Saturday, 26 January 2013 12:14

“ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የተባረሩ ተማሪዎች ቁጥር ከ700 በላይ ደርሷል” - ተማሪዎች “ከግቢው የወጡት ሕግ አናከብርም ያሉ ጥቂት ተማሪዎች እንጂ የተባረረ ተማሪ የለም” - ዩኒቨርስቲው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(18 votes)

በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ሥር በሚገኙ አራት ካምፓሶች የሚማሩ ከ700 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ከግቢው መባረራቸውን የገለፁ ምንጮች፤ ለተማሪዎቹ መውጣት ምክንያቱ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የትኛውም የሃይማኖት ሥርዓትን ማከናወን እና የሃይማኖት አልባሣትን መልበስ የሚከለክለው ደንብ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ “ኒቃን” የተባለውን ቀሚስ ለብሰው በተገኙ 15 ሴት የእስልምና እምነት ተከታይ ተማሪዎች ላይ በተጣለ የዲስፕሊን እገዳ እንደሆነ ጠቆሙ፡፡ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፖሊቴክኒክ ግቢ ተማሪ እንደገለፀው፤ በእስልምና ሃይማኖት በቀን አምስት ጊዜ የስግደት ሥርዓት እንደሚከናወንና በአቅራቢያቸው መስጊድ ባለመኖሩ በግቢ ውስጥ በጋራ እንደሚሰግዱ፣ በሌላ በኩል በሃይማኖት ሥርዓት አንዲት ሴት “ኒቃን” የተባለውን ልብስ መልበስ ከጀመረች በኋላ ማውለቅ ክልክል እንደሆነ ጠቁሞ፣ በዚህም ምክንያት የወጣውን ደንብ ሊያከብሩ አለመቻላቸውን ተናግሯል፡፡ ባለፈው ሰኞም በ15 ሴቶች ላይ በተወሰደው የማባረር እርምጃ በፈጠረው አለመግባባት ፔዳ፣ ፖሊ፣ ዘንዘልማና ይባብ ከተባሉ አራት ካምፓሶች ከ700 በላይ ተማሪዎች መባረራቸው ታውቋል፡፡

“ምንም እንኳ ደንቡ የሁሉንም እምነት ተከታዮች የሚገዛ ቢሆንም ለእስልምና እምነት ተከታዮች ግን እጅግ ከባድ ነው” ስትል ለአዲስ አድማስ የገለፀችው ሌላዋ የፔዳ ተማሪና የእስልምና እምነት ተከታይ ወጣት፤ “በቀን አምስት ጊዜ ከግቢ እየወጡ መስገድ ከባድ መሆኑንና ይህም እንዲሻሻል በተደጋጋሚ ብንደራደርም ደንቡ ሊሻሻል ባለመቻሉ ችግሩ ሊከሠት እንደቻለ ተናግራለች፡ ፡ ሌላው ወጣት በበኩሉ፤ “ጉዳዩ በሠላማዊ መንገድ እንዲያልቅ ብዙ ድርድር ቢደረግም ደንቡን አክብረን የማንማር ከሆነ ከግቢ መውጣት እንዳለብን በዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት በዶ/ር ባይሌ ሲነገረን፣ ጥቂቶቹ ተባረው አብዛኞቻችን አንማርም በሚል በልጆቹ ላይ የተወሰደውን እርምጃ በመቃወማችን ነው” ብሏል፡፡ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች፤ ዩኒቨርስቲው “ሴት ተማሪዎች ‘ኒቃን’ መልበስ ካልተፈቀደላቸው እና የተባረሩት ተማሪዎች የተወሰደባቸው የዲስፕሊን እርምጃ ተነስቶላቸው እንዲማሩ ካልተደረገ ገብተን አንማርም” ብለዋል፡፡ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ኃላፊ፤ ግቢውን ጥለው የወጡት ተማሪዎች “ሕግ አናከብርም ያሉ ተማሪዎች በገዛ ፈቃዳቸው ነው እንጂ ዩኒቨርስቲው አንድም ተማሪ አላባረረም” ብለዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት፤ በግቢው ውስጥ በቡድን መስገድና ሃይማኖታዊ አልባሣት መልበስ የተከለከለ መሆኑን እያወቁ ድርጊቱን መፈፀማቸው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ይህን ደንብ ባላከበሩ ሦስት ሴቶችና በአንድ ወንድ ተማሪ ላይ የዲስፕሊን እርምጃ መወሰዱንና 15 ሴቶች ተባረሩ የሚለው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

ከ700 በላይ ተማሪዎች ከግቢው ተባረዋል ለሚባለውም “ከግቢ የወጡት 100 አይሞሉም፣ የወጡትም ዩኒቨርስቲው አባሯቸው ሳይሆን በአራቱ ተማሪዎች ላይ ለምን የዲስፕሊን እገዳ ተደረገ በሚል ነው፡፡” ብለዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በአጠቃላይ 20ሺህ ተማሪዎች መኖራቸው የገለፁት ሀላፊው፤ ይህን ሁሉ ተማሪ በተረጋጋ መንፈስ እንዲማር ለማድረግ ጥቂት ሕግ የማያከብሩ ተማሪዎች ላይ እገዳ መጣሉ አግባብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ “ለጉዳዩ እልባት ለመስጠትና ተማሪው ትምህርቱን በአግባቡ እንዲቀጥል የሀይማኖት አባቶችንና የተማሪ ወላጆችን ጠርተን በሰፊው ከተነጋገርን በኋላ፣ ጉዳዩ በዚህ መልኩ መቀጠሉ አግባብ አይደለም፡፡ በግቢው ውስጥ የየትኛውም እምነት ተከታይ የሆነ ተማሪ በግሉ መስገድና መፀለይ ተፈቅዶለት ሳለ፡ የግድ በሕግ የተከለከለውን ካላደረግን ማለት የሀገሪቱን ሕግና መመሪያ መናቅ ይሆናል” ብለዋል፡፡ በአቅራቢያቸው የፀሎት ቦታ አለመኖሩን በተመለከተም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመመካከር ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ እንደሚጥሩ ገልፀዋል። ተማሪዎች ወደ ግቢ ተመልሰው ትምሕርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ እናስተላልፋለንም ብለዋል፡፡

Read 4433 times Last modified on Saturday, 26 January 2013 17:12