱ እንደሚያደርገው ሰርቼ ስጠብቀው ከዛ በኋላ ሁለት ክፍል አንድ ክፍል እያደረገ እንዳነጥፍ እየለቀቀልኝ መጣ፡ ፡ ደሞዜም በቀን እስከ አስራአምስት ሊሬ በሳምንት መቶ ሃምሳ ሊሬ ሆነልኝ፡፡ ብስክሌት መግዛትና ምቾት መልመድ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ በብስክሌቴ እናቴን ለማየት በየሳምንቱ መሄድ ጀመርኩኝ ባለብስክሌት ነበርኩኝ ማለት ነው(ሳቅ) ጣሊያን ጥሩ ገዥ አይደለም፡ ፡ በርግጥ ጥሩ ሰራተኛ ነው በግዛቱ ይሄን አድርጎልናል፤ ለህዝብ ይመቻል የሚባል ነገር የለውም፡፡ እንደውም አፓርትይድ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ በጣሊያን ጊዜ ከፊት አውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ድልድይ ወዲህ ማዶ እንደውም ሃበሻ አይሻገርም ነበር፡፡ የፈረንጅ ከተማ ነው ማዶ መርካቶ ግን የሀገር ህዝብ መኖሪያ ነው እስከዚህ ድረስ የሚለያይ መንግስት ነበረ ደግነቱ ረጅም ጊዜ አልኖረም እንጂ ጥሩ አልነበረም፡፡

ግን እኮ በወቅቱ ትልልቅ ድልድዮችንና መንገዶችን ሰርቷል----

እርግጥ ነው በጣም ትልልቅ መንገዶችን ሰርቷል፣ ድልድዮችንም ሰርቷል፡፡ ዋና ዋና የሆኑ መንገዶችን፤ ከአዲስ አበባ ጅማ፤ ከአዲስ አበባ አስመራ.. የመሳሰሉትንም ዘርግቷል፡፡ ግን መንገዱን የሰራው ለህዝቡ ጥቅምና ለኢኮኖሚ እድገት ብሎ ሳይሆን ለራሱ ጦር መዳረሻ ብሎ ነው፡፡ ስለዚህ የጣሊያን ብዙ እዳ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በርግጥ የስራ ባህል ሰጥቶናል፡፡

በስልሳ ዓመት የሥራ ዘመንዎት በሀገር ውስጥ የማይደፈሩ፣ ምላሽ ያጡ፣ አይሆንም የተባሉ፣ የተረሱ የሚባሉ አካባቢዎችን፣ አይቻልም የሚባሉ ጉዳዮችን እንደ አጀንዳ በማንሳትና በመከራከር ወደ አንድ ደረጃ ያመጡ ነበር፡ ፡ ለዚች ሃገርም ባለውለታ ነዎትና ዛሬ ይሄን ሳላደርገው ብለው የሚፀፅትዎት ነገር አለ?

ላደርግ ሲገባኝ ሳላደርግ ቀረሁ፤ ይሄን ማድረግ ሲገባኝ ተበላሸብኝ ብዬ የማስታውሰው ነገር ብዙም የለም፡ ፡ በርግጥ አንዳንድ የከሸፉ ጥሩ ሃሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነሱን ማንሳት ለአሁኑ ትውልድ የሚጠቅመው አይሆንም፡ ፡ ይሄ ቂም ነው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ውስጥ አንዱን ለመጥቀስ ይህል፣ እኛ ቦሌን ሰርተን አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ እየገነባን ሳለ እኔ ሞንቲሪያ ስብሰባ ላይ ነበርኩ፤አንድ ሃሳብ አገኘሁና---- ኬኤው የሚባል አለማቀፍ ድርጅት እየረዳ ትምህርት ቤት ያቋቁማል፣ በአንዳንድ በሰለጠኑ ሃገሮች ኢትዮጵያ የእንግሊዝም ሆነ የጣሊያን ተናጋሪ ችግር ስለሌላት፤ትምህርት ቤቱን ኢትዮጵያ ውስጥ ብታደርግ ለሁላችንም ይጠቅማል ብዬ አሰብኩና ያለውን አሮጌውን አውሮፕላን ማረፊያ ከነፋሲሊቲው እንሰጣችኋለን፡ ፡ የአቪየሽንን ኮሌጅ(ተማሪ ቤት) አዲስ አበባ አሮጌውን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ አድርጉልን አልኳቸው፡፡ እሽ አሉኝ፡፡ መንግስት ያን ተቀብሎ ካፀደቀው በኋላ ላኩብንና እንመጣለን አሉ፡፡ በጣም ትልቅ ነገር ነበረ፡፡ እኔ ከአሜሪካኖች ጋር ብዙ ፍቅር አልነበረኝም፤ መንግስት ከሲቪል አቬሽን ወደ ትራንስፖርት ቢሮ አሻገረኝ፡፡ እኔን የሚተካ ሰው ለማግኘት ሲቪል አቬሽን ስድስት ወር ነበር የፈጀባቸው፡፡ ሰው ጠፍቶም አልነበረም፣አሜሪካን የሚወድ ሰው ሲፈልጉ ነው እኔ ደግሞ ከአሜሪካን ጋር ጠብ የለኝም፡፡ እነሱ እንኑር ይላሉ፣ እኔ ደግሞ እኛ እንተካቸው ነው የምለው፣ የጥቅም ትግል ነው፡፡ በእኔ ቦታ አባተ አግደው የተባሉ አሜሪካን አገር ካውንስላችን ሆነው ይሰሩ የነበሩ ተሾሙና መጡ፡፡ እኔ ወጣሁ ‹‹አውሮፕላን የማያይበት ሃገር ይሂድ፡፡” ነበር የተባልኩት፣ ሲፈረድብኝ፡ ፡

አውሮፕላን ማብረር ስለሚወዱ ነው----

አውሮፕላን ማብረር ስለምወድና ስለ አውሮፕላን እድገት ብዙ ስለምከራከር ነው፡፡ ልጅ አባተ ወረቀት አገኙና ንጉሱ ጋር ሄዱ፡፡ የሲቪል አቬሽኑ ት/ቤት ራቲፊኬሽን ከማግኘት ይልቅ ይሄ እብድ መቶ አለቃ ያመጣብን ጣጣ ስለሆነ ይሰረዝልን ብሎ ተከራከረ፣ ተሰረዘ፡፡ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ያን ጊዜ አቪየሽን ኮሌጅ እዚህ ቢሆን ኖሮ፤ ዛሬ የት ደርሰን ነበር፡፡ የሆኖ ሆኖ እንግዲህ ይሄ ቂም ነው፡፡ በተረፈ ረዥም ጊዜ የሰራሁት ኤርትራ ውስጥ ነው፡፡ የስራ ዕድሜዬ ጥሩው ክፍል (21 ዓመት) ማለት ነው፡፡ በስኬት እንጂ በውድቀት የማስበው ነገር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ያልለማውን ዳህላክ ደሴት እንኳን ለማልማት ችያለሁ፡፡ ቀላል አይደለም ይሄ ስኬት ደስ የሚለኝና የምኮራበትም ነው፡፡

በአፄውም ጊዜ ሆነ በደርግ ዘመን፤ በተለያዩ መንግስታት በሃላፊነት ሲሰሩ ቤተመንግስት ቤትዎ ነበር፡፡ ለንጉሱና ፕሬዚዳንቱም ቅርብ ነበሩ፡፡ ዛሬ ያሉበትን የኃላፊነት ደረጃ አልመውት ያውቃሉ? እንዴት አርጎ ሰው እዚህ እገባለሁ ብሎ ያልማል፡፡ ሰው መቼም ህልም አለው --- ፕሬዚዳንት፣ ጠ/ሚኒስቴር፣ ዶክተር ብሆን ወይም እሆናለሁ ብሎ ያልማል----

ሠራተኛ እንጂ ህልመኛ አልነበርኩም፡፡ ሹመት ጠይቄ አላውቅም፤ የደሞዝ ጭማሪ ጠይቄ አላውቅም፡፡ ከመስራት በስተቀር፡፡ ስራ ከተሰራ ግን የሚፈለግ ነገር ሁሉ መገኘት እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ ስራውን ከመስራትና ስራውን ከማሸነፍ ውጪ በምኞት ደረጃ ይሄን አገኛለሁ ብዬ አነጣጥሬ የሰራሁት ነገር የለም፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው ንግስና በደም ነው፡፡ የንጉስ ልጅ፣ የንግስት ልጅ የምን... እንደውም ከደምም አልፎ የሰለሞን ዘር ወይም የዘር ሃረግ የሆነ ነበር ለንግስና የሚመረጠው፡፡ እኔ ይሄ የለኝም፣ የገበሬ ልጅ ነኝ፡፡ እና ይሄንን ማለም አልችልም ነበር፡፡ ትልቅ ቦታ ደረስኩ ከተባለ ... ሚኒስቴር ደረጃ ልደርስ ብችል ለእኔ በቂዬ ነበር፡፡ እና ሳላስበው ነው እዚህ የደረስኩት፡ ፡ የታሪክ አደጋ ነው፡፡ ዲሞክራሲ በመፈጠሩ ምክንያት፣ የንጉስ ደም የሌለው፣የሰለሞን ዘር ....ያልሆነ ማንም ሰው ተመርጦ ርዕሰ ብሄር የሚሆንበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡

የስልሳ ዓመት የስራ ዘመን ኢዮቤልዩ በዓልዎ በቅርቡ ሲከበር ባደረጉት ንግግር፣ በስራ ዘመንዎ የተቀዳጁት ስኬት እግረ መንገድዎን ያገኙት እንጂ ሆን ብለው አነጣጥረው የሰሩት እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ ትክክል ነው፣

ፈረንጆች ይሄን ዊንድፎል ይሉታል ሳታስቢው የምትደርሽበት እና የምታገኝው ነገር ነው፡፡ ለማሰብም ለመመኘትም ሁኔታው አልነበረም፡፡ የሆኖ ሆኖ እዚህ በመድረሴ ተደስቻለሁ፡፡

በሦስት መንግስታት ውስጥ አገልግለዋል፡፡የመንግስታቱን ጠንካራና ደካማ ጎን እንዴት ይገልፁታል?

የሃይለስላሴ መንግስት ምንም ደካማ ጎን አልነበረውም፡ ፡ ግን ህዝባዊ አልነበረም፡፡ የህዝብ ወገን ያልሆነ የዘውድ አገዛዝ ስለሆነ የምወደው እና የማደንቀው ሳይሆን የምቃወመው ዓይነት መንግስት ነው፡፡ ቀጥሎ የመጣው የወታደር መንግስት በመጀመሪያ አያያዙ የምደግፈው ዓይነት ነበር፡፡ የህዝብን ሃሳብ ለማሟላት፤ የህዝብን ነፃነት ለማረጋገጥ የመጣ ነው አንዳንድ ምሁራን ነን የሚሉ መጥተው ኮሚኒስት አደረጉት፤ ኮሚኒስት የሚባል ነገር የማይታወቅበት ሃገር ፍጅት አመጡ፤ ነገሩ ሌላ ሆነ፡፡ እንግዲህ የማላውቀውና የማይገባ ነገር ስለሆነ ስለዛ መናገር አልፈልግም ሂደት ስለሆነ ግን በዛ ማለፍ ነበረብን ማለት ነው፡፡ ከዛ ከነበረው ሲስተም አሁን ያለንበት ላይ ለመድረስ በመሀከሉ የነበረውን ዓይነት ሲስተም መታለፍ ነበረበት፡ ፡ ያለዚያ አሁን የምናደርገውን አናውቀውም ነበር፡ ፡ የአሁኑ ዲሞክራቲክ ነው፤ ዲሞክራሲ ደግሞ ከሁሉም የበለጠ የህዝብን ነፃነት ያከብራል፡፡ የህዝብን እድገት የሚወድ፤ህዝብ ከድህነት እንዲወጣ የሚሰራ፤የሚያስፈልግ ዓይነት መንግስት ነው፡፡ የዚህ መንግስት አባል በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል፡፡

ወደ ንግድ ዓለምም በመግባት ላቅ ያለ ስራ ሰርተዋል፡፡ የከፋ ኢሊባቡር የእንጨት ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር፤ በጊቤ ወንዝ ተፋሰስ እርሻ ብርቱካንና ማንጎ ተክል፤ የትንባሆ የጥጥና የበቆሎ እርሻ የመሳሰሉትን ከግለሰቦች ጋር በጋራና በግል ሰርተዋል፤በመጨረሻ ምን ደረሰ?

የእንጨት ኢንዱስትሪውን ደርግ ወረሰው፡ እርሻው መንግስት ሲለወጥ እኛ አልነበርንም፤ኦፊሻሊ ተወረሰ ባይባልም ያው ተወስዷል፡፡ እርሻው ግን ጥሩ ታሪክ ያለው እርሻ ነው፡፡ አራት ሆነን ነበር ማህበር የመሰረትነው፡ አራታችንም ከተለያየ ቦታ ነው የመጣነው፤ በሃይማኖትም ሆነ በጎሳ አንድ አይደለንም፡፡ አንደኛው አቶ ዑስማን መሐመድ (ኤርትራዊ)፤ ብላታ በየነ ቢያድግልኝ (ኮንሰርቫቲቭ ኦርቶዶክስ የአድዋ ሰው)፤ዶክተር አማኑኤል ገብረ ስላሴ (የመሰረተ ክርስቶስ ሃላፊ) አራተኛው እኔ ነኝ፤ እኔም ወታደር ነበርኩ፡፡ የስራ ክፍፍል ስናደርግ ብላታ በየነ አስተዳደርና ሂሳብ፣ አቶ ዑስማን መሐመድ የቴክኒክ ሰው ስለሆኑ ትራክተር ቢበላሽ ፓምፕ ቢበላሽ የቴክኒክ ስራ የርሳቸው ነው፡፡ ከመንግስት፤ከአካባቢውና ከዝንጀሮዎች ጋር ሳይቀር ሰላም መፍጠር ደግሞ የእኔ ስራ ነው፡ ከዝንጀሮዎች ጋር የሠላም ውል ተፈራርመናል (ሳቅ)፡፡

እንዴት ማለት?

እነሱ አለም ውስጥ እኮ ነው የገባነው፡፡ ውሃ ለመጠጣት በሺህ ነው የሚመጡት እናም አልፈው የእኛን እርሻ ድምጥማጡን አጥፍተውት ነው የሚሄዱት፡፡ አንድ አሳቻ ቀን ስናያቸው አንዱ በአንዱ ላይ ቆሞ ታወር ሰርተው ምልክት ሲነገራቸው ነው የሚሸሹት፡፡ ከእኛ የበለጠ ያውቃሉ ማለት ነው፡፡ ከአዋቂ ህዝብ ጋር መሟገት አንችልምና እንገብራለን አልንና ወንዝ ወዲያ ማዶ ቀጥ ያለ እርሻ አረስን፡፡ አንድ ልጅ ጠባቂ ቀጠርን፡ ፡ በልተው ጠጥተው ከዚያ መሻገር ከፈለጉ ይመታቸዋል፡፡ መመለሱን ለመዱ፤ እኛ ነፃ ሆንን፡፡ ከመንግስትና ከዝንጀሮ ጋር መፈራረም የእኔ ፋንታ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ማህበር አይዘልቅም የሚባል ነገር ነበር፤ግን የማንተዋወቅ ሰዎች አንድ ሆንን፤ ስራውም ባይኖር አብረን ሰርተን፣ ከብረን፣ ከስረን፣ አሁንም አብረን አለን፡፡

ስለ ባለቤትዎ ወ/ሮ ሳሌም ሲናገሩ ‹‹ሳሌም ለእኔ ዛሬም ውብና ቆንጆ ናት፡፡ ማራኪ..›› ብለዋል የትናንትናና የዛሬ የፍቅርና የትዳር ዘመናችሁን እንዴት ይገልፁታል?

አህ....(የመገረም ሳቅ) እንግዲህ ፍቅር ማለት ብዙ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያ አፍላ ፍቅር አለ፤ ከዛም በመጋባት መካከል ልጅ በመውለድ.. ከዛ ደግሞ የኃላፊነትና የአብሮ መኖር ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ እኛ ይሄንን ደህና ተወጥተነዋል አሁንም አብረን ነን፡፡ ሁለታችንም አርጅተናል፣ደክመናል(ሳቅ)፡፡ ከተጋባን 65 ዓመታችን ነው፡፡ ቀላል አይደለም፡፡ ከልጆችዎ መካከል የእርስዎን አርዓያ በመከተል ወደ መንግስት ስራ፣ ወደ ፖለቲካ የገቡ አሉ? ከልጆቼ በውስጣችን የፖለቲካ ልዩነት ያለን አንድ ልጃችን ናት፡፡ እርሷም ኢህአፓ ስለነበረች የመንግስት ተቃዋሚ ነኝ ብላ ፈረንሳይ ነው ያለችው፡፡ የቀሩት ግን አንዱ ካናዳዊ ነው፤አሁን እዚህ ነው ያለው፡፡ አንዷ አሜሪካን አገር አስተማሪ ነበረች፤እስዋም እዚህ ነው ያለችው፡፡ የቀሩት የሉም፡፡ ያሉት ደህና ናቸው፡፡ በ2006 ዓ.ም. የስልጣን ዘመንዎን ይጨርሳሉ፡፡ ከሥልጣን ሲወርዱ ምን ሊሰሩ አስበዋል? ስራ ፈት አልሆንም፡፡ የምሰራውም አላጣም ይሄን ይሄን እሰራለሁ ብዬ ያቀድኩት ግን የለም፤ የሆኖ ሆኖ ሽምግልናም አንድ ስራ ሊሆን ይችላል፤የተለያዩ ሽማግሌን ሊያሳትፉ የሚችሉ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሪሶርስ ፐርሰን ሆኖ የማማከር ሁናቴ አለ፤ ጤና ካለኝ ስራ ፈት አልሆንም፡፡

የህይወት ታሪክዎን የመፃፍ ሃሳብስ ----- እኔ የብዕር ሰው አይደለሁም፡፡ ከዚህ በፊትም ወዳጆቼ ናቸው የጻፉት፡፡ እኔ የጻፍኩት ‹‹አየርና ሰው›› የምትለውን ብቻ ነው፡፡ እቅድ የለኝም፤ ከመጣልኝ ግን አንዳንድ ነገር እሰራለሁ፡፡

በትርፍ ጊዜዎ ምን ይሠራሉ?

መጽሐፍ ማንበብ እወዳለሁ፡፡ የተማርኩትም በማንበብ ነው፡፡ ዘፈን መስማት እወዳለሁ፡፡ መጫወትም መደንስም እወድ ነበር፡፡ እነ ራሔል ዮሐንስ ደስ ይሉኛል፡፡ አሁን አለች እንደሆነ አላውቅም፡፡

አለች

አሁን አራዳውን አናውቀውምና እገሌ ይሻላል ለማለት... (ሳቅ) ይቸግራል፡፡ በጊዜዬ ግን የዘፈንና የደስታ ጠበኛ አይደለሁም፡፡ ሰው ከሰራ በኋላ ደስ ሊለው ይገባል ባይ ነኝ፡ ፡ ሰው ከሰራ በኋላ አንጎሉን ማስጨነቅ የለበትም፤ ሪላክስ ማድረግ አለበት፡፡ ሪላክስ ማድረግ ደግሞ የሚችለው በዘፈን በዳንስ ... ነው፤ እኔ በዚህ ተጠቅሜበታለሁ፡፡

የእናንተ ዘመን የአራዳ መሰባሰቢያ ደጃች ውቤ ሰፈር ነበር?

አይደለም፤የእኛ እንኳን ካሳንቺስ እነ ራሔል ዮሐንስ ጋ ነበር፡፡ አሁን ይኖሩ ይሆናል፣ ጠባያቸውን ሳይቀይሩ አይቀርም እንጂ!!

በመንግስት የሥራ ዘመንዎ በተጨዋችነታቸው የሚያስታውሷቸው ሰዎች አሉ?

በተጫዋችነት ብዙ ሰው አላውቅም፡፡ በስራ ግን ንጉሰ ነገስቱን አደንቃለሁ፡፡ ከእሳቸው ጋር በተለያየ የስራ አጋጣሚ ስለምንገናኝ ከማደንቃቸው ሰዎች አንዱ ነበሩ፡፡ በጨዋታ ካልሽ ግን እንደ እኔ ተጫዋች የለም፡፡

አንዳንድ ብሩህ ተስፈኞች ኢትዮጵያ ወደፊት ተለውጣና ከራሷ አልፋ ሌሎችን በዲቪ የምትቀበል አገር ትሆናለች ይላሉ፡፡ እርስዎ የነገዋን ኢትዮጵያ እንዴት ይገልፁዋታል----

ኢትዮጵያ አሁን በሙሉ ኃይሏ እየሰራች ነው ድህነት መውጣት የመጀመሪያው ነገር ነው፡፡ እየወጣን ነው፡፡ 31 ዩኒቨርስቲ ይዘን ብዙ አዋቂ እያፈራን፣ ከድህነት የማንወጣበት ምክንያት የለም፡፡ እንግዲህ በዲቪ የሚመጡ ካሉ እንቀበላለን፡፡ ከሁሉ በፊት ዲያስፖራ እንዲመለስ እናደርጋለን፡፡ አገሩ ይሻለዋል፡፡ ከዛ የተቀሩት መምጣት ከፈለጉ እንቀበላለን፡፡

Read 6130 times Last modified on Saturday, 02 February 2013 15:35